Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉ​​​​​​​የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወኪል ለሆነው የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ትኩረት ይሰጥ!

​​​​​​​የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ወኪል ለሆነው የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ትኩረት ይሰጥ!

ቀን:

በገብረ እግዚአብሔር ወንዳፈረው መኩሪያ (ኮሎኔል)

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለአገሩ አኩሪ ተግባር ሠርቷል፣ የአገሩን ዳር ድንበር አስከብሯል፣ አንድነቷን ጠብቆ ለተከታይ ትውልድ አስተላልፏል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክብርና ዝና ተችሮታል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ሠራዊት በአቶ መለስ ዜናዊ ትዕዛዝ መበተኑም ይታወሳል፡፡ መበተን ብቻ ሳይሆን በማንኛውም የሥራ መስክ ተቀጥሮ እንዳይሠራ በውስጥ መመርያ በመከልከሉ፣ ቤተሰቡ ጭምር ሜዳ ላይ ተበትኖ ቀስ በቀስ እየሞተ ይገኛል፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅትም ግንባር ቀደም ተሠላፊ በመሆን የአገር አለኝታነቱን በተግባር አስመስክሯል፡፡ ከድል በኋላ ግን ገድሉ እንዲሰማ አልተፈለገም፡፡ እንዲያውም የድሉ ባለቤት እኛ ነን በማለት የከፈለው መስዋዕትነት ሳይነገርለት ድሉን ተነጥቆ ያለ ምሥጋና ተሸኝቷል፡፡ የመከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን የተቋቋመበት ዋናው ዓላማ በአገራችን የመከላከያ ተቋም ገብተው የሕይወት መስዋዕትነት ለመክፈል በውትድርና ሙያ ያገለገሉና በማገልገል ላይ ለሚገኙ አባላት፣ በዕድሜ ጣሪያና በተለያዩ ምክንያቶች ከሠራዊቱ በክብር ሲሰናበቱ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት እንደታየው የትም ተበትነው እንዳይቀሩ፣ ተቀጥረው እንዳይሠሩም በውስጥ መመርያ በመከልከል ለከፋ ችግር እንደ መሰባሰቢያ ማዕከል በማዘጋጀት፣ ተገቢውን ክብርና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ በሙያቸው አገልግሎት ሊሰጡ በሚችሉበት መስክ እንዲሠሩ፣ በቀሪ ዘመናቸው የተመቻቸ ሕይወት እንዲኖራቸው፣ ገጠመኞቻቸውን በግንባር ከተሳተፉ አባላት ምስክርነት መመዝገብ፣ በተለያየ ሁኔታ ተበታትነው የሚገኙትን ሰነዶች ማሰባሰብ፣ በስማ በለውና ባልዋሉበት ግንባር ከእኔ ሌላ ላሳር መሰል ጽሑፎችን በማረም ትክክለኛና ያልተዛባ የሠራዊቱን አኩሪ ታሪክ መጻፍና ለመጪው ትውልድ ማቆየት፣ በማንኛውም ወቅት የኢትዮጵያ ዳር ድንበር እንዳይደፈር ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ፣ በዚህም ሒደቱ ሳይቋረጥ ዘለዓለማዊ ሆኖ የሚቀጥል የጦር ኃይሎች ቬተራንስ አሶሴሽን እንዲኖር ማድረግ ነው።

ለመከላከያ ዕድገትና ለመጪው ትውልድ አደራን ማስተላለፍ ባህል እንዲሆን ለማድረግ የተቋቋመው የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን የአገርን ዳር ድንበርና ክብር መጠበቅ፣ የዘመኑ ዕድገትና ሥልጣኔ መለኪያ እየሆነ የመጣውን ይህን ዓላማ ከበርካታ አገሮች ተሞክሮ በመውሰድ በዓለም አቀፍ ከሚገኙ መሰል አሶሴሽኖች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ለዓለም ሠላምና መረጋጋት አስተዋጽኦ ማድረግ፣ በአብዛኛው ዓለም ይህን መሰል አሶሴሽን በመንግሥትና በሕዝቡ ድጋፍ ስለሚቋቋም የአገሮች ፓርላማና ኅብረተሰቡም ከፍተኛ ድጋፍና ክብር ይሰጠዋል፡፡ ያለፉት መንግሥታት ትኩረት ባለመስጠት እንዲቋቋም አለማድረጋቸው አሳዛኝ ክስተት እንደሆነ ተመልክተናል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በሌላው ዓለም የሚገኙ የውጭ ዜጎች ስለኢትዮጵያ ሠራዊት በሰፊው ጽፈዋል፡፡ ለዘመናት በውጭ ጠላት አገሩ እንዳትደፈር ብሎም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሥር በመዝመት የኢትዮጵያን ክብር ለመጠበቅ ያደረገውን ተጋድሎ በማስተዋል በርካታ የታሪክ መጻሕፍትን ስለእኛ ከመጻፋቸው ባሻገር፣ በአሁኑ ዘመን በሌላው ዓለም እንዳለው የቬተራንስ አሶሴሽን በኢትዮጵያም ለምን እንደሌለ በየጊዜው ይጠይቃሉ፡፡ እኛም ቢዘገይም ከሚቀር ይበጃል በሚል የመንግሥትን የሥራ ድርሻ ወስደን ላለፉት 16 ዓመታት ካለችን አነስተኛ ገቢ በማቋቋም እዚህ አድርሰናል፡፡ ከዚህ በኋላ የመንግሥት ድጋፍና የዜጎች ተሳትፎ ይጠይቃል እንላለን።                                                               

በርካታ አባላት ጡረታ አያገኙም፣ በሚመለከተው አካል ተጣርቶ መብታቸው እንዲከበር፣ ከወቅታዊ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጋር የተገናዘበ የጡረታ ክፍያ ማሻሻያ እንዲኖርና በቂ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ፣ አባላቱም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በተጨማሪም የጦር አካዳሚ ቀድሞ በነበረበት ሁኔታና ደረጃ ተመልሶ እንዲቋቋም ጥረት ማድረግ፣ የውጊያ፣ ጥናትና ምርምር ማዕከል እንዲኖርና የግጭቶች መንስዔና መፍትሔ ማቅረብ፣ ማማከር፣ የወታደራዊ ሙያ እንዲጠነክር ማድረግ፣ በሚደረጉ ውጊያዎች የምክር አገልግሎት መስጠት፣ የውትድርና ሙያ የተከበረና የአገር ፍቅር ማሳያ መሆኑን ማሳወቅ፣ በወታደራዊ ግዳጅ ላይ ተሞክሮዎችን፣ ገጠመኞችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሕዝባዊ መድረኮች ገለጻ ማድረግ፣ መጽሔቶችን፣ ጋዜጦችን፣ መጻሕፍትን ማዘጋጀት፣ ማሳተምና ለንባብ ማብቃት፣ ቤተ መጻሕፍት፣ መዝናኛ፣ የስፖርትና የጤና ማዕከል ማቋቋም፣ አባላቱ በአካልና በአዕምሮ ጤነኛ እንዲሆኑና ደስተኛ ሕይወት እንዲኖሩ ማድረግ። የዓለም አቀፍ ቬተራንስ አሶሴሽን አባል በመሆን የልምድ ልውውጥ ማድረግና በአገራችን የልማት መስክ መሰማራት።

የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ባለፉት ዓመታት ካከናወናቸው ተግባራት መካከል የዲላይት አስጎብኚ ድርጅት ውስጥ የቬተራንስም ቢሮ እንዲሆን ተፈቅዶልን ሳምንታዊ ስብሰባ ያለ ማቋረጥ በማድረግ፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ የዕውቅና ደብዳቤና ሰርተፊኬት ጥቅምት 8 ቀን 2003 ዓ.ም. አገኘን፡፡ ሊቀ መንበራችን ጄኔራል አበበ ወልደ ማርያም በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ደስታም ሆነ፡፡ በአዲስ አበባ ከሚኖሩ የበርካታ አገሮች ወታደራዊ ሚሲዮኖች ጋር ጠንካራ ግንኙነት ጀመርን በየጊዜው እየመጡ ምክረ ሐሳብ ይሰጡን ነበር፡፡ በገጠመን የኢኮኖሚ ችግር ምክንያት ቢሮ መከራየት አልቻልንም፡፡ መከላከያም ቃል ከመግባት ባሻገር ተጨባጭ ድጋፍ ማድረግ አልቻለም፡፡ ሆኖም ቋሚ አድራሻ እስኪኖረን ከየአገሮች አሶሴሽኖች ጋር ግንኙነት ለመመሥረት ጊዜ እንዲሰጡን ጠይቀናል፡፡ ቀደም ሲል ጀምሮ አሶሴሽኑ ቢሮ እንዲኖረው ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡፡ ጄኔራል አበበ ወልደ ማርያም፣ እኔና ጄኔራል አሳምነው ሆነን ጄኔራል ሳሞራን አነጋግረናል፡፡ ዓላማውን ካደነቁ በኋላ በቅርቡ ይህ የመከላከያ ቢሮ ወደ ሌላ ቦታ ይዛወራል፣ ይህ ሕንፃ የመከላከያ ሙዚየም ስለሚሆን ለእናንተም እዚሁ ቢሮ ይኖራችኋል ብለውን ነበር፡፡ የቀድሞ አራተኛ ክፍለ ጦር የመከላከያ ፋይናንስ ምክትል ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ስለነበር ከምክትል ሚኒስትሩ አቶ ብርሃኑ ጋር ተገናኘን፣ እንተዋወቅ ስለነበር ተደስተው ቢሯቸው ገብተን ተወያየን፡፡ ጄኔራል አበበ የቀድሞ አለቃቸው ስለነበሩ በመገናኘታቸው ተደስተው ቢሮ እንደሚያፈላልጉልንና የቀድሞ ጦር ኃይሎች የዕድር ገንዘብ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ በመከላከያ አካውንት ውስጥ በመቀመጡ መቸገራቸውን፣ አሁን እናንተ ባለቤቱ ስለሆናችሁ ማስረከብ ይቻላል ብለውን ነበር፡፡ ሆኖም አድራሻ ስለሌለን ዓላማችንን ለማሳካት በመቸገራችን  አጥብቀን መከታተል አልቻልንም፡፡                                                                  

የዘገየበት ዋና ምክንያቶች በወቅቱ የነበሩት መከላከያ ሚኒስትሩን አቶ ሲራጅ ፈጌሳና ጄኔራል ሳሞራን ቢሮ እንዲሰጡን ደጋግመን ጠይቀናል፡፡ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስም በስልክም በደብዳቤም ተማፅነዋል፡፡ የቢሮ ነገር እልባት ማግኘት ባለመቻሉ ከወታደራዊ ሚሲዮኖች ጋር የነበረን ግንኙነት ተቋረጠ፡፡ በሰኔ ወር 2004 ዓ.ም. እኔ ወደ ውጭ ሄድኩ፡፡ ጄኔራል አበበና ኮሎኔል አበራ ኃይለ ማርያም ተከታትለው አረፉ፡፡ የአሶሴሽኑ አመራሮች ተበተኑ፡፡ ሁለት የባህር ኃይል አባላት ማስተር ቺፍ ገረመውና ማስተር ቺፍ ሥዩም ኃላፊነቱን ወስደው ተከታትለዋል፡፡ ሆኖም ፈቃዳችን እንደማይታደስ የሚገልጽ ደብዳቤ የማኅበራት ኤጀንሲ ሰጣቸው፡፡ ከሁለት ዓመታት የውጭ አገር ቆይታ በኋላ ስመለስ ይህንኑ ደብዳቤ ሰጡኝ፡፡ ትክክል አለመሆኑን ስለተረዳሁ የማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሪክተር የሆኑት አቶ መሠረት ገላውን በአካል ሄጄ አነጋገርኳቸው፡፡ ሐሳቤን በመደገፋቸው ከተወካዮች ምክር ቤት ጋር ተነጋግሬ ሰሞኑን እደውልልሃለሁ በማለት ስልኬን ተቀበሉ፡፡ በሳምንቱ ቃላቸውን አክብረው ነገ ቢሮ እንገናኝ ብለው ደወሉልኝ፡፡ ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ጋር ማለትም ብርጋዴር ጄኔራል ካሳ ወልደ ሰማያት፣ ሜጀር ጄኔራል መርዳሳ ሌሊሳ፣ ካፒቴን ፀጋዬ ወልደ ዮሐንስ፣ ብርጋዴር ጄኔራል ተጫኔ መስፍን፣ ብርጋዴር ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ፣ ማስተር ቺፍ ገረመው ኃይሌና እኔም ሆነን ቀረብን። ከውይይቱ በኋላ ፈቃዳችን ለአንድ ዓመት ተራዘመልን፡፡ ስለማኅበራት ጉዳይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተያዘ ጉዳይ በመሆኑ ዝም ብላችሁ ሥራችሁን ሥሩ በማለት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ወ/ሮ ፋንታዬ ለሁለተኛ ዓመት አራዘሙልን፡፡ ከዚያም የተወካዮች ምክር ቤት የኤጀንሲውን ዕግድ በማንሳቱ ለሦስት ዓመታት የሚቆይ ዕድሳት ተሰጠን፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የአንድ ሰው ኮሚቴ እንዳይመስል አልፎ አልፎ ብርጋዴር ጄኔራል ካሳ ብቻህን ደከመህ እያሉ ይመጡ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔት እስካሁን ድረስ አሶሴሽኑ ሳይሞት እንዲቆይ አድርጌያለሁ፡፡

የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ከጅምሩ አንስቶ የሐሳቡ አመንጪና አባልም ስለነበሩ፣ በየጊዜው ቤተ መንግሥትም በነበሩበት ወቅትም ሆነ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ እንወያይ ነበር፡፡ በተለያየ ጊዜ በስልክም በደብዳቤም የመከላከያ ኃላፊዎችን ድጋፍ እንዲያደርጉ ከመጠየቅ አልቦዘኑም፡፡ እኔም በየጊዜው በአካልም በስልክም በማግኘት ከመከላከያ ተገቢውን ድጋፍ አለማግኘታችንን፣ ለመከላከያ ሚኒስትሩ ለጻፉት ደብዳቤ ምንም ምላሽ አልተሰጠም እል ነበር፡፡ ጥር 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በሪፖርተር ጋዜጣ ስለቬተራንስ አሶሴሽን አመሠራረት ጽፌ ነበር፡፡ በቬተራንስ ዙሪያ የምትሠራ አንዲት ሳንዲያጎ የምትኖር አሜሪካዊት ጋዜጠኛ ጉግል ስታደርግ ጽሑፌን አገኘች፡፡ ወዲያውኑ ኢሜይል አደረገችልኝ፣ መልስ ሰጠኋት፡፡ በቅርቡ እንደምትመጣ ስትነግረኝ ለኮሚቴው በመንገር ዝግጅት አደረግን፣ ሉሲ ኦብራይን ትባላለች፡፡ እ.ኤ.አ. ማርች 2 ቀን 2016 መጣች፡፡ ባህር ኃይል ክበብ ተዘጋጅተን ጠበቅናት፣ ዕቅፍ አበባ ተበረከተ፡፡ ፕሮግራሙን አስተዋወቅሁ፡፡ ከእሷ ጋር በባህር ኃይል ክበብ የካቲት 25 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ ከስምንት እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ተወያይተን ታሪኳን በአጭሩ አጫወተችን፡፡ እሷም የወታደር ልጅ መሆኗን፣ አባቷ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የአየር ኃይል አብራሪ ሆነው ሂሮሺማና ናጋሳኪ በተጣሉት ቦምቦች በአንደኛው ቦምበር ላይ ተካፋይ እንደነበሩ፣ በአሁኑ ወቅት በዚህ ዙሪያና በመላው ዓለም እየተዘዋወረች ሰብዓዊ ተግባር እንደምታከናውን ነገረችን፡፡ በመቀጠ የሦስቱም ኃይሎች ተወካዮች በየተራ ስለቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ከማግ (የአሜሪካን ወታደራዊ ተራድኦ ድርጅት) ጋር ስለነበረው ወታደራዊ ድጋፍ ገላጻ አደረጉ፡፡ በማግሥቱ ጧት አፍንጮ በር አፋፉ ላይ ከሚገኘው የኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ይዣት ሄድኩ፡፡ ኮሎኔል መለስ ገለጻ አደረጉልን፣ ሙዚየሙንም አስጎበኙን፣ ሁለት ሰዓት ያህል ከቆየን በኋላ ተሰናብተን ወጣን፣  ከምሳ በኋላ ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ቤት ሄድን፣ ለአንድ ሰዓት ያህል ታሪካቸውን በአጭሩ አጫወቷት፣ አንዳንድ ጥያቄዎችን በማንሳት ተወያይታለች፡፡ ወደ አገሯ ስትመለስ ከአሜሪካ ቬተራንስ ጋር ለማስተዋወቅ እንደምትሞክር ነገረችን፡፡ 

ከመከላከያ በእጅ የሚዳስስና የሚጨበጥ ነገር አሁን ድረስ አላገኘንም፡፡ ብዙ ጠቃሚ ተግባራትን ማከናወን አልቻልንም፡፡ እንደ መጀመርያው በኅብረት አለመንቀሳቀስ፣ በተለይ በጄኔራል መኮንኖች ይባስ ብሎ መጠላለፍ፣ በራሳችን ጊዜና ጉልበት የምንሯሯጠውን በርታ በማለት ከማገዝ ይልቅ ለመርዳት አለመሻት፣ በርካታ ዕቅዶች ይዘን ምንም ማድረግ ሳንችል ቀርተናል፡፡ በርካታ ጠቃሚ ጉዳዮችን ከሚሊተሪ አታሼዎች ጋር ተወያይተናል፡፡ መልካም ነገር እያሰቡልን ቢሆንም አድራሻ ካለመኖሩ ባሻገር ኅብረትም በመጥፋቱና መገናኘት ባለመቻላችን ማግኘት የሚገባንን ጥቅም አላገኘንም፡፡ በክፍለ አገር ለሚገኙ አባላት እስካሁን ደሴና አካባቢው፣ ጎጃምና አካባቢው፣ ጎንደርና አካባቢው፣ ድሬዳዋና አካባቢው፣ ሐረርና አካባቢው፣ ባሌና አካባቢው፣ አምቦ/ጊንጪና አካባቢውና ሶማሌ ክልል ለሚገኙ የቀድሞ ሠራዊት አባላት እንዲሰባሰቡና እንዲመዘገቡ፣ ተደራጅተው መብታቸውን እንዲጠይቁና አመራሮቹን እንዲያሳውቁን በገለጽነው መሠረት መልካም ግንኙነት ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ከየክልሉ የሚገኙት አመራሮች አዲስ አበባ እየመጡ ተዋውቀዋል፣ ግንኙነት ተጠናክሯል፡፡ በተገለጹት አካባቢዎች በርካታ አባላት ተመዝግበዋል፣ ሆኖም ምዝገባ እንዲቆይ አድርገናል፡፡ ወደፊት እንደ ሁኔታው አመቺነት ሒደቱ በሌሎችም ቦታዎች ይቀጥላል፡፡ በቅርቡም ከሶማሌ ክልል የደኅንነትና የፍትሕ ቢሮ ደውለው ከመከላከያ ደብዳቤ ቢደርስን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልጸውልኛል።

ከአቶ አባዱላ ገመዳ ጋር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በነበሩበት ወቅት ተወያይተናል፡፡ የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን መቋቋምን በተመለከተ ገለጻ አድርገናል፣ የገጠሙንን ችግሮች አስረድተናል፣ ሜጀር ጄኔራል ሆነው የአገር መከላከያ ሚኒስትር ስለነበሩ የአሶሴሽኑ አባል መሆን እንደሚችሉ ነግረናቸዋል፡፡ ስለዚህ የሳቸው ድጋፍ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች በማንኛውም መስክ ድጋፍ እንድናገኝ፣ የቢሮ/መሰብሰቢያ ቦታና የሚዲያ ሽፋን እንድናገኝ፣  በተወካዮች ምክር ቤት የቬተራንስ አሶሴሽን ቋሚ መቀመጫ እንዲኖረው ሌሎችንም ጥያቄዎች አቅርበናል፡፡ ባደረግነው ገለጻ መሠረት ለቀደመውም ሆነ አሁን በሥራ ላይ ላለው ሠራዊት ዘለዓለም የሚጠሩበትን ታሪካዊ ሥራ እንዲሠሩ ጭምር አሳስበናቸዋል። ከወታደራዊ ማኅበራት አንዱና ቀዳሚው የአርበኞች ማኅበር ሲሆን፣ በአንድ ወቅት የተከናወነ (በአምስት ዓመት የፋሺስት ጣሊያንን ወረራ ለማስቆም የተመሠረተ የአርበኝነት ታሪክ) ነው፡፡

በሕይወት የነበሩ ብቸኛ አርበኛ ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ የዚህ አሶሴሽንም መሥራችና እስከ ዕለተ ሞታቸው አባል ነበሩ። ዛሬ በሕይወት የሉም። የአርበኞች ማኅበር አባል የነበሩት እኚህ አዛውንት ከአርበኛ ማኅበር በወር 600 ብር ከአነስተኛ የጡረታ ደመወዝ ጋር እንኳን ለሕክምና ለቤት ወጪም የሚሸፍን አልነበረም፡፡ እንዲያውም አፈ ጉባዔው ቢሮ ከመቅረባችን ከአንድ ቀን በፊት በግል ባደረግሁት ጥረት ደጃዝማች ባልቻ ሆስፒታል ተኝተው እንዲታከሙ አድርጌያለሁ። ለረጅም ዓመታት ካቴተር ተሸክመው የሚያደርጉትን የሥቃይ ኑሮ ሊቀንስላቸው ችሏል፡፡ ከቀናት በኋላ ተነጋግረው ይመስለኛል በጦር ኃይሎች ሆስፒታል እንዲታከሙ ተፈቅዷል፣ ከባልቻ ሆስፒታል ለቤታቸው ቀረብ ስለሚል በመጨረሻ ወቅት ተረድተውበታል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጥያቄ በኮሪያ ምድር ለዘመተው ሠራዊታችን የኮሪያ ዘማቾች ማኅበርም በቅርቡ በኢትዮጵያና በኮሪያ መንግሥታት ድጋፍ የተቋቋመ ነው፡፡ እነዚህ ማኅበራት የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ሲደራጅ አንድ ላይ እንደሚጠቃለሉ ይታመናል።

የኮንጎ ዘማቾች አስተዋሽ አላገኙም፣ ገሚሶቹ ኮሪያም የዘመቱ ስላሉ በዚያ ታቅፈዋል፣ ሊቋቋም ይገባዋል፡፡ የሶማሊያ መንግሥት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በመጣስ በተደጋጋሚ በኦጋዴንና በባሌ የወረራ ሙከራ አድርጓል፡፡ ይህም ወደፊት በቬተራንስ አሶሴሽን የሚዘከር ይሆናል። በቅርቡም በሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ ላይቤሪያ፣ ዳርፉር፣ ሶማሊያና አቢየ ግዛት፣ እንዲሁም በኢትዮ-ኤርትራ ውጊያ መስዋዕትነት ለከፈለውና አሁንም ዳር ድንበር በማስከበር ላይ ለሚገኘው ሠራዊታችን በክብር ሲሰናበት መሰባሰቢያ ማዕከል እንዲሆን ነው፡፡ በሠለጠነው ዓለም የየአገሩ መንግሥታት የመከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን እንዲቋቋም ያግዛሉ፣ ሕዝቡም ዓላማውን ተረድቶ የገንዘብና የማቴሪያል ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ግንዛቤ እንዲያገኝ ያስተዋውቃሉ፡፡ የቬተራንስ (የጦር ጉዳተኞች) ቀን፣ እንዲሁም ለአገራቸው ክብር በግዳጅ ላይ ለወደቁ አባላት የሙታን መታስቢያ ቀን በየዓመቱ የየአገሮቹ መሪዎችና ባለሥልጣናት በተገኙበት በደማቅ ሁኔታ ይከበራል፡፡ በተለያዩ የውጭ አገሮች ለወደቁ አባላት በየዓመቱ የመታስቢያ ቀን አላቸው፣ በኢትዮጵያ ለወደቁት የእንግሊዝ ወታደሮች ዊንጌት አካባቢ ባለው መካነ መቃብራቸው ያከብራሉ፡፡

በመሆኑም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትኩረት ሰጥቶ በሚመርጣቸው ሁለት ቀናት የቬተራንስ ቀንና ለወደቁ አባላት የመታሰቢያ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ጠይቀናል። በእንግሊዝ አገር ከ500 በላይ በጎ አድራጎት ድርጅቶ ሲኖሩ የሁሉም የበላይ ጠባቂ ንግሥት ኤልሳቤጥ ናቸው፡፡ እኛም በመተዳደሪያ ደንባችን እንደተመለከተው የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዚዳንት) የበላይ ጠባቂ ናቸው ስለሚል ይኸንኑ እንዲቀበሉልን። የቬተራንስ አሶሴሽን በአምስት ክልሎች መሥራች አባላት አሉት፡፡ በአጠቃላይ በመላ አገሪቱ የሚገኙ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ሠራዊት አባላት “አባል” ይሆናሉ፣ በአሁኑ ወቅት በአገልግሎት ላይ የሚገኙት የመከላከያ ሠራዊት አባላትም “አባል” እንደሆኑ የአሶሴሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ተመልክቷል፡፡ አሁን ድረስ የጡረታ መብትና የሕክምና አገልግሎት የማያገኙ በርካታ አባላት ስላሉ ጉዳዩ ተመርምሮ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲያገኙ፣ እንዲሁም የሠራዊቱ የጡረታ ደመወዝ የአገራችንን ምጣኔ ሀብት ያላገናዘበ መሆኑ ታውቆ ሊያኖር በሚያስችል ደረጃ ተጠንቶ ክፍያው ተገቢ ማሻሻያ እንዲደረግ ጠይቀናል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት በገንዘብ (በጀት) ችግር፣ በቢሮና የመሰብሰቢያ ቦታ ዕጦት የተፈለገውን ያህል መንቀሳቀስ አልተቻለም፡፡ የመከላከያ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ለአሶሴሽኑ ድጋፍ እንደሚስጡ ከመግለጽ ባሻገር የረባ ነገር አልፈጸሙም፡፡ ጉዳዩን በየጊዜው ለመከላከያ ሚኒስትሮችና ለጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሞች አቅርበናል፡፡ ባለፈው ዓመት አቶ ለማ መገርሳን አነጋግረን ቢሮ እንድናገኝ ለቤቶች ኮርፖሬሽን ደብዳቤ ጽፈውልናል፣ ቤቶች ኮርፖሬሽን ውሳኔ መስጠት አልቻለም፡፡ ላቀረብናቸው ሌሎች ጥያቄዎችም ከመከላከያ ካውንስልና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር ተነጋግረው እንደሚገልጹልን ተስፋ ሰጥተውን እልባት ሳናገኝ ቀርተናል፡፡ ረጅም ጊዜ በመፍጀቱ መሥራቾችም እያለፉ በመሆኑ ዓላማውን ከንቱ እያደረገብን ነው። በመሆኑም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ስለሆኑ ስለአሶሴሽኑ መቋቋም ዕውቅና እንዲሰጡ በተደጋጋሚ በደብዳቤ ጠይቀናል፡፡ የኢትዮጵያን የመከላከያ ኃይል የሚያቅፍ አሶሴሽን እንደመሆኑ መጠን በተወካዮች ምክር ቤት የታዛቢነት ቦታ እንዲኖረን ጠይቀናል። የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ያለበትን ሁኔታ ለመንገር በየጊዜው ማብራሪያና መግለጫ ለመስጠት፣ ለማስተዋወቅና ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ ለማድረግ የሚዲያ ሽፋን እንድናገኝ ጠይቀናል።

ከዚህ በላይ የተመለከተውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፣ ስለመቋቋሙ በተለያዩ ጋዜጦች እንዲሠራጭ ተደርጓል። የመከላከያ ፋውንዴሽንም ከእኛ አሶሴሽን ጋር ከጎናችን እንደሚቆም ገልጾልናል፣ ወደፊት መጠቃለል እንዳለበት እናምናለን ዓላማው ተመሳሳይነት አለውና፡፡ በሥነ ምግባር ከአሶሴሽኑ የተለዩትን ጄኔራል መኮንኖችን በመያዝ አዲስ ማኅበር የመሠረቱ የምድር ጦር አባላት አሉ፡፡ በየክልሉ እየተዘዋወሩም ቅጽ ሙሉ መብታችሁን ልናስከብር ነው በማለት ከዚህ ደሃ ወታደር ገንዘብ እንደሚሰበስቡ ይነገራል፡፡ በየክልሉ የሚገኙት አመራሮች እየደወሉ አሳውቀዋል፣ ከእኛ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ገልጸናል፣ ይህንኑ መልዕክት በአካባቢያቸው ላሉትም እንዲነግሩ አሳውቀናል።

የቀድሞ የጦር ኃይሎች አባላት አገልግሎት ላይ በነበሩበት ወቅት የጡረታ መዋጮ ከፍለዋል፣ ሆኖም ባለፈው የኢሕአዴግ መንግሥት በጥላቻና በረቀቀ ብቀላ እንዲዋረዱ ተድርጎ ከፍተኛ የሆነ የመብት ጥሰት ደርሶባቸዋል፡፡ ከሕግ ውጪ የጡረታ መብትም ተከልክለዋል። ነገር ግን ለቀድሞ ታጋዮች በሙሉ የጡረታ መዋጮ ሳይከፍሉ ኢትዮጵያን በሽፍትነት ለዓመታት ሲጎዱ፣ ባንክ ሲዘርፉ፣ ድልድይ ሲያፈርሱ፣ የልማት ተቋማትን ሲያወድሙ ለኖሩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ካዝና ወጪ ተደርጎ እንዲከፈላቸውና ጡረታ እንዲያገኙ በውሳኔ ቁጥር 5/አስ12/ው299/2010 ተወስኗል። ይህን በተመለከተ የኢፌዴሪ አምስተኛው የምርጫ ዘመን የሚኒስትሮች ምክር ቤት 12ኛ አስቸኳይ ስብሰባ ስለቀድሞ ታጋዮች መብት ጉዳይ ችግራቸውን ለመቅረፍ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አጭር የውሳኔ ሐሳብ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ሰኔ 18 ቀን 2010 ዓ.ም. አቅርቧል፡፡ ምክር ቤቱም ከተወያየ በኋላ ከ1983 ዓ.ም. በፊት በትጥቅ ትግል ተሳትፈው በቦርድ ለተሰናበቱ ታጋዮች በትግሉ ከተቀላቀሉበት ጊዜ እየታየ እንዲያዝላቸው፣ ከመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር ታጋዮች ወደ ትግል ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ እስከ ግንቦት ወር 1983 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ለፈጸሙት አገልግሎት በየወሩ መከፈል የሚገባው የአሠሪ መሥሪያ ቤትና የሠራተኛ ድርሻ የጡረታ መዋጮ ታስቦ በመንግሥት እንዲሸፈን፣ እያንዳንዱ የክልል አስተዳደር በዚህ ውሳኔ መሠረት በትግል ላይ ያሳለፉት ጊዜ በጡረታ ሊታሰብላቸው የሚገባቸው የቀድሞ ታጋዮች ዝርዝር መረጃ በማጠናከርና በማረጋገጥ ለመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ እንዲያስተላልፍ፣ የማኅበራዊ ድጋፍ በብሔራዊ ማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ የሚታይ በመሆኑ ከመንግሥት በየዓመቱ የሚመደበው የድጋፍ በጀት በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና በየደረጃው የሚገኙ የክልል ቢሮዎችና ጽሕፈት ቤቶች አስተባባሪነት ክፍያ እንዲፈጸም ተወስኗል።

ር 16 ቀን 2011 ዓ.ም. በቁጥር መ10/ሠጠ35/ተ/2511/11 የቀድሞ ጦር ኃይሎች አባላት ላቀረቡት ቅሬታ ለመከላከያ ሚኒስቴር በተጻፈ አስተያየት፣ 20/45 በሚለው መመርያ መሠረት እየተሠራ መሆኑ፣ ጡረታ አዋጅ ቁጥር 714/2003 የጉዳዩ ባለቤት ከሆነው ከሠራተኛና ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ጋር መነጋገር ተገቢ መሆኑን፣                                                             ከአሥር ዓመት በላይ ላገለገሉ አባላት ይሠራ እንኳን ቢባል የግል ማኅደራቸውን ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህም አራት በመቶ መዋጮ ተመላሽ ማድረጉ ተገቢ ቢሆንም የተሟላ የደመወዝ ሰነድ አለመኖሩ፣ ይህን ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩ ከ1987 እስከ 1989 ዓ.ም. በተለያዩ ምክንያቶች የተሰናበቱ ታጋዮች፣ ከ1993 ዓ.ም. ጦርነት በኋላ በክብር የተሰናበቱ፣ እስከ 2007 ዓ.ም. የኮበለሉና አሁን በምሕረት የተመለሱ፣ እንዲሁም ከ1999 ዓ.ም. በፊት የአራት በመቶ ተመላሽ ከመጀመሩ በፊት የተሰናበቱ በሙሉ ይመለስልን ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ገንዘቡ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም ይህን ሁሉ ሠራዊት ማስተናገድ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ስለዚህ በመንግሥት በኩል ይህ ግንዛቤ ተወስዶ እንደ የማዕረጋቸው የአንድ ጊዜ ድጎማ ወይም መቋቋሚያ ክፍያ ቢደረግ የተሻለ ነው በማለት የዋና መምሪያው ኃላፊ አሳስበዋል። መልካም አማራጭ ነው እንላለን አሁን ድረስ ግን ተግባራዊ አልሆነም። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን  ከቀድሞ ጦር ኃይሎች አባላት በቀረበለት አቤቱታ መሠረት የምርመራ ቡድን በማዋቀርና ምርመራ በማድረግ የምርመራውን ምክረ ሐሳብና የተሰጠ ውሳኔ 13 ገጽ አባሪ አድርጎ ጥቅምት 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በቁጥር ሰመኮ /2.1/ 46/12 ለኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሚኒስቴርና ለኢፌዴሪ ማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በመላክ ውጤቱ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲገለጽ ጠይቋል፡፡ ይህም መልስ ሳይሸጥ ሁለት ዓመት ሊሆን ነው።

ጥቂት ስለኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር

የሠራዊቱ አባላት እያሉ በሙያው ያላለፉ የቤተ ክህነት ሰዎችና ሲቪሎች ሠራዊቱን ወክለው የአርበኞች ማኅበርን እየመሩት ነው፡፡ የአርበኞች ማኅበር የተመሠረተው በማይጨው ጦርነት ወቅት በአምስቱ ዓመት የአርበኝነት ዘመን ሰሜን ሸዋ ነው፡፡ ከድል በኋላ አብዛኛው ወደ ግል ሥራው ሲመለስ የተወስነው በጦር ሚኒስቴር በፈቃደኝነት በውትድርና ቀጠለ፡፡ ከተወስነ ጊዜ በኋላ በርካታ ወገኖች አርበኛ ነበርን እያሉ በማመልከት የሚኒስቴሩን መሥሪያ ቤት በጥያቄ ስላስቸገሩ፣ በጦር ሚኒስትሩ (ራስ አበበ አረጋይ) ጥያቄና በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ ውለታ በማክበር አርበኛነታቸውን እያመሳከረ የሚመዘግብና የሚከታተል ክፍል በማስፈለጉ የአርበኞች ማኅበር ሕጋዊ ሰውነት አግኝቶ፣ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤትም አሁን በሚገኝበት አራት ኪሎ ተቋቁሟል። በአሁኑ ወቅት አባላቱ በሙሉ በሕይወት የሉም፡፡ የመጨረሻ አርበኛ ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ ሕይወታቸው እስካለፈ ድረስ የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ሊቀመንበር፣ መሥራችና አባል ነበሩ፡፡ የአርበኞች ማኅበርን የሚያስተዳድሩት ሰዎች አባቶቻችን አርበኞች ነበሩ የሚሉ ልጆችና የልጅ ልጆች ናቸው፡፡ ለቀጣዩ ትውልድ በወታደራዊ ትምህርትና ዕውቀት የተደገፈ ታሪካዊ ቅርስ ማቆየት ያስፈልጋል፡፡ በተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ሕዝባዊ መድረኮች ስለወታደራዊ ክንውኖች ገለጻ ማድረግ፣ በውጭ አገር ከሚገኙ መሰል ወታደራዊ ቬተራንስ አሶሴሽኖች ጋር አገራችንን ወክለው መወያየትም ሆነ መነጋገር፣ በማናቸውም የቬተራንስም ሆነ ሕዝባዊ በዓላት ላይ ሠራዊቱን ወክሎ መገኘት የሚገባው የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ነው፡፡                                                                                                                                                

በየትኛውም ዓለም እንደሚታየው በቬተራንስ ቀን ከአገሮች መሪዎች ጋር በክብር እንግድነት የሚገኙት የሠራዊቱ አባላት እንጂ ልጆቻቸው አይደሉም፡፡ ዘላቂነት እንዲኖረው ስለሚያስፈልግ ከዚህ በኋላ ሊታረምና ሊስተካከል ይገባል። የሙያው ባለቤት በሆነው ከመከላከያ ሠራዊት በክብር በተሰናበቱት የሠራዊቱ አባላት በተመሠረተው ሕጋዊ ዕውቅና ባገኘው በአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ሥር ሊታቀፍ ይገባዋል፡፡ ዘለዓለማዊ ሆኖ የሚቀጥለውም የሙያው ባለቤት በሆኑት የመከላከያ ሠራዊት አባላት አስተዳደር ሥር ሲሆን ብቻ ነው።

በቅርቡ ከፖስታ ድርጅት ጋር በመነጋገር ቴምብሮች እንዲታተሙ ተድርጓል፡፡ የሚገርመው በሕይወት የነበሩት ብቸኛ አርበኛ ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ በዚህም ተረስተዋል፡፡ ጄኔራል ጃገማ በመጨረሻዎቹ ዘመናቸው በፕሮስቴት ሕመም የአልጋ ቁራኛ ሆኑ፡፡ አርበኞች ማኅበር በወር 650 ብር ይሰጣቸው ነበር፡፡ ሕክምና በተገቢው                                           መንገድ ባለማግኘታቸው በግል ክሊኒኮች በኮንትራት ታክሲ እየተመላለሱ በአምላክ ፈቃድ 96ኛ ዓመታቸውን አክብረዋል፡፡ በሰኔ ወር 2008 ዓ.ም. ባልቻ ሆስፒታል ነፃ ሕክምና እንዲያገኙ ማስፈቀዴን ለአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ማስታወሻ አቅርቤ ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ በጦር ኃይሎች ሆስፒታል ለጥቂት ጊዜ ታክመዋል። በእነ ጄኔራል ካኒንግሃም፣ በእነ ጄኔራል ዊንጌት ስም መንገድና ትምህርት ቤት ሳይቀር ሲሰየም ለአርበኞቻችን ክብር አልተሰጠም፡፡ በዚያ ክፉ ዘመን የሕዝብን መሬት የግላቸው በማድረግ ሕዝብን ያስለቀሱ፣ በአርበኝነት ስም አርበኛውን ሳይቀር ጭሰኛ በማድረግ ግፍ የፈጸሙ አርበኛ ነን ባዮች እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ ባንዳ የነበሩ የተሾሙበትና የተከበሩበት፣ እውነተኛ አርበኛው የተጣለበት ዘመን እንደነበር አይረሳም፡፡ ፋሺስት ጣሊያን እንኳን ያላደረገውን አርበኛው እንደ ሌባ በአደባባይ የተሰቀለበት አሳፋሪ ታሪክም እንዳለን አይዘነጋም፡፡ ይህን ሁሉ ማስከበር የሚቻለው የታሪኩ ባለቤት የሆነው የአገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ሲመራው ነው።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት ለአገሩ አኩሪ ተግባር ሠርቷል፣ የአገሩን ዳር ድንበር አስከብሯል፣ አንድነቷን ጠብቆ ለተከታይ ትውልድ አስተላልፏል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክብርና ዝና ተችሮታል፣ ሰላም የሚገኘው መንግሥት ሁሉንም ዜጋ በእኩል ዓይን ማየት ሲችል ነው፡፡ አሶሴሽኑ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሠለጠነ የአገሪቱን ሠራዊት ያቀፈ ነው፣ ስለዚህ በቅርቡ የተላለፈው የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የአንድነት ጥሪ ለኢትዮጵያ አገሩ ሲሞትና ሲቆስል ሲንገላታ ለኖረው የቀድሞ ሠራዊት በስደት ያሉትን ጭምር ምሕረት ሲያደርግ ነው። በመንግሥት መቋቋም የነበረበትን ታላቅ ሥራ ፈጽመናል፣ ከዚህ በኋላ ሥራውን መንግሥት ተረክቦን እንዲቀጥልበት እናሳስባለን።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የመከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን ዋና ጸሐፊ ሲሆኑ፣ ጽሑፌ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...