Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​መንግሥት ለትርፍ ኅዳግ ቆንጣጭ ሕግ ያውጣልን!

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የታየውን እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ንረት ተከትሎ ገበያውን ለማረጋጋት በመንግሥት በኩል እየተሠራ ነው የሚባለው ለውጥ አምጥቷል ተብሎ አይታመንም፡፡ ለዚህም ገበያው ከመሻሻል ይልቅ ከዕለት ዕለት የዋጋ ንረቱ እየጨመረ መምጣቱ ማሳያ ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ በመንግሥት ድጎማ ይደረግባቸዋል የተባሉ ምርቶች ዋጋቸው አልተረጋጋም፡፡ እንደምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው የምግብ ዘይት ነው፡፡ በአገር ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ምርት የሚያመርቱ የዘይት ፋብሪካዎች ሥራ መጀመራቸው በተገለጸበት በዚህ ወቅት የዘይት ዋጋ አልቀመስ ብሎ ሸማቹን እየፈተነ ነው፡፡

ሰሞኑን መንግሥት ዘይት አስመጣለሁ፣ ገበያውንም አረጋጋለሁ ብሏል፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሰሞናዊ መረጃው አሁን ያለውን አገራዊ የገበያ አሻጥር ከመከላከል ጎን ለጎን መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ከውጭ በማስመጣት የኅበረተሱቡን ኑሮ ለመደጎም እየሠራሁ ነው ብሏል፡፡

‹‹ከውጭ በሚገባ ምርት ብቻ ገበያውን ማረጋጋትም ሆነ የኅብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና የአገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ የማይቻል በመሆኑ በ2013 በጀት ዓመት ሁለት ትልልቅ የዘይት አምራች ፋብሪካዎች ተመርቀው ወደ ሥራ መግባታቸው ይታወቃል፤›› የሚለው መረጃው፣ ፋብሪካዎቹ አስፈላጊው የግብዓት አቅርቦት በአገር ውስጥ እስኪሟላላቸው ድረስ በልዩ ሁኔታ ውጭ ምንዛሪ ተፈቅዶላቸው ድፍድፍ ዘይት ከውጭ በማስመጣት እያጣሩ ለገበያ እንዲያቀርቡ እየተደረገ እንደሚገኝም ያመለክታል፡፡

‹‹በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ጊዜዊ አለመረጋጋት በመጠቀም በሰው ችግርና ሞት የራሳቸውን ኪስ ለማደለብ የሚሠሩ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎችና አከፋፋዮች መኖራቸውን ሚኒስቴሩ ደርሶበታል፤›› በማለትም በአጭር ጊዜ የማያዳግም ዕርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል፡፡

ይኼው የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚገልጸው፣ እየተከሰተ ያለውን የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ መጨመር ለማስተካከል ይረዳ ዘንድ 31 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓት አቅራቢ ድርጅት ከ24 ሚሊዮን ሌትር በላይና በንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን አማካይነት 12.5 ሚሊዮን ሌትር በድምሩ ከ36.5 ሚሊዮን ሌትር በላይ የምግብ ዘይት ግዥ እየተከናወነ ነው፡፡

የግዥ ሥርዓቱ እንደተጠናቀቀ ምርቱ በፍጥነት ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡ የዘይት ምርቱ ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በፍጥነት የሚደርስበት ሥርዓት ቀድሞ የተሠራ በመሆኑ፣ የማጓጓዝ ሒደቱ እንደጠናቀቀ ለኅብረተሰቡ የሚሠራጭ እንደሚሆንም ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ወቅታዊ የዋጋ ንረት በዚህ ብቻ የሚገለጽም አይደለም፡፡ እያንዳንዱ ምርት ዋጋው አስደንጋጭ ሆኗል፡፡ መጨመር የለባቸውም የሚባሉ ምርቶች ሳይቀሩ በገበያ ውስጥ አፍ የሚያስይዝ ዋጋ ይዘው ገበያውን ሲያተረማምሱ እየታየ እንኳን ‹‹ለምን ይህ ሆነ?›› ተብሎ የማያዳግም ዕርምጃ ሲወሰድ አይታይም፡፡ ይህ የዋጋ ጭማሪ በፍፁም ምክንያታዊ ነው ባይባልም፣ በተለይ ከዶላር የምንዛሪ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞና ሌሎች የአገልግሎት ወጪዎች ዋጋ ከፍ ማለት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለዋጋ ንረቱ የየራሳቸውን አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ይሁንና ሆን ተብሎ ገበያውን ለመረበሽ የሚደረጉ ሸፍጦች የዋጋ ንረቱን እንዳባባሱ መረዳት ይቻላል፡፡ በቅርቡ አገር ውስጥ የገባ አርማታ ብረት በየቦታው ተሸሽጎ መገኘቱን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህ በገበያው ውስጥ ብረት ጠፋ ተብሎ ዋጋው እንዲንር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

የሲሚንቶ ገበያ ላይ በተመሳሳይ የሚታየው ንረትም በገበያው ውስጥ ጡንቻ ያላቸው አካላት የፈጠሩት ስለመሆኑ መግለጽ ይቻላል፡፡ ሌሎች ምሳሌዎችም ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የጨው ዋጋ እንዲህ አፍጥጦ የመምጣቱ ጉዳይ በደንብ ከተፈተሸ ገበያ የመረበሽ አባዜ የተጠናወታቸው፣ ስለዜጋና አገር ደንታ የሌላቸው አካላት እጅ ሊኖርበት እንደሚችል መገመት አያቅትም፡፡

ሰበብ እየተፈለገ የሚጨመረው ዋጋ በዘፈቀደ መሆኑ የሚያሳየውም የትርፍ ኅዳግን የተመለከተ ቆንጣጭ ሕግ አለመኖሩ ነው፡፡

የዘይት ጉዳይ ከተነሳም ዘንድሮም ስለዘይት እጥረትና መወደድ እንድናወራ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ ገበያው በአግባቡ እንዲመራ አለመደረጉ ነው፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገበያን ለማረጋጋት ከውጭ ማስመጣቱ የሚደገፍ ቢሆንም፣ ይህ ዓይነቱ ዕርምጃ ዘለቄታ የሌለው መሆኑ ያሳስባል፡፡ ምክንያቱም ገበያን ለማረጋጋት ተብለው የሚወሰዱ ጊዜያዊ ዕርምጃዎች አንዳንዴ ለገበያው ነቀርሳ፣ ለሕገወጦች ደግሞ አላግባብ መበልፀጊያ መሆናቸውን አይተናል፡፡  

ንግድ ሚኒስቴር እንዳለው ዋጋ ተምኖ የሚሸጥ መሆኑ መልካም ነው፡፡ ግን ምን ያህል ይተገበራል? የሚለው አጠራጣሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ከዚህ ቀደም እንዲህ ቢባልም ዋጋው ናረ ምርቱም ጠፋ እንጂ እንደተባለው በሁሉም መሸጫ ሱቆች አልተተገበረም፡፡ አንዳንድ መፍትሔ ተብለው የሚወሰዱ ዕርምጃዎች በአግባቡ ካልተያዙና ሥርጭታቸው ላይ ካልተሠራ ችግሩን ያብሳልና ይህ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ በቂ ምርት ማቅረብና በአግባቡ ለሸማቹ ስለመድረሱ ማረጋገጥም ያስፈልጋል፡፡

የገበያ ማረጋጋት ሥራው ዘላቂ ካልሆነም መልሶ ገበያውን ማመስ ይሆናልና ይህ እንዳይሆን በአግባቡና በጥንቃቄ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት ምርቱን ከውጭ ማስገባት ብቻ ሳይሆን በአግባቡ እንዲሠራጭ፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን መሥራትም አለበት፡፡

መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች በአግባቡ ሸማቾች ጋር የሚደርሱበት አሠራር መዘርጋትም አለበት፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ሸማቾችን እያጎበጠ ያለው የኑሮ ውድነት እንዳይባባስ እየተወሰዱ ነው የሚባሉ ዕርምጃዎች በግልጽ መታወቅና በየጊዜው ተገቢ መረጃ ሊሰጥባቸው ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ሆን ተብለው የሚሠሩ ሸፍጦችን በማነፍነፍ ምንጩን መዝጋትና ገበያው አማራጮች እንዲኖሩት ማድረግ ይገባል፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት