Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከወሰን ማስከበርና ከካሳ አከፋፈል ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደገጠሟቸው ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ቦታዎች ሙሉ በሙሉ አለመከለላቸው፣ ከወሰን ማስከበርና ከካሳ አከፋፈል ጋር ያሉ ችግሮች አለመቀረፋቸው በፓርኮቹ አፈጻጸም ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተገለጸ፡፡

ይህ የተገለጸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት የሥራ እንቅስቃሴውንና የዕቅድ አፈጻጸሙን በተመለከተ፣ ዓርብ ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአጠቃላይ በሁሉም የመንግሥት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከወጪ ንግድ 247.9 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ አስታውቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የበጀት ዓመት ዕቅዱን ተግባራዊ በማድረግ የተገኙ ውጤቶች እንደተጠበቁ ቢሆንም፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችም እንደነበሩ ተጠቅሷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የትራንስፎርሜሽንና የዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ ማሞ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ያለውን የመሬት ይዞታ ማስከበር በዋነኛነት የተሰጠው ለከተማ አስተዳደሮች እንደሆነ ጠቁመው፣ ሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች የተሰጣቸው መሬት የሚታወቅና የይዞታ ማረጋገጫ ያላቸው ቢሆኑም፣ ነገር ግን የኢንዱስትሪ ፓርኮቹን ይዞታ በማስከበር ረገድ ዕክሎች እንዳጋጠሙ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በፓርክ አስተዳደሩ አካላት ላይ ሥጋት መፈጠሩን፣ በተለይም ከካሳ ክፍያና ከይዞታ ይገባኛል ጋር በተያያዘ ያለው ጉዳይ በብዙ ፓርኮች ያልተፈታ ችግር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በዚህም ሳቢያ በፓርኮች የሥራ እንቅስቃሴ ላይ እክል ሲፈጠር እንደቆየ የተብራራ ሲሆን፣ በዕቅድ አፈጻጸሙ ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ ማሳደሩ ተጠቅሷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ይህ ዓይነቱ ችግር በስፋት እንደሚስተዋል የተገለጸ ሲሆን፣ ለአብነት በድሬዳዋ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ የውኃ ጉድጓዶችን ለመቆፈር የውኃ መስመር በሚያልፍበት ቦታ ላይ ያሉ ያለካሳና ለይገባኛል ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠት ጊዜ መውሰዱን፣ በዚህም ምክንያት ፓርኮቹ ውስጥ የሚገኙ አልሚዎችን ወደ ሌሎች ፓርኮች እስከ መዘዋወር ያደረሰ ችግር እንደተፈጠረ ተመላክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አራት ፓርኮች እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ አዲሱ እነሱም ቂሊንጦ፣ ቦሌ ለሚ፣ አይሲቲ ፓርክና አዲስ ኢንዱስትሪ መንደር ናቸው ብለዋል፡፡ አዲስ አበባ በአገሪቱ ውስጥ በቁጥር በርከት ያለውን የኢንዱስትሪ ፓርክ ቁጥር እንደመያዙ የተሻለ ድጋፍ ሊደረግበት የሚገባ ቢሆንም፣ ውስብስብ ችግሮች ከሚገኝባቸው አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በአዲስ አበባ ከሚገኙት ፓርኮች ሙሉ በሙሉ አጥሩ የተከለለ ፓርክ እንደሌለ የገለጹት ኃላፊው፣ ሆኖም ኮርፖሬሽኑ ውል ሲዋዋልና ፓርኮቹ ሲገነቡ አጥራቸውን ጭምር ገንብቶ ለማስረከብ የተደረገ እንደነበር አቶ አዲሱ አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ኮንትራክተሮች በግንባታ ውላቸው መሠረት አጥር ለመገንባት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የይዞታ ይገባኛል ጥያቄዎች እንደሚነሱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ኮርፖሬሽኑ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአንድ አካባቢ ሲገነባ የአካባቢውን ኅብረተሰብ ለመጥቀም እንደመሆኑ መጠን፣ ሁሉም ፓርኮች በሚገነቡበት አካባቢ ላይ ያሉ የልማት ተነሺዎች ፓርክ ውስጥ በሚገኙ ሁሉም ሥራዎች እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ ይህንን በማድረግ ሒደት ፓርኩ የሚጠበቅበትን እያደረገ ቢገኝም ሆኖም ግን የከተማ አስተዳደሩ የይዞታ ይገባኛል ጥቄዎችን ከመመለስ አንስቶ ከፓርኩ ውጪ የሚገኙ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን የማከናወን ሒደት ላይ ውስንነቶች አሉበት፤›› ብለዋል፡፡

የቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ትንሳዔ ይማም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የአሥር ዓመቱን የኮርፖሬሽኑን መሪ ዕቅድ መሠረት በማድረግ ኢንዱስትሪ ፓርኩ ከሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሪና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ተያይዞ የተቀመጡ ዕቅዶችን በማስፈጸም ረገድ በርካታ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ከዚህ ባሻገር ኢንዱስትሪ ፓርኩ የተለያዩ አካላት ማለትም ከመሬት አስተዳደር ጋር ተያይዞ ከከተማ አስተዳደሩ፣ ከክፍለ ከተማና የወረዳ አስተዳደሮች ጋር በቅርበት የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታትና ከእዚያም በላይ ካሳ ካልተከፈላቸው ነዋሪዎች ጋር በተያያዘ፣ እንዲሁም ካሳ ተከፍሏቸው በድጋሚ ከሚመጡ ጋር በተገናኘ፣ ካሳ ያልተከፈላቸው በከተማ አስተዳደሩ በኩል በፍጥነት ካሳ እንዲከፈላቸውና ምትክ ቦታ እንዲመቻችላቸው ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የማመቻቸት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እንዳለ ያስታወሱት አቶ ትንሳዔ፣ በአዋጁ ውስጥ የከተማ አስተዳደሮች ለፓርክ ልማት የሚሆን መሬት ካሳ ከፍለው፣ የምትክ መሬት ካስፈለገ ሰጥተውና ከይገባኛል ነፃ አድርገው ያዘጋጃሉ የሚል እንደሠፈረ ገልጸዋል፡፡ ከእያንዳንዱ የከተማ አስተዳደር ጋር መሬትን በፕላን ፎርማት ሲረከቡ የሚገባ ውል እንዳለ የገለጹ ሲሆን፣ በውሉ ላይ እንደተቀመጠው የካሳ ክፍያንና መሬትን ከይገባኛል ነፃ አድርጎ የማስረከብ ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ስለዚህ ከዚህ አንፃር የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ፣ ካሳ ሊከፈላቸው የሚገቡ ገበሬዎች እንዳሉና ሊከፈላቸው እንደሚገባ፣ ካሳ ይከፈላችኋል ተብለው ሰርተፊኬት የተሰጣቸው እንደሚገኙ፣ ኮርፖሬሽኑ መሬቱን ያለማ ቢሆንም፣ ካሳ ያልተቀበሉ አርሶ አደሮች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም በከተማ አስተዳደሩ በ2011 ዓ.ም. በወጣ የካሳ አከፋፈል መመርያ መሠረት የፕሮጀክቱ ባለቤት ካሳ ከፍሎ ሥራ መጀመር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኩ ያለበትን መሬት ከተረከበ ከሰባትና ከስምንት ዓመት በፊት እንደሆነ ያስታወሱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ የኮርፖሬሽኑ የሕግ ማዕቀፍም ካሳ ለመክፈል የሚፈቅድ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች