ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በ2013 በጀት ዓመት በዓይነት ገቢ የተደረጉ ንብረቶችን ጨምሮ፣ በሙስናና በሌሎች የተደራጁ የኢኮኖሚ ወንጀሎች የተመዘበረ 2,162,175,071 ብር የሚገመት ሀብት ማስመለስ መቻሉን አስታወቀ፡፡
ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በድረ ገጹ እንዳስታወቀው፣ በ2013 በጀት ዓመት በወንጀል ፍሬ የተገኘን ሀብት ከማስመለስ ጋር ተያይዞ ከፍተኛ መጠን ያለው ሀብት ወደ መንግሥትና ሕዝብ እንዲመለስ አድርጓል፡፡ እንዲመለስ ከተደረገው ጠቅላላ ሀብት ውስጥ 68‚949‚567.52 ብር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት በተሰየመው የሕወሓት ስም የተገኘ መሆኑንና በሕግ አግባብ ወደ ምርጫ ቦርድ ገቢ መደረጉን ጠቁሟል፡፡
በጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ዓለም አንተ አግደው እንዳብራሩት፣ በአገር ኢኮኖሚና ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ከባባድ ወንጀሎችን በአግባቡ ለመከላከል፣ በአጥፊዎች ላይ ከሚጣለው ከእስርና ከገንዘብ ቅጣት በተጨማሪ በወንጀል ያገኙትንና ወንጀል ለመሥራት የዋለን፣ በሕዝብና መንግሥት ላይ የደረሰን ጉዳት ለማካካስ ሀብቱን በምርመራ ለይቶና በአግባቡ ይዞ በማቆየት ሀብቱን በማስመለስ በ2013 በጀት ዓመትም 2,162,175,071 ብር የሚገመት ሀብት ለሕዝብና መንግሥት ገቢ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም 1,369,187,672 ብር ደግሞ ለሕዝብና መንግሥት ገቢ ለማድረግ በተለያየ ደረጃ በሒደት ላይ እንደሚገኝ፣ 5,763,316,448 ብር የሚገመት ሀብት በወንጀል ለደረሰ ጉዳት ማካካሻ በፍርድ ቤት እንዲታገድ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የተለያየ መጠን ያለው ገንዘብን ጨምሮ፣ ብዛት ያላቸው ሕንፃዎችና የተለያዩ ንብረቶችም ለወንጀል መፈጸሚያ እንዳይውሉ ለመከላከል ሲባል ከተጠርጣሪዎች እጅ ወጥተው በሦስተኛ ወገን እንዲተዳደሩ ተደርገዋል፡፡ ከአገር የሸሸ ሀብትን ለማስመለስም ከተለያዩ አገሮች መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል፡፡
ንብረትነታቸው የትራንስ ኢትዮጵያ የሆኑና ግምታቸው ሁለት ቢሊዮን ብር የሆኑ 179 የደረቅና የፈሳሽ ከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችን በፍርድ ቤት የሕግ ትብብር ለጂቡቲ መንግሥት ጥያቄ በማቅረብ ማስመለስ መቻሉን አቶ ዓለም አንተ አስረድተዋል፡፡