በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ገበያ ውስጥ የሚገቡ ኩባንያዎች የማቋቋሚያ ካፒታል መጠን ሊጨምር መሆኑ ተጠቆመ፡፡
ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቅርበት ካላቸው ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ እስካሁን ሲሠራበት የነበረው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የመመሥረቻ ካፒታል እንዲሻሻል ተወስኖ በዚሁ መሠረት አዲስ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የማቋቋሚያ ካፒታል መጠን ይፋ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ፣ አዲስ ለሚመሠረቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የማቋቋሚያ ካፒታል አሁን በሥራ ላይ ከሚገኘው የካፒታል መጠን ከፍተኛ ጭማሪ ይደረግበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በሥራ ላይ ያሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ካፒታላቸውን እንዲያሳድጉ ይደረጋል፡፡
ሥራ ላይ ባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት፣ ሕይወት ነክና ሕይወት ነክ ያልሆነ የኢንሹራንስ አገልግሎትን አጣምረው ለሚሰጡ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ይጠየቅ የነበረው የመመሥረቻ ካፒታል መጠን 65 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሕይወት ነክ ያልሆነ የኢንሹራንስ አገልግሎትን ደርበው የሚሠሩ ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ የአሥር ሚሊዮን ብር ካፒታል ይጠየቅ ነበር፡፡ ይህም ሁለቱን የኢንሹራንስ አገልግሎቶች አጣምሮ ለመስጠት 75 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የሚጠየቅበት ነበር፡፡
አሁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣዋል ተብሎ በሚጠበቀው መመርያ የሕይወትና ሕይወት ነክ አጣምረው ለሚሠሩ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ካፒታላቸው ከሦስት እጅ በላይ ሊጨምር እንደሚችል የሚጠቁሙት ምንጮች፣ ለሕይወት ኢንሹራንስ በተናጠል ይጠየቅ የነበረውም የተከፈለ ካፒተል መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ሁለቱን የመድን አገልግሎቶች እየሰጡ የሚገኙት 11 ሲሆኑ፣ ሰባቱ ሕይወት ነክ ያልሆነ ኢንሹራንስ የሚሰጡ ናቸው፡፡
ከ1983 ዓ.ም. ወዲህ የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንዲቋቋሙ ሲፈቀድ በወቅቱ የኢንሹራንስ ኩባንያ ለማቋቋም ያስፈልግ የነበረው የካፒታል መጠን ሦስት ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡
በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች ማቋቋሚያ የተከፈለ ካፒታል መጠን ከ500 ሚሊዮን ብር ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ካወጣው መመርያ ጋር ተያይዞ፣ በመቋቋም ላይ ያሉ ባንኮች በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል ባንኮቻቸውን መመሥረት እንዲችሉ የተሰጠው የጊዜ ገደብ እየተጠናቀቀ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የባንኮች ማቋቋሚያ የካፒታል መጠን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል ሲወስን፣ በመቋቋም ላይ የሚገኙ ባንኮች ግን በነባሩ መመርያ በ500 ሚሊዮን ብር በተከፈለ ካፒታል እንዲቋቋሙ ዕድል ሰጥቶ ነበር፡፡
በዚህም መሠረት በመቋቋም ላይ ያሉ ባንኮች በስድስት ወራት ውስጥ 500 ሚሊዮን ብር ካፒታል አሟልተው የቀረቡ ባንኮች ምዝገባው የሚፈጸምላቸው ሲሆን፣ ይህ ካልሆነ ግን አዲስ በወጣው መመርያ መሠረት ባንኮቻቸውን ማቋቋም የሚችሉት የተከፈለ አምስት ቢሊዮን ብር ሲያሟሉ ብቻ ነው፡፡
በዚህ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ መሠረት በመቋቋም ላይ ካሉት ባንኮች ውስጥ አብዛኛዎቹ የሚፈለግባቸውን አሟልተው ለምዝገባ የቀረቡ ሲሆን፣ ጥቂት በምሥረታ ላይ የነበሩ ባንኮች ግን በ500 ሚሊዮን የተከፈለ ካፒታል ለመቋቋም የተሰጣቸውን ዕድል ባለመጠቀማቸው በመዋሃድ ይቀርባሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ለመቀላቀል በተለያየ የዝግጅት ደረጃ ላይ የሚገኙ ከ16 በላይ ባንኮች አሉ፡፡