Wednesday, February 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግሉ ዘርፍ በጤና ኢንቨስትመንት እንዲሠማራ መንግሥት ዘርፉን በልዩ ሁኔታ እንዲያበረታታ ተጠየቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግሉ ዘርፍ በጤና ኢንቨስትመንት ተሳትፎው እንዲጎለብት፣ መንግሥት ዘርፉን በልዩ ሁኔታ እንዲያበረታታ ተጠየቀ፡፡ ኦርቢት ሔልዝ የዲጂታል ጤና ልማት ድርጅት ከዱባይ ቻምበርና ሃንስ ሴይድል ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር፣ የተለያዩ የጤና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ “ጤና አዋጭ የኢኮኖሚ ምሰሶ” በሚል ርዕስ የተሰናዳ የፓናል ውይይት ማክሰኞ ነሐሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል አከናውኗል፡፡

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) የጤና ዘርፍ ብዙውን ጊዜ እንደ አንድ የኢንቨስትመንት ዘርፍ ያለማየት ልምድና አተያይ እንዳለ ገልጸው፣ በተደረጉ ጥናቶች እንደተረጋገጠው የጤናው ዘርፍና በውስጡ የሚከናወኑ ልማቶች ለአንድ አገር ጠንካራ የኢኮኖሚ ምሰሶ ከሚባሉት ጉዳዮች ውስጥ የሚመደቡ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የግሉ ዘርፍ በጤናው ዘርፍ በስፋት እንዲሳተፍ መደረጉ በአንድ አገር የሚሰጠውን የዘርፉን አገልግሎት ብቁና ተወዳዳሪ የሚያደርግ እንደሆነ ያስታወቁት ሚኒስትሯ፣ ከዚህም በሻገር ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠርና የዲጂታል ዘርፉን አቅም በማጎልበት ውጤታማ ሥራ ለማከናወን የሚያስችል እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የተለያዩ ተቋማት በመቀናጀት የሚያደርጉት ዘርፉን የማሳደግ ርብርቦሽ፣ የሚደረገውን የጤና አገለግሎቶች ተደራሽነትና መንግሥት በስፋት ያልዳሰሳቸውን የጤና አገልግሎት ዓይነቶች ለማገዝ የሚረዳ እንደሆነ ሚኒስትሯ አስረድተዋል፡፡

ዲጂታል የጤና አገልግሎቶችን ማስፋፋት ዘርፉን ወደ ፊት እንዲጓዝ ከሚረዱት ጉዳዮች ዋነኛው እንደሆነ በመድረኩ የተነሳ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚታሰበውን ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ሥርዓት ለማስፋፋት የግሉ ዘርፍ ሚናም ጉልህ እንደሆነ ተብራርቷል፡፡

የኦርቢት ሔልዝ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓዚዮን ቸርነት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የጤናው ዘርፍ ከኢኮኖሚው ገንዘብ የሚወስድ እንጂ ለኢኮኖሚው አበርክቶት ያለው ዘርፍ ተደርጎ አይወሰድም፡፡ ነገር ግን የጤናው ዘርፍ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የራሱ የሆነ ሚና ያለው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ጤናማና አምራች የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር፣ የጤናው ዘርፍ አንዱ ለኢኮኖሚ ግንባታ ጉልህ ሚና ከሚጫወቱ መካከል መሆኑን ሊታወቅ እንደሚገባና ይህም ከሥራ ፈጠራ፣ ከዲጂታል አገልግሎት መስፋፋትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የዘርፎች ቅንጅት በተለይም በጤናው ዘርፍ ያለው በሚጠበቀው ልክ የጎለበተ እንዳልሆነ የጠቆሙት አቶ ፓዚዮን፣ ይህ ፓናል በዋነኛነት ሲዘጋጅም የተለያዩ ዘርፎች ጤናን በተመለከተ እንዴት ተቀራርበው ሊሠሩ ይገባል የሚለውን በአንድ ጠረጴዛ አገናኝቶ ወደ ቅንጅታዊ መንገድ ለመምራት ከማሰብ በመነጨ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በአንድ ዘርፍ የሚመጣ ለውጥ ተቋማት ተገናኝተው በመጀመርያ ሲመክሩበትና ምን እየተሠራ ነው? ምንስ ክፍተት አለብን? የሚለውን ከመነጋገር የሚነሳ እንደሆነ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ከዚህም በመነሳት ፖሊሲዎችንና መመርያዎችን ተፈጻሚ በሚሆኑበት ልክ ለማዘጋጀት እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡

የውጭ ባለሀብቶች በጤናው ዘርፍ ከአገር ውስጥ ባለሀብቶችና የጤና ባለሙያዎች ጋር በጥምረት እንዲሳተፉ ማድረግ ኢኮኖሚውን ለመገንባት ከሚያደርገው አስተዋጽኦ ባሻገር፣ ዘርፉን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አቶ ፓዚዮን ገልጸዋል፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች እንዳነሱት መንግሥት በጤናው ዘርፍ ለመሠማራት ፍላጎት የሚያሳዩ ባለሀብቶችን ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ የጠየቁ ሲሆን፣ ይህም ለልማት የሚሆኑ መሬቶችን ከማዘጋጀት አንስቶ በንግድ ባንኮች ተመጣጣኝ የወለድ መጠን ያለው ብድር እስከ ማመቻቸት የሚደርስ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች