Wednesday, September 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማዕድን ሚኒስቴር ለቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ልማት የሰጠውን የማስጠንቀቂያ ጊዜ ገደብ አራዘመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኩባንያው የፋይናንስ ችግሩን የሚቀርፍ 356 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን አስታውቋል

የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ከፊ ሚነራል በተባለው የእንግሊዝ ኩባንያ አማካይነት የሚካሄደው ቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ልማት በዕቅድ መሠረት እየተከናወነ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ ለኩባንያው ሰጥቶ የነበረውን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የጊዜ ገደብ አራዘመ።

የማዕድን ሚኒስቴር የወርቅ ማዕድኑ ሳይለማ ለስድስት ዓመታት በመጓተቱ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ለኩባንያው ሰጥቶ የነበረ ሲሆንኩባንያው የገጠመውን ችግር ፈቶ ወደ ሥራ ለመግባት ተጨባጭ ጥረቶችን በማድረጉ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ለተወሰኑ ወራት እንዲራዘምለት የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መወሰኑን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል።

ኩባንያው የማዕድን ልማቱን ለማከናወን ያልቻለው በገጠመው የፋይናንስ ችግር ሲሆን፣ ይኼውም በአገሪቱ ካለው ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ጋር የሚገናኝ መሆኑን የኩባንያው ኃላፊዎች ይገልጻሉ። 

የኩባንያውን ምክንያት ያልተቀበለው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር፣ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ለኩባንያው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ (Letter of Notice) ሰጥቶ ነበር።

በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ስመኝ ውቤ የተጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ኩባንያው የወርቅ ማዕድን ልማቱን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ፋይናንስ አፈላልጎ እስከ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ የማይገባ ከሆነ፣ በማዕድን አዋጁ መሠረት አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ ያስገነዝባል።

ኩባንያው የወርቅ ማዕድን የማምረት ፈቃዱን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ ... በሚያዝያ ወር 2015 ቢያገኝም፣ ላለፉት ስድስት ዓመታት ወደ ምርት አለመሸጋገሩን የሚኒስቴሩ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይገልጻል። 

የወርቅ ክምችቱን ለማምረት የሚያስፈልገውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ማግኘት ባለመቻሉ ኩባንያው ወደ ማምረት ሥራ መሸጋገር አለመቻሉ የታወቀ ሲሆንየማዕድን ሚኒስቴር በጻፈው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ እስከ ሰኔ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የሚያስፈልገውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ኩባንያው አግኝቶ ወደ ሥራ ካልገባ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ የማዕድን አዋጁን አንቀጽ 46(3) በመጥቀስ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።

የአዋጁ አንቀጽ 46(3) ፈቃዱን የሰጠው አካል የማዕድን ማምረት ፈቃዱን ከመሰረዙ ወይም ከማገዱ አስቀድሞ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ለባለ ፈቃዱ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ሲሆን፣ ይኼንንም ለማድረግ ከሚገደድባቸው ምክንያቶች አንዱ ባለፈቃዱ በገባው ውል መሠረት ወደ ምርት ሒደት መግባት ካልቻለ፣ ለማምረት የሚያስፈልገውን የፕሮጀክት ፋይናንስ ካላገኘና የምርት ሒደቱ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ከታወቀ የሚሉት ይገኙበታል።

ማስጠንቀቂያ የደረሰው ኩባንያ በተሰጠው የጊዜ ገደብ የመፍትሔ ዕርምጃ ካልወሰደ ወይም የገጠመውን ችግር በተመለከተ በበቂ ምክንያት ፈቃድ ሰጪውን አስረድቶ ማስጠንቀቂያው ቀሪ እንዲሆን ካልተደረገ በስተቀር፣ ሚኒስቴሩ የሰጠውን ፈቃድ መሰረዝ እንደሚችል በአዋጁ ተደንግጓል።

ኩባንያው ማስጠንቀቂያው ከደረሰው በኋላ ባደረገው ሰፊ ጥረት የወርቅ ማዕድን ልማቱን ለማከናወን የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለማግኘት የሚያስችል መተማመኛ እንዳገኘ፣ ይህንንም ለሚኒስቴሩ በዝርዝር በማሳወቁ የማዕድን ሚኒስቴር የሰጠውን የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የጊዜ ገደብ ለአጭር ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑንና ለኩባንያው ማሳወቁን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል።

በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ዴኤታዋ ወ/ሮ ስመኝ ተፈረሞ ነሐሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ለኩባንያው የተላከው ደብዳቤ፣ እስከ መጪው ጥቅምት 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የጊዜ ማራዘሚያ መፈቀዱን ያመለክታል።

‹‹ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በሐምሌ በጻፋችሁት ደብዳቤ የጠየቃችሁን የጊዜ ማራዘሚያ በጥንቃቄ በመገምገም ... እስከ ኦክቶበር 31 ቀን 2021 ድረስ የጊዜ ማራዘሚያ እንዲሰጣችሁ ተወስኗል። የጊዜ ማራዘሚያው የተፈቀደው በዚህ ጊዜ ውስጥ ለማዕድን ልማቱ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ በማፈላለግ ወደ ሥራ እንደምትገቡ በተደረሰው የጋራ መግባባት መሠረት ነው፤›› በማለት ደብዳቤው ይገልጻል።

የከፊ ሚኒራል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሃሪ አዳምስ ሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ ለቱሉ ካፒ የወርቅ ልማት የሚያስፈልገው ፋይናንስ ከተለያዩ ተቋማት መገኘቱን አስታውቀዋል።

እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ የቱሉ ካፒ የወርቅ ልማትን ለማስጀመር 356 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስ መገኘቱን፣ ከዚህ ውስጥም 63 በመቶ የሚሆነው ቅድመ ሁኔታን መሠረት አድርጎ ፀድቋል።

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ሕግ የተቋቋመው የቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ኃላፊነቱ የተወሰነ ማኅበር የሥራ ኃላፊ ከበደ ኃይሉ (/)፣ ፕሮጀክቱን ለማስጀመር የሚፈለገው ፋይናንስ መገኘቱንና በኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማት በኩል መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች ከተከናወኑ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ለመጀመር እንደሚቻል ገልጸዋል።

ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሚጠበቀው ፈቃድ በወቅቱ ከተገኘና በሌሎች የመንግሥት ተቋማት መፈጸም ያለባቸው ጉዳዮች በፍጥነት ከተከናወኑ፣ ፕሮጀክቱን ማስፈጸም እንደሚቻል አስረድተዋል።

የከፊ ሚነራል ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሃሪ አዳምስ በሰጡት አስተያየትም የተገኘው ገንዘብ የቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ልማትን ለማስጀመር የሚያስፈልጉ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላትና የኦፕን ፒት የወርቅ ልማቱን ለማስጀመር፣ እንዲሁም በከርሰ ምድር ወርቅ ልማቱ ላይ ቅድመ ሥራዎችን ለማከናወንና አጠቃላይ ልማቱን በመጪው ጥቅምት ወር ለማስጀመር የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል።

በቱሉ ካፒ የወርቅ ክምችት መኖሩ ከተረጋገጠ 70 ዓመታት በላይ ቢያልፉምየወርቅ ክምችቱን ለማውጣት ለመጀመርያ ጊዜ ሙከራ የተደረገው ... 1930ዎቹ ውስጥ በጣሊያን ኩባንያ አማካይነት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። 

ይህ ሙከራ ብዙም ውጤት ሳያስገኝ የወርቅ ክምችቱ ለበርካታ ዓመታት ሳይለማ ቆይቶ ... 2009 ኖዮታ ሚነራል በተባለ ኩባንያ በቱሉ ካፒ አካባቢ የማዕድን ፍለጋ ፈቃድ በመውሰድ፣ ሰፊ የፍለጋ ሥራና የጉድጓድ ቁፋሮ በማካሄድ ... 2012 ከፍተኛ የወርቅ ክምችት መኖሩን ካረጋገጠ በኋላ ወደ ምርት የመሸጋገር ሒደት ጀምሮ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይሁን እንጂ ኖዮታ ሚነራል ኩባንያ በአካባቢው ያገኘውን የወርቅ ክምችት መጠን በማስተዋወቅ በክምችቱ ላይ የነበረውን ሕጋዊ የማልማት ፈቃድ ተንተርሶ፣ የኩባንያውን 75 በመቶ ድርሻ ... 2013 ከፊ ሚነራል ለተባለው ለአሁኑ ኩባንያ እንደሸጠ መረጃው ይገልጻል።

በቀጣዩ ዓመትም የቀረውን 25 በመቶ ድርሻ ለዚሁ ኩባንያ አስተላልፎ ከኢትዮጵያ የወጣ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ... 2015 ከፊ ሚነራል ለተባለው ኩባንያ በቱሉ ካፒ የተገኘውን የወርቅ ክምችት አምርቶ ለገበያ እንዲያቀርብ 20 ዓመት የሚቆይ የከፍተኛ ማዕድን ልማት ፈቃድ ሰጥቷል።

ኩባንያው ይህንን ፈቃድ ካገኘ በኋላ ወደ ምርት ለመግባት የተለያዩ ጥረቶችን ያደረገ ቢሆንም፣ ፈቃዱን ከወሰደበት ጊዜ አንስቶ ላለፉት ስድስት ዓመታት ግን ተጨባጭ ወደ ሆነ የማምረት ሥራ አልተሸጋገረም። 

የቱሉ ካፒ የተረጋገጠ የወረቅ ክምችት 1.7 ሚሊዮን ኦንስ እንደሆነ የከፊ ሚነራል መረጃ የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህ የወርቅ መጠን በአንድ ጊዜ ወጥቶ ጥቅም ላይ ባይውልም፣ አሁን ባለው ዓለም አቀፍ የወርቅ አማካይ ዋጋ መሠረት ሲሰላ ግን 2.5 ቢሊዮን ዶላር ወይም በወቅቱ የብር ምንዛሬ 109 ቢሊዮን ብር እንደሚያወጣ ይገመታል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች