ላለፉት ሁለት ዓመታት የተከናወነውን የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ተከትሎ፣ የኢትዮጵያን ቡና የሚገዙ አገሮች ቁጥር ከአምስት ወደ 31 ለማሳደግ እንደተቻለ ተነገረ፡፡
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የኢትዮጵያ ቡና ጥራትና ደረጃው ተስተካክሎ ለውጭ ገበያ እንዲቀርብና የተሻለ ዋጋ ማግኘት አለበት የሚለውን ታሳቢ በማድረግ፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከተደረጉት ሥራዎች መካከል የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር (cup of excellence) አንዱ ነው፡፡
የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ከመደረጉ በፊት አገሪቱ በዓመት ውስጥ የምትልከው ቡና ከ200 ሺሕ ቶን እንደማይበልጥ ያስታወሱት አዱኛ (ዶ/ር)፣ ውድድሩ መደረግ ከተጀመረ አንስቶ ከ248 ሺሕ እስከ 270 ሺሕ ቶን የሚደርስ ቡና በተከታታይ ሁለት ዓመታት ውስጥ በመሸጥ፣ በአገሪቱ የቡና ኤክስፖርት ታሪክ ከፍተኛ የተባለውን 907 ሚሊዮን ዶላር በ2013 ዓ.ም. ማጠናቀቂያ ለማግኘት እንደተቻለ አስታውሰዋል፡፡
የገበያ አድማስ ከማስፋት አኳያም የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር መምጣቱን ተከትሎ፣ ላለፉት 20 ዓመታት የኢትዮጵያን ቡና በተከታታይ ሲገዙ የነበሩት አምስት አገሮች እንደነበሩና እነርሱም ሳውዲ ዓረቢያ፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ አሜሪካና ጀርመን ናቸው፡፡ ሆኖም ከውድድሩ መምጣት ጋር ተያይዞ የቡና ገዢ አገሮች ቁጥር ከአምስት ወደ 31 ከፍ እንዳለ ተገልጿል፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በኦንላይን ጨረታ የተሳተፉት ከ130 እስከ 160 የሚደርሱት ቡና ገዢዎች ከ33 የተለያዩ አገሮች የተወጣጡ እንደነበሩ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የኢትዮጵያ ቡና ገዢ አገሮች መዳረሻ ቁጥር ከፍተኛ በሆነ መልኩ ለማሳደግ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡
የቡና መዳረሻ አገሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ አገሪቱ ያላትን ምርት በከፍተኛ ሁኔታ እንድትጨምር፣ ጥራቱንም በዚያው ልክ ለማስቀጠል የሚያግዝ ነው ያሉት አዱኛ (ዶ/ር)፣ የገበያ አድማስ እንዲሰፋ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ሲደረግ በዋነኛነት አራት ነገሮችን ትኩረት አድርጎ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ አንደኛ አገሪቱ ያላትን እምቅ አቅም አውጥቶ ለመጠቀም በማሰብ እንደሆነ፣ ይህም ልዩ ጣዕም ያላቸውን የቡና ዝርያዎች ለይቶ በማውጣት የማብዛት ሥራ ተጠቃሹ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተመረቱ የሚገኙት የቡና ዝርያዎች ያረጁና በ1974 ዓ.ም. አካባቢ የተተከሉ እንደሆነ፣ ከዛ ጊዜ አንስቶ ምንም ዓይነት ለውጥ ያልተደረገባቸው ዝርያዎች እንደሆኑ ያስታወሱት አዱኛ (ዶ/ር)፣ እነዚህን ዝርያዎች መቀየር አለባቸው የሚለው ታምኖበት እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የቡና ግብይት ሰንሰለቱ የተራዘመና ውስብስብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ቡና አምራች አርሶ አደሩ ቡናና የሰብል አህል አምርቶ በዋጋ የሚያገኘው ልዩነት ለውጥ የሌለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የቡና መሬቱን ለጫትና ባህር ዛፍ ልማት ሲያውል እንደቆየ ያስታወቁት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንን አርሶ አደር ወደ ቡና ልማት ለመመለስ ያመረተው ምርት በተሻለ ዋጋ የሚሸጥበትን መንገድ ለማመቻቸት አስፈላጊ መሆኑን በማመን የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር ተግባራዊ ማድረግ ታምኖበታል ብለዋል፡፡
በመጀመሪያው ዙር ውድድር አንደኛ የወጣው አርሶ አደር አምስት ኬሻ (300 ኪሎ) ቡና በመሸጥ ስድስት ሚሊዮን ብር እንዳገኘ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ቁጥሩ ጭማሪ በማሳየት 19 ኬሻ (1,140 ኪሎ) በመሸጥ ወደ 16 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር በግለሰብ ደረጃ እንደተገኘ ተጠቁሟል፡፡
ቡና በውድድር መልክ ቀርቦ ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ውጤት በመገኘቱ የቡና አምራች ገበሬን ከምንጊዜውም በላይ እንዳነቃቃው የተናገሩት አዱኛ (ዶ/ር)፣ ቀደም ሲል መሬታቸውን ለሌላ ሰብል ያዋሉ አርሶ አደሮች ሁሉ በክላስተር በመደራጀት ቡናዎችን የመትከል ሥራ ተጀምሮ ውጤት እየተገኘ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በተደረገው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር የመጨረሻ ተወዳዳሪ ለነበሩ 39 ቡና አብቃይ ተወዳዳሪዎች ሐሙስ ሚያዚያ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ዕውቅና የመስጠት ፕሮግራም እንደሚከናወን ተገልጾ፣ ሦስተኛው ዙር ውድድር በመጪው ታኅሳስ 2014 ዓ.ም እንደሚጀምር አዱኛ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
በ2013 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው የባለ ልዩ ጣዕም ቡና ቅምሻ ውድድር 30 በጥራታቸው ልዩ የሆኑ ቡናዎች ተመርጠው ግልጽ በሆነ ዓለም አቀፍ ጨረታ መሸጣቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 1.8 ሚሊዮን ዶላር በላይ ተገኝቷል።