በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአንድ ዓመት የተራዘመው የቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ የኢትዮጵያ ልዑካን በተገኘበት ነሐሴ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ተጀመረ፡፡
የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ቡድን በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በባህል አልባሳት ደምቆ ታይቷል፡፡ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዛ ልዑኩን እየመራች ወደ ስታዲየሙ የገባችው ትዕግሥት ገዛኸኝ ናት፡፡
የቶኪዮ ፓራሊምፒክ እስከ ነሐሴ 30 ቀን ድረስ የሚካሄድ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ በ1,500 ሜትር ሩጫ ሁለት ወንድና አንድ ሴት አትሌቶችን ታሳትፋለች፡፡ ተወዳዳሪዎቹም ታምሩ ደምሴ፣ ገመቹ አመኑና ትዕግሥት ገዛኸኝ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በፓራሊምፒክ የተሳተፈችው በቴልአቪቭ 1968 ፓራሊምፒክ ሲሆን፣ ውጤታማ መሆን የጀመረችው ደግሞ በ2012 እና በ2016 በተካሄዱት የለንደንና የሪዮ ፓራሊምፒክ ነው፡፡ በለንደን ወንድዬ ፍቅሩ፣ በሪዮ ታምሩ ደምሴ በ1,500 ሜትር ሩጫ የብር ሜዳሊያ አግኝተዋል፡፡