Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትኬንያ የደመቀችበት ከ20 በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ኬንያ የደመቀችበት ከ20 በታች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ቀን:

ኢትዮጵያ ከቀደሙት ሻምፒዮናዎች የላቀ ውጤት አስመዝግባለች

የዓለም 20 በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኬንያ አስተናጋጅነት ለአምስት ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ እሑድሐሴ 16 ቀን 2013 .ም. ተጠናቋል። ሻምፒዮናው ከፍተኛ ፉክክር ከማስተናገዱም በላይ፣ አዳዲስ ክብረወሰኖች፣ የቦታውም ሰዓት የተሻሻለበት ሆኗል፡፡ እንዲሁም በቀጣዩ የፓሪስ ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ይደምቃሉ ተብለው ተሰፋ የተጣለባቸው አዳዲስ ወጣት አትሌቶችንም አመላክቷል።

አዘጋጇ አገር ኬንያ በበላይነት ባጠናቀቀችበት በዚህ ሻምፒዮና፣ በርካታ አዳዲስ ክስተቶች ተስተውሎ አልፏል። ኬንያ በብቃት እንደተወጣች በዓለም አትሌቲክስ (ወርልድ አትሌቲክስ) ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ጭምር ሙገሳን ተችሯታል። በተለይ በአፍሪካ አገሮች እምብዛም ማሰናዳት ባልተለመደበትዓለም ሻምፒዮናን በብቃት መወጣት መቻሏ፣ በቀጣይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ለማሰናዳት የዕድል በር እንደከፈተላት ተጠቁሟል፡፡

 ምንም እንኳን አሜሪካ፣ እንግሊዝና ቻይናን የመሳሰሉ በአትሌቲክስ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ አገሮች በኮቪድ-19ና በሎጂስቲክጥረት ምክንያት መሳተፍ ባይችሉም፣ የምሥራቅ አፍሪካዋ አገር ኬንያ የዓለም አገሮችን ቆፍጠን ብላ የማስተናገድ አቅም እንዳላት አስመስክራለች። ይኼም የረዥም ጊዜ የአትሌቲክስ ተቀናቃኟ አገር ኢትዮጵያ ‹‹ምን ላይ ነች›› የሚል የቤት ሥራ መስጠቷ አልቀረም። ኢትዮጵያ አኅጉራዊውን ሻምፒዮና ማዘጋጀቷ ሳይዘነጋ፡፡

ኢትዮጵያ ለ18ኛ ጊዜ የተሳተፈችበት የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና  በ3 የወርቅ፣ በ7 የብር እና በ3 የነሐስ ሜዳሊያዎች ከዓለም አራተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ ከአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃን መያዝ ችላለች፡፡ ኢትዮጵያ በሁለቱም ፆታ በአጠቃላይ 12 ሜዳሊያዎችን ስታመጣ፣ ከዚህም ውስጥ ሁለት ወርቅ በሴት አትሌቶች የተገኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ወርቅ ያገኘችው በ3000 ሜትር በታደሰ ወርቁ ነበር፡፡ ታደሰ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 7፡42.09 በመግባት የኮርሱን ክብረወሰን መጨበጥ ችሏል፡፡ ታደሰ 3000 ሜትር በተወዳደረ በማግስቱ በ5000 ሜትር ፍጻሜ የብር ሜዳሊያ ማምጣት ችሏል፡፡ በ5000 ሜትር ፍጻሜ 13፡20.65 ሁለተኛ በመሆን ሁለት ሜዳሊያዎችን ማሳካት ችሏል፡፡ በ1,500 ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ወገኔ አዲሱ 3፡37.86 ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ መልኬነህ አዘዘ 3፡40.22 በሆነ ሰዓት የነሐስ ሜዳሊያን አግኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው በሴቶቹ ሁለት ወርቅ አግኝታለች፡፡ በ800 ሜትር አያል ዳኛቸው 2፡02.96 ወርቅ፣ እንዲሁም በሴቶች 5000 ሜትር ሚዛን ዓለም 16፡05.61 በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት ችላለች፡፡ በውድድሩ ያልተገባ መስመር ረግጣለች ተብሎ ውጤቷ ተሰርዞ የነበረው መልክናት ውዱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቴክኒካል ባለሙያ ባደረገው ክርክር አማካይነት የብር ሜዳሊያዋን ማግኘት ችላለች፡፡

ሁለቱም አትሌቶች በዓለም አቀፍ ውድድር ላይ ሲሳተፉ የመጀመሪያቸው ሲሆን በሻምፒዮናው ያሳዩት ድንቅ ብቃት በቀጣይ ተስፋ የተጣለባቸው አትሌቶች ሆነዋል፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች 3000 መሰናክል ዘርፌ ወንድምአገኝ 9፡35.22 በሆነ ሰዓት የብር ሜዳሊያ አሸናፊ ሆናለች፡፡

ኢትዮጵያ ዘንድሮ ያስመዘገበችው አጠቃላይ ውጤት ከቀደሙት 17 ሻምፒዮናዎች የላቀ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የናይሮቢው ሻምፒዮና አራት አዳዲስ የዓለም ክብረ ወሰኖች፣ 15 የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን፣ 68 ብሔራዊ ክብረ ወሰን እንዲሁም 10 ብሔራዊ የአዋቂዎች ክብረወሰን ተመዝግቦበታል፡፡

ሻምፒዮናውን በበላይነት ማጠናቀቅ የቻለችው ኬንያ በመጨረሻው ቀን ብቻ በ800 ወንድ፣ 1,500 ሜትር ሴቶች፣ እንዲሁም በ3000 ሜትር መሰናክል ሦስት ወርቅ ማሳካት የቻለችበት አጋጣሚ ነበር፡፡

በሻምፒዮናው ከ100 በላይ የሚሆኑ የዓለም አገሮች ሲሳተፉ፣ 18 አገሮች የወርቅ ሜዳሊያ፣ 33ቱ ሜዳሊያዎችን እንዲሁም 68 አገሮች ከአንድ እስከ ስምንት ባለው ደረጃ ውስጥ መካተት ችለዋል፡፡

 ኬንያ፣ ፊንላንድ፣ ናይጀሪያና ቦትስዋና ከምንጊዜውም ምርጥ ከ20 ዓመት የዓለም ሻምፒዮና ያሳለፉበት ጊዜ ነው፡፡ ናሚቢያና እሥራኤል በታሪክ የመጀመሪያቸውን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያሳኩ፣ ቆጵሮስ ለመጀመሪያ ጊዜ የመጀመሪያ ሜዳሊያን ማግኘት የቻለች አገር ሆናለች፡፡

ሻምፒዮናው በ70 አገሮች የቴሌቪዥን ሥርጭት ሲያገኝ፣ አገሮች ሻምፒዮናውን በዩቲዩብ የሚከታተሉበተን አማራጭም ተመቻችቶላቸው ነበር፡፡

‹‹ይኼ ሻምፒዮና ተከናወነ ብቻ ተብሎ የሚታለፍ ሳይሆን ስኬታማ ነበረ ማለት ይቻላል፤›› ሲሉ የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያንኮ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በሻምፒዮናው ላይ የተሳተፉ አትሌቶችን በተመለከተም ‹‹የተተኪ አትሌቶችን ብቃትና መጠን መመልከት ችለናል፤›› ሲሉም አድናቆታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

እንደ ፕሬዚዳንቱ አስተያየት እ.ኤ.አ 2018 ላይ በፊንላንድ ቴምፕር ላይ ድንቅ ብቃታቸውን ማሳየት የቻሉ አትሌቶችን በኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ማየት መቻላቸውንና በዘንድሮ የወጣቶች ሻምፒዮን ላይ የተመለከቷቸውን ወጣቶች ከሦስት ዓመት በኋላ በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ እንደሚደምቁ ምንም ጥርጥር የለኝም ብለዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በዚህ ሻምፒዮና ላይ መሳተፍ ከቻሉ አትሌቶች መካከል በኮሎምቢያ ካሊ በሚሰናዳው ከ20 በታች የዓለም ሻምፒዮና ላይ የመካፈል ዕድል ያላቸው እንዳሉም ተጠቁሟል፡፡

ኬንያ በ8 ወርቅ፣ በ1 ብር እንዲሁም በ7 ነሐስ በድምሩ በ16 ሜዳሊያ አንደኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ፣ ፊንላንድ በ4 ወርቅ፣ በ1 ብር በድምሩ በ5 ሜዳሊያ ሁለተኛ፣ ናይጀሪያ በ4 ወርቅና በ3 ነሐስ በድምሩ በ7 ሜዳሊያዎች ሦስተኛ ደረጃን፣ እንዲሁም ኢትዮጵያ በ3 ወርቅ፣ በ7 ብርና በ2 ነሐስ በድምሩ በ12 ሜዳሊያዎች አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...