Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሱዳንና ደቡብ ሱዳን የዘጓቸውን ድንበሮች ሊከፍቱ ነው

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የዘጓቸውን ድንበሮች ሊከፍቱ ነው

ቀን:

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃ ወጥታ የራሷን መንግሥት ከመሠረተች ማግሥት ጀምሮ አገሮቹ በነዳጅ አጠቃቀምና ክፍፍል፣ በአቢዬ ግዛት ይገባኛልና በሌሎች የጥቅም ጉዳዮች አለመግባባት በርካታ ድንበሮቻቸውን ዘግተው ለ11 ዓመታት ያህል ቆይተዋል፡፡

የሁለቱን አገሮች የንግድ ትስስር ያሽመደመደው፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና አካባቢያዊ ግንኙነታቸውን የገደበውና ኢኮኖሚያቸውን ሆነ ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ያስተጓጎለው የድንበር መዘጋት እንዲከፈት የተለያዩ ውይይቶች ሲደረጉም ቆይተዋል፡፡ የፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ከሥልጣን መወገድን ተከትሎም የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አብደላ ሃምዶክ ድንበሮቹ ይከፈታሉ የሚለውን ተስፋ ያጫሩት እ.ኤ.አ. በ2019 ነበር፡፡

ዘ ኢስት አፍሪካን እንደዘገበው፣ ሁለቱ አገሮች ባለፈው ሳምንት ምክክር ካደረጉ በኋላ ድንበራቸውን በጥቅምት ለመክፈት ወስነዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ሃምዶክ የተመራው ልዑካን  ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪርና ሌሎች ባለሥልጣናት ጋር በደቡብ ሱዳን ጁባ በነበረው ውይይት ሁለቱን አገሮች የሚያገናኙ አራት የድንበር መንገዶችን ለመክፈት ተስማምተዋል፡፡

ሱዳንና ደቡብ ሱዳን የዘጓቸውን ድንበሮች ሊከፍቱ ነው

የመጀመርያው ድንበር የሚከፈተው በጥቅምት 2021 መሆኑን ለሦስት ቀናት በደቡብ ሱዳን ቆይታ ያደረጉት የሱዳን ልዑካን ያሳወቁ ሲሆን፣ ሁለቱ አገሮች በቀጣይ ኢኮኖሚያቸውንና የንግድ ፍላጎታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት አሠራር ላይ መክረዋል፡፡

ውይይቱ ያተኮረው ከ11 ዓመታት በፊት ጀምሮ የተቋረጠው የውጭ ንግድ እንዲቀጥልና የድንበር ንግድን ማጠናከር በሚቻልበት ላይ እንደሆነም የሱዳን ንግድ ሚኒስትር አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ ደግሞ የየብስና የባህር ትራንስፖርት ለመጀመርም አገሮቹ ተስማምተዋል፡፡

በሒደት ሰዎችንና ዕቃዎችን በባህርና በየብስ ለማጓጓዝ ከተደረሰው ስምምነት በተጨማሪ፣ የፋይናንስ ዘርፉን ያስተጓጎሉ አሠራሮችን ቀርፈው የባንክ አገልግሎት የሚጀምሩም ይሆናል፡፡

በሁለቱም አገሮች የባንክ ቅርንጫፎች እንደሚከፈቱና የገንዘብ ዝውውር እንደሚጀመር የሱዳን ሬዲዮን ጠቅሶ ዘ ኢስት አፍሪካን ዘግቧል፡፡

አገሮቹ በመስከረም አራትና አምስት በአገሮቹ የጋራ የፖለቲካ ደኅንነት ሜካኒዝም ላይ በጁባ ዳግም ለመምከር ቀጠሮ የያዙ ሲሆን፣ በውይይቱ በነዳጅ ንግድ ላይ የጋራ ስትራቴጂ ይነድፋሉ ተብሏል፡፡

የሁለቱን አገሮች ሕዝቦች ደኅንነት ለመጠበቅም ባለሥልጣናቱ በደኅንነትና በፀጥታ ዙሪያ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል፡፡

በጥቅምት 2021 የአል ጀብሊን ሬንክ ድንበር የሚከፈት ሲሆን፣ በቀጣይ አል ሜሪያም አዊል፣ ቡራም ቲምሳህ እንዲሁም ካራሳና ባንክዊግ ድንበሮች የሚከፈቱ ይሆናል፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል ነግሦ የነበረውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውዝግብ ለማርገብና ሰላም ለማውረድና የተለያዩ ስምምነቶችን ለማድረግ ተጠምዶ እንደነበርና አሁን እየተሳካ እንደሆነ የሚገልጸው የሱዳን መንግሥት ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነፃ ከወጣች በኋላ ተደርሰው የነበሩ ስምምነቶች ዳግም እንደሚከለሱም አስታውቋል፡፡

ሱዳንና ደቡብ ሱዳንን የሚያዋስኑ 2,000 ያህል ድንበሮች የተዘጉት በቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር አስተዳደር ዘመን ነው፡፡ ይህም በሁለቱ አገሮች ሕዝቦችና የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ኪሳራ አድርሷል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2011 ድንበሮቹ የተዘጉት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በመሻከሩ በተለይ ደቡብ ሱዳን ነፃ ስትወጣ የአገሪቱን ሲሶ ነዳጅ ዘይት ይዛ መሄዷ ባስከተለው የጥቅም ግጭት ምክንያት ነው፡፡

በዚህና በሌሎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮችና በአብዬ ግዛት ይገባኛል ጥያቄ ውዝግብና ግጭት ውስጥ የገቡት አገሮቹን ድንበር ለመክፈት እ.ኤ.አ. በ2016 በኦማር አልበሽር ትዕዛዝ ቢተላለፍም ተፈጻሚ አልሆነም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...