Saturday, December 9, 2023

​​​​​​​መቋጫው በውል ያልተለየው ጦርነትና የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በወርኃ ጥቅምት መጨረሻ አካባቢ በፌዴራል መንግሥትና በሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተጀመረው ጦርነት፣ ያለ ምንም መፍትሔና መቋጫ የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈና በርካቶችን እያፈናቀለ ዘጠነኛ ወሩን ሊሻገር ነው፡፡

ጦርነቱ በተጀመረ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ የትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና የሆነችውን መቀሌ መቆጣጠሩን ተከትሎ፣ የፌዴራል መንግሥቱ ጦርነቱ መጠናቀቁንና በክልሉ የሚኖረው ቀጣይ ሥራም የዳግም ግንባታና በጦርነቱ የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ዳግም ወደ አገልግሎት መመለስ ላይ እንደሚያተኮር ገልጾ ነበር፡፡

የፌዴራል መንግሥት ሦስት ሳምንታት ከወሰደ የዘመቻ ሥምሪት በኋላ፣ የትግራይ ክልልን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር መቻሉን ከመግለጽ ባለፈ በፌዴሬሽን ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሁንታ የተቸረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አንዳንድ ሥራዎችን መሥራት ጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በተለያዩ ወቅቶች ይሰነዘሩ የነበሩ የደፈጣ ጥቃቶች እንቅስቃሴውን ከመቀሌ ውጪ እንዳያደርግ አግደውት ነበር፡፡

መቀሌ ከተማ የነበረው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ክልሉን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር፣ የፌዴራል መንግሥቱ ቃል የገባውን ክልሉን ዳግም የማነፅና የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ወደ ቀደመ አቋማቸው የመመለስ ተልዕኮን ማሳካትም አቀበት ሆኖበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ጦርነቱ ተጠናቋል ከተባለበት የኅዳር ወር ጀምሮ የመከላከያ ኃይሉ በክልሉ መደበኛ ውጊያዎች ላይ ባይሳተፍም፣ እዚህም እዚያም ይሰነዘሩ የነበሩ የደፈጣ ጥቃቶችን ለመመከትና የደፈጣ ተዋጊዎቹን ለመዋጋት ከቦታ ቦታ ይዘዋወር በነበረበት ወቅት ከፍተኛ አደጋ ይደርስበት እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ በሕዝብ ተወካዮች ፊት ቀርበው ባብራሩበት ወቅት መግለጻቸው እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡

ከስምንት ወራት ቆይታ በኋላ የፌዴራል መንግሥት ባልተጠበቀ ሁኔታ ሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ያስተላለፈው የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ያልተጠበቀና በርካቶችን፣ በርካታ ዓይነት መላምቶችን እንዲሰነዝሩ በር የከፈተ ነበር፡፡

የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው በተላለፈበት ወቅት መንግሥት ካስቀመጣቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የነበረው፣ ‹‹ገበሬው ወደ እርሻ ሥራው ተመልሶ እስከ እርሻ ወቅት ማጠናቀቂያ ድረስ ተግባራዊ ይሆናል፤› የሚለው አባባል ከመጀመርያው በርካቶችን ለጥርጣሬ የዳረገ በመሆኑ አንዳንዶች እንዲያውም፣ ‹‹መንግሥት አቅም አንሶኛል›› ላለማለት የፈጠረው ምክንያት ነው በማለት ሲገልጹም ነበር፡፡

በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ለጥቂት ቀናት የሰነበተው የሰሜኑ የአገሪቱ ሁኔታ ከተነናጠል ተኩስ አቁሙ ውሳኔ በኋላ በተለይ የሕወሓት ተዋጊዎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች የሰነዘሯቸው ጥቃቶችና የተቆጣጠሯቸው ሥፍራዎች፣ በርካቶች ከመጀመርያው ሲያነሱት የነበረውን ጥያቄ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ዕድል የሰጠ ነበር፡፡

በወቅቱ የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ምክንያት፣ ‹‹የመንግሥት አቅም መዳከምና ጦርነት ማስቀጠል ባለመቻሉ ነው፤›› በማለት በርካቶች ሲገልጹ የነበረ ቢሆንም፣ ውሳኔውን ተከትሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹እንደሚባለው መንግሥት አቅም አጥቶና ጦርነቱን ማስቀጠል ባለመቻሉ ሳይሆን፣ ለሰላም ዕድል ለመስጠት ነው፤›› በማለት አስተያየቶቹን ውድቅ አድርገዋል፡፡

‹‹የተከበረው ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘበው የምፈልገው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ አሥርና ሃያ ዓመት ጦርነትን ማስቀጠል ይቻላል፡፡ ክላሹም፣ ጥይቱም፣ ሰውም አለ ምንም ችግር የለውም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያን ውስጥ ማምጣት የማይቻለው ዕድገትን ለአሥርና ለሃያ ዓመት ነው፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተው ነበር፡፡

ከዚህም ባሻገር አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ መልሰው መቀሌ መግባት እንደሚችሉ በመግለጽ የሚሰነዘረውን ትችት አጣጥለው ነበር፡፡

ሆኖም የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው ከተላለፈ በኋላ የተፈጠሩ ለውጦችና የጦርነት አቅጣጫዎች መስፋት፣ በርካቶችን የዚህ ጦርነት ማብቂያ መቼና እንዴት ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን እንዲሰነዘሩ ምክንያት ሆኗል፡፡

በርካቶች የሚሰነዝሩንትና የሚጋሩትን ጥያቄ የሰላምና ደኅንነት ጥናት ተመራማሪዎች፣ የፖለቲካ ሳይንስ፣ እንዲሁም የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪዎችም የሚያነሱት ጥያቄ ሲሆን፣ ከተርታው ሕዝብ በተለየ መንገድ ግን ከጥያቄው ባለፈ በጥናትና በታሪክ ላይ የተመረኮዘ ምላሽ ለመስጠት ይሞክራሉ፡፡

በተለይ ደግሞ የተናጠል ተኩስ አቁም ስምምነቱ በታወጀ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ የሕወሓት ኃይሎች የክልሉን ዋና ከተማና አጠቃላይ ክልሉን መቆጣጠራቸው፣ እንዲሁም ደግሞ አዋሳኝ ወደ ሆኑት የአማራና የአፋር ክልሎች ጦርነቱ መስፋፋቱ ከመጀመርያው የፌዴራል መንግሥት አካባቢውን ለቅቆ ሲወጣ የተሰነዘሩትን የጥርጣሬና የሥጋት ስሜትን ገዝፎ እንዲነሳ አድርጎታል፡፡

በተለይ ደግሞ የሕወሓት ኃይሎች ወደ የተለያዩ የአማራና የአፋር ክልሎች ሥፍራዎች ዘልቀው መግባታቸውና እንደ እነ ላሊበላን የመሳሰሉ ከተሞችን መቆጣጣራቸው፣ የአማራ ክልል መንግሥት የክተት አዋጅ እንዲያውጅ አስገድዶት ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሰነበተው የአካባቢው ውጥረትና ጦርነት ካለፈው ሳምንት መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ ደግሞ በሌላ ዜና ተወጥሯል፡፡ የአማራ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ በየዕለቱ በሚያወጣቸው መግለጫዎች አማካይነት፣ በሕወሓት ኃይሎች ተይዘው የነበሩ ሥፍራዎችን እያስለቀቀ እንደሆነ በማስታወቅ ላይ ይገኛል፡፡

ከመጀመርያው ይህ ጦርነት መቼና እንዴት ይቋጫል የሚል ጥያቄ ለሚሰነዝሩ በርካቶች፣ ‹‹ይህንን ሥፍራ አስለቅቀናል፣ ወደ እዚህ ሥፍራ እያመራን ነው፤›› በሚል በሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የሚሰጡ መግለጫዎች መግተልተል ከግምት ላስገባ፣ ይህ ጦርነት በቅርብ እንደማይመስል መገንዘብ ይቻላል፡፡

ከዚህ አንፃር ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ከትግራይ ክልል ውጪ በሚያደርጉት ጦርነት እየተፈናቀሉ ያሉ ዜጎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ ከመሆኑ አንፃር፣ እንዲሁም በሁለቱም ወገን ጦርነቱን ከመግፋት ውጪ የተሻለ አማራጭ አለመቅረቡን በመመልከት ጦርነቱ ከመቋጫው የራቀ እንደሆነ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡

ምንም እንኳን የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረትን የመሳሰሉ አገሮች ዓለም አቀፍ ተቋማትና የምዕራቡ ዓለም ሁለቱም ወገኖች ለሰላም ቅድሚያ ሰጥተው ልዩነታቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ቢወተውቱም ሁለቱም ወገኖች ጥሪውን ጆሮ ዳባ ብለውታል፡፡

ለዚህ ደግሞ የፌዴራል መንግሥቱ የተናጠል ተኩስ አውጃለሁ የሰላም ጥሪውን አልቀበልም ያለው ሕወሓት ነው በማለት የሚከስ ሲሆን፣ ሕወሓት በበኩሉ ደግሞ ወደ ትግራይ የተዘረጉ መሠረተ ልማቶች ማለትም ቴሌ፣ መብራት፣ ውኃ እንዲሁም የባንክ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ በተዘጋበት ሁኔታ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ቁጭ ብሎ መነጋገር የማይታሰብ ነው በማለት ያስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሟሉ ድርድር እንደማይኖር በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ ይገኛል፡፡

እዚህ ላይ መታወስ ያለበት አንድ ሀቅ ግን የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ኃይሎች እያደረጉት ባለው ጦርነት በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ይህ መፈናቅልና ስደት ደግሞ ባለው የተካረረ ሁኔታ በቅርቡ የሚቆም አይመስልም፡፡  

እንዲህ ያለው ሁኔታ እየተራዘመመ በሄደ ቁጥር ግን በአገሪቱ አጠቃላይ ህልውና ላይ ከፍተኛ የሆነ ፈተና እንደሚደቅንና ምናልባትም ሌሎች ተዋንያንንም  ሊጋብዝ ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸውም አሉ፡፡ የዚህ ሥጋት ሁኔታም እንዲያው ዝም ብሎ ከመሬት የተነሳ ሳይሆን፣ አሁን ላይ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚታየውን የኃላያን አገሮች ተፅዕኖ የመፍጠር እሽቅድምድምን ከግምት ውስጥ ባስገባ ሁኔታ እንጂ፡፡

በተለይ በፍጥጫ የሚታወቀው የአሜሪካና የሩሲያ የኃይል አሠላለፍ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ ከመጣ መሰንበቱን ተከትሎ የሁለቱ አገሮች አሠላለፍ ግና በቅጡ ይፋ ባይሆንም፣ ሁለቱም አካላት ግን እጃቸውን ለመስደድ እየተዘጋጁ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር ከተከሰተ ደግሞ የብዙዎቹ፣ ‹‹ይህ ጦርነት እንዴትና መቼ ነው የሚያልቀው?›› የሚለው ጥያቄ ለረዥም ጊዜ ምላሽ ሳያገኝ የሚቆይና የሚንከባለል ግን አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን አይቀሬ ያደርገዋል፡፡

የጦርነቱ መቋጫ እንዲህ እየረዘመ በሄደ ቁጥር ደግሞ የኢትዮጵያን አጠቃላይ ማኅበራዊ ድርና ማግ ለመበጣጠስ ዓይነተኛ ግብዓት መሆኑ አይቀሬ መሆኑን የሚናገሩ አሉ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሊያርስ የሚገባው ኃይል በጦርነት ተሰማርቶ በመገኘቱ የበርካቶች ማሳ ፆም እንደሚያድር፣ ወደ ትግራይ ክልል የሚደርሰው የሰብዓዊ ዕርዳታ መስተጓጉልን ተከትሎ በርካቶች ለጉዳት መዳረጋቸውን በመግለጽ፣ እንዲህ ባለ ሁኔታ ጦርነቱ ወደ ሌላ ተጨማሪ ዓመት ተላለፈ ማለት አጠቃላይ የአገር ውስጥ የግብርና ምርትን ሊያሽመደምድ እንደሚችል በማሳሰብ፣ አሁንም ለችግሩ የድርድር መፍትሔ እንዲገኝ ያሳስባሉ፡፡

ምንም እንኳን የተደራደሩ ጥሪዎች ቢሰሙም፣ ጥሪዎቹ ግን ተቀባይነት ያገኙ አይመስልም፡፡ የፌዴራል መንግሥት ያቀረበውን የተናጠል የተኩስ አቁም ጥሪ በሕወሓት በኩል ‹‹ቀልድ›› ነው የሚል ምላሽ ማግኘቱን ተከትሎ ጦርነቱ አድማሱን አስፍቶ ቀጥሏል፡፡

በዚህ መሀል ነሐሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹የህልውና ዘመቻው ፍፃሜ የሚወሰነው ትህነግ ከአማራ ክልልም ሆነ ከኢትዮጵያ ተደምስሶ ሲጠፋ ብቻ ነው፤››› በማለት የጦርቱን ፍፃሜ በሕወሓት መጥፋት ላይ እንደሚወሰን አስታውቋል፡፡

ነገር ግን ሕወሓትን ሙሉ በሙሉ ከአማራ ክልልም ሆነ ከኢትዮጵያ ጠራርጎ ለማጥፋት ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚቻለው በጊዜ ሒደት ብቻ በመሆኑ ይህን መጠበቅ ግድ የሚል የጥያቄው መልስ ነው፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን፣ ‹‹ረሃብ ስንት ቀን ይፈጃል?›› በማለት ድርቅን አስመልክቶ የከተቧት ድንቅ ግጥም አለች፡፡ በዚህ ዘመን ቢኖሩ ደግሞ፣ ‹‹ይህ ጦርነት መቼ ያልቃል?›› ብሎ የሚመለከታቸውን መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ ይህ ጦርነት ግን መቼ ያልቃል? ኢትዮጵያስ እንዲህ ካለው የጦርነት አዙሪት መቼ ነፃ ትወጣለች?

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -