- ሰማህ አይደል ጉድ እንዳደረግናቸው?
- ማንን ክቡር ሚኒስትር?
- ልዩ ልዑኩን ነዋ?
- ኧረ ጨርሶ አልሰማሁም፣ ምን ጉድ ተደረጉ?
- እንደ ሴትየዋ ጉድ ሠራናቸው እኮ?
- የቷ ሴትዮ?
- ማን ነበረች? ሰምአቷ ነው?
- እ… ሰማንታን ነው?
- አዎ ሰማንታ፣ ሰማአቷ አልኩ፣ ነገሩ ያው ነው?
- እሺ፣ እንደ እሷ ጉድ አደርግናቸው ያሉትን እስኪ ይቀጥሉ ክቡር ሚኒስትር?
- እሷ ስትመጣ ወደ አፋር ክልል ለሥራ ብለው ሄደው ጉድ እንዳደረጓት ልዩ ልዑኩንም ደገሙት፣ ጉድ አደረጉት፡፡
- እንዴት?
- እሱ ሲመጣ ደግሞ ወደ አስመራ፡፡
- አስመራ ሄዱ እንዴ?
- ምን አስመራ ብቻ?
- እ…?
- ከአስመራ ደግሞ በዚያው ወደ አዲስ አበባ ሳይመለሱ ወደ ቱርክ ሄደው ጉድ አደረጓቸው።
- እና ልዩ ልዑኩ አልተበሳጩም?
- እሱማ ተበሳጭተው ነበር ግን አቀዘቀዝናቸው።
- ምን አድርጋችሁ?
- ምክትሉን አግኟቸው አልናቸዋ።
- እሺ … ከዚያስ?
- ምክትሉን አግኝተው ትንሽ ከተረጋጉ በኋላ ወደ ትግራይ ካልሄድኩ አሉ።
- ወደ ትግራይ?
- አዎ፣ ግን ማን ፈቅዶላቸው።
- እና አልሄዱማ?
- አልሄዱም፣ ግን ተበሳጭተው እልህ ውስጥ ገቡ።
- እልህ ውስጥ ገቡ?
- አዎ፣ ትግራይ ካልሄድኩ አለቃ እስኪመጡ እጠብቃለሁ አሉ።
- ከቱርክ እስኪመጡ ድረስ?
- አዎ።
- እና አገኟቸው?
- አዎ፣ በመጨረሻ አገኟቸው፣ ምን ይደረጋል ብለህ ነው ታዲያ?
- ክቡር ሚኒስትር ይኼ አካሄድ ግን ትክክል ነው?
- እናንተ አማካሪዎች ደግሞ ተመሳሳይ ችግር አለባችሁ።
- ተመሳሳይ ችግር ነው ያሉት?
- አዎ፣ የሚያመሳስሏችሁ ችግሮች አሏችሁ።
- እንዴት? ምን ያመሳስለናል ክቡር ሚኒስትር?
- አንደኛ አንተ እንዳደረግከው አማክሩ ስትባሉ መካሪ የምትሆኑት ነገር አለ።
- ሌላስ በምን እንመሳሰላለን?
- ለአሜሪካ በመንበርከክ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ተሳስተዋል።
- ሌላው የሚያመሳስላችሁ ይኼ ነው፣ ተሳስተዋል ማለት ይቀናችኋል።
- ክቡር ሚኒስትር እኔ በበኩሌ ለአገራችን ጥቅም በመጨነቅ ነው ሥጋቴን የገለጽኩት።
- ለአሜሪካ መንበርከክ ማለት እሱ ነው።
- የቱ?
- ለአገሬ እያላችሁ ነው የምትንበረከኩት።
- ክቡር ሚኒስትር ተሳስተዋል።
- ይኸው ተናግሬ ሳልጨርስ አልከው።
- ምን አልኩ?
- የሚያመሳስላችሁን ነገር አልክ!
- ክቡር ሚኒስትር እንደዚያ ማለቴ አይደለም፣ ነገር ግን የአሜሪካ ጉዳይ በጥንቃቄ ቢታይ ጠቃሚ እንደሚሆን አምናለሁ።
- በጥንቃቄ መታየት አለበት ያልከው ለምንድን ነው ብዬ አልጠይቅህም።
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- የምትሰጠውን ምክንያት ስለማውቀው።
- እሺ ምክንያቴን ይነገሩኝ ክቡር ሚኒስትር?
- ማዕቀብ ነዋ! ሌላ ምን ልትል ትችላለህ?
- ክቡር ሚኒስትር ተሳስተ….ማለቴ …
- ጨርሰው… ግድ የለም በለው።
- ክቡር ሚኒስትር የእኔ ሥጋት ማዕቀብ አይደለም።
- እና ምንድነው?
- ክቡር ሚኒስትር አሜሪካ በሥጋት ከምታያቸው አገሮች የጦር መሣሪያዎችን እንደገዛን የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ባሉበት ሰዓት…
- እና ብንገዛስ? ሉዓላዊ መብታችን አይደለም እንዴ?
- መብታችን ነው፣ ነገር ግን ወደ እዚህ ደረጃ ከተዘለቀ እነሱም አንድ ዕርምጃ ለመሄድ ዕድል ያገኛሉ።
- ወዴት ነው አንድ ዕርምጃ የሚሄዱት?
- በተለይ ከኢራን ጋር የሚደረግ የመሣሪያም ሆነ ሌላ ግንኙነትን አሜሪካ እንደ ብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት ነው የምታየው።
- እንደፈለገች ትየው፣ በአገራችን ጉዳይ የመወሰን ኃላፊነት የእኛ ብቻ ነው።
- እሱ ትክክል ነው።
- ምንድን ነው የምትለው ታዲያ?
- አሜሪካ ብሔራዊ የደኅንነት ሥጋት አለኝ ካለች የምትሄደው ርቀት ሰፊ ነው።
- እና የሆነስ እንደሆን?
- እንደሚያውቁት አሜሪካ በብሔራዊ ደኅንነት ምክንያት በኢራቅ ያደረሰችውን ካደረሰች በኋላ ነው የደኅንነት ሥጋት እንደሌለ የታወቀው።
- እና ምን ይሁን ነው የምትለው?
- አሜሪካኖቹን ከመሸሽ ይልቅ ተገናኝቶ ማስረዳቱ ይሻላል ማለቴ ነው።
- እኛም እኮ እስከ መጨረሻው አልሄድንም፣ ከቱርክ ሲመለሱ አገኟቸው አልኩህ አይደል እንዴ?
- አዎ ብለውኛል።
- ታዲያ ምንድነው?
- ምን?
- ልምከር ልምከር የምትለው?!
- Advertisment -
- Advertisment -