Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት ከጥንታዊው አክሱም ሥልጣኔ እስካሁን

የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት ከጥንታዊው አክሱም ሥልጣኔ እስካሁን

ቀን:

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት ከጥንታዊው የአክሱም መንግሥትና ከጥንታዊው ባይዛንታን መንግሥት ጋር የተያያዘ ብቻ ሳይሆን፣ ከቁስጥንጢንያ መንግሥት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታዮች እምነት የመስቀል ደመራ ተብሎ መስከረም 17 ቀን የሚከበረው በዓል የቁስጢንጢኒያ እናት የሆነችው ንግሥት ኢሌኒ፣ የክርስቶስን መስቀል ከማግኘቷ ጋርም የተያያዘ ነው፡፡ የዚህ መስቀል ግማድ (ከፊል) በኢትዮጵያ በተለይም በአምባሰሏ ግሸን ማርያም ውስጥ ይገኛል ተብሎ ይታመናል፡፡ በዘመነ ባይዛንታይን (ስድስተኛው ክፍለ ዘመን) ኢትዮጵያና የባይዛንታይን ከዓለም አራት ኃያላን አገሮች ሁለቱ የነበሩ ሲሆን፣ በዚያን ወቅት በተለይም ኢትዮጵያ ድንበር ዘለል ግዛቷን በመካከለኛው ምሥራቅ አስፋፍታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የነበረው ከክርስትናና ከእስልምና እምነት ጋር የተያያዘ ግንኙነት በአጭሩ ከቀረበ በኋላ፣ ጥንታዊውና ዘመናዊው የንግድ ግንኙነታቸው ደግሞ በመጠኑ ተተንትኖ ይቀርባል፡፡

በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የነበረው ጥንታዊ ግንኙነት

ከዚህም በተጨማሪ ጥንታዊትና ገናናዋ ኢትዮጵያ ከባይዛንታን ሥርወ መንግሥት ጋር ወዳጅ የነበረች አገር መሆኗን ቱርኮች ይገነዘባሉ፡፡ የራሳቸው የዓረብ ታሪክ ጸሐፍት እንደሚመሰክሩትና በቁርዓን ውስጥ በ105ኛው ምዕራፍ ማለትም በሱረቱል ፊል ውስጥ በግልጽ እንደሰፈረውና ከዚያም ምዕራፍ በመነሳት በርካታ የእስልምና ታሪክ ጸሐፍት በድርሳናቸው እንዳሰፈሩት፣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የቀይ ባህርን ድንበር አቋርጣ የመንን የገዛች ሲሆን የመጀመሪያው 340 እስከ 378 (እ.ኤ.አ) በነበረው ጊዜ ነው፡፡ ሁለተኛው 575 እስከ 600 ባለው ጊዜ ነበር፡፡ ኸኸኸውም አፄ ካሌብ ወይም ግሪኮች ሄሌስታኢሰስ ወይም ኢላአጽበሐ፣ ወይም ኢላስባስ በነበሩበት በአፄ ካሌብ ዘመነ መንግሥት ነበር፡፡ አፄ ካሌብም የመንን 570 አካባቢ ማለትም ነቢዩ ሙሐመድ በተወለዱበት ጊዜ ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነና ሠራዊት በዝሆን ተጭኖ እስከ መካ በመጓዝ ዓረቢያን ይወራሉ፡፡ ወረራውንም ያካሄዱት በቀይ ባህር ድንበሮቻቸው በርካታ መርከቦችን በመሥራትና ከሌሎችም አገሮች በመጨመር ነበር፡፡ አፄ ካሌብ ዓረቢያን በወረሩበት ጊዜ የሠለጠኑ ዝሆኖችን እንደተጠቀሙ ሲታወቅ፣ ከሁሉ የገዘፈና ካዕባን ገርስሶ ለመጣል የተዘጋጀው ዝሆን ስምም ‹‹ማህሙድ›› ተብሎ ይታወቅ እንደነበር ይነገራል (Hajjah Adil, Amina, “Prophet Muhammad“, ISCA, Jun 1, 2002, ISBN 1-930409-11-7)፡፡ ይሁንና ግዙፉ ማህሙድ ወደ ካዕባ ለመቅረብ ሳይችል ቀረ፡፡ ይህም ዘመን በቁርዓን ውስጥ 105ኛው ምዕራፍ እንደተጠቀሰው ‹‹የዝሆን ዘመን›› ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ በቅርቡ በዓረቢያ የተገኙ የታሪክ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ የዝሆን ዓመት 568 ወይም 569 ሊሆን እንደሚችል ያስገነዝባሉ፡፡ ወደዚህም ዝንባሌ የተደረሰው የሳሳኒያ ሥርወ መንግሥት 570 በአክሱማዊው መንግሥት (በአፄ ካሌብ) እና በባይዛንታን መንግሥት ይረዳ የነበረውን የመን መንግሥትን ከሥልጣኑ እንዳስወገደው ስለሚታወቅ ነው (“Abraha.” Dictionary of African Christian Biographies. 2007. (last accessed 11 April 2007)፡፡

ዶ/ር ላጲሶ ጌ ደሌቦ እንደሚነግሩን የንጉሥ ካሌብና የቁስጥንጥንያ ባለ ቃል ኪዳን ዘመቻ መጨረሻ የሆነ ድል አድራጊነትን ተቀዳጅቶ በዓለም ፊት ገኗል፡፡ ደቡባዊ ዓረብ ሁሉ የኢትዩጵያ ግዛት ሆኖ ክርስቲያኖችም ሙሉ ነፃነት አግኝተዋል፡፡ ይህ ክርስቲያናዊ ዘመቻ የተደረገው በዘመነ ክርስትና በ525 ዓ.ም. ነው፡፡

ስለሁለተኛው የአፄ ካሌብ ዘመቻ በታሪክ ሊቃውንት ለጦርነቱ ስለተነቃነቁት መርከቦች የተሰጠው የብዛት ቁጥር የተለያየ ነው፡፡ ለምሳሌ ዶ/ር ሥርግው አፄ ካሌብ 230 መርከቦችን በአገር ውስጥና በውጭ አገር አሠርተው እንደ ዘመቱ ይገልጻሉ (ሥርግወ ሀብለ ሥላሴ eew p.132)”፡፡ ወደ ዓረቢያ የተደረገው ዘመቻ እጅግ ግዙፍ እንደነበረ የሚገልጹት ዶ/ር ተወልደ ደግሞ ‹‹ዘመቻው ግዙፍ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ቀይ ባሕርን አቋርጠው የመን የደረሱት በ191 የቤዛንታይን የንግድ መርከቦችና አፄ ካሌብ ባሠራቸው በ170 መርከቦች ተሳፍረው ነበር፡፡ አፄ ካሌብ ዘመቻ ያካሄደው በሁለት ዙድ ነበር፤›› ይላል፡፡

በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የነበረው ግንኙነትና የክርስትና እምነት

ከታሪክ ማህደራት እንደምናገኘውና አሁንም በዕውን ከሚገኘው መረጃ እንደምንገነዘበው፣ በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የነበረው ግንኙነት ከክርስትና እምነት በተያያዘ ሲፈተሸ ጥልቅ መሠረት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በዚህም መሠረት፣  ቱርክ በተለይም አናቶሊያ ከጥንት ጀምሮ የበርካታ የክርስትና እምነት ሐዋሪያት፣ ቅዱሳን የሃይማኖቶች አባቶች የትውልድ ሥፍራ ስትሆን ከእነዚህም ውስጥ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር የሆኑት ቅዱስ ጳውሎስ፣ ጢሞቲዎስ፣ ኒኮላስ፣  ሚይራና ሌሎች ብዙዎች ይገኙበታል፡፡ በቅዱስ ጴጥሮስ በአንጾኪያ የተቋቋመው ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው በቱርክ ነው፡፡ ሐጊያ ሶፊያ የተባለው በዓለም ትልቁ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው በቱርክ ውስጥ ነው፡፡ የዮሐንስ ራዕይ የተላከው ወደ ቱርክ ሲሆን፣ ቅዱስ ዮሐንስም ድንግል ማርያምን የወሰዳት ወደ ኤፌሰስ (ምዕራብ ቱርክ) ነው፡፡ ቅድስት ማርያም ሕይወቷ ያለፈውም በቱርክ ሲሆን፣ ቦታውም እስካሁን ድረስ የድንግል ማርያም ተብሎ ይታወቃል፡፡ ወደ እዚህም ሥፍራ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ክርስቲያኖች፣ እንዲሁም ሙስሊሞች በመሄድ ፀሎት ያደርሳሉ፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሰባት የክርስትና ጉባዔዎች የተካሄዱት በቱርክ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜም የግሪክ፣ የአርሜኒያና የአሶሪያ ኦርቶዶክስ፣ የካለዲያውያን ካቶሊክ እምነት ተከታዮች፣ እንዲሁም የቡልጋሪያና የጆርጂያ ፕሮቴስታንት ተከታዮች በቱርክ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የቅዱስ ዲሚጥሮስ ቤተ ክርስቲያንም ከትልልቆቹ ቱርክ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር በጥብቅ በተሳሰረው መንገድ የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት ታሪካዊ መሠረቱን አፅንቶ ቆይቷል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከቱርክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ጥንታዊ የሆነ ግንኙነት የነበራት ሲሆን፣ በተለይም ኢየሩሳሌም የሚገኘውና የኢትዮጵያ ይዞታ የሆነው የዴር ሡልጣን ገዳም ባለቤትነቷ እንዲረጋገጥ ለዓመታት ጥረት ስታደርግ ነበረ፡፡ ይህንን በሚመለከትም በርካታ የደብዳቤ ልውውጦች ተደርገዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ጥረት ተሳክቶ ባለቤትነቷ በድጋሚ የተረጋገጠው በአሁኑ ወቅት በሥልጣን ላይ ካለው የቱርክ መንግሥት እንደሆነ በታሪክ ምዕራፍ የሚታወስ ነው፡፡ በ13ኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ታላቁ ሳላሃዲን አዩቢ የማን ነው ብለው ሲጠይቁ የሐበሾች ተብሎ ይነገራቸዋል፡፡ እነዚህም ንጉሥ የሐበሾችን ይዞታ እንዳንነካ ነብዩ ሙሐመድ የከለከሉን ስለሆነና የእነርሱ ይዞታ እንዳይነካ ብለው በማዘዛቸው፣ የኢትዮጵያ ይዞታ ሆኖ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ ከዚያ በኋላ ቱርኮች በ19ኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዞች ተሸንፈው ከግብፅና ከፍልስጤም ግዛት ሲወጡ፣ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችው ግብፅ የይገባኛል ጥያቄ አነሳች፡፡ ይልቁንም ኢትዮጵያ ሲኖዶስ በማቋቋም የራሷን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ከመረጠች ወዲህ የመከራከሪያ ነጥብ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የነበረው ግንኙነትና በእስልምና እምነት

በጣም የሚገርመው ደግሞ የክርስትና እምነት ተከታዮች ከቱርክ ጋር የሚያያዟቸው ቅዱሳን ሥፍራዎች፣ በቱርክ ውስጥ ስለሚገኙ ጉብኝት የሚያደርጉት ወደዚያው ወደ ቱርክ በመሄድ ሲሆን፣ ለቱርኮች ደግሞ ከእስልምና እምነት ጋር የተያያዙ ሥፍራዎችና ታላላቅ ሰዎች (በነብዩ መሐመድ የተወደዱ ጭምር) የሚገኙት በኢትዮጵያ ውስጥና ስለሆነ ልቦናቸው ወደ ኢትዮጵያ በማድረግ ፀሎት የሚያደርጉ መሆናቸው ነው፡፡ በእርግጥም በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የሚገኘው የእስልምና እምነት ግንኙነትም እንደ ክርስትናው ሁሉ ጥብቅ መሠረት ያለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ቱርኮች ኢትዮጵያን በነብዩ መሐመድ የተወደደች፣ የተወደሰች፣ የተከበረች አገር መሆኗን ከመጥቀሳቸው ጋር በጥብቅ ይያያዛል፡፡ ቱርኮች ከሁሉ አስቀድሞ የነብዩ ሙሐመድ ተከታዮች ፍትሕ ወደ የማያዛባውና እውነተኛ ወደ ሆነው ኢትዮጵያዊው ንጉሥ መላካቸው፣ ከዓለም አገሮች በተቀዳሚነት እስልምና የተሰበከባት መሆኗ፣ የቢላልና የሌሎች ውድ የነብዩ መሐመድ ወዳጆች አገር በመሆኗ ነብዩ መሐመድ ኢትዮጵዊ ሞግዚት፣ ኢትዮጵያዊ ሚስትና እስከ መቃብራቸው ያልተለዩዋቸው ኢትዮጵያዊ ወዳጆች መገኛ በመሆኗ፣ የፀሎት ጥሪ ማድረግ ለኢትዮጵያውያን የተሰጠባት አገር በመሆኗ፣ ከነብዩ መሐመድ ጎን በጀግንነት የተሠልፉ የእስልምና አርበኞች መገኛ በመሆኗ፣ በሌሎችም በዚህ ጽሑፍ ዘርዝረን የማንዘልቃቸው (ለተጨማሪ መረጃ የፕሮፌሰር አደም ካሚልን መጻሕፍት ይመልከቱ) ምክንያቶች ኢትዮጵያን ይወዷታል፡፡ ኢትዮጵያውያንንም ‹‹ነብዩ ሙሐመድ ያከብሯቸው ነበር›› ብለው ያከብሯቸዋል፡፡ እዚህ ላይ ግልጽ መሆን ያለበት ዋነኛ ጉዳይ ቢኖር ነብዩ መሐመድ የሃይማኖት ልዩነት ሳያደርጉ ኢትዮጵያውያንን የሚወዱና የሚያከብሩ እንደነበሩ ሁሉ፣ ይህን ሀቅ የሚገነዘቡ ቱርኮችም ኢትዮጵያውያንን ሃይማኖት ሳይለዩ የሚያከብሩ መሆናቸው ነው፡፡ ለቱርኮች ኢትዮጵያ በነብዩ መሐመድ የተባረከችና የተቀደሰች አገር ናትና ይህንን አጥብቀው ይከተላሉ፡፡

በ16ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የነበረው ግንኙነት

ቱርካውያን በ16ኛው ክፍለ ዘመን ኢማም አሕመድ ኢብራሂም አልቓዚን ለመርዳት የተሠለፉ ሲሆን፣ በመላው ኢትዮጵያ በተካሄዱት ጦርቶችም የኢማም አሕመድ ኢብራሂም አጋር ሆነው ተዋግተዋል፡፡ ደማቸውንም አፍስሰዋል፡፡ የግራኝ ትክል ድንጋዮች ተብለው በሚጠሩት ሥፍራዎች ሁሉ ቱርካውያን ተቀብረዋል፡፡ በተለይም ከክርስቶፎር ደጋማ ጋር ሰሐርቲ ግጀት ላይ በየካቲት 1542፣ ሐሸንጌ በነሐሴ 1542፣ ደጎማ በ1543 በተደረገው ጦርነት ቱርኮች የከፈሉት መስዋዕትነት በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡

16ኛው ክፍለ ዘመን አፄ ልብነ ድንግል ለመርዳት የመጡ ፖርቱጋላውያን እንደዘገቡት የኢትዮጵያና የፖርቱጋል መንግሥት እንቅስቃሴ ክርስትናን፣ የኦቶማን ሥርወ መንግሥት እንቅስቃሴ እስልምናን መሠረት ያደረገ ቢሆንም፣ በሁለቱም ወገኖች የነበረው እውነተኛው ፍላጎት የቀይ ባህርን፣ የኤደን ባህረ ሰላጤንና የህንድን የንግድ መስመር ለመቆጣጠር እንደሆነ የሚተነትኑ ሊቃውንት አሉ፡፡  

በዓፋር ክልል በኮናባ ወረዳ በበልበል ቀበሌ የቱርኮች መቃብር መኖር

ምንም እንኳ ቱርኮች ወደ አፋር ክልል፣ ኮናባ ወረዳ፣ በልበል ቀበሌ መቼ እንደመጡና ለምን ያህል ጊዜ እዚያ እንደኖሩ፣ እንዲሁም ለምን እንደመጡ በትክክል ባይታወቅም የቱርኮች መንደር መኖሩ ግን የአካባቢው ሰዎች ያስረዳሉ፡፡ ይህ ቦታ 16 ካሬ ሜትር ያህል ስፋት ባለው የድንጋይ ካብ በአራት ማዕዘን ቅርፅ የተከበበ ሲሆን፣ በግቢው ውስጥ የሰዎች መኖሪያዎች፣ በወቅቱ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ እንደ ወፍጮ ያሉ ቁሳቁሶች፣ የወዳደቁ የአንገት ጌጣጌጦች፣ የከበሩ ድንጋዮች ስብርባሪዎች፣ በኢትዮጵያ ከሚሠሩ ለየት ያሉ የሸክላዎች ሥራ ስብርባሪዎች ይገኛሉ፡፡ የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንደገለጹለት፣ ‹‹ዘመኑ ባልታወቀ ጊዜ በዚህ ሥፍራ ቱርኮች መሬቱን እያለሙ ሲኖሩ በሆነ ምክንያት ረሃብና በሽታ በአካባቢው ይከሰታል፡፡ በዚህ ጊዜ በርካታ ሕፃናት ስለነበሩ ወላጆቻቸው የሚችሉትን ያህል ይዘው ሲሄዱ ሊወስዷቸው ያልቻሉትን በር ዘግተውባቸው ሄዱ፡፡ ሕፃናቱም ቤቱ ሲፈርስ ተቀብረው ቀሩ፤›› ይላሉ፡፡  በእርግጥም በድንጋይ ቁልሉ ሥር የሕፃናት አፅም የሚታይ ሲሆን፣ ዘመኑ መቼ እንደሆነ በጥናት ለማረጋገጥ የሚቻል ይመስላል፡፡

በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል ያለው ዘመናዊ ግንኙነት

የሁለቱ አገሮች ማለትም የኢትዮጵያና የቱርክ ግንኙነት ከጥንት ጀምሮ የነበረ ሲሆን፣ የኦቶማን ሥርወ መንግሥት ግብፅን ካስገበረ ወዲህ ማለትም እ.ኤ.አ. በ1875 በምሥራቅ ኢትዮጵያ በኩል በመግባት በሐረር አሻንጉሊት መንግሥት ለማቋቋም በቅቶ ነበር፡፡ የግብፅ አሻንጉሊት ከሐረር ከወጣ በኋላ አፄ ምኒሊክ አቶ ዮሴፍንና ኮንት ሌዮንቲፍን በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር አድርገው ልከው ነበር፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በርካታ ስጦታዎችን ለኦቶማን ንጉሥ በመላክ በኢየሩሳሌም በተለይም በዴር ሡልጣን ገዳም የሚገኘው የኢትዮጵያ ጥቅም እንዲጠበቅ የድጋፍ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ በወቅቱ የቱርክ መሪ የነበሩት ዳግማዊ አብዱላሂ መልስ መስጠታቸው ይታወቃል፡፡ ይህም በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል ከ1890ዎቹ ጀምሮ የዲፕሎማቲክ ግንኙነት መመሥረቱን የሚያመለክት ነው፡፡ የኦቶማን ሥርወ መንግሥት እ.ኤ.አ. ከ1910-1912 በሐረር ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ነበረው፡፡ በአዲስ አበባ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ1925 በጉዳይ አስፈጻሚ የሚመራ ጽሕፈት ቤት ነበረው፡፡ ይህም ቱርክን ከመጀመሪያዎቹ ስድስት አገሮች አንዷ እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

የኦቶማን ሥርወ መንግሥት ከተንኮታኮተ በኋላ ኢትዮጵያ ከቱርክ ጋር የመሠረተችው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እ.ኤ.አ. ከ1926 ይጀምራል፡፡ በዚህ ዘመን ቱርክ ወደ ኢትዮጵያ የላከችው አምባሳደር ከሰሃራ በታች ካሉት አገሮች የመጀመሪያው መሆኑም ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳን ቱርክ በተጠቀሰው ጊዜ አምባሳደሯን ወደ ኢትዮጵያ የላከች ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ አምባሳደሯን የላከችው እ.ኤ.አ. በ1933 ነው፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቱርክን በይፋ በመጎብኘት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ መሪ ሲሆኑ፣ ይህም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እስከ ደርግ መንግሥት ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ ከ1984 ዓ.ም. ጀምሮ ግን ተቋርጦ ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የቀጠለው የደርግ መንግሥት ከወደቀ ወዲህ ሲሆን፣ ይህም በ2006 ዓ.ም. ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቱርክን በ2008 ዓ.ም. በይፋ ሲጎበኙ በኢስታምቡል ተካሂዶ በነበረው የአፍሪካና የቱርክ ጉባዔ ምክትል ሊቀመንበር እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፌዴራል ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ክቡር ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ከሰባት ዓመታት በላይ ማገልገላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ‹‹ወርልድ አናዶሉ›› ለተባለ አንድ የቱርክ የዜና ማዕከል በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል የሚገኘው የኢንቨስትመት ግንኙነት እጅግ በጣም ጥሩ ሊባል የሚችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከተመሠረተ ወዲህ በርካታ ቱርካውያን ኢንቨስተሮች ወደ አገራችን በመምጣት ልዩ ልዩ ኢንዱስትሪዎችን የዘረጉ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ለብዙ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል የከፈቱ የቱርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ይህም የልማት እንቅስቃሴ ቻይናና ህንድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚያደርጉት ተወዳዳሪ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከአዋሽ-ወልድያ የተዘረጋው የባቡር ሐዲድ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች የተቋቋሙት የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡  

እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 22 ቀን 2015 ኢትዮጵያ ለይፋዊ ጉብኝት መጥው የነበሩት ፕሬዚዳንት ረጀብ ጠይብ ኤርዶሃንም ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት የቱርክ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር መልካም በኢነርጂ፣ በኮንስትራክሽንና በመከላከያው ዘርፍ መልካም ግንኙነት እንዳላቸው ገልጸው ወደፊትም ይህን ግንኙነት ለማጠናከር መንግሥታቸው ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ ሁለቱ መንግሥታት በኢኮኖሚ በማኅበራዊና በባህል የሚያደርጉትን ግንኙነት ለማዳበር የሚያስችላቸውን ስምምነትም አድርገዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከቱርክ ከምታስገባው የኢንዱስትሪ ውጤት ጋር የማይመጣጠን ቢሆንም የእንስሳት ውጤቶች፣ የቆዳና ቆዳ ነክ ውጤቶች፣ ጨርቃ ጨርቅና የተሰፉ ልብሶች፣ የወረቀትና የፕላስቲክ ውጤቶችን ትልካለች፡፡ በአንፃሩም ከብረታ ብረት ጀምሮ የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ፣ የምግብ፣ የቤት ቁሳቁስ፣ ወዘተ ውጤቶችን ታስገባለች፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርብይ አህመድና የቱርኩ ፕሬዚዳንትጂብ ጠይብ ኤርዶሃን ወዳጅነት የሁለቱን አገሮች የኢኮኖሚና የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ያደርሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ማጠቃለያ

ቱርክ በኢትዮጵያ ውስጥ የጀመረችውን ልማት ለማጠናከር የሚያስችላት ጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ያላት ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ቀደም ሲል ለመጥቀስ እንደተሞከረው በኩናባ በልበል ቀበሌ የቱርኮች የጠፋ መንደር ስላለ ያንን መንደር በጥንቃቄ ቆፍረው፣ ከመቃብሩ ውስጥ የሚገኘው አፅም መርምረው በማረጋገጥ የቱሪስት መስህብ ቢደረግ፣ በነጋሽም፣ በአፅቢ ወንበርታና በኮናባ ያሉ የነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) ተከታዮች መቃብሮችን እንደገና ታጥረውና ለምተው በመላው ዓለም ለሚገኙ ሙስሊም ቱሪስቶች መስህብ ቢሆኑ፣ 16ኛው ክፍለ ዘመን ከኢማም አህመድ ኢብራሂም ጎን ተሠልፈው ኢትዮጵያን 12 ዓመታት ለረዱ ቱርካውያን ጎንደር ላይ፣ እንፍራንዝ ላይ፣ ዞብል ላይ ሐሸንጌ ላይ ሐውልት ቢሠሩም የሁለቱን አገሮች ወዳጅነት ሊያጠናክር ይችል ይሆናል።  በዚህም ምክንያት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ቱሪስቶች ወደ አገራችን ሊመጡ ይችላሉ። ከባይዛንታይን ዘመን ጀምሮ የነበረውን ወዳጅነታችን በአዲስ መንፈስ ተጠናክሮ ቢቀጥል መልካም ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...