Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየአርኖ ሚሼል ዳባዲ ምስክርነትና የወቅቱ የብሔር ፖለቲካ

የአርኖ ሚሼል ዳባዲ ምስክርነትና የወቅቱ የብሔር ፖለቲካ

ቀን:

(ክፍል አንድ)

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት

በመጀመርያ አርኖ ሚሼል ዳባዲ ማነው የሚለውን ጥያቄ እንመልከት፡፡ አርኖ ሚሼል ዳባዲ ትውልዱ ፈረንሣይ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ጁላይ 24 ቀን 1815 ተወልዶ በኖቬምበር 13 ቀን 1893 ያረፈ ሰው ነው፡፡ በፈረንሣይ ባስክ የሚባል ከተማ ተወልዶ ያደገው አርኖ ሚሼል ዳባዲ ከወላጆቹ አምስት ልጆች አንዱ ሲሆን፣ ከታላቅ ወንድሙ አንቷን ቶምሰን ዳባዲ ጋር በመሆን የሠሯቸው ሥራዎች ናቸው የዚህ ጽሑፍ ትንተና መሠረት፡፡

ይህ ጽሑፍ ለመረጃ ምንጭነት የተጠቀመው ወ/ሮ ገነት አየለ አንበሴ፣ ከፈረንሣይኛ ቋንቋ ወደ አማርኛ ከተረጎመቻቸው ሁለት መጻሕፍት ውስጥ የተወሰደ ነው፡፡ ሦስተኛውን መጽሐፍ በመተርም ሒደት ላይ ስለሆነች በዚህ ዝግጅት ውስጥ አልተካተተም፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ‹‹በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች ቆይታዬ›› የሚል ነው፡፡ ይህ የወ/ሮ ገነት አየለ ትርጉም መጽሐፍ አገራችን ኢትዮጵያ በመሳንፍቱ ዘመን ምን ትመስል እንደነበር በጣም በሚያስደንቅ አገላለጽ የሚገልጽ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን የታሪክ መሠረት ሳያውቁ የባጥ የቆጡን ለሚቀባጥሩ የወቅቱ ፖለቲከኛ ተብዬዎች ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ ታሪክ እ.ኤ.አ. ከ1784 እስከ 1855 ያለው ጊዜ (The Era of the Princes) ወይም የመሳፍንት ዘመን ተብሎ ይጠራ የነበረ ዘመን በመሆኑ፣ አገሪቱ በየቦታው የራሳቸውን ግዛት ይዘው ንጉሠ ነገሥት ለመሆን የሚፋለሙ መሳፍንቶች እጅግ የሚዘገንን ጦርነቶችን እያካሄዱ ሲፋለሙ የነበረበት ዘመን ነው፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ ከፈረንሣይ ሳይንስ አካዴሚ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ጥናታዊ ሥራ እንዲሠራ ተመድቦ እጅግ የሚደንቅ መረጃ ጥሎልን አልፏል፡፡ ወ/ሮ ገነት አየለም ይህንን መጽሐፍ በመተርጎም የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪኩን እንዲያውቅ በማድረጓ የአገራችን ታላቅ ባለውለታ ነች፡፡ እዚህ ላይ ራሷ እንደጠቀሰችው ባለቤትዋ የትርጉም ሥራውን እንድትሠራ ያደረገውን ማበረታታትም አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡ የዚህ ትርጉም ሥራ በተቋም ደረጃ መሠራት ሲኖርበት በግሏ በመሥራቷ በድጋሚ ልናደንቃት ይገባል፡፡ በዚህ ጽሐፉ የአርኖ ሚሼል ዳባዲ ስም ተደጋግሞ ስለሚነሳ በምኅፃረ ቃል (አሚዳ) እያልኩ ስለምጽፍ ይህ ጽሐፉ ወ/ሮ ገነት ያሳተመችው መጽሐፍ ሁለት ስለሆነ (መ1)፣ (መ2) መጽሐፍ አንድና መጽሐፍ ሁለት የሚል ትርጉም እንደሚኖረው አንባቢያን እንዲገነዘቡ አሳስባለሁ፡፡

በእነዚህ መጻሐፍት ውስጥ ጎልተው የተዘገቡ የጎጃሙ ንጉሥ ራስ ጎሹ፣ የጎንደሩ መስፍን ራስ ዓሊና የትግሬው መሳፍንት ደጃዝማች ውቤ ሰፊ ቦታ ይዘዋል፡፡ የሸዋው ገዥ ሳህለ ሥላሴ ግን አርኖ ሚሼል ዳባዲ ወደ ሸዋ ዘልቆ መረጃ ለመሰብሰብ ያደረገው ጉዞ ያልተሳካ በመሆኑ በስፋት አልተዘገበም፡፡

ወደ መጽሐፉ ይዘት ከመግባቴ በፊት በአውሮፓ በዚህን ወቅት የኢንዱስትሪ አብዮት በስፋት የተካሄደበት ወቅት የነበረ በመሆኑ፣ ፈረንሣዮች እጅግ ብልህነት በተሞላው አካሄድ የጦር ኃይል ከመላካቸው በፊት ሊወሩ ላሰቡት አገር በቂ መረጃ ለማሰባሰብ ይሠሩ እንደነበር ከዘገባው መረዳት አይከብድም፡፡ የአርኖ ሚሼል ዳባዲ ወንድም አንቷን ዲባዲ ዳራስ በተመሳሳይ ወደ ብራዚል ተልኮ ሰፊ ጥናታዊ ሥራዎች ሠርቷል፡፡

ፈረንሣዮች በዚህ ሁኔታ ጥናት አድርገው የኢትዮጵን ሕዝብ የመንግሥት አወቃቀር፣ የውትድርና ብቃት፣ የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ በበቂ ሁኔታ ጥናት አድርገው በጦርነት ኢትዮጵያን ማሸነፍ እንደማይችሉ ተገንዝበዋል፡፡ ፈረንሣዮች በየትኛውም ወቅት ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ አልገቡም፡፡ አርኖ ሚሼል ዳባዲ የሰበሰባቸው መረጃዎች በቂ ትምህርት ሰጥቷቸዋል፡፡

በተቃራኒው ጣሊያኖች እንዲህ ዓይነት ጥናት ባለማድረጋቸው ኢትዮጵያን በኃይል ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ፣ በዓድዋ ጦርነት ከንቱ መስዋዕትነት እንዲከፍሉ አድርጓቸዋል፡፡ አፄ ምኒልክ የዓድዋውን ጦርነት በድል ካጠናቀቁ በኋላ በአገር ውስጥ እዚህም እዚያም ንጉሠ ነገሥት ለመሆን ያልሙ የነበሩ መሳፍንቶች በሙሉ አደብ መግዛት ችለዋል፡፡ ከዓድዋ ድል በኋላ አንድም መሳፍንት ከአፄ ምኒልክ ፊት መቆም አልቻለም፡፡

በሌላ አነጋገር አሁን ያለችውን ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ዋናው መሠረት የተጣለው በዓድዋ ድል ምክንያት ነው፡፡ ከዓድዋ ጦርነት በኋላ የአውሮፓ ወረሪዎች ከጦርነት ይልቅ ዲፕሎማሲን እንዲመርጡ ተገደዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የአውሮፓ ኃያላን መንግሥታት ተራ በተራ በአዲስ አበባ ኤምባሲ መክፈት ጀመሩ፡፡

በአርኖ ሚሼል ዳባዲ መጻሕፍት ውስጥ ሌላው ትልቅ ትምህርት የሚሰጠን መረጃ በኢትዮጵያ በመሳፍንቱ ዘመን ይደረግ የነበረው ሽኩቻ፣ አንዱ መሳፍንት የሌላውን መሳፍንት ግዛት በጦርነት አሽንፎ ሰፊ ግዛትና ግብር ገባሪ ለማግኘት ይደረግ የነበረ ትግል እንጂ ምንም ዓይነት የብሔር ቅርፅ ያለው ጦርነት እንዳልነበረ መረዳት አይከብድም፡፡ የብሔር ቅርፅ ይዞ ይደረግ የነበረው ጦርነት ደጃዝማች ጎሹ ከኦሮሞዎች ጋር በተደጋጋሚ ያደረጉት ጦርነት ሲሆን፣ ደጃዝማች ጎሹ ከኦሮሞዎች ጋር በተደጋጋሚ ጦርነት ያድርጉ እንጂ ጎሹ ኦሮሚኛ ተናጋሪ እንደነበሩ በመጽሐፉ ውስጥ በስፋት ተዘግቧል፡፡

ስለብሔር አሠፋፈር በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሰው (መ1) ገጽ 44 ላይ እንዲህ ይላል

‹‹በሰኔ ወር የክረምት ወራት በመግባቱ መንገዱ ሁሉ ጭቃማ ሆኖ ደርቀው የከረሙት ወንዞችና ጅረቶች ሞልተው መፍሰስ ሲጀምሩ፣ የአማራና የትግራይ ግዛቶችን የሚያዋስነውን የተከዜ ወንዝ ለመሻገር ጨርሶ የማይሞከር ይሆናል፡፡ ተከዜ የሚሞላው ከሰኔ ወር መጨረሻ እስከ መስከረም አጋማሽ ነው፡፡ በእነዚህ ወራት በትግራይና በአማራ ግዛቶች መካከል ያለው ግንኙነት አንዳንድ ደፋርና ጎበዝ ዋናተኞች ወንዙን አቋርጠው ለመሄድ የቻሉ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡›› እዚህ ላይ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አስተያየት የሚሆነው አርኖ ሚሼል ዳባዲ ይህንን መረጃ የሰጠን፣ የወንዙን መሙላት ሊነግረን ፈልጎ እንጂ ስለብሔር አሠፋፈር መረጃ ሊሰጠን ፈልጎ አይደለም፡፡

ወደ ጥንታዊ የአክሱም ሥልጣኔ ሄደን ስንመለከት ደግሞ በአክሱም ሥልጣኔ ወቅት የተሠሩ የኪነ ሕንፃ ሥራዎች የትኛውም የጎንደር ግዛት ውስጥ ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ ይልቁኑም የአክሱም ሥልጣኔ አሻራ በቀላሉ በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ላይ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ የሚያመላክተን በትግራይና በጎንደር በኩል ከነበረው ግንኙነት በተሻለ፣ በትግራይና በላሊበላ በኩል የነበረው ግንኙነት የበለጠ እንደነበር ነው፡፡

በነገራችን ላይ የዚህ ጽሐፍ አዘጋጅ በተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ላይ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ሐሳቤን የመግለጽ ልምድ አለኝ፡፡ ይህ ጽሑፍ መቶኛዬ ሲሆን፣ ይህ ሥራ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ባያስገኝም በጥናት ላይ የተመሠረተ አሠራር እንዲኖር ይረዳል ብዬ ስለማምን ወደፊትም አቅም በፈቀደ ሁኔታ እቀጥልበታለሁ፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ ወደ ኢትዮጵያ ጉዞውን የጀመረው እ.ኤ.አ. በ1837 ዲሴምበር 25 ነበር፡፡ ለጉዞው የሚያስፈልጉትን ሁሉንም ግብዓቶች ይዞ በተጨማሪ አሽከሮቹን አስከትሎ የተለያዩ ቦታዎችን አልፎ ጂዳ እንደደረሰ፣ ከዚያም ጉዞውን ወደ ምፅዋ ለማድረግ ሲነሳ ከአሽከሮቹ አንዱ ዓሊ የሚባል፣ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የሚደረገው ጉዞ አደገኛ እንደሆነ በመገመት አልሄድም ብሎ ወደ ካይሮ ተመለሰ›› (መ1) ገጽ 14፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ አሽከር ዓሊ ወደ ኢትዮጵያ አልሄድም አደገኛ ነው ያለው ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ይህ አባባል የሚነግረን በዚያን ወቅት ኢትዮጵያውን ምን ያህል ተፈሪነት እንዳተረፉ ያመላክታል፡፡ ግብፆች በኋላ በጉርአና በጉንደት ጦርነት ከፍተው ከመደምሰሳቸው በፊት፣ በመሳንፍንቱ ዘመን ወደ ተለያዩ የጎንደርና የጎጃም ግዛቶች የወረራ ሙከራ አድርገው ሁሌም ሽንፈትን ቀምሰዋል፡፡ የአርኖ ሚሼል ዳባዲ አሽከር ዓሊ ይህንን ታሪክ ስለሚያውቅ ነው ወደ ኢትዮጵያ አልሄድም ለማለት የደፈረው፡፡

ግብፆች የባይን ምንጭ ለመቆጣጠር ሁሌም የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ሁሌም ሽንፈትን ነው ያደረሰባቸው፡፡ ለሽንፈታቸው ዋናው ምክንያት የኢትዮጵያውን አርበኝነት ቢሆንም፣ ሌላም ምክንያት አለ፡፡ ሌላኛው ምክንያት አንደኛ ግብፆች እንደሚታወቀው ሁሉም የሚኖሩት እጅግ ዝቅተኛ በሚባል ቦታ በመሆኑ፣ በዝቅተኛ ቦታ ያለው የኦክስጂን ክምችት ከፍተኛ ስለሆነ ይህንን ቦታ ለምደው ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ሲመጡ የኦክስጂን ክምችቱ ስለሚቀንስ፣ ከፍተኛ የሆነ የድካም ስሜት ስለሚሰማቸው በቀላሉ በጦርነት ይሸነፉ ነበር፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ፈረሶቻቸው ሽንጠ ረዣዥም የሆኑና ለሩጫ የሚመቹ እንጂ ተራራ ለመውጣት ልምድም ችሎታም ስለሌላቸው፣ ወደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራሮች በሚመጡበት ጊዜ መራመድ የሚያቆሙበት ሁኔታ ስለሚፈጠር ለግብፆች በኢትዮጵያ ምድር በተከታታይ መሸነፍ እነዚህን ከላይ የተጠቀሱ ምክንያቶች እንደ ግንዛቤ መውሰድ ይቻላል፣ ከብዙ በጥቂቱ፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ የካቲት 11 ቀን 1838 ዓ.ም. ምፅዋ ደረሰ

ምፅዋ ላይ ወንድሙን አንቷንን ትቶ የጉዞና የጉብኝት ፈቃድ ለመጠየቅ ወደ ደጃች ውቤ አመራ፡፡ ደጃች ውቤ በወቅቱ የትግራይ ገዥ ሲሆኑ፣ ከምፅዋ ወደ ዓድዋ በሚደረገው ጉዞ መካከል ሐባይ የምትባል ቦታ ያለች ሲሆን፣ የዚህ ቦታ ገዥ ደግሞ ደጃዝማች ካሳ ናቸው፡፡ ደጃዝማች ካሳ በመላው ኢትዮጵያ ዝናን ያተረፉ የደጃዝማች ሰባጋዲስ ልጅ ናቸው (መ1) ገጽ 26፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ ሐላይን ሲገልጹት ተራራማ እያለ በመሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ ከምፅዋ አጠገብ የምትገኝ ተራራማ ቦታ ኢሮብን ሳይሆን አይቀርም ሐላይ እያለ የጠራት፡፡ በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ፈረንጆች ሃይማኖታቸው ካቶሊክ በመሆኑ በኢትዮጵያ ሲደርሱ ብዙ ችግር ይገጥማቸው ነበር፡፡ አርኖ ሚሼል ዳባዲ ግን ስሙን ሲያስተዋውቅ ሚካኤል እያለ ወንድሙን ደግሞ ዮሴፍ እያለ ያስተዋውቅ የነበረ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የነበራቸው ቆይታ የተሳካ እንዲሆን ረድቷቸዋል፡፡ ቋንቋን በተመለከተ አርኖ ሚሼል ዳባዲ መጀመርያ በአስተርጓሚ ይገለገል የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ግን ራሱ አማርኛ አቀላጥፎ መናገር በመቻሉ ያለ አስተርጓሚ ሥራውን መሥራት ችሎ ነበር፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ ከደጃች ውቤ ፈቃድ ካገኘ በኋላ ወንድሙን ከምፅዋ ይዞ ወደ ደጃች ውቤ ግዛት ወደ ዓድዋ ገባ፡፡ በወቅቱ ከአውሮፓ የሚመጡ ተጓዦች ሁሉም ስጦታ ይዘው መምጣታቸው የተለመደ በመሆኑ፣ አሚዳ ለዳጃች ውቤ አይተውት የማያውቁትን አዲስ የጦር መሣሪያ አበረከተላቸው፡፡ በተጨማሪም ተኩሶ አሳያቸው፡፡

አሚዳ ከምፅዋ ተነስቶ በርካታ የኢትዮጵያ ግዛቶችን ሲያጠና አሁን ኤርትራ የምትባለዋ ምድር የተለያ ስሞች የነበራት መሆኑን ነገረን እንጂ፣ አንድም ቦታ ሁለቱም መጻሕፍት ውስጥ ኤርትራ የሚባል ቦታ መኖሩን አልነገረንም፡፡ አሚዳ ከትግራይ ቆይታው በበለጠ ወደ ጎንደርና ጎጃም መሄድ ፈልጎ የነበረ ቢሆንም፣ ይህ የጉዞ ዕቅዱ እምብዛም በደጃች ውቤ አልተወደደለትም፡፡ የሆነ ሆኖ ደጃች ውቤን በማሳመን ጉዞውን ወደ ጎንደር መቀጠል ችሏል፡፡

አሁን እያጨቃጨቀን ስላለው የወልቃይት ግዛት የሰጠን መረጃ አለ (መ1) ገጽ 44 ላይ፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የአማራንና የትግራይን ግዛት የሚያዋስነው የተከዜ ወንዝ ብሎ የጠቀሰ ሲሆን፣ (መ2) ገጽ 23 ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ከአክሱም ወደ ሰሜን አቅጣጫ በመሄድ የወልቃይት ክርስቲያኖችን አገር ከጥቋቁር ሻንቅላዎች አገር በሚያዋስነው መንገድ ለመጓዝ ነው ያሰብኩት፡፡ ወልቃይት የደጃች ውቤ አገር ነች (ግዛት ነች)›› እዚህ ላይ እኔ የገባኝ ከአክሱም በስተሰሜን ሌላ ወልቃይት የሚባል ቦታ በዚያን ጊዜ ነበር ማለት ነው፡፡

ሌላው ስለትግሬና አማራ ድንበር ብሎ እግረ መንገዱን የነገረን መረጃ (መ2) ገጽ 42 ላይ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹እሳቸው እንደሚሉት እንደ ምንም ብዬ ከደጃች ጦር ጋር ቆይቼ ወደኋላ ለመቅረት ብችል፣ ደጃች ውቤ ተከዜን በመሻገር ትግሬን ለቀው እንደወጡ እሳቸው ቦታውን ስለሚይዙ ከእሳቸው ጋር መቆየት እንደምችል ነው፡፡››

እነዚህ ሁለት የአሚዳ መጻሕፍት ውስጥ በትክከል የምንረዳው ነገር በዘመነ መሳፍንት ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የብሔር አሠፋፈር እንዳልነበረ፣ አንዱ መሳፍንት ሌላውን ወግቶ በማሸነፍ ግዛቱን ማስፋትና የግብር ገባሪውን ቁጥር ለመጨመር ይሠሩ ነበር እንጂ፣ በወቅቱ የብሔር አጀንዳ የማንም አጀንዳ አልነበረም፡፡ ደጃች ውቤ የትግራይ ንጉሥ ይሁኑ እንጂ ተወልደው ያደጉት ጎንደር ውስጥ እንደነበር አሚዳ ነግሮናል፡፡ በተጨማሪ ደጃች ውቤ የቤተ መንግሥት ቋንቋቸው አማርኛ እንደነበር፣ ከአሚዳ ጋርም በአማርኛ ቋንቋ መግባባት እንደቻሉ በሁለቱም መጻሕፍት ውስጥ ተደጋግሞ ተጠቅሷል፡፡

ሌላው በእነዚህ መጻሕፍት በስፋት የተገለጸው ጉዳይ ሁሉም መሳፍንቶች የበላይነታቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው እጅግ ደም አፋሳሽ ጦርነት ያድርጉ እንጂ፣ አንዱ ብሔር ከአንዱ ብሔር ጋር በጋብቻ የተሳሰሩ ነበሩ፡፡ ነገር ግን የጋብቻ ዝምድናቸው እርስ በርስ ከመዋጋት አግዷቸው አያውቅም፡፡ ጋብቻ ጠላትን ወዳጅ ለማድረግ የሚረዳ የፖለቲካ መሣሪያ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ከጦርነት በኋላ የተሸነፈው መስፍን እገብራለሁ ብሎ ከተስማማ፣ በፊት ይዞት የነበረውን ግዛት ምናልባትም ተጨማሪ ግዛት እንዲገዛ ሊመረቅለት ይችላል፡፡ ደጃች ውቤና ራስ ዓሊ ጦርነት ገጥመው ደጃች ውቤ በመሸነፋቸው ራስ ዓሊ እስከ ምፅዋ ባለው ግዛት ባለቤት ሆነው ነበር (መ2) ገጽ 60፡፡

ራስ ዓሊ በደጃች ውቤ ላይ ባገኙት ድል በመኩራራት የሸዋ ገዥዎችን ደብረ ታቦር ድረስ መጥተው እንዲገብሩ፣ አለበለዚያ ጦር ልከው እንደሚያስገብሯቸው ይዝቱ ነበር፡፡ በመሳፍንቱ ዘመን ከብሔር ሽኩቻ ይልቅ የሃይማኖት ማንነት የበለጠ ቦታ ነበረው፡፡ ይህም በዋናነት የእስልምና ሃይማኖትን ለማስፈፋት ሙከራ በሚያደርጉ ሰዎች ላይ ከባድ ቅጣት ይፈጸም ነበር፡፡ በወቅቱ እጅና እግር መቁረጥ በጣም የተለመደ ነበር፡፡ ቅጣቱ በዋናነት የሰውነት ክፍል በማጉደል መፈጸም የተለመደ ነበር፣ ዓይን ማውጣትንም ይጨምራል፡፡

አሚዳ ስለኦሮሞ ማኅበረሰብ የሰጠን መረጃ

ደጃች ጎሹ የጎጃም መሳፍንት ሲሆኑ በተደጋጋሚ ከኦሮሞዎች ጋር ጦርነት አድርገዋል፡፡ ኦሮሞዎች ምርጥ ፈረሶች ያሏቸው ቢሆኑም፣ ጥይት የሚተፋ የጦር መሣሪያ ምን እንደሆነ አያውቁም ነበር፡፡ በተጨማሪም ፈረሶቻቸው የጥይት ድምፅ የማያውቁ ስለሆኑ ጠመንጃ ሲተኮስ የመበርገግ ባህርይ ነበራቸው፡፡ (መጽ 1) ገጽ 199 ላይ እንዲህ ይላል፣ ‹‹ከዓባይ ጀምሮ አቋርጠን የመጣነው አገር ሁሉ በጣም ያምራል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ በከብት አርቢነት የሚኖር ሲሆን፣ የምናያቸው ከብቶች ሁሉ በጥንቃቄና በእንክብካቤ የተያዙ መሆናቸው ያስታውቃል፡፡ የከብቶቻቸውን ጭራ ተከትለው በመምጣት አሁን የያዙትን አገር ወረው ያዙ፤›› ይለናል፡፡

አሚዳ በሁለቱ መጻሕፈት ደጋግሞ እንደጠቀሰው ወሎን ሙሉ በሙሉ የኦሮሞ አገር ብሎ ነው የጠራው፡፡ ‹‹(መጽ 1) ገጽ 244 ክርስቲያንም ሙስሊምም ያልሆኑ፣ የራሳቸውን አምላክ የሚያመልኩ ኦሮሞዎች፣ እንዲሁም ሻንቅሎች ማለትም ‹ባሪያ› የሚሏቸው ብሔረሰቦች ጦርነት በሚዋጉበት ጊዜ ለጠላቶቻቸው ርኅራኄ እንደሚያደርጉ ይታወቃል፡፡ ክርስቲያኖች ኢትዮጵያውያን ግን ከእነሱም በተሻለ ለጠላቶቻቸው በተለይ ለምርኮኞች ደግነትንና ርኅራኄን ያሳያሉ፡፡ በተለይ በጭካኔያቸው ከታወቁት ከጎረቤቶቻቸው ሙስሊሞች ማለትም ከወሎ ኦሮሞዎች፣ ከአዳሎች፣ ከጥልጣሎችና ከጃዊዎች ጋር ብናወዳድራቸው ክርስቲያኖቹ ምሕረት በማድረግና በቀልን ባለመፈጸም የደግነት ተግባር እንደሚፈጽሙ ተመስክሮላቸዋል፤›› ይላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ወሎ በአማራ ክልላዊ መንግሥት ሥር ብትሆንም፣ ከላይ የተጠቀሰው የታሪክ ማስረጃ በዚያን ጊዜ ወሎ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች የሚኖሩባት ክልል እንደነበረች ያስረዳናል፡፡

በመሳፍንቱ ዘመን በተጨባጭ የተከሰተው ነገር ቢኖር ጦርነት ያሸነፈ የተሸነፈውን መሬት ይይዛል፣ ያስገብራል እንጂ ይኼ መሬት የአንድ ብሔረሰብ ነው ተብሎ ግዛቱ ተከብሮለት የተተወ የመሬት ክፍል የለም፡፡ የተሸነፈ ወይ ገባሪ ይሆናል፣ ወይ ደግሞ ሸሽቶ ይሄዳል፡፡ የኦሮሞ ማኅበረሰቦች ከጎሳ ሥርዓት ወጥተው ንጉሣዊ ሥርዓት መሥርተውና ግብር የሚሰበስብ ማዕከላዊ መንግሥት ኖሯቸው ስለማውቅ፣ በተጨማሪ በተሰበሰበው የግብር ገንዘብ በዘመኑ የነበረን ምርት የጦር መሣሪያ እየገዙ መጠቀም ባለመቻላቸው በተደጋጋሚ ለጥቃት ተጋላጭ ነበሩ፡፡ ይህ ታሪክ በአሚዳ መጻሕፍትም፣ በአቶ ይልማ ዴሬሳ የኢትዮጵያ ታሪክ በሚለው መጽሐፍ ውስጥም በስፋት ተጠቅሷል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ማኅበረሰቦችን ብንመለከት በሁለት ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የመጀመርያዎቹ አንድ ቦታ ተረጋግተው፣ የተለያዩ ግንባታዎችን ገንብተው፣ የእምነት ተቋማት፣ የእርሻ ሥራ እየሠሩ የሚኖሩና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ የሚኖሩ ሕዝቦች ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የኦሮሞ ማኅበረሰብ ከሁለተኛው ክፍል የሚመደብ በመሆኑ የጋራ ሥነ ልቦና ለማበልፀግ የሚመች ሁኔታ ተፈጥሮ አያውቅም፡፡

እነ ደጃች ጎሹም ራሳቸው ኦሮሚኛ ተናጋሪ በመሆናቸው ከላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ ስለሚያውቁ ኦሮሞዎችን በቀላሉ ያጠቁ ነበር፡፡ የሆነው ሆኖ ኦሮሞዎች በመላው ኢትዮጵያ ኖረው፣ አሻራቸውን ትተው እንደሄዱ በሁሉም አገሪቱ ክፍል የኦሮሚኛ መጠሪያ ያላቸው ወንዞች፣ ተራሮችና ሐይቆች ምስክር ናቸው፡፡ እውነቱን ለመናገር አሁን በአገራችን ተግባራዊ ተደርጎ ያለው የብሔር ክልል በምንም መመዘኛ የአንድን ብሔር አሠፋፈር የማይገልጽ ከመሆኑም በላይ፣ አገር ለማፍረስና ሕዝብ ከሕዝብ ለመጋጨት ተብሎ ብቻ ተግባራዊ የተደረገ ለመሆኑ በጣም በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ኢትዮጵያ ከመሳፍንቱ ዘመን ጀምሮ በነፍጠኛ ሥርዓት ውስጥ እንደኖረች ብዙም የሚያከራክር አይደለም፡፡ ነገር ግን በአማርኛ ተናጋሪ ነፍጠኞችና በእንግሊዝኛ ወይም በፈረንሣይኛ ተናጋሪ ነፍጠኞች መካከል ትልቅ ልዩነት አለ፡፡ አማርኛ ተናጋሪ ነፍጠኞች አንድን ቦታ ወረው ግብር ገባሪ ይፈጥሩና የሰበሰቡትን ሀብት ለወታደር ቀለብና የቤተ መንግሥት ወጪን ይሸፍኑበታል እንጂ፣ ለአገርም ሆነ ለዜጎች የሚጠቅም ምንም ሥራ ሠርተው አያውቁም፡፡ አገርን ከወራሪ (ከውጭ ወራሪ) ከመጠበቅ በቀር፡፡ እንግሊዝኛ ወይም ፈረንሣይኛ ተናጋሪ ነፍጠኞች ግን ከፍተኛ የሚባል የቴክኖሎጂ ሥራ ከማከናወናቸው በተጨማሪ፣ በርካታ ገንዘብ ለምርምርና ጥናት ያወጡ ነበር፡፡ በመሆኑም ኦሮሚኛ ተናጋሪ ሕዝቦች በአማርኛ ተናጋሪ ነፍጠኞች ሥር መውደቃቸው ምንም የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት ባያመጣላቸውም ቋንቋቸው ግን ተጠብቆ ቆይቷል፡፡

ለምሳሌ ኬንያ የሚኖሩ ኦሮሞዎች በአመዛኙ ቋንቋቸው ጠፍቶ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ሆነዋል፡፡ ኦሮሞዎች ያለ ንጉሥ በጎሳ አለቃቸው አማካይነት በርካታ ዘመቻዎችን አካሂደዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ (በመጽ 1) ገጽ 86 ላይ እንዲህ ይላል፣ ‹‹ሸዋ ከወሎ በመጡ ሙስሊም ኦሮሞዎች ወረራ ተቀስፎ የተያዘ ግዛት ነው፡፡›› በተጨማሪ እናሪያ ተብሎ ይጠራ የነበረ ግዛት አሁን ወለጋን ይዞ እስከ በደሌ ያለው ቦታ ‹‹ያልሠነጠ›› ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ ይህ ቦታ በአሚዳ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት የኦሮሞ አገር እየተባለ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ቦታ የኦሮሞ ግዛት ይባል እንጂ፣ አሁንም በተለያዩ መኳንንቶች ወረራዎች ተካሂደውበታል፡፡  

የኢትዮጵያውያን አሠፋፈር በተመለከተ አሚዳ እንደሚነግረን በገጽ 72 (መጽ 1) ላይ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ያለው አሠፋፈር እንደ አውሮፓ በአንድ ቦታ በጣም ጥቅጥቅ ያለ ሳይሆን፣ ዘርዘር ብሎ የሠፈረ ሕዝብ ነው ያለው፡፡ በሽታ፣ ረሃብ ወይም ጦርነት በመጣ ቁጥር ቦታውን ለቆ ወደ ሌላ አካባቢ ይሰደዳል፡፡ ከአውሮፓ የመጣ ተጓዥ ግር የሚለው አንድ አገር አለ፡፡ በሚያልፍበት አካባቢ የሚያየው አንድ ሕዝብ መካከል ከሌላ ቦታ ተሰዶ የመጣ የሌላ አካባቢ ሰው፣ ቤተሰብ እንዲያውም አንዳንዴ መንደር ሙሉ ሰው ከነባሩ ጋር ሠፍሮ ሲኖር ማየቱ ነው፡፡ ከነባሩ ነዋሪ ጋር በዘር ወይም በጎሳ የማይዛመድ ፍፁም የተለየ ብሔር ቢሆንም እንኳን፣ ተቀላቅሎ መኖር አንዳችም ችግር አይፈጥርም፡፡ ለመልካም አብሮ የመኖር ዘዴ የነባሩን ነዋሪ ወይም ብሔር ሕግና ልምድ አክብሮ መስሎ መኖር ብቻ ሲጠበቅበት፣ በበኩሉ አያት ቅድመ አያቶቹን ሳይክድ፣ ማንነቱን ሳይረሳና ጥንታዊ ልምዱን ሳይሽር መኖር ይችላል፡፡››

(መጽ 1) ገጽ 47 ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ኦሮሞዎች ሥር መሠረታቸው በአዋሽ ወንዝ ዙሪያ ነው ይባላል፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ቋንቋቸው እንደ ሳሆ ሁሉ ከአፋር ጋር ተመሳሳይ የቋንቋ ቤተሰብ ነው፡፡ ኦሮሞዎች ከባህሩ ጠረፍ ዙሪያ ባሉ ቦታዎች ነዋሪ ሲሆኑ፣ በዙሪያቸው የነበሩትን ቀደምት በመውረር በአካባቢ ብሔሮች ግዛት ውስጥ ከገቡ በኋላ ወይ አጥፍተዋቸዋል፣ አሊያም አባረዋቸዋል፡፡ ሶማሌዎች ብቻ ከዚህ ወረራ ያመለጡ ይመስላል፡፡››

የአሚዳ መጽሐፍ ውስጥ በስፋት ከተገለጸው ነገር አንዱ ከአማርኛ ተናጋሪው ወራሪ ይልቅ የኦሮሞ ወራሪዎች መስፋፋት ሰፊ ጊዜ እንደሚወስድ መረዳት ቀላል ነው፡፡ ነገር ግን አማርኛ ተናጋሪ ነፍጠኛ (የተሻሻሉ መሣሪያዎች ባለቤት የነበረ በመሆኑ) ኦሮሞዎች ከሌሎች ብሔሮች የወረሱትን ግዛት ነው የወረረው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው አፄ ምኒልክ ከዓድዋ ድል በኋላ የበርካታ ድሎች ባለቤት በመሆናቸውና ሊፋለማቸው ፍላጎት ያለው መሳፍንት በመጥፋቱ፣ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት ‹‹ወንዝ ዳር እንደ ተተከለ ዛፍ›› ቀጥ ብሎ ማደግ ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ እስከ 1983 ዓ.ም. ድረስ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ እስኪወጣ ድረስ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከዚያ በኋላ የተጀመረው የብሔር መንግሥት የመመሥረት ቅዠት ምንጊዜም ከቅዠትነት አያልፍም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሰማንያ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች ይኑሩ እንጂ፣ የአንዳቸውንም ድንበር ማንም ፈልጎ አያገኘውም፡፡ መቼም ደግሞ አጨቃጫቂ ያልሆነ ድንበር ፈልጎ ማግኘት አይቻልም፡፡ ‹‹ልፋ ያለው አንድ እንጨት ያስራል›› እንደሚባለው ውጤቱ ልፋት ብቻ ነው፡፡ (ይቀጥላል)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...