የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው መሾማቸውን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ‹‹ሹመቱ የተሰጠው በመላው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም፣ ደኅንነትና አካባቢያዊ መረጋጋት እንዲሰፍን ካለው ቁርጠኝነት ነው›› ተብሏል።
በተለይም ኦባሳንጆ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው መሾማቸው ከሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር፣ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ፅኑ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር ያስችላል ተብሏል፡፡
ኦባሳንጆ የኅብረቱ የጋራ ፍላጎትን ለማሳካት ሲባል ይህን ስትራቴጂካዊ የፖለቲካ ተልዕኮ መቀበላቸውን፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ መሐመት አመሥግነዋል፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷን አገር ናይጄሪያን ለስምንት ዓመታት የመሩት ኦባሳንጆ ለረዥም ዓመታት ያካበቱትን ጠለቅ ያለ የፖለቲካ ልምድ በመጠቀም፣ የአፍሪካ ቀንድን ሰላም ከፍ ወዳለ ደረጃ እንደሚያሳድጉት ተነግሯል።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሁሉም ባለድርሻ አካላትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሁሉንም ዓይነት ድጋፍ ለከፍተኛ ተወካዩ እንዲያደርግ ኅብረቱ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ አዲሱ የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ኦሊሴጐን አባሳንጆ በሚቀጥሉት ሳምንታት ወደ ቦታው እንደሚደርሱ በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ መንግሥት በአፍሪካ ቀንድ ባሉ አገሮች ውስጥ ስላሉ ጉዳዮች በቅርበት የሚከታተሉለትን ልዩ መልዕክተኛ የሆኑትን ጄፍሪ ፊልትማንን አድርጎ የሾመው በሚያዚያ 2013 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሐምሌ 2013 ዓ.ም. የአውሮፓ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው የተሾሙት አኔት ዌበርን ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ በኢትዮጵያና በአውሮፓ ኅብረት ስላለው ግንኙነትና የልዩ መልዕክተኛዋን ተልዕኮዎች በተመለከተ ሰኞ ነሐሴ 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡