Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ምርት ያላግባብ የሚያከማቹ ነጋዴዎችን ምርት በመሸጥ ገቢው በአደራ የሚቀመጥበት አሠራር ተጀመረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋና የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ በመጨመሩን ሳቢያ፣ ምርት ያላግባብ ሲያከማቹ የተገኙ ነጋዴዎችን ምርት በቀጥታ በመሸጥ የተገኘውን ገቢ በአደራ በሚመለከተው የመንግሥት አካል የሚቀመጥበትን አሠራር ተግባራዊ ማድረግ እንደጀመረ ተገለጸ፡፡

በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ዕቃዎች ጥናትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በ13 ቦታዎች ተከማችቶ የተገኘ ከሰባት ቢሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ከአንድ ሺሕ በላይ የጭነት መኪና ብረት በሕጋዊ መንገድ ወደ ገበያ ገብቶ እንዲሸጥና ገንዘቡ ለመንግሥት ገቢ እንዲሆን ተወስኗል፡፡ ከዚህ በኋላ እንደ ዘይትና መሠረታዊ ሸቀጣ ሸቀጦችን የሚያከማቹ ነጋዴዎች ሲገኙ፣ በቀጥታ ምርቶቹ ተሸጠው የተገኘው ገንዘብ በአደራ የሚቀመጥበትን አሠራር ተግባራዊ ማድረግ እንደ ጀመረ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ከዚህ በኋላ ሱቆችን በማሸግ ሌላ የእጥረት ችግር አንፈጥርም፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ በአንድ ቦታ የተከማቸ ምርት ሕገወጥ መሆኑ በተቋቋማው ግብረ ኃይል ሲረጋገጥ፣ ምርቱ በቀጥታ ወደ ገበያ ቀርቦ ዋጋ ለማረጋጋት ለሽያጭ እንደሚቀርብ አስረድተዋል፡፡ ምርቶቹን ያከማቸው ግለሰብ ተግባሩን በመቃወም ክስ ቢያቀርብ እንኳን፣ ምርቱ ተሸጦ ገንዘቡ በአደራ መልክ በመንግሥት ካዝና ስለሚቀመጥ፣ በሕግ ሲወሰን ገንዘቡ ለግለሰቡ ተመላሽ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡

ይህ ዓይነቱ ዕርምጃ ገበያን በማረጋጋት ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ያስታወቁት አቶ ካሳሁን፣ ከዕርምጃው አተገባበር ጋር በተያያዘ ሕገወጥ የሆኑ ንብረቶች ሲገኙ እንዴት ይሸጣሉ የሚለውን የሚመልስ የመንግሥት አሠራር እንዳለ ገልጸዋል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ዕርምጃ ዋነኛ ዓላማ ምርቱ ለገበያ ፍጆታ በማዋል ዋጋ እንዲያረጋጋ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ሕጋዊ ሆኖ የተገኘ ነጋዴ በሚደረገው ማጣራት ትክክለኛ ከሆነ የንብረቱ ዋጋ እንደሚመለስለት፣ ተገቢውን ማስረጃ አሟልቶ ሳይገኝ ሲቀር ደግሞ ንብረቱ ወይም ከሽያጭ የተገኘው ገንዘብ እንደሚወረስ አክለዋል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትቴር ኢኮኖሚውን ለማዳከም እየተደረገ ያለውን አሻጥር ለመቀልበስ ሦስት አገር አቀፍ የውይይት መድረኮች ለማድረግ በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ ካሳሁን፣ የመጀመርያው ከአምራቹ ዘርፍ ጋር የሚደረገው ምክክር ነው ብለዋል፡፡ ይህም ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአዲስ አበባ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረና በቀጣይ በፌዴራል ደረጃ እንደሚቀጥል አስታውሰዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ከአስመጪዎች ጋር የምክክር መርሐ ግብር እንደሚኖር ገልጸው፣ በተለይ የምግብ ሸቀጦችና የኮንስትራክሽን ዕቃዎች አስመጪዎች ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡ በተለይም አስመጪዎች በገበያ ውስጥ ወሳኝ የሆኑ አካላት በመሆናቸው ምርት በበቂና ምክንያታዊ በሆነ ዋጋ እንዲሸጡ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡

ሦስተኛው ከኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር የሚደረገው ምክክር እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ግብረ ኃይሉ በሚያወጣወ ዕቅድ መሠረት የምክክር መድረኮቹ በተከታታይ የሚደረጉ እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ሚኒስቴሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ የመጣውን የኑሮ ውድነት መንስዔ በመለየት ዕልባት ለመስጠት ያለመ ውይይት፣ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደር የንግድ ቢሮ ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሳምንት አጋማሽ በበይነ መረብ ማካሄዱ ይታወሳል።

በውይይቱ ላይ በመሠረታዊ የፍጆታቃዎች ላይ በየዕለቱ ለሚስተዋለው የዋጋ ጭማሪ መንስዔ ናቸው የተባሉ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ በቅንጅታዊ አሠራር አለመጠናከር ምክንያት የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጠን ችግር ከመከሰቱ ባሻገር፣ የኅብረት ሥራ ኤጀንሲዎችና ዩኒየኖች ዋጋ የማረጋጋትራቸውን ወደ ጎን በመተው ትርፍ ለማካበትና ምርት የመደበቅ ድርጊት እየፈጸሙ መሆናቸውን፣ ያልተናበበ የኬላዎች ቁጥጥር፣ በደረሰኝ የተረጋገጠ የንግድ ሥርዓትና ወጥነት ያለው የዋጋ ተመን አለመኖርም ለችግሩ ምክንያት ተጠቃሾቹ ጉዳዮች መሆናቸው ተወስቷል፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲን መረጃ ጠቅሶ እንዳስታወቀው፣ በኢትዮጵያ 70 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎት መኖሩ በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ የምታመርተው የስንዴ መጠን 36.3 ሚሊዮን ኩንታል ነው፡፡ የስንዴ ምርትና ፍላጎትን ለማመጣጠን ከዓለም አቀፍ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና ከሌሎች ምንጮች ሰባት ሚሊዮን ኩንታል፣ መንግሥት በግዥ ከሚያቀርበው 7.8 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ፣ በጠቅላላው 51.1 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በየዓመቱ ወደ አገር ውስጥ ቢገባም፣ በአቅርቦትና ፍላጎት መካካል ያለው ልዩነት 18.9 ሚሊዮን ኩንታል እንደሆነ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ወርኃዊ የምግብ ዘይት ፍላጎት 74 ሚሊዮን ሊትር ሲሆን፣ ይህንን ፍላጎት ለመሸፈን 2.3 ሚሊዮን ሊትር በአገር ውስጥ ምርት፣ 5.3 ሚሊዮን ሊትር በነፃ ገበያ ከውጭ በሚያስገቡ ነጋዴዎች፣ እንዲሁም መንግሥት ከቀረጥ ነፃ በሚያስገባው 40 ሚሊዮን ሊትር፣ በአጠቃላይ 48 ሚሊዮን ሊትር ወርኃዊ ፍጆታ የሚሸፈን ቢሆንም፣ በፍላጎትና አቅርቦት ምጣኔ አንፃር የ26 ሚሊዮን ሊትር ልዩነት እንዳለ ይታወቃል፡፡

የአገሪቱ ዓመታዊ የስኳር ፍላጎት ሰባት ሚሊዮን ኩንታል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፈነው አራት ሚሊዮን ኩንታል፣ ቀሪው ሦስት ሚሊዮን ኩንታል ከውጭ በሚፈጸም ግዥ እንደሚሸፈን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መጪውን በዓልና ወቅታዊውን የመሠረታዊ ፍጆታ ዕቃዎች ግሽበት መሠረት በማድረግ፣ በዚህ ወቅት አራት ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ፣ 36.8 ሚሊዮን ሊትር ዘይት፣ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ግዥዎችን በመፈጸም ምርቶቹን ወደ አገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች