Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየሕወሓት ታጣቂዎች የተቆጣጠሯቸውን ቦታዎች አንዳቸውንም “ በውጊያ እንዳልያዙ ” ተገለጸ

የሕወሓት ታጣቂዎች የተቆጣጠሯቸውን ቦታዎች አንዳቸውንም “ በውጊያ እንዳልያዙ ” ተገለጸ

ቀን:

የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራና በአፋር ክልሎች በቁጥጥር ሥር ያዋሏቸውን ቦታዎች፣ አንዳቸውንም ተዋግተው እንዳልያዙ የአገር መከላከያ ሠራዊት ገለጸ፡፡

‹‹አሸባሪው ኃይል በሚለቀው ወሬ የተነሳ መጡ መጡ በሚል ሥነ ልቦና በመስለብና በማሸበር ሕዝቡን ቦታ እንዲለቅ በማድረግ ከመግባታቸው ውጪ፣ ፊት ለፊት ተዋግተው የያዙት ቦታ የለም፤›› ሲሉ የአገር የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ጌትነት አዳነ (ኮሎኔል) ተናግረዋል፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በየወሩ የሚካሄደው አዲስ ወግ ውይይት ‘ፅናት ለአገር ህልውና’ በተሰኘ ርዕስ፣ ረቡዕ ነሐሴ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ ኮሎኔል ጌትነትን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሃት፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣  እንዲሁም የሥነ አዕምሮ ባለሙያው ምሕረት ደበበ (ዶ/ር) የውይይት መነሻ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

ኮሎኔል ጌትነት፣ ‹‹መንግሥት እንደ መንግሥት እንጂ እንደ አንድ ተራ ወመኔ አሸባሪ ወሬን በፈለገው ጊዜ እንደሚረጨው ሁሉ በመርጨት አገር አያስተዳድርም፤›› ብለዋል፡፡ ለአብነትም ከመረጃ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ ከሰሞኑ በማኅበረሰቡ ዘንድ በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የጦር ጄኔራል ወይም ኮሎኔል ተያዘ ሲባል መንግሥት ለምን አይነግረንም የሚሉ አቤቱታዎች መብዛታቸውን በመጥቀስ፣ መንግሥት ከተያዘው ግለሰብ ጠቃሚ የሚባል መረጃ እንደሚያገኝበት ካመነ፣ ስለተያዘው ግለሰብ ከማወጅ እንደሚቆጠብ አስታውቀዋል፡፡

በቀደሙት ዘመናት በተለይም በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ የጣሊያንን ወራሪ ኃይል ጨምሮ ከውጭ የመጡ ኃይሎች ኢትዮጵያውያንን ለማንበርከክ ደፋ ቀና ባሉባቸው ጊዜያት፣ ኢትዮጵያውያን ‹‹አገሬን ለጠላት አልሰጥም›› ብለው ለአንድ አገራቸው ሲዘምቱ፣ ሲዘምሩ፣ ሲዘፍኑ፣ ሲዋደቁና ሲጋደሉ እንደቆየ አስታውሰው፡፡ ኢትዮጵያውያን  ሁልጊዜም የአገራቸውን ዳር ድንበር ለዘመናት አስጠብቀው ለጠላት እንቢ አልገዛም ብለው ስለመኖራቸው አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሁኑ ጊዜ  በኢትዮጵያ ለግጭት ምክንያት አንዱ መንስዔ ከሆነውና ኢትዮጵያውያን ከማንም ገንዘብ፣ ጉልበትና ዕውቀት ሳይጠይቁ እየገነቡት ያለው የህዳሴ ግደብ፣ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር ሌላም የሚያመነጨው ጉልበት በመኖሩ፣ ይህን ከማይመኙ ኃይሎች የተለያዩ ሴራዎች እየተጠነሰሱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

‹‹በእኔ እምነት አሁን ከሁለተኛው ሙሌት በኋላ  እንደ ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሁሉ የሱዳንና የግብፅ የመከላከያ ሠረዊት ሁሉ ሊጠብቁት ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጉዳት ቢደርስ ጉዳቱ የሁላችንም ስለሚሆን፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን አንጠብቅም ቢሉ ግን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመጠበቅ ወደኋላ እንደማይል አክለው ገልጸዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረው የአገር ውስጥና የውጭ ጠላት ባህሪና መልክ የእጅ አዙር እየሆነ፣ እንደቀደመው ወኔው ሁሉ አትንኩኝ የሚል ሕዝብ፣ መሪና የአገር መከላከያ ሠረዊት የተመሠረተበት ወቀት ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡

በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ከምንጊዜውም በላይ አንድነቷን እያስጠበቀች ያለች አገር ስለመሆኗ ገልጸው፣ የአገር መካላከያ ሠራዊት ባደረገው የሕግ ማሻሻያ፣ አዲስ አደረጃጀትና የለውጥ ሥራ ሠራዊቱ ኢትዮጵያዊ ቁመና እንዲይዝ ከመደረጉም ባለፈ፣ ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በላይ ስለአገራቸው ጉዳይ በአንድነት ቆመው የፅናት ተምሳሌት እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተደረጉት የሕግ ማሻሻያዎች በተጨማሪ የሠራዊቱን ሕይወት ሊያሻሽሉ የሚችሉ የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ሥራዎች በመከናወናቸው፣ ሠራዊቱ ለአገር ዘብ ሲቆም የሚለብሰውን የደንብ ልብስ ገዝቶ እንዲለብስ ይደረግ የነበረው አሠራር ተቀይሮ፣ በመንግሥት ወጪ በነፃ ጥራቱን የጠበቀ አለባበስ ስለቀረበለትና ሌሎች ድጋፎችን ከቀድሞው በተለየ በማግኘቱ እንደ ተቋም ገለልተኛ፣ በማንም ፖለቲከኛና ካድሬ እጁ የማይጠመዘዝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በሕዝቡ ዘንድ የተቸረው ድጋፍና ፍቅር ለመከላከያ ሠራዊቱ ስንቅ እንደሆነው፣ ለዚህም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም.  የሰሜን ዕዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ በሕወሓት ታጣቂዎች የተካሄደበትን አገር የማፍረስ አሳፋሪ ተግባር በሚገባ መቀልበስ አስችሎታል ብለዋል፡፡

አፄ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን ለባዕዳን አልሰጥም ብለው አገርን እንዳስቀደሙ ሁሉ፣ የትግራይ ሕፃናትና ልጆችን አልመታም ያሉ ትልልቅ ገድሎችን የሠሩ በርካታ ‹‹ቴዎድሮሶችን›› በመፍጠር፣ በትግራይ ክልል በተፈጠረው ጦርነት ‹‹የትግራይን ሕዝብ ከምናጠፋ ራሳችንን እናጥፋ›› ብለው ራሳቸውን መስዋዕት ያደረጉ ጀግኖች መፈጠራቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ የምታሳሳ እናትና ለዘመናት በደምና በአጥንት የተገነባች የጋራ ጎጇችን እንጂ፣ በቅጥረኛ ባንዳዎች ትፍረስ  የምትባል የጨረቃ ቤት አይደለችም፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በኪነ ጥበቡ ዘርፍ የመወያያ ርዕስ የመነሻ ሐሳብ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ባህልና ኪነ ጥበብ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰርፀ ፍሬስብሃት በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ፅናት ለሉዓላዊነት በሚጠየቅበት ጊዜ ላይ በመሆኗና ከባድ የፈተና ወቅት በመሆኑ፣ የኪነ ጥበብ ሚና ለአገር ህልውና ትልቅ ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡ ለአሸናፊነት የሚያበቁ ሁለት ጉዳዮችን ያቀረቡ ሲሆን፣ አንደኛው የሥነ ልቦና የበላይነትን የተጎናፀፈ ወኔ፣ የጠራና ግራና ቀኝ የሌለው ምክንያታዊነት ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ከብዙ ዓመታት በፊት አብዛኞቹ ኪነ ጥበብ ተቋማት ኢትዮጵያዊነትንና የአገር ፍቅርን መሠረት አድርገው መቋቋማቸውን በመገለጽ፣ የጥበቡ ዘርፍ ትልቅ በትር እያረፈበት ኢትዮጵያውያን የነበራቸውን በጦርነት የማሸነፍ ወኔና አገር ወዳድነት በጥበባቸው እንዳይገልጹ ተገድበው እንደቆዩ ገልጸዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ማሞ ምሕረቱ በበኩላቸው በቀደሙት ዘመናት የኢኮኖሚው ዘርፍ እንዳያንሰራራ አድርገውት የነበሩት መዋቅራዊ ተግዳሮቶችን ሲገልጹ፣ አገራዊ ልማቱ በብድርና በዕርዳታ ተይዞ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማምጣት ተስኖት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በተለይም ከ27 ዓመታት በላይ በሕወሓት በበላይነት ሲመራ በነበረው የመንግሥት ሥርዓት የፈጠረውን አገራዊ ፈተና በተቀበለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት፣ በለውጥ ማግሥት ኢትዮጵያውያን ፈተናን ወደ ሌላ ተስፋ መሸጋገሪያ የሚያደርጉ ሕዝቦች መሆናቸው ታይቷል ብለዋል፡፡

በዚህም የኢኮኖሚው ዘርፍ ከነበሩበት ማነቆዎችና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ላይ ከተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽን፣ ከሰላም ዕጦት፣ ከዓለም አቀፍ ጫና፣ ከአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ ወጥቶ ማገገሙን በመግለጽ፣ የውጭ ብድር አጠቃላይ አገራዊ ምርት ጋር ሲወዳደር በ2010 ዓ.ም. ከነበረው 36.7 በመቶ በ2013 ዓ.ም. ወደ 27 በመቶ ዝቅ ማለቱን አስታውቀዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. ለውጭ ገበያ ከተላከው ምርት ወደ አራት ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን በመጥቀስ ትልቅ የሚባል ሥራ መሠራቱን በመጥቀስ፣ በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚው ዘርፍ  በችግሮች ውስጥም ሆኖ ያለው ተስፋ ብሩህ ነው ብለዋል፡፡

በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ከተከሰተው የዋጋ ንረትና በአገር ውስጥ ከተፈጠሩ ችግሮች ጋር ተዳምሮ በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው የገበያ አለመረጋጋት ማስታገሻ የሚሆን፣ 400 ሺሕ ኩንታል ስንዴና 36.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ተገዝቶ ጂቡቲ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

የሥነ አዕምሮ ባለሙያው  ምሕረት ደበበ (ዶ/ር)፣ የፅናት ሥነ ልቦና ከሌሎች መሣሪያዎች ሁሉ አሸናፊነት ላይ እንደሚያደርግና ያልታየን አቅም የሚያሳይ መሣሪያ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹ፅናትን የሚፈጥረው የዓላማ ትልቅነት በመሆኑ እንደ አገር የት ልንደርስ እንችላለን ብሎ ማሰብ ትልቅነት ስለሆነ፣ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ካለብን የእርስ በርስ ቁርሾ፣ ግጭት፣ የዓላማ ግልጽ አለመሆን፣ በተሳሳቱ ዓላማዎች ከመቆምና እርስ በርስ ከመጋጨት መውጣት ይኖርብናል ሲሉ፤›› ተናግረዋል፡፡

ፅናት በእምነት መሄድን እንደሚጠይቅና አገርን ወደ የሚቀጥለው የተሻለ ደረጀ መውሰድ ስለመሆኑ በመጠቆም፣ ፅኑ ሕዝቦችና መሪዎች ወደፊት የሚመጣውን ዕድል በመመልከት፣ የኋላ ታሪክን ማየትና የአሁኑን ሁኔታ መገንዘብ የሚያስችል የመንፈስ ጥንካሬ ያላቸው መሆን እንደሚገባቸውም አመላክተዋል፡፡

የአገር ህልውና የሁሉም መሠረት በመሆኑ የሆነውና ያልሆነውን ማውራት ትቶ፣ ዕድል ላይ ያተኮረና ሊደረስበት የሚችለው ጉዳይ ላይ ትኩረት መፍጠር እንደሚያስፈለግ አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...