Wednesday, June 19, 2024

በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ሲባል መፍትሔ ይፈለግ!

በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የንፁኃን ደም በከንቱ እየፈሰሰ ከመሆኑም በላይ፣ የአገርና የዜጎች ንብረትም እየወደመ ነው፡፡ ሰላም ሲጠፋ ማረስ፣ መነገድ፣ መማር፣ ከቦታ ወደ ቦታ መንቀሳቀስና የመሳሰሉት የሰላም ትሩፋቶች ይጠፋሉ፡፡ በምትካቸው ዕልቂትና ውድመት ይተካሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት መዋል የሚገባው የሰው ኃይል፣ ሀብትና ጊዜ በከንቱ እየባከነ ነው፡፡ ይህ ጦርነት በፍጥነት መቋጫ ማግኘት አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ለአገር ህልውና መዘዝ አለው፡፡ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው ከገባችበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ በፍጥነት እንድትወጣ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህ ኃላፊነት ጦርነቱን በፍጥነት ለመቋጨት የሚረዱ የመፍትሔ ሐሳቦችን ማመንጨት ያካትታል፡፡ ጦርነት ሲራዘም የዜጎች ሕይወትና ሀብት ብቻ ሳይሆን፣ የአገር ህልውናም ከፍተኛ አደጋ ይደቀንበታል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጦርነት በሚካሄድባቸው አካባቢዎች በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ሞት፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት፣ መፈናቀል፣ የንብረት ውድመትና ማኅበራዊ ቀውስ የሚያስከትለው ጠባሳ በቀላሉ የሚገላገሉት አይደለም፡፡ በጦርነቱ ሳቢያ እየደረሰ ካለው ጉዳት በተጨማሪ ኢኮኖሚውም እየተንገዳገደ ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ የኑሮ ውድነቱ ሊቋቋሙት የማይችል ባላጋራ እየሆነ ነው፡፡ መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ይህንን አደገኛ ሁኔታ በማጤን፣ ጦርነቱ በፍጥነት ተቋጭቶ አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍን አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ መከራ ውስጥ ላሉ ወገኖች ሲባል ለሰላም መስፈን ማንኛውም ዓይነት መስዋዕትነት መከፈል አለበት፡፡

በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝና በሶማሌ ክልሎች በንፁኃን ላይ እየደረሱ ያሉ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎች፣ ዘረፋዎችና ውድመቶች ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ተደማምረው ለአገር ህልውና ብርቱ አደጋ ጋርጠዋል፡፡ አርሶ አደሮች ከመኸር የእርሻ ሥራቸው ከመስተጓጎላቸው በተጨማሪ፣ ከእነ ቤተሰቦቻቸው እየተገደሉና እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ከማጀታቸው ጀምሮ እስከ ከብቶቻቸው ድረስ ዘረፋ ይፈጸምባቸዋል፣ ጎጆዎቻቸው ይቃጠሉባቸዋል፡፡ ልጆቻቸው የአስነዋሪ ድርጊቶች ሰለባ ይሆናሉ፡፡ በሕይወት የተረፉት ማቄን ጨርቄን ሳይሉ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ለአስቸኳይ ዕርዳታ ጠባቂነት ተዳርገዋል፡፡ ሕፃናት፣ ነፍሰ ጡሮች፣ አራሶች፣ አቅመ ደካማ አዛውንቶችና የአካል ጉዳተኞች በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች ሰለባ ሆነዋል፡፡ ይህ ሁሉ አልበቃ ብሎ ሕፃናት በግዳጅ ለውጊያ ተመልምለው ጦር ሜዳ መሠለፋቸው አስደንጋጭ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ጊዜ በብዙ ሥፍራዎች የሚስተዋሉ ምስቅልቅሎች በፍጥነት መፍትሔ ካልተበጀላቸው፣ ለአገር ህልውና ከፍተኛ መዘዝ እንደሚያስከትሉ መገንዘብ ይገባል፡፡ ወገኖቻችን የግጭትና የጥቃት ሰለባ እየሆኑ አንድ ዕርምጃ ወደፊት መጓዝ ስለማይቻል፣ መንግሥትን ጨምሮ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ለሰላማዊ መፍትሔ ርብርብ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጦርነት ከዕልቂትና ከውድመት በስተቀር ውጤት አያመጣም፡፡

ኢትዮጵያ ከሰላማዊና ከሕጋዊ የፖለቲካ ትግል ውጪ የአመፅ መንገድ አያዋጣትም፡፡ ኢትዮጵያ የታሪኳ አብዛኛው ክፍል የጦርነት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከዚህ ቀደም የውጭ ወራሪዎችን ለመመከትም ሆነ በእርስ በርስ የሥልጣን ትግል በርካታ ጦርነቶች ተደርገዋል፡፡ ዘመነ መሣፍንትን እንዲያበቃ ካደረጉት አፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ በተደረጉ ጦርነቶች በርካቶች አልቀዋል፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፣ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ጦርነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያተረፈው ነገር ቢኖር ከመጠን ያለፈ የመረረ ድህነትና ኋላቀርነት ነው፡፡ ከግጭትም ሆነ ከጦርነት አስተሳሰብ ውስጥ መውጣት ይበጃል፡፡ ማንም አሸናፊ የማይሆንበትን የዕብሪት መንገድ መተው ይሻላል፡፡ ማንም በማንም ላይ የበላይ መሆን አይቻለውም፡፡ ይህ ጊዜ ያለፈበት አስተሳሰብ ሥሩ ተነቅሎ መጣል አለበት፡፡ በእኩልነት ላይ የተመሠረተች ዴሞክራሲያዊት አገር እንዴት እንደምትገነባ የበሰሉ ሐሳቦችን ማቅረብ የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ ጥቂት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ብቻ የበላይ ሆነው አገር ስትታመስና ሕዝብ ተስፋው ሲደበዝዝ፣ ለምን ብሎ የሚነሳ ጠያቂና ሞጋች ትውልድ ማፍራትም ሌላው የጊዜው ጥያቄ ነው፡፡ 110 ሚሊዮን በላይ የሆነው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተንቆ፣ ተገፍቶና ለሥቃይ ተዳርጎ መቀጠል አይቻልም፡፡ ለወገኖቻችን ቅድሚያ ይሰጥ፡፡

በዚህ ዘመን ትዕግሥት፣ ማስተዋልና አርቆ አሳቢነት በጎደላቸው ፖለቲከኞችና ልሂቃን ምክንያት ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ ነው፡፡ ለሕዝብና ለአገር ኃላፊነት የማይሰማቸው በሕዝብ መካከል መጠራጠርና ጥላቻ ይዘራሉ፡፡ በብሔርና በሃይማኖት ለማጋጨት ያደባሉ፡፡ በእነሱ የተቀሰቀሱ ኃላፊነት የማይሰማቸው ወገኖች ግጭት በማስነሳት የንፁኃንን ሕይወት ያጠፋሉ፣ ንብረት ያወድማሉ፣ ቤተ እምነቶችን ያቃጥላሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው የአገርን ህልውና እየተፈታተኑ የሕዝብን ደኅንነት ያቃውሳሉ፡፡ ከእንዲህ ዓይነት ችግሮች በስተጀርባ ያሉ ኃይሎች ዓላማ ሥልጣንና ጥቅም ብቻ ስለሆነ፣ ለሕዝብም ሆነ ለአገር ሰላም ፈፅሞ ደንታ የላቸውም፡፡ ከታሪክ ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ስላልሆኑ የሚደርሰው አደጋ ንፁኃንን ያጠፋል፡፡ ሕዝቡ ለዘመናት አብሮ የገነባቸውን ታሪካዊ እሴቶች መናድ ማለት አገር ማፍረስ እንደሆነ እያወቁ፣ ከራሳቸው አደገኛ ፍላጎት ውጪ ምንም ነገር አይታያቸውም፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ ያጋጠመው እንዲህ ዓይነቱ ፈተና ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ መከራው እንዲያበቃ ለሰላም መስፈን መፍትሔ መፈለግ ይበጃል፡፡

የኢትዮጵያን አጠቃላይ ሁኔታ በወፍ በረር ስንመለከተው ችግራችን የሚጀምረው ከቤተሰብ ነው፡፡ ቤተሰብ ሰላማዊና የተረጋጋ ሕይወት የማይመራ ከሆነ ለማኅበረሰቡ የሚያቀርበው የተንጋደደ ሰብዕና ነው፡፡ ወሬ ከሚበዛበት ቤተሰብ ውስጥ ወሬኞች እንደሚፈጠሩ ሁሉ፣ ተንኮል ከሚጎነጎንበት ቤተሰብ ውስጥ መሰሪዎች ይገኛሉ፡፡ ሌብነት፣ ሐሜት፣ ክፋት፣ ሴራ፣ ወዘተ. የዚህ ውጤት ናቸው፡፡ ማኅበረሰቡም እነዚህን ችግሮች ማረቅ ካልተቻለው የላይኛው እርከን ድረስ ጦሱ ይከተላል፡፡ የሥራ ከባቢዎችም ብዙ ጊዜ ችግር የሚገጥማቸው እንዲህ ዓይነት ሰብዕና የተላበሱ ሰዎች ሲቆጣጠሯቸው ነው፡፡ እነዚህ የኃላፊዎችን የመወሰን ድርሻ ጭምር በመውሰድ ወይም የተጣመመ መረጃ በማቅረብ መሰናክል ይፈጥራሉ፡፡ የትምህርት ተቋማት ሊያርቁዋቸው ያልቻሉ ሰብዕናዎች ሲበዙ ደግሞ ጦሱ ለአገር ይተርፋል፡፡ በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች ላይ የሚቀመጡ ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ የሚገባቸው የመሰሪዎች ሰለባ እንዳይሆኑ ነው፡፡ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የሙያና የሲቪል ማኅበረሰቦችና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች የጦርነት ሰለባዎች ሰቆቃ እንዲያበቃ መፍትሔ ይፈልጉ፡፡

ኢትዮጵያ ታላቅ ተስፋ ያላት አገር ናት፡፡ ተስፋዋ ግን የሚለመልመው ልጆቿ ሲስማሙ ብቻ ነው፡፡ ይህ ስምምነት መጠራጠርንና ቁርሾን ማስወገድ ይገባዋል፡፡ በሐሰት ከመሸነጋገል በመውጣት ለአገር ቁምነገር መሥራት የሚቻለው፣ ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር እንደሌለ መተማመን ሲኖር ነው፡፡ የኢትዮጵያን ስም ለመስማት የሚፀየፉ ቢኖሩ እንኳ ችግራችሁ ምንድነው መባል አለበት፡፡ ምክንያቱም ባለፉት ዓመታት የተፈጸሙ አጓጉል ድርጊቶች የበርካቶችን አዕምሮ አበላሽተዋል፡፡ የተበላሹ አዕምሮዎችን ለማስተካከል ከፍተኛ ትዕግሥትና ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ትውልዱን የመረዙት አጓጉል ነገሮችንም ማስተካከል እንዲሁ፡፡ ማንነትንና እምነትን መዝለፍና ማዋረድ የተዘራው መርዝ ውጤት ነው፡፡ በግራም ሆነ በቀኝ ተሠልፈው አፀያፊ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩትን ማረም ይገባል፡፡ የተለያዩ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ አመለካከቶች፣ ፍላጎቶች፣ ወዘተ ባሉባት አገር ውስጥ መቀንቀን ያለበት ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አንድነት ነው ኢትዮጵያዊያንን በዓለም አቀፋዊ ደረጃ አንቱታ ያተረፈ ስም ያስገኘላቸው፡፡ ብዝኃነትን ሳይቀበሉ የኢትዮጵያዊነትን ፕሮጀክት ማሳካት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነትን በማናናቅና በማዋረድ የተሰማሩም የተያያዙት መንገድ አያዋጣም፣ አያዛልቅም፡፡ አክራሪ ብሔርተኝነት የመጨረሻ ግቡ ምን እንደሆነ የታወቀ ነውና፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ለሁሉም እኩል የሆነች የጋራ ቤት ማድረግ ከተፈለገ መከባበር፣ መደማመጥና መደራደር ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ሰላም ይሰፍናል፣ የዕድገት መንገድ ይያዛል፡፡ በዚህም ምክንያት በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ሲባል መፍትሔ መፈለግ ይገባል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...

ብሔራዊ ባንክ ጥርስ እያወጣ ይሆን እንዴ?

በአመሐ ኃይለ ማርያም ‹‹Better late than never›› (ከቀረ የዘገየ ይሻላል) የኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...