Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቀድሞ ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ትምህርት ቤት በቱርኩ ማሪፍ ፋውንዴሽን እንዲተዳደር መወሰኑ ቅሬታ...

የቀድሞ ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ትምህርት ቤት በቱርኩ ማሪፍ ፋውንዴሽን እንዲተዳደር መወሰኑ ቅሬታ አስነሳ

ቀን:

ትምህርት ቤቱ ባለድርሻዎች ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል

በቱርክ ባለሀብቶች ተመሥርቶ በኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት በላይ “ኢትዮ ተርኪሽ ትምህርት ቤት” በሚል ስያሜ በተለያዩ አካባቢዎች አገልግሎት ሲሰጥ ከቆየ በኋላ ለጀርመን ባለሀብቶች ተሸጦና ስያሜውን ኢንተሌክቹዋል ትምህርት ቤት (Intellectual School) በሚል ቀይሮ የመማር መስተማር ሒደቱን የቀጠለ ቢሆንም፣ በ2009 ዓ.ም. በቱርክ ተደርጎ በነበረ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር በተያያዘ፣ ትምህርት ቤቱና ንብረቱ፣ በቱረኩ ማሪፍ ፋውንዴሽን እንዲተዳደር ብይን መስጠቱ ቅሬታ አስነሳ፡፡

ቅሬታቸውን በጠበቆቻቸው አማከይነት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት አንደኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ያቀረቡት የትምህርት ቤቱ ባለቤቶች እንዳስረዱት፣ ካይናክ ኤዱኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የቱርክ ዜግነት ባላቸው ባለሀብቶች የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን፣ ‹‹ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ›› የተባለ ትምህርት ቤት በተለያዩ አካባቢዎች ከፍቶ አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ትምህርት ቤቱ በአሁኑ ጊዜ የጀርመን ዜግነት ላላቸው የቱርክ ተወላጆች ተሸጦና ስያሜውን ኢንተሌክቹዋል ትምህርት ቤት (Intellectual School) በሚል  ቀይሮ አገልግሎት እየሰጠ ቢሆንም፣ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በቀረበበት ክስ ምክንያት ትምህርት ቤቱንና ንብረቶቹን ማሪፍ ፋውንዴሽን የተባለና መቀመጫውን በቱርክ ባደረገ ግብረ ሰናይ ድርጅት እንዲተዳደር ብይን መስጠቱን አብራርተዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ትምህርት ቤቱና ንብረቶቹ በሌላ ተቋም እንዲተዳደር የተደረገበት ምክንያት ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ አንደኛ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ባቀረበው አቤቱታ አቤቱታ ነው፡፡

ዓቃቤ ሕግ በአቤቱታው እንዳብራራው ስቴም (Science, Technology, Engineering and Mathematics) ካይናክ ኤዱኬሸን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ነጃሺ ኢትዮ ተርኪሽ ትምህርት ቤትን ያቋቋመ ነው) የተካ ድርጅት ነው፡፡ ካይናክ ኤዱኬሸን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ደግሞ በኬንያ አገር ‹‹ኦማሪዬ ፋውንዴሽን›› በሚል በሲቪል ማኅበራት ተመዝግቦ የሚገኝ ድርጅት ነበር፡፡ ነገር ግን ‹‹ኦማሪዬ ፋውንዴሽን››  ፍፁም ሕገወጥ በሆነ ተግባር በኢትዮጵያ የኢንቨስትመት ፈቃድ አውጥቶ ከቆየ በኋላ፣ በጊዜ ሒደት ስያሜውን ወደ ካይናክ ኢዱኬሽን ኃላፊነቱ የተወነ የግል ማኅበር በመቀየር፣ በትምህርት ዘርፍ ላይ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ የማኅበሩ ባለቤቶች እ.ኤ.አ. በ2016 ተደርጎ ባልተሳካው በቱርክ መፈንቅለ መንግሥት ላይ መሳተፋቸውን፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘን ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ በማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል መሳተፉቸውን፣ በቱርክ የዳኝነት አካል በቅድመ ምርመራ መረጋገጡን ዓቃቤ ሕግ በአቤቱታው ዘርዝሮ፣ ንብረቱም እንዲታገድ መደረጉንና የቱርክ መንሥትም ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ የካይናክ ድርጅት ንብረት ተላልፎ እንዲሰጠው (እንዲወረስ) መጠየቁንም አክሏል፡፡

ካይናክ ግን የንብረቱን መወረስ ለማስቀረት በማሰብ ንብረቱ ለሦስተኛ ወገን የተሸጠ በማስመሰልና ውል በመፈጸም፣ አሁን ስቴም ኢዱኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በሚልና  ነጃሽ ኢትዮ ተርኪሽ ይሠራው በነበረው የትምህርት ሥራ ላይ የሚገኝ እንደሆነ በመጥቀስ፣ ንብረቶቹን በሙሉ አሳግዶ እንደነበር  አስታውሷል፡፡ የድርጅቱ ባለቤቶችም በወንጀል እንደሚፈለጉ በመጠቆምና መጥፋታቸውን በመግለጽ ለንብረቱ አስተዳዳሪ ማሪፍ ፋውንዴሽን የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት እንዲሾምለት መጠየቁን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብይን በዝርዝር አስፍሯል፡፡

ፍርድ ቤቱ በዓቃቤ ሕግ የቀረበውን አቤቱታ ላይ ጭብጦችን በመያዝ ከተለያዩ የአገሪቱ ሕጎች ጋር በማገናዘብ መዝገቡን መርምሮ ብይን ሰጥቷል፡፡ የንብረት ጠባቂ ለመሾም ከሚቀርብ ማመልከቻ ጋር በተያያዘም ፍርድ ቤቱ እንደ ሁኔታው የሌላኛውን ተከራካሪ ወገን አስተያየት መጠየቅ ሳያስፈልገው መወሰን የሚችል መሆኑን አዋጅ 434/97 አንቀጽ 17(6) እንደሚደነግግ፣ ፍርድ ቤቱ ሲያምንበት ካልሆነ በስተቀር የሌላኛውን ተከራካሪ ወገን አስተያየት መጠየቅ አስገዳጅ እንዳልሆነም ጠቁሟል፡፡ ዓቃቤ ሕግ በቃለ መሃላ አስደግፎ የቀረበው አቤቱታም እውነት መሆኑን ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁሞ፣ ማሪፍ ፋውንዴሽን የስቴም ኢዱኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (የቀድሞ ካናይክ ነጀሽ ኢትዮ ተርኪሽ ትምህርት ቤት) የአሁኑ ኢንተሌክቸዋል ስኩል ኢንተርናሽናል ካምፓስ (የስቴም  ንብረቶችን) እንዲያስተዳደር፣ የንብረት አስተዳዳሪ (ጠባቂ) እንዲሆን ብይን መስጠቱን አስታውቋል፡፡

ባልሰሙበትና ምንም ባላወቁበት ወይም ፍርድ ቤቱ እንዲያውቁና እንዲቀርቡ ሳያደርግ የሰጠውን ብይን የተቃወሙት የስቴም ኢዱኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር (ኢንተሌክቸዋል ስኩል/ኢንተርናሽናል ካምፓስ) ባለቤቶች፣ በጠበቆቻቸው አማካይነት ባቀረቡት አቤቱታ እንዳብራሩት፣ ስቴም ኢዱኬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ነው፡፡ መጀመርያ የተቋቋመው በ2001 ዓ.ም. ሲሆን፣ ኦሜሪዬን የገዛው ደግሞ በ2002 ዓ.ም. ነው፡፡ ድርጅትን መጀመርያ ያቋቋሙ ግለሰቦች የተጠረጠሩት ድርጅቱ ከተቋቋመና ከተስፋፋ ከስምንት ዓመታት በኋላ በ2009 ዓ.ም. በቱርክ ተደርጓል የተባለውን መፈንቅለ መንግሥት በገንዘብ ረድተዋል ተብሎ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዚህ ምርመራ መሠረት የሆነው ደግሞ በ2005 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ቁ.780/2005 ነው፡፡

በ2001 እና 2002 ዓ.ም. የተፈራረመውና ኢንቨስት የተደረገ ንብረት፣ በ2005 ዓ.ም. በወጣ አዋጅ “ምንጩ ያልታወቀ ነው” ተብሎ ወደኋላ ተመልሶ በወንጀል የሚጠየቅበት የሕግ አግባብ የለም፡፡ የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ እንደማይሠራ (Non-Retrospective Application of Law) በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ተደንግጎ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

ድርጅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተቋቋመ በኋላ እንደ ዓቃቤ ሕግ አባባል ፍፁም ሕገወጥ በሆነ ተግባር ላይ እንዳልተሰማራ የገለጹት ጠበቆቹ፣ በተፈቀደና በሕጋዊ ሥራ መስክ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የተሰማራው የሰው ልጆችን አዕምሮ በትምህርት በሚያንፅ የትምህርት ሥራ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የትምህርት ሥራ ሕገወጥ ሥራ አለመሆኑንም አክለዋል፡፡

ድርጅቱ የንግድ ሥራውን ሲያስፋፋ የገዛው ኦሜሪዬምም ቢሆን ተሰማርቶ የነበረው የትምህርት ሥራ ዘርፍ መሆኑንና ኢትዮጵያ ውስጥም በበጎ አድራጎት ድርጅትነት የተቋቋመ ቢሆንም፣ የተሰማራው ግን በትምህርት ሥራ ላይ ስለነበር ሕገወጥ በሆነ ተግባር ላይ ነው ሊባል እንደማይችልና በርካታ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ጭምር በትምህርት ሥራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በቱርክ እ.ኤ.አ. በ2016 በተደረገው ያልተሳካ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ላይ ሽብርተኝነትን በገንዘብ በመርዳት ወንጀል ተሳትፎ ማድረጉን የቱርክ መንግሥት የዳኝነት አካል ባደረገው ቅድመ ምርመራ አረጋግጦበታል ብሎ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበው ፍሬ ነገርም ቢሆን፣ የሕግ ድጋፍ የሌለውና በተለመደው ዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት “ቱርክ ኢትዮጵያ ውስጥ ጀርመኖች ወንጀል ፈጽመውብኛል” ብላ በምርምራ ማጣራት እንደማትችልም አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያና በቱርክ መካከል ደግሞ የቅድመ ምርመራ ውጤት ተቀባይነት ያለው ማስረጃ እንዲሆን የተደረገ የሁለቱ አገሮች የሁለትዮሽ ስምምነት (Bilateral Treaty) እንደሌለ፣ በአንዱ አገር ፍርድ ቤት የተሰጠ ፍርድን በሌላኛው አገር ፍርድ ቤት ለማስፈጸም የተደረገ ስምምነት (Treaty for Execution of Foreign Judgments) እንዳልተደረገም አክለዋል፡፡

ድርጅቱ በወቅቱ በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተሳትፏል ብሎ ለመጠርጠር ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው አካውንት ወደ ቱርክ ገንዘብ መላኩንና ገንዘቡም ለተባለው ዓላማ መዋሉን በብሔራዊ ባንክም ሆነ በሌሎች ባንኮች ወይም የፋይናንስ ደኅንነት ተቋማት ሳይረጋገጥ ወይም ቢያንስ በአመልካች ተጨማሪ ማስረጃ ሳይቀርብ፣ በቃለ መሃላ ተደግፎ በመቅረቡ ብቻ ፍርድ ቤቱ ቃለ መሃላውን አምኖ በመቀበል ንብረቱን የማስተዳደር ግዙፍ መብት የሚገድብ ትዕዛዝ መስጠቱ መሠረታዊ ስህተት መሆኑንም ጠበቆቹ በአቤቱታቸው አብራርተዋል፡፡

የስቴም ኢዱኬሽን ባለቤቶች የሆኑት ጀርመናውያን መሆናቸውንና አክሲዮኖች የገዙት የንብረቱን መወረስ ለማስቀረት በሚል ዓላማ እንዳልሆነ የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ባለሀብቶቹ ድርጅቱን የገዙበትን ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እ.ኤ.አ. ጥር 06 2020 (እ.ኢ.አ. ታኅሳስ 27 2012 ዓ.ም.) በጻፉት ሰፊ ሰነድ ማብራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ጀርመናውያን ድርጅቱን የገዙት ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ኢንቨስትመንት ዕድልና የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመኖሩና ለኢንቨስትመንት ጥበቃ በቂ የሕግ ማዕቀፍ በመኖሩ መሆኑን፣ ግዥውንም የፈጸሙት የንብረቱን መወረስ ለማስቀረት በማሰብ በማሰብ እንደሆነ ተደርጎ በዓቃቤ ሕግ የቀረበው ፍሬ ነገር ስህተት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ስቴም ኢዱኬሽን ወደ ጀርመናውያን የተላለፈው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ወደ ማሪፍ ፋውንዴሽን እንዲተላለፍ መመርያ ከሰጠ በኋላ እንደሆነ መሃላ አረጋግጦ ያቀረበው ፍሬ ነገር ስህተት መሆኑንና ጉዳዩን ከሕግ አኳያ ሲታይ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የግለሰብ ኢንቨስተሮችን ንብረት የቱርክ መንግሥት ስለጠየቀ ብቻ አሳልፎ እንዲሰጠው የሚፈቅድ ሕግ ሆነ ሥልጣን እንደሌለው  አስረድተዋል፡፡

በድርጅቱ የቀድሞ የቱርክ ባለሀብቶችና በጀርመናውያኑ ባለሀብቶች መካከል የአክሲዮን ሽያጭ የተደረገው በሕገወጥ መንገድ ሳይሆን በሕጋዊ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ጋብዟቸው፣ የኢትዮጵያ ኢሚግሬሽንና ባለሥልጣን የንግድ ቪዛ ሰጥቷቸውና ከጠበቃቸው ጋር ተመላልሰው፣ በወቅቱ የነበረው የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ  ባለሥልጣንና ንግድ ሚኒስቴር ክሊራንስ ሰጥተዋቸውና በውልና ማስረጃ ቃለ ጉባዔያቸውን አስፀድቀው መሆኑን ጠበቆቹ በአቤቱታቸው ዘርዝረው አቅርበዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ የአክሲዮኖቹ ሽያጭ ‹‹ለማስመሰል›› የተደረገ ሳይሆን በመንግሥት ተቋማት በተደረጉት በርካታ መንግሥታዊ ማረጋገጫ ሰነዶች ሆኖ ሳለ፣ ሽያጩ ለማስመሰል እንደሆነ አድርጎ በቃለ በመሃላ ማረጋገጫ ማቅረብ፣ የቃለ መሃላን ዋጋ ማሳጣት እንደሆነም አክለዋል፡፡ አንድ አገር በወንጀል የተጠረጠረን የውጭ አገር ዜጋ አሳልፎ የሚጠው በሁለቱ አገሮች መካከል አሳልፎ የመስጠት ስምምነት (Treaty for Extradition) ሲኖር መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆቹ፣ ከዚህ አኳያ የጀርመን ዜጎች ለቱርክ መንግሥት ተላልፈው የሚሰጡበት የሕግ ሥርዓት ስለሌለ ዓቃቤ ሕግ በቃለ መሃላ አረጋግጦ ያቀረበው ፍሬ ነገር ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ጠበቆቹ አቤቱታ፣ ፍርድ ቤቱ ለተጠሪ ድርጅት የንብረት አስተዳዳሪ የሾመው፣ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 9 (4) መሠረት ንብረቱን ከጉዳት ለመከላከል የሚጠቅም ትዕዛዝ እንዲሰጥለት በጠየቀው መሠረትና ፍርድ ቤቱም በዚሁ ድንጋጌ መሠረት ተገቢ መስሎ ስለታየው መሆኑን ግምታቸውን የገለጹት ጠበቆቹ፣ በእነሱ እምነት ዕግዱ ለምርመራው በቂ ሆኖ እያለና ትክክለኛ ጉዳት እንደሚደርስ ምክንያታዊ ግምት ለመውሰድ የሚያስችል ተጨባጭ ሁኔታ (Objective Circumstance) ሳይኖር፣ በድርጅቱ ላይ በተጨማሪነት አስተዳዳሪ መሾም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የበለጠ እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ዓቃቤ ሕግ እንዳለው ማሪፍ ፋውንዴሽን የበጎ አድራጎት ድርጅት ከሆነ በንብረት አስተዳዳሪነት ሊሾም እንደማይችል የገለጹት ጠበቆቹ፣ ምክንያቱ ደግሞ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚመሩባቸው መርሆዎች፣ ሕጎችና አሠራሮች የንግድ ድርጅት ከሚመራባቸው ጋር ስለማይገናኙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 434/97 አንቀጽ 17(5) መሠረት የንብረት አስተዳዳሪ ሆኖ የሚሾመው ድርጅት የሕግ ሰውነት ያለው ድርጅት ከሆነ መሟላት ያለባቸው መሥፈርቶች ማሟላት እንደሚኖርበት ጠቁመው፣ ማሪፍ ፋውንዴሽንን ግን ከእስቴም ኢዱኬሽን ጋር ቀጥተኛ የጥቅም ግጭት ያለበትና ገለልተኛ ያልሆነ ድርጅት መሆኑን አክለዋል፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የሰጠው ትዕዛዝ ስህተት መሆኑን በተረዳ ጊዜ ትዕዛዙን የማንሳት ሥልጣን ስላለው ያቀረቡትን ዳኝነት ተመልክቶ እንዲያነሳላቸው ባቀረቡት አቤቱታ ጠይቀዋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. የቀረበለትን  አቤቱታ ተቀብሎ  ዓቃቤ ሕግ ጳጉሜን 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ምላሽ እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

‹‹ደስታ›› የተባለችው አማርኛ ተናጋሪ ሮቦት በሳይንስ ሙዚየም

‹‹እንደ ሮቦት ዋነኛው አገልግሎቴ ውስብስብ የሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንና አሠራሮችን...