Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበምሥራቅ ወለጋ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው የፀጥታ ኃይሎች ሥምሪት ላይ...

በምሥራቅ ወለጋ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት ምክንያት የሆነው የፀጥታ ኃይሎች ሥምሪት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ተጠየቀ

ቀን:

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ ኪራሙ ወረዳ ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በአካባቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሌላ አካባቢ በመንቀሳቀሳቸው ሳቢያ፣ ነሐሴ 12 ቀን ኦነግ ሸኔ በተባለ የታጣቂዎች ቡድን ለተገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ዜጎች ምክንያት የሆነው የፀጥታ ኃይሎች ሥምሪት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቀ፡፡

ኮሚሽኑ ሐሙስ ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡ በመግለጫውም ከላይ በተጠቀሰው ቦታ በታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት ከ210 በላይ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል፡፡

ግድያው ከመፈጸሙ አስቀድሞ በአካቢው ተሰማርተው የነበሩ የፀጥታ ኃይሎች፣ ከቦታው ለቀው የወጡበት ምክንያት በአጽንኦት እንዲጣራ  ጥሪ አቅርቧል፡፡

በተጨማሪም ለታጣቂ ኃይሎች ጥቃት ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን የፀጥታ ሁኔታ በዘላቂነት ወደ ነበረበት ለመመለስና የተቋረጡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር፣ የፀጥታ ኃይሎችን በማጠናከር የፌዴራል መንግሥት በትኩረት እንዲሠራ ጠይቋል፡፡

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባዔ ሐሙስ ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን በቂልጡ አቦ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. በሸኔ ታጣቂዎች መገደላቸውን በመጥቀስ፣ ከተገደሉት ውስጥ አምስቱ የአንድ ቤተሰብ አባል መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡

ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ አጋሳ አቦ፣ ትንብያ ሚካኤል አብያተ ቤተ ክርስቲያን፣ መንደሩንና የአማራ ብሔር ተወላጅ ቤተሰቦችን ታጣቂዎቹ እየመረጡ ማቃጠላቸውን ኢሰመጉ ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በእለቱ አሹ ኩሳየ ቀበሌ ውስጥ ከብት በመጠበቅ ላይ የነበሩ የአማራ ተወላጆችን ገድለው ከብቶቻቸውን መንዳታቸውን፣ እንዲሁም መርጋ ጃሬኛ ቢንዳሮ የተባለ ቀበሌ በመግባት የአማራ ተወላጅ የሆኑ 41 ሰዎችን መግደላቸውን፣ በተጨማሪም በምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ከ300 በላይ የአማራ ተወላጆችን እንደገደሉ አስታውቋል፡፡

ከተገደሉት በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ የበርካቶች ቤትና ንብረት እንደተዘረፈና እንደተቃጠለ፣ እንዲሁም ከ90 ሺሕ በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ኢሰመጉ በመግለጫው አክሏል፡፡  

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተደጋጋሚ በሚሰነዘሩ ጥቃቶች ሳቢያ የበርካታ ሰው ሕይወት እንደጠፋና ጉዳት እንደደረሰ፣ ንብረት እንደወደመ፣ እንዲሁም በርካቶች ከቀዬአቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉን አስረድቷል፡፡

በመሆኑም መንግሥት የደኅንነት ሥጋት አለባቸው የሚባሉ ቦታዎችን በመለየት የፀጥታ ሁኔታዎችን በትኩረት በመከታተል፣ የሰዎች በሕይወት የመኖርና የንብረት መብቶች እንዲጠበቁ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሲል ጠይቋል፡፡

ኢሰመጉ የአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የማኅበረሰብ አንቂዎች የሚታዩ ችግሮች በውይይት የሚፈቱበት ሁኔታ እንዲፈጠርና በየአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን፣ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ከሚገኘው የትግራይ ግጭት ጋር በተገናኘ በደቡብ ጎንደር ደብረ ታቦር ከተማ የተፈጸመውን የከባድ መሣሪያ ጥቃትና ግድያ፣ ዘረፋና መፈናቀል በተመለከተ ምርመራ ለማካሄድ የባለሙያ ቡድን እንደሚልክ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...