Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መንግሥታዊ ውሳኔ ካልታከለ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር አልሠራም አለ

አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መንግሥታዊ ውሳኔ ካልታከለ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር አልሠራም አለ

ቀን:

ከቶኪዮ ኦሊምፒክ እንዲሁም ከዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተመለሰው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን በጃፓን ስለነበረው ቆይታ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለኦሊምፒክ ጨዋታው፣ ብሔራዊ ቡድኑ ሲያደርግ የነበረው ቆይታ አጠቃላይ ዝግጅት፣ ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ፣ ከብሔራዊ ኮሚቴ ኦሊምፒክ ጋር ስለገባው እሰጣ ገባና በቶኪዮ ኦሊምፒክ ተፈጠሩ ስለተባሉ ጉዳዮችና ስለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ፣ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚሳተፉ አትሌቶችንና ኦፊሻሎችን በመመልመልና በማሠልጠን ለሚመለከተው አካል ማስተላለፉን ጠቅሷል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ፣ የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በዛብህ ወልዴ (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቢልልኝ መቆያ እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ ቴክኒክ ባለሙያና ቡድን መሪ ገዛኸኝ አበራ በጋራ በመሆን ሰጥተዋል፡፡

የአትሌቶች ዝግጅትና ተከሰቱ የተባሉት አለመግባባቶች

ፌዴሬሽኑ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ውድድሮችን መሠረት ያደረገና በሁሉም ርቀት ላይ ሚኒማ ያሟሉና ሊያሟሉ የሚችሉ ከ100 በላይ አትሌቶችን ዝግጅቱን ሲያደርግ እንደቆየ ተብራርቷል፡፡

በአጠቃላይ ከ800 ሜትር እስከ 10,000 ሜትር 28 አትሌቶች፣ በማራቶን በሁለቱም ፆታ ከነተጠባባቂያቸው ስድስት አትሌቶች፣ እንዲሁም በዕርምጃ ውድድር አንድ አትሌት በድምሩ 35 አትሌቶችን ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በግምባር ማቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ሥልጠናውን የሚያካሂዱ 17 አሠልጣኞች፣ ሁለት ሐኪሞች፣ አራት ወጌሻዎችና አምስት ኦፊሻሎችን ለኦሊምፒክ ኮሚቴ መላኩን ይጠቅሳል፡፡

ሆኖም አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ሥራዬን በአግባቡ ሠርቼ ባጠናቅቅም፣ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ጣልቃ ገብነት ችግሮች በመፈጠራቸው ተናቦ መሥራት እንዳልተቻለ ያብራራል፡፡

‹‹አትሌቶቹ የመሠለፍና አለመሠለፋቸውን ባለማወቃቸው የሥነ ልቦና ጫና መድረሱ፣ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የታየውና አገሪቷን የማይመጥን ገጽታ መታየቱ በውጤቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አድርጓል፤›› በማለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አስረድተዋል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አስተያየት ከሆነ፣ አትሌቶችንና አሠልጣኞችን የመምረጥና አዘጋጅቶ የመምረጥ ሥልጣኑ በኦሊምፒክ ኮሚቴ ጣልቃ ገብነት ሲፈተን እንደቆየ ይጠቅሳሉ፡፡ ለዚህም 3000 ሜትር መሰናክል ለመወዳደር ሲዘጋጅ የነበረውን አትሌት ለሜቻ ግርማ በፌዴሬሽኑ ፍላጎት ለስምንት ወራት ልምምዱን ሲሠራ እንደቆየና ከደረሰበት የእግር ጉዳት እንዲያገግም የሕክምና ክትትል ሲደረግለት ቢቆይም እስከ መጨረሻው ማሳወቂያ ቀን ባለማገገሙ ፌዴሬሽኑ የመጨረሻው የስም ዝርዝር ወስጥ እንዳላካተተው አብራርተዋል፡፡

‹‹ኦሊምፒክ ኮሚቴው ለሜቻ በማንኛውም ጊዜ ማስመዝገብ እንደሚቻል እያወቀ፣ ፌዴሬሽኑን ማማከር ሲገባው፣ በራሱ ሥልጣን እንዲወዳዳር ማድረጉ አግባብ አለመሆኑን እየጠቀስን፣ አትሌቱ ባመጣው ውጤት ግን ፌዴሬሽኑ ደስተኛ ነው፤›› ሲልም ፌዴሬሽኑ አስተያየቱን ሰንዝሯል፡፡

እንደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አስተያየት፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ስሙን ያስተላለፈውን አትሌት ከአየር ማሪፊያ እንዲመለስ ተደርጓል ብሎ ቢከስም የኦሊምፒክ ኮሚቴ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ‹‹ያልተመረጡ አትሌቶች ለምን ኤርፖርት ሄዱ?›› ሲል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ የተመረጡ አትሌቶች በሙሉ ዝግጅት ከማድረጋቸውም ባሻገር ሊያመሩ ሦስት ቀን ሲቀራቸው የኮቪድ ምርመራ ሲያደርጉ እንደነበረና ኦሊምፒክ ኮሚቴ አልተመረጣችሁም ብሎ ከኤርፖርት መመለሱ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

ከዚህ ጋር ለረዥም ጊዜ የአትሌቶችን ጤንነት፣ የአመጋገብና ሌሎች የጤና ክትትል ሲያደርጉ የነበሩ የሕክምና ባለሙያዎች እያሉ፣ ከአትሌቶቹ ጋር በመቆየት ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሌሎች ሐኪሞችን በማሳተፍ በአትሌቶች ላይ የራሱን አሉታዊ  ሥነ ልቦና ጉዳት ማድረሱን ፌዴሬሽኑ በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት በዛብህ ወልዴ (ዶ/ር) አስተያየት ከሆነ፣ ለዓመታት አትሌቶችን መርጦና አዘጋጅቶ ሲያዘጋጅ የነበረ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ቡድን መሪን ከድጋፍና ክትትል ውጪ በማድረግ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስፈጻሚዎችን በመመደብ ያላዘጋጁትን አትሌትና አሠልጣኝ እንዲመሩ በማድረግ፣ የፌዴሬሽኑን ባለሙያዎች ግማሹን አገር ውስጥ በማዘግየት፣ ግማሹን ቶኪዮ ሆቴል ወስጥ መገደቡን አስረድተዋል፡፡

በተለይም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትና የአትሌቲክስ ቡድን መሪው ከማንኛውም እንቅስቃሴ በመገደብ የተሰጣቸውን ኃላፊነትና ተግባር እንዳይወጡ መደረጉን ፌዴሬሽኑ ገልጿል፡፡ 

አትሌቶች ምን ገጠማቸው?

ለስምንት ወራት በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ የተነገረላቸው አትሌቶች ወደ ቶኪዮ አምርተዋል፡፡ በተለያዩ ርቀቶች ላይ አገራቸውን የወከሉት የተወሰኑ አትሌቶች  ውድድር ማጠናቀቅ ሲሳናቸው ተስተውሏል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የጤና እክል እንዳጋጠማቸው እየታወቀ፣ በውድድር ላይ እንዲካፈሉ መደረጉ ፌዴሬሽኑ ሲወቀስ ነበር፡፡

  ከዚህ ጋር ተያይዞም የ10,000 ሜትር ተወዳዳሪዋ ጽጌ ገብረሰላማ ጉዳት እንደገጠማት እየታወቀ እንድትሮጥ መደረጉ አግባብ እንዳልነበር ሲነገር ቆይቷል፡፡ ሆኖም በርካታ አትሌቶች እስከመጨረሻው ሰዓት ድረስ የጤናቸው ጉዳይ ላይ በባለሙያዎች ክትትል ሲደረግበት እንደቆየ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡

‹‹ከበርካቶቹ አትሌቶች ጋር እስከመጨረሻው ድረስ ጥሩ ግንኙነት ነበረን፡፡ በአካል ካገኘዋቸው ባሻገር በስልክም ስለጤንነታቸው የጠየኳቸው አትሌቶች ነበሩ፡፡ ሆኖም መታመማቸውን እያወቁ እንዲወዳደሩ ያደረጉ የጤና ባለሙያዎችም ሆኑ አሠልጣኞች ካሉ ፌዴሬሽኑ ዕርምጃ ይወሰድባችዋል፤›› በማለት ፕሬዚዳንቷ አስታየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

እንደ ፌዴሬሽኑ ማብራሪያ ከሆነ፣ በዝግጅት መጠናቀቂያ ወቅት የጤና እክል እንዳጋጠማቸው የተጠቀሱ አትሌቶች ቢኖሩም፣ እነሱን በሌሎች ተጠባባቂ አትሌቶች እንዲተኩ ያደረጉበት መንገድ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በነበረ ክፍተት እንዳልተሳካ ተጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል የ800 ሜትር አትሌት ወርቅውኃ በተገኘባት የቴስትሮን መጠን ከፍተኛ መሆን ምክንያት መካፈል እንደማትችል የሚጠቅስ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ መድረሱን ተከትሎ መታገዷ ተነግሯል፡፡

በወንዶች ማራቶን ሹራ ኪጣታ በመጨረሻ ሰዓት ጉዳት እንዳጋጠመው ቢታወቅም ፌዴሬሽኑ እንደተጠባባቂ የተያዘውን አትሌት በኦሊምፒክ ኮሚቴ ጣልቃ ገብነት ምክንያት ይዞ መጓዝ እንዳልተቻለና የመጨረሻው የስም ዝርዝር ላይ የነበረው ቀነኒሳ በቀለ መሆኑና በጊዜው እሱ በፌዴሬሽኑ ምርጫ ውስጥ አለመካተቱ ምክንያት ማሳተፍ እንዳልተቻለ ተብራርቷል፡፡

ከአትሌቶች ምርጫ ጋር በተያያዘ ሁለት ቦታ የረገጡ አሠልጣኞች መኖራቸውና ጉዳዩን የበለጠ እንዳወሳሰበው በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቁሟል፡፡

የአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የኦሊምፒክ ኮሚቴ አለመግባባት መቋጫ

የሁለቱ ተቋማት ያለየለት አለመግባባት ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንዳለ ለማየት ከቶኪዮ ኦሊምፒክ የሚበልጥ ምሳሌ የለም፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት መንግሥት ጉዳዮን እልባት እንዲሰጠው ጥሪውን አቅርቧል፡፡ የፌዴሬሽኑና የኦሊምፒክ ኮሚቴው የሥራ ኃላፊነትና ተግባር ለይቶ ማሳወቅ ከሚመለከተው የመንግሥት አካልም እንደሚጠብቅ አስቀምጧል፡፡

ከዚህም በሻገር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በቀጣይ ሥራዎች መሥራት የሚችለው ሕግና ሥርዓት ተስተካክሎና ኃላፊነቱን እንዲከበር መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጦ የማይጓዝ ከሆነ አብሮ መሥራት እንደማይችል በግልጽ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...