Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየሰላም ዋጋ መቼ ታሰበ?

የሰላም ዋጋ መቼ ታሰበ?

ቀን:

በአይተን ጂ.

‹‹በጦር መርታት ነው፣  የሁሉም ተስፋው

የሰላም ዋጋ  መቼ  ታሰበ?

አብሮ ለመኖር መላው የጠፋው

አብሮ ለመሞት ተሰባሰበ››

በዕውቀቱ ሥዩም

በትግራይ ክልል ጦርነት ከተጀመረ 10ኛ ወሩን አስቆጥሯል፡፡ በጦርነቱ በሰዎችና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት እስካሁን በቅጡ አልታወቀም፡፡ ይሁንና በጣም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት፣ አሰቃቂ ጥቃቶች የተፈጸሙበት አውዳሚ ጦርነት እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከመቀሌ መውጣቱንና የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ጦርነቱ አንድ አይነት መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋ አጭሮ የነበረ ቢሆንም፣ ተስፋው ዕውን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ጭራሹኑ ጦርነቱ ወደ ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ተስፋፍቷል፡፡ አገር ወደ ጦርነት መንፈስ ጨርሳ ገብታለች፡፡  ክተት ታውጇል፡፡ ከአገር መከላከያ ሠራዊት በተጨማሪ የክልል ልዩ ኃይሎች፣ ሚሊሻዎችና አቅም ያላቸው ዜጎች ጭምር ለግዳጅ ተጠርተዋል፡፡ በማስ ሚዲያና በማኅበራዊ ሚዲያው የጦርነት ፕሮፓጋንዳው ጦፏል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የጦርነቱን መነሻ መንስዔዎች መተንተን አይደለም፡፡ የትኛው ወገን ጥፋተኛ እንደሆነ ማሳየትም አይደለም፡፡ ጽሑፉ በዋነኝነት የቀጠለውንና በመስፋፋት ላይ ያለውን ጦርነት  በፍጥነት መግታትና ማስቀረት ለምን አስፈላጊ እንደሆነ ለማሳየትና ይህንን በምን መንገድ ማድረግ እንደሚቻል መነሻ ሐሳቦችን ለማቅረብ ያለመ ነው፡፡

በዚህ ወቅት እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ማቅረብ ከሁሉም አቅጣጫ ተቃውሞ ያስነሳል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጎልተው የሚሰሙ ድምፆች የጦርነቱ ተሳታፊዎች ወይም ደጋፊዎቻቸው ድልን ወይም ሽንፈትን የመዘገብ፣ አቋማቸውን የማስተጋባት፣ የማነሳሳትና የማኮፈስ ድምፆች ናቸው፡፡ ስለሰላም መናገር በሁለቱም በኩል እንደ ገለልተኝነት አይታይም፡፡ ጭራሽ ለጥቃት ያጋልጣል፡፡

በጦርነት መንፈስ ውስጥ ጠልቀን ስለገባን ሥጋት፣ ጥርጣሬና ጥላቻ አስተሳሰባችንን ሸብቦታል፡፡ ይሁንና በጦርነት ተጋጥሞ ከመሸናነፍ በመለስ መፍትሔ እንዲፈለግ የሚፈልጉ፣ በአንዱ ወይም በሌላው ጥቃትና ማሸማቀቅን በመፍራት ወይም ብናገረውም ሰሚ የለም በሚል የተስፋ መቁረጥ ስሜት ዝም ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉ አምናለሁ፡፡ ስለዚህም ከተቻለ እንዲሰማ ካልሆነም ለታሪክ መቀመጥ ስላለበት ሐሳቡን አቀርባለሁ፡፡

መነሻዎች

በሕወሓትና በፌደራል መንግሥቱ በኩል በተሰለፉ ኃይሎች መካከል የተካሄደውና በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ከዚህ በላይ መቀጠል እንደሌለበት ለማሳየት፣ ሁለት አመክኖአዊ መከራከሪያዎችን ማንሳት ያስፈልጋል፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ ጦርነቱ መቆም ያለበት ሁሉም ተሳታፊዎች በጦርነቱ ኺደት የሞራል ልዕልናቸውን በማጣታቸው ነው፡፡ ጦርነት በተፈጥሮው የመጠፋፋትና የውድመት ሒደት ቢሆንም፣ የራሱ የሆኑ ዓለም አቀፍ ሕጎች አሉት፡፡ እነዚህ ሕጎች በጦርነትም ውስጥም ቢሆን ተዋጊ ኃይሎች መከተልና ማክበር ያለባቸው አነስተኛ የሞራል ግዴታዎችን ይጥላሉ፡፡ በዚህ ጦርነት የተሳተፉት ሁሉም ኃይሎች፣ መጠኑ ሊለያይ ይችላል እንጂ በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያና ጥቃት በመፈጸም፣ በሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር፣ በንብረት ላይ ዝርፊያ፣ ውድመትና ሌሎች አሰቃቂ ጥቃቶችን መፈጸማቸው በተደጋጋሚ የተገለጸ ነው፡፡ እኔ ንፁህ ነኝ ሊል የሚችል አካል የለም፡፡

በፌዴራል መንግሥት በኩል የሰሜን ዕዝ ሠራዊት በተኛበት ተጠቅቷል በሚለው አግኝቶት የነበረው የሞራል የበላይነት በጦርነቱ ጊዜ በራሱ ኃይሎችም ሆነ በሌሎች አጋር ኃይሎች በተፈጸሙ ጥሰቶች፣ በተለይም በታሪክ ለመጀመሪያ ሊባል በሚችል ደረጃ የኤርትራ ሠራዊት አደረሳቸው በተባሉት ሰቅጣጭ ጥቃቶች ምክንያት አጥቶታል፡፡ ይህም የትግራይ ክልልን ተቆጣጥሮ በነበረባቸው ወቅቶች በትግራይ ሕዝብ ተቀባይነት ላለማግኘቱና በተቃራኒው ሕዝቡ በአብዛኛው የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ለመደገፉ ምክንያት ሆኗል፡፡

በትግራይ በኩል ተወርሬያለሁ፣ ተጠቅቻለሁ በሚል ለመገንባት የተሞከረው የሞራል መሠረት ጦርነቱን ወደ ሌሎች ሥፍራዎች በማስፋፋቱ ምክንያት እየጠፋ መጥቷል፡፡ ግቡ በሥልጣን ላይ ያለውን በሌሎች አገሪቱ አካባቢዎችና ኅብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ትንሽ የማይባል ድጋፍና ተቀባይነት ያለውን መንግሥት ወደ ማፍረስ ሲሸጋገር ይህ የሞራል መሠረት ይጠፋል፡፡ በተመሳሳይም በጦርነቱ ሒደት የትግራይ ታጣቂዎችም ሰቅጣጭ ወንጀሎችን በሲቪል ሰዎች ላይ ፈጽመዋል፡፡ 

ሁለተኛው ምክንያት ለጦርነቱ መንስዔ የሆነው ፖለቲካ ችግር በጦርነት የማይፈታ መሆኑ ነው፡፡ በአንድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ሆነው አገራችንን ሲመሩ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተከፋፍለው በአገረ መንግሥቱ ግንባታ ሁኔታ፣ በአገረ መንግሥቱ ቅርፅ፣ በሥልጣንና በሀብት ክፍፍል ጉዳዮች ተለያይተው ልዩነታቸው እየሰፋ፣ አለመተማመናቸው እየጎላ መጥቶ ሙሉ ለሙሉ ወደ ጦርነት ገብተዋል፡፡ እነዚህ ልዩነቶች በአገሪቱ የፖለቲካ ልሂቅ መካከል ያሉና የነበሩ፣ ምናልባትም ወደ ፊት የሚቀጥሉ ልዩነቶች ናቸው፡፡ ፌደራል መንግሥት ተሳክቶለት ሕወሓትን በጦርነት ቢያሸንፍ፣ ወይም በተቃራኒው ሕወሓት ይኼንን መንግሥትን ቢያፈርስ እነዚህ ፖለቲካ ልዩነቶች ቀሪ አይሆኑም፡፡  

ጦርነት ሀሳብ ተሸካሚ የሆነን ሰው በማጥፋት ሐሳብን ለማጥፋት የሚደረግ ብኩን መንገድ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ለአገራችን ቀጣይነት ያለው የቂም አዙሪት መፍጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በመደመር መጽሐፋቸውን እንዲህ ገልጸውታል፡፡

‹‹በአገራችን ተቀናቃኝን በሙሉ አቅምና ጉልበት ደፍጥጦ ከጨዋታ ውጪ ማድረግ የተለመደ ክፉ ባህላችን ነበር፡፡ በተቀናቃኛችን ውድቀትና መቃብር ላይ ካልሆነ በቀር አሸናፊነታችንን ለማረጋገጥ የምንችል አይመስለንም፡፡ ጀግና ለመፍጠር ጦርነት፣ አሸናፊ ለመባል ተሸናፊ እንዲኖረን ብዙ እንደክማለን፡፡ ይህ ሒደት ደግሞ ከድህነትና ከጉስቁልና በቀር የትም እንደማያደርሰን በታሪካችን ውስጥ በተደጋጋሚ አረጋግጠናል፤›› (መደመር መጽሐፍ ገጽ 123)፡፡ 

እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የሰፋ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የታሪክ አረዳድና የፖለቲካ አቋም ልዩነት ባለባቸው አገሮች ይቅርና፣ አንድ ዓይነት ማንነት ባላቸው አገሮችም ጦርነት ሐሳብን አጥፍቶ አያውቅም፡፡ ስለዚህም መስዋትነቱ፣ ደም መቃባቱና ውድመቱ ይቀጥል ይሆናል እንጂ ልዩነቱ ሌላ ባለቤት ይዞ ብቅ ማለቱ አይቀርም፡፡

በተቃራኒው በጦርነቱ ደጋፊ የሆኑ ወገኖች ሲሉ እንደሚደመጠው ሐሳቡ ሊኖር ቢችልም፣ እንኳን የሐሳቡን ተሸካሚ ኃይልና አቅም በጦርነት አሸንፎ በማጥፋት ወይም በማዳከም አደጋ እንዳይሆን ማድረግ በቂ ዓላማ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ የፌደራል መንግሥትና አጋሮቹ  ‹‹ሕወሓት ካንሰር ነው››፣ ‹‹መጥፋት አለበት›› ሲባል በሕወሓት በኩል ደግሞ፣ ‹‹ጠቅላይ ሚኒስትሩ መወገድ አለበት፣ የዚህ ብሔር ልሂቅ መውደም አለበት፣ ጣቱ መቆረጥ አለበት…›› የሚል አቋም ይገልጻሉ፡፡

ይኼኛው ዓላማና አቋም ትክክለኛነት በሁለት ተጨማሪ መለኪያዎች መለካት ይኖርበታል፡፡ የመጀመሪያው ጦርነቱ አሸናፊ ወይ ተሸናፊ ሊኖረው የሚችል ዓይነት መሆኑ ሲሆን፣ ሁለተኛው ይህንን ግብ ለማሳካት በጦርነት የሚከፈለው ዋጋ ከሚገኘው ውጤት ጋር ያለው ተመጣጣኝነት ነው፡፡

በእኔ እምነት ካለፉት አሥር የጦርነቱ ወራት የተረዳነው ነገር ቢኖር፣ ጦርነቱ የተራዘመና አሸናፊ የሌለበት የሚመስል እየሆነ መሄዱ ነው፡፡ በፌደራል መንግሥት በኩል ትግራይን ተቆጣጥሮ፣ አስተዳዳሪ መድቦ ሕወሓትን፣ ‹‹እንደ ጉም በትኛለሁ፣ ዋሻ ገብተዋል፣ በአጭር ጊዜ እንደ ዱቄት ተበትነዋል…›› ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ጠፋ የተባለው ድርጅት አገግሞ ጭራሽ ወደ ሌሎች ክልሎች ገብቶ ጥቃት ለመፈጸም ችሏል፡፡

በሕወሓት በኩልም ‹‹የሰሜን ዕዝን ትጥቅ ይዣለሁ፣ እስከ አፍንጫችን ታጥቀናል፣ ማንም ቢመጣ እበታትናለሁ›› ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ በዋናው ጦርነት ተሸንፎ፣ ከስልጣን ወርዶ የነበረና እንደገና አገግሜያለሁ ብሎ ወደ ሌሎች ክልሎች የጀመረው ጥቃትም መከላከል እየገጠመው፣ በሳምንታት ጊዜ ውስጥ አፈርሰዋለሁ ያለው መንግሥት የተጠናከረ መከላከል እያደረገ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር ቀጣይነት ያለው ጦርነት እየሆነ ነው፡፡   

ጦርነቱ ከተጀመረና ዋጋም ከተከፈለበት አይቀር በአጭር ጊዜ አንደኛው ወገን ቢያሸንፍ ምናልባትም የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ይህ ግን አልሆነም፡፡ ተሞከረ አልተሳካም፡፡ ጦርነቱ ተራዝሞ ወደ ሌሎች ስፍራዎች እየተስፋፋ በሁለት የተደራጁና የታጠቁ ቡድኖች መካከል ከሚካሄድ ጦርነት ይልቅ፣ በሕዝቦችና በብሔሮች መካከል የሚደረግ ጭልጥ ወዳለ የእርስ በርስ ጦርነት እያደገ ነው፡፡ በዚሁ ከቀጠለ አገሪቱን በሙሉ የማበጣበጥ አቅም ያለው ጦርነት እየሆነ ነው፡፡ 

በጦርነቱ የሚሳተፉ አካላት አቅም እየተቀራረበ፣ በትጥቅም በሰው ኃይልም ሁሉም ወገን የመዳከም አዝማሚያ የታየበት ነው፡፡ ግጭቱን ከዚህ በላይ ማስቀጠል፣ ተጎጂዎችን መጨመር፣ ሐዘኑ በየቤቱ እንዲገባ ማድረግ፣ በዚያውም የመታረቅንና አብሮ የመኖርን ዕድል በእጅጉ የማጥበብና የማይቋረጥ የግጭት አዙሪት ውስጥ የመግባት ፋይዳ ይኖረው ይሆናል እንጂ፣ ማሸነፍን እንኳ ለማጣጣም የሚያስችል ፋይዳ አይኖረውም፡፡ 

በዚህ ረገድ ሁለተኛውን የተመጣጣኝነት መለኪያ የተመለከትን እንደሆነ፣ ከዚህ ሁሉ በኋላ ድል እንኳን ቢገኝ ያስከፈለው ዋጋ እጅግ የተጋነነ ይሆናል፡፡ የጦርነቱ አውዳሚነትና በዚያም ምክንያት በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ኃይሎችንና ሕዝቦችን አብዝቶ የጎዳ፣ የቀጠለ እንደሆነም ጉዳቱ እጅግ እየተባባሰ የሚቀጥል መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በኢኮኖሚ ደረጃ የአገሪቱ መንግሥትን ለከፍተኛ ወጪ የዳረገ፣ ተጨማሪ ሕዝቦችን ለድህነትና ለረሃብ ያጋለጠ፣ በስንት ትግል የተገነቡ መሠረተ ልማቶችን ያወደመ ጦርነት ሆኗል፡፡ በማኅበረሰብ ደረጃ በኅብረተሰቦች መካከል ጥርጣሬንና ጥላቻን ያባባሰ ብቻ ሳይሆን፣ ጭራሽ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ፣ ተጨማሪ ቁርሾ የጫረና በዚህም ምክንያት አንዱ ወገን ቢያሸንፍ እንኳን ቅቡልነት አግኝቶ ለማስተዳደር እጅግ አስቸጋሪ የሚሆንበት ዓውድ የፈጠረ ጦርነት ሆኗል፡፡ የፌደራል መንግሥትና አጋሮቹ ሕወሓትን ቢያሸንፉ የትግራይን ሕዝብ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የማስተዳደር ቅቡልነት ይኖራቸዋል? ሕወሓትስ መንግሥትን ቢገለብጥ እንደገና አራት ኪሎ ገብቶ አገር ለማስተዳደር የሚያበቃ ድጋፍ ይኖረዋል? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም በዲፕሎማሲና በውጭ ግንኙነት ረገድ ወደኋላ የመለሰን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደገና በጦርነትና በችግር የምትጠራ አገር ያደረገን ጦርነት ነው፡፡ አሸናፊ ቢኖረው እንኳን የደቀቀች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዳከመች አገር አሸናፊው የሚወርስበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ጦርነቱን መቀጠል ይህንን ውድቀት ማስቀጠል፣ ሁሉንም ወገን ማዳከም፣ የሌለን ሀብት ማባከንና በኑሮው በቅጡ ያልተመቸውን ሕዝብ ለቀጣይ ሥቃይ መዳረግ ነው፡፡

ይህ ጉዳት በትግራይ በኩልም ሆነ በፌደራል መንግሥቱና በአጋሮቹ ዘንድ በግልጽ የሚታወቅ ነው፡፡ በወታደሮችም ሆነ በሲቪሎች ላይ የሚደርሰው ጉዳት በድል ከሚገኘው ጥቅም እጅግ የላቀ ነው፡፡ ይህንን ጉዳት ዛሬ በማስቀረትና ከአሥር ቀና በኋላ በማስቀረት መካከል እጅግ ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ የማይጠፋ ሕይወት፣ የማይወድም ንብረት፣ የሚቀር ሰቆቃና እንባ አለ፡፡  ጦርነቱ መቆም ብቻ ሳይሆን በፍጥነት መቆም ያለበት ስለዚህ ነው፡፡

የሰላም አማራጭ ተግዳሮቶች

ጦርነቱ ይቁም ስል በዋነኝነት ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ ይፈለግ እያልኩኝ ነው፡፡ ሰላማዊ መፍትሔ ማለት በግጭቱ ተሳታፊ በሆኑ አካላት መካከል ተኩስ አቁሞ፣ ድርድርና ውይይት በማድረግ በሚደረሰው ስምምነት መሠረት ግጭቱን ለመፍታት መሞከር ማለት ነው፡፡ በሕወሓትም ሆነ በፌደራል መንግሥት በኩል ያሉ ኃይሎች እየተጠላሉም ቢሆን አብረው ለመኖር መስማማት፣ አለበለዚያ ደግሞ በጋራ ከመጥፋትና ቀጣይ ዕልቂት ውስጥ ከመግባት የዘለለ ዕድል የላቸውም፡፡

ይሁንና በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላትን ጨምሮ ሰላማዊ መንገድን የማይቀበሉና በጦርነት መቀጠል ይሻላል ብለው የሚያምኑ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ በጦርነቱ ተሳታፊ የሆኑ  ወገኖች የሰላም አማራጭ ፈላጊ እንደሆኑ ወይም እንደነበሩ በተደጋጋሚ ሲገልጹ ቢሰማም፣ በተግባር ግን ሁለቱም ወገን የሰላምን አማራጭ ከልባቸው እንዳልተቀበሉት ግልጽ ነው፡፡

ለአፋቸውና ለዓለም አቀፍ ገጽታቸው ሲሉ ሰላምን እንደሚደግፉ፣ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎች ቢሟሉ ለሰላማዊ መፍትሔ ቁርጠኛ እንደሆኑ ቢገልጹም ከልባቸው የሰላምን መንገድ አምነውበታል ብዬ አላምንም፡፡ ሁሉም ወገን አሁንም ጦርነት የመጀመሪያ ምርጫው ነው፡፡ ያነሳሳል፣ ያደራጃል፣ ያስታጥቃል፣ ኃይል ያሰባስባል፡፡ ከዚህ ሁሉ ውድመት በኋለ፣ ከዚህ ሁሉ ውድመትና ጉዳት በኋላ እንኳን ሁሉም ወገን ገና አልበቃውም፡፡

በፌዴራል መንግሥቱና አጋሮቹ ዘንድ ለምሳሌ ጦርነቱን ለማቆምና ለሰላም ቁርጠኝነት እንዳለ ለማሳየት የሚቀርበው የተናጠል ተኩስ አቁሙ ነው፡፡ ተስፋ ሰጪም ነበረ፡፡ ይሁንና ተኩስ አቁሙ መሠረታዊ ህፀፆች ነበሩበት፡፡ ጥሪው ለውይይትና ለድርድር በር የከፈተ አልነበረም፡፡ ይልቁንም በሁለቱ አካላት መካከል የንግግር መንገድ የዘጋ ነበር፡፡ በተጨማሪም የትግራይን ሕዝብ በጅምላ የመውቀስና የመኮነን ሁኔታ ነበረ፡፡ በትግራይ ያለው የመንገድ መዘጋት፣ የባንክ፣ የስልክ፣ የመብራትና የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት መቋረጥ፣ በትግራይ ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው ማሳደድና ሌሎች እየተፈጸሙ ያሉ ተግባራት ለሰላም መንገድ ያለው ቁርጠኝነት አናሳ እንደነበረ ያመላክታሉ፡፡

በትግራይ በኩል ለድርድር የሚሆኑ ምናልባትም ከባድ ሊባሉ የሚችሉ ቅድመ ሁኔታዎች ከማስቀመጥ ባሻገር ጦርነት ለማቆምና ለመግታት ምንም ዓይነት ምልክት አልታየም፡፡ በውይይትና በድርድር መደረስ ያለባቸውን ጉዳዮች እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ በራሱ ለሰላማዊ መፍትሔ ያለውን እውነተኛ ቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ይልቁንም በድል መንፈስ የመሆንና የመታበይ አዝማሚያ ማሳየት፣ ማስፈራራት፣ ዛቻና በተግባርም ግጭቱን ወደ ሌሎች ክልሎች ማስፋፋት ከዚህ ተቃራኒ የሆኑ አካሄዶች ናቸው፡፡

ይህ የሆነበት አንደኛውና ግልጹ ምክንያት ሁለቱም ወገን አሁንም በጦርነት አሸንፋለሁ የሚል እምነት ስላለው ይመስለኛል፡፡ ይኼ ትክክለኛና ሊሳካ የሚችል ግብ እንዳልሆነ ከላይ ለማስረዳት ሞክሪያለሁ፡፡

ሌላኛው ምክንያት ግን ከኅብረተሰቡ በቂ የሰላም ጥሪ አለመደረጉ ይመስለኛል፡፡ አገራዊ ውትወታው በጣም ደካማ ነው፡፡ ተደራደሩ፣ ተስማሙ የሚሉ ድምፆች ኮስምነዋል፡፡ ሁለቱንም ወገን አግባብተው፣ አሳምነውና ተፅዕኖ አሳድረው ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ሊያመጡዋቸው የሚችሉ አገራዊ ተቋማትና ግለሰቦች የሉንም፡፡ ወይም በአንዱ ወገን የግጭቱ ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡

መደምደሚያ

በአገራችን ታሪክ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ልዩነታችንን በጦርነት ለመፍታት መሞከር መቀጠል አሁንም የያዝነው መንገድ ይመስላል፡፡ በእኔ ንባብ በታሪካችን የጦርነት መንገድን ያስቀየርነበት አካሄድ አልነበረም፡፡ ሁልጊዜም ጦርነት ይጀመራል፣ ማስቆም ወይም ሒደቱን ማስቀየር አይቻልም ወይም አይፈለግም፡፡ ስለዚህ ሒደቱን ይጨርስ ይባላል፡፡ ብዙዎች ሞተው፣ ተሰውተው፣ ውድመት ደርሶና ዓመታትን ፈጅቶ አንዱ ያሸንፋል ወይም ያሸነፈ ይመስላል፡፡ ከዚያም ጥቂት ዓመታተ ቆይቶ ደግሞ ወደ እዚያው የጦርነት አዙሪት ይገባል፡፡

የእኔ ትውልድ ከዚህ የተለየ አጋጣሚ ያለው ይመስለኝ ነበር፡፡ የዚህ ዘመን መሪዎች ባያሳድጉንና ሕይወታችንን ባያሻሽሉት እንኳን ለጦርነት አይማግዱንም የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ እሱም ይቅር በሁለቱም ወገን ተገደን ገባንበት ሊሉ ይችላሉ፡፡ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ግን ጉዳቱን፣ ግፉን፣ ሰቆቃውን ካዩ በኋላም ቢሆን በሁሉም ወገን ያሉ መሪዎች ያላቸው አቋም አሁንም የሌለን ሀብት አሰባስበው፣ በፕሮፓጋንዳ አጡዘው፣ ግጭቱን ማስቀጠል ከሆነ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አስከፊም ነው፡፡ ለሰላም ቁርጠኛ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ይህንን ታሪክ ሊሠሩ ይገባል፡፡

በሕዝቡም ዘንድ የሰላም ድምፆች መሰማት አለባቸው፡፡ አገራዊ መፍትሔዎችና ደፋሮች ያስፈልጉናል፡፡ ፖለቲከኞቹ ብትስማሙ ምንም አይደለም መባል አለበት፣ የጦርነት ዋጋ ከፋይ ሕዝብ ነው፡፡ የሚሞተው ሕዝብ፣ የሚወድመው ሀብት የሕዝብ ነው፡፡ በድህነትም ቢሆን ለመኖር የሚቸገረው ሕዝብ ነው፡፡ ለለውጥ ያህል ሌላ መንገድ እንሞክር ማለት አለብን፡፡ ስለዚህ የንግግር በር መከፈት አለበት፡፡ አለበለዚያ ተያይዘን እናልቃለን፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...