Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትእሰየው! ኢትዮጵያ ህልውናዋን ማስተማመኗ እያማረበት ነው!!

እሰየው! ኢትዮጵያ ህልውናዋን ማስተማመኗ እያማረበት ነው!!

ቀን:

(ይህ ጽሑፍ ለአገር ወዳድ ወጣቶቻችን የተበረከተ ነው)

በበቀለ ሹሜ

በዕድሜዬ ብዙ ዓይቻለሁ፡፡ በ1969 ዓ.ም. ሶማሊያ የወረረችን፣ አሜሪካም ገንዘብ የከፈልንበትን የመሣሪያ ግዥ ነፍጋ አስወራሪ የሆነችብን፣ የውስጥ ፖለቲካ ቀውሳችንና ፀረ-አሜሪካ የሆነ ልዕለ ኃያላዊ ወገንተኛነት ውስጥ ተሸጉጠን የአሜሪካ አውጋዥ መሆናችን ለአደጋ ስላጋለጠን ነበር፡፡ በፍጥነት የሚገሰግስ ወረራ እየተካሄደ በነበረበት ሰዓት እንኳ የፖለቲካ ልዩነት ይደር ብሎ በተቀዳሚ አገር በማዳን ተግባር ላይ አንድ ላይ በመግጠም በኩል በተቃዋሚም በመንግሥት በኩልም ችግሮች ነበሩብንና በእኛው ድክመት፣ ሁለት ልዕለ ኃያላን በኢትዮጵያ ምድር ላይ ኢትዮጵያውያንንና ሶማሊያውያንን መፋለሚያ አደረጉን፡፡

ዛሬም ማለፍ ወይ መውደቅ ያለበት ፈተና ውስጥ ነን፡፡ በውስጥና በውጭ ሆነው የጉልበተኞች ጦር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ/የአየር ድብደባ እንዲካሄድብን የሚለማመኑ፣ ለግብፅና ለሱዳን ወራሪ ቅጥረኛ ለመሆን በላይ በታች የሚሉ፣ አገራችንን በማስመታት ትርፍ እናገኛለን የሚል የፖለቲካ ዳፍንት የያዛቸው ፅንፈኞች በቅለውብናል፡፡ እከሌ ከእከሌ ሳንል፣ ምዕራባዊ ጌታ አገሮች በጥቅሉ ኢንዱስትሪያዊ ያልሆኑ አገሮች በዴሞክራሲ ውስጥ ለመኖር ገና ናቸው በሚል ዘረኛ አመለካከት ተደግፈውና እኛም በዘረክራካነታችን አግዘናቸው ክፉኛ ንቀውናል፡፡ ለእኛ የሚመኙልን ምን እንደሆነ የሕወሓት-ሸኔ ደጋፊ በመሆን እየነገሩን ነው፡፡ አሜሪካ አኅጉር-አከል አገር ታቅፋ፣ አውሮፓ ኅብረትም ክፍለ አኅጉራዊ ማኅበረሰብ እየገነባች ኢትዮጵያን በተመለከተ ግን የበጣጣሾች አጋዥ መሆናቸው የሚገርም ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡ ሳንንሸቀሸቅና ሳናደገድግ በጥንቃቄና በብልኃት ከበለጥናቸው የሚያስቡልንን ደባ ሁሉ መበታተንና ባለድል መሆን እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ቢዘገይም ከትናንትና ተምረናል፣ ፈርጀ-ብዙ ብርቱ አቅም የማደርጀትና ሁለገብ ተጋድሎ የማካሄድ ሥራችን ተሳልቶ በመጧጧፍ ላይ ነው፡፡

  1. መላ ኅብረተሰባችን ሆ ብሎ ተነስቷል!

የኢትዮጵያ ሕዝቦች ከሞላ ጎደል፣ አገራቸውን ፌዴራላዊና ዴሞክራሲያዊ አድርጎ በመገንባት ላይና ሰላምን በመናፈቅ ላይ፣ አንዳችም ማወላወል እንደ ሌላቸው በምርጫው ጊዜም ሆነ ከምርጫው በፊትና በኋላ በነበራቸው ርብርብ ቁልጭ አድርገው አሳውቀዋል፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ይቅርና፣ ሰላም-አልባነት ባለበትም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ተሳስበው መኖር እንደሚችሉ በተደጋጋሚ አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ የሕዝቦች ታላቅነት ውስጥ መብቀልና መኖር መታደል ነው፡፡ ማንም አይበታትነንም በማለት ሆ ብለው በተነሱ ጊዜ ለመከላከያ ሠራዊት ያሳዩት ፍቅርና የስንቅ ድጋፍ በዚህ ጽሑፍ ተወርቶ አያልቅም፡፡

መከላከያ ሠራዊታችን ትግራይ ከገባ በኋላ የትግራይን ሕዝብ ለመርዳት ያሳዩት ርብርብ ምን ያህል ወገናዊ አንጀት እንዳላቸው የመሰከረ ነበር፡፡ የሕወሓት አሸባሪ ጦረኞች፣ ደም አቃብቶ ሕዝብ በሕዝብ ላይ እንዲዘምት ለማድረግና የሕዝብን ኑሮ ትርምስምስ በትርምስምስ ለማድረግ አፋርና አማራ ላይ ወረራ በፈጸሙ ጊዜ ያሳየው ‹‹የወገኔ ጥቃት የእኔም የኢትዮጵያም ጥቃት›› ያለ፣ ከስንቅ አልፎ በደምና በአጥንት የተገለጸ ርብርብ፣ እየተረባረበም ግፈኛው ሕወሓት ለሚማግዳቸው ትግራዊ ሕፃናትና አዛውንት ያሰማው ‹‹ዓለም ፍረድ!›› ያለ ጩኸትና ለትግራዊ ምርኮኞች የሚያደርገው ወገናዊ እንክብካቤ፤ ኦነግ-ሸኔና ሕወሓት ተብዬ አሸባሪዎች የሽብር ጉድኝታቸውን ይፋ ባደረጉ ጊዜ ያሳየው አክ እንትፍ ያለ ውግዘት ሁሉ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በአገራዊ አንድነታቸውና በሰላማቸው ላይ፣ እንዲሁም በወገናዊ መተሳሰባቸው ላይ አንዳችም ማወላወል እንደሌላቸው ያረጋገጠ ነው፡፡ ለዚህ አገር አቀፍ የሕዝብ ታላቅነት ፖለቲካ ቀመሶች መሬት ለጥ ብለን እጅ ብንነሳ ያንስብናል እንጂ አይበዛብንም፡፡

  1. ወጣቶቻችን ተስመው ተስመው የማይጠገቡ ሆነዋል!

ኢትዮጵያ አገራችን በረዥም ዘመን ባለታሪክነቷ አሮጊት ነች፡፡ ግን እውነተኛ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊነት የመገንባት ጥረት ውስጥ እንደ መሆኗና አብዛኛው የሕዝብ ክፍሏ ወጣት እንደ መሆኑ፣ ኢትዮጵያን ወጣት ሙሽራ ብንላት ስህተት አይሆንም፡፡ የአሁንና የወደፊት ስኬቷም (በፖለቲካ ሰላም፣ በልማትና በሥልጣኔ) በወጣቶቿ እጅ ነው፡፡ ያበቀላቸውን የዚህን ኅብረተሰብ ታላቅነት ለመውረስ ወጣቶቻችን እስከቆረጡ ድረስም ኢትዮጵያን በየትኛውም ዳገት ላይ ይዘው መውጣት ይችላሉ፡፡ የጠመዱንንም በእርግጠኝነት ማሳፈርም ይችላሉ፡፡

ወጣቶቻችን ለዚህ ይበቃሉ የሚል እርግጠኛነት ነበረን? ካልዋሸን በቀር ሁላችንም ትነስም ትብዛ ጥያቄ ነበረን፡፡ የሕወሓት አሸባሪዎች በአፋርና በአማራ ላይ ዲያቢሎሳዊ ወረራ መክፈታቸውን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አቅምና ዕድሜው የፈቀደለት ለመዝመት እንዲነሳ፣ ቀሪው አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅ እንዲተጋ ላደረገው አገራዊ ጥሪ ወጣቱ የሰጠው ምላሽ ከግምት በላይ ብቻ አልነበረም፣ አፍ አስበርግዶ ‹‹በኢትዮጵያ ምድር ተዓምር ታየ!›› ያስባለ ነበር፡፡ በ1969 – 1970 ዓ.ም. ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ እንኳ ለዘማችነት ከውዴታ ባሻገር ሰው ይታፈስ ነበር፡፡ የእኔም የገጠር አጎት ‹‹መሣሪያ ትታደላላችሁና በዚህ ቀን ተሰብሰቡ›› በሚል ዘዴ ነበር ታፍሶ የተወሰደው፡፡ ዛሬ ግን ለሆነው ነገር ‹‹ሁሉም በውዴታ›› ብሎ ወሬ ምን ሊመጥነው!!! 50 ዓመት ያህል፣ ከ50 ዓመታት ውስጥም 27 ዓመታት በፌዴራልና በአካባቢ መንግሥታት ደረጃ ሲሠራበት የቆየ ጎጣዊ ሽንሻኖ የተካሄደበት አስተሳሰብና ወገናዊነት የት ገባ?! የአውንና የደርግን ዘመን ያዩትን ትውልዶች በተመለከተ፣ ኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ያጎረች ጉረኖ ያለመሆኗ (በዘመነ ዘመናት የሕዝብ ለሕዝብ መወራረስ የመገንባቷ) ሀቅ፣ በብሔርተኛ የአመለካከት ሽንሻኖ ውስጥ ተደብቆና ተዳፍኖ ቆይቶ ቀን ሲመቸው ሳይሳቀቅ ወጣ ቢባል አይደንቅም፡፡

በሕወሓት/ኢሕአዴግ የ27 ዓመታት ገዥነት ውስጥ ተወልደው ባደጉ ወጣቶች ዘንድ ግን ምን ተዓምር ተፈጠረ? ‹‹የወጣቶቻችን አስተሳሰብ ተከታተፈ፣ በበቀል፣ በጥላቻና በጭካኔ ማቀቀ›› እስከማለት ያደረሰንና ብዙ ጥፋት ሲያሠራ ያየነው ስሜት የት ደረሰ? ከምንጊዜው እንደ ቅርፊት ደርቆ ከሽልሎና ተሰነጣጥቆ፣ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ፀጉር የአገር ፍቅር ነዲድ ሲምበለበል ለማየት በቃን?! ‹‹ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ፀጉር›› ስላልኩ ያጋነንኩ የመሰላችሁ ካላችሁ፣ ልንገራችሁ ይህም አይመጥነውም፡፡ የታየው የወጣቶቻችን የክተት እንቅስቃሴ እኮ የአካባቢ ርቀት፣ የባህልም ሆነ የቋንቋና የፆታ አጥር ያልገደበው፣ ሥራ መያዝ አለመያዝ፣ የሥራ ልሂቃዊ መሆን አለመሆን፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መጨረስ አለመጨረስ ያላበላለጠው (በአሁኑ ዓመት ተመርቆ ወደ ተመልማይነት መሄድ ሁሉ የታየበት) መሆኑን ልብ ብላችኋል?!! በኢትዮጵያ ታሪክ እንዲህ ያለ በዕንባና በቁርጠኛ ወኔ የመቶ ሺዎች ወጣቶች የውዴታ መገመሻሸር ታይቶ ይታወቃል? ይህ ሁሉ ለውጥ የመጣው በሦስት ዓመት ክትባት ነው? አይምሰላችሁ፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልሂቃን ለ50 ዓመታት ስለተበጣጠሱም ሆነ ከፋፋይ አመለካከት ለ27 ዓመታት ነግሦ ስለቆየ የኢትዮጵያነትና የኢትዮጵያዊነት ግንባታ አልተቋረጠም፡፡ አደባባያዊው ርዕዮተ ዓለም ምንም ሆነ ምን/ምንም ይበል ምን፣ የኢትዮጵያዊነት ግንባታ በ‹‹ደመ ነፍሳዊ›› ሰበዞች ሳናውቀውና ልብ ሳንለው ሲካሄድ ኖሯል፡፡ ዛሬ በወጣቶቻችን ሲንበለበል ያየነውም፣ ታስሮና ተሸሽጎም በነበረበት ጊዜ በግብታዊነት ድምፅ አጥፍቶ ሲደረጅ የቆየውን እነፃ ነው፡፡ የአሁኑ የሦስት ዓመት ጊዜ ተቃርኗዊ ልምድ ያዋጣው ነገር ቢኖር፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የታየው ጨርቁን ጥሎ ተናካሽ የሆነ ፅንፈኝነትና ይህንን የተናነቀው የአንድነትና የለውጥ ኃይሎች ተጋድሎ፣ በግብታዊነት ሲደረጅ በቆየው አገር ወዳድነት ላይ ብርቱ ጉትጎታ ማድረሳቸው ነው፡፡ እናም ተሸማቆ ሲደረጅ የቆየው የአገር ፍቅር፣ ከሁለት በኩል በአሉታዊና በአዎንታዊ ወስፌ ሲነዘነዝ ኃፍረትና መሳቀቁን በርቅሶ ወጣና ተንፎለፎለ፡፡ ስንት ወቀሳና ትችት ያጎረፍንባቸው ወጣቶቻችንም አገር መውደድ የስሜትና የቁርጠኝነት ስፋቱና ጥልቀቱ የት ድረስ እንደሆነ፣ ተግባራዊ አገላለጹም እንዴት እንደሆነ ከእኛ ተማሩ ሊሉን በቁ፡፡ ኢትዮጵያ ትቀጥል ይሆን የሚል ጥርጥራችንንና ሥጋታችንንም ኃፍረት አከናነቡትና አረፉ፡፡ ‹‹ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አገረ መንግሥት ግንባታችንን ኢትዮጵያን ከማዳን ጋር አታምታቱት›› የሚል መልዕክት በኢትዮጵያ ምድር ከዳር ዳር ነዙልን፡፡ መልዕክት የሚገባን ከሆነ፣ ፖለቲካ የምናወራና በሚዳሰስና በማይዳሰስ ሚዲያ ላይ ቃላት የምንለቀልቅ ሁሉ፣ በካምፕና በጦር ሜዳም ሆነ በአካባቢ ጥበቃ የልጆቻችን ውሎዎች ሥር ተኮልኩለንና ደብተር ዘርግተን ብንማር ያምርብናል፡፡

የወጣቶቻችን ተስሞ ተስሞ አለመጠገብና አስተማሪነት መቼ በዚህ ብቻ የሚወሰን ሆነና!! ከወዲህ የፈረንጅነት አዚምን ከ‹ዋው!›/‹ኡፕስ!› እስከ ስሜት-ልቦና ካልቀዳን የሚሉ ወጣቶች እንዳሉን ሁሉ፣ በተንጨፈጨፈ ኢትዮጵያዊነት ውስጥ መሠልጠንን የሚያስቡ፣ ትምህርት ተምረው የማይጠግቡ (አንዱን ተምረው ወደ ሌላው የሚፈጥኑ፣ በአንድ ጊዜ ሁለት ዓይነት የዕውቀት/የሙያ መስክ የሚማሩ)፣ እየተማሩም የልብ ወለዱ የፖለቲካውና የፍልስፍና ንባቡ ሁሉ አይቅርብን የሚሉ አንዳንድ ፍሪት ወጣቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የማወራው በሙስሊምም በክርስቲያንም በኩል አጀብ እያልኩ ያየሁትን ነው፡፡ በተለይ በሴት ልጆቻችን ዘንድ ያለው መፍለቅለቅና መመንደግ ወደፊት ብዙ ዕንቁዎች እንደሚወጡ የማያጠራጥር ነው፡፡

ከሆሊውድ ፊልሞች ቦጨቅ ቦጨቅ እየተደረገ የተገጣጠመ የታሪክ ሰንሰለትና የአኗኗር ፀባይ ‹‹የእኛ›› ፊልም ተደርጎ እየቀረበ መድረሻ እንዳላሳጣንና ማየት የጀመርነውን ፊልም መጨረስ እንዳላስቸገረን፣ ከእኛው የኑሮ ገጽታ የተዘገነ፣ ሳይቦተልክ የሚቦተልክ፣ ሳይደሰኩር የመለወጥ ጥማታችንን የሚዳስስ ‹‹እረኛዬ›› የተሰኘ ተከታታይ ፊልም በሴት ደራሲያንና መሪ-አሰናጅነት እንካችሁ ተባልን፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ህዳሴ ሌላ ምልክት ነው፡፡ ውዳሴዬ ጭፍን አይደለም፡፡ ፊልሙ በታሪክና በገጸ ባህርይ አገነባብ ረገድ የማይናቁ የተዓማኒነትና ዕውናዊ ዕጦትን በምኞት የማጣጣት ችግሮች አሉበት፡፡ ይህንን ጠቆም ያደረኩት ብርቅዬ ደራሲዎቻችን በውዳሴ እንዳይቀልጡብኝ (መስላት፣ መትባታቸው በመኩራራት ሞራ እንዳይደፈን በመሳሳት) ነው፡፡ ከእንግዲህ የፊልም ሥራ ጸሐፊም ሆነ የፊልም አሰናጅ ነን ባዮች፣ ኢትዮጵያዊ ፊልም መሥራት ማለት የፈጠራ እትብትን ከኢትዮጵያ ኑሮ ጋር ማገናኘት መሆኑን ‹‹እረኛዬ›› ሠርቶ አሳይቷል፡፡ ካወቁ ይወቁበት፡፡

ሌላም ነገር ልጨምር፡፡ እንደ መድረክ ቴአትር የትዕይንቶች መፍሰስ በሌለበት የፈልም ቁርጥርጥ ቀረፃ ውስጥ ተዋንያን የተሰጣቸውን ገጸ ባህርይ እውነተኛ ስሜት ተጎናፅፎ መተወን ከባድ ይሆንባቸዋል፡፡ የፊልም ሥራ መዋጣትም ከተዋንያን አተዋወን ባሻገር ከካሜራ አቀራረፅ አንስቶ ከቀረፃ መልስ የብዙ ባለሙያዎች እጅ የሚያርፍበት ነው፡፡ ያ እንዳለ ሆኖ በ‹እረኛዬ› ውስጥ ያየነው ትወና በጥቅሉ አንድ ከፍታን አምጥቷል፡፡ በተለይ ሳያት ደምሴ ላይ ያየሁት እዩኝ እዩኝ የማይል የትወና ብቃት የሚደንቅ ነው፡፡ ሌሎቹ ተዋንያን በፊልሙ ውስጥ የሚሠሩትን የምከታተለው እየተወኑ መሆናቸው ሳይረሳኝ ነው፡፡ የሙሉዓለም ታደሰን በግራ መጋባትና በጭንቀት መባዘን የምከታተለው ሙሉዓለምነቷን ረስቼ ነው፡፡ ሳያት ደምሴ ስትተውንማ፣ ሳያት ተመልሳ መምጣቷ እስኪያጠራጥር ድረስ፣ ሳፊ የከብት እረኛ ነው የምናየው፡፡  የፊልም ተዋንያን ነን ብለው ኩራት በኩራት የሆኑ፣ መተወን ማለት እጅንና የፊት ገጽን ማፈራገጥ የሚመስላቸው ሰዎች፣ እነ ሳያት የትወና ትምህርት ቤት እንደ ከፈቱላቸው ልብ ይበሉ፡፡ የወጣቶቻችን አመነዳደግ ይህንን ያህል ደፍሮ እስከ መናገር አድርሷል፡፡ በጥቅሉ በሙዚቃና በውዝዋዜ መስክ፣ በጋዜጠኝነት፣ በበጎ አድራጎት ሥራዎች፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራና በሳይንስ ምርምር፣ ወዘተ ሁሉ አሁን አሁን በወጣቶቻችን ዘንድ የምናየው ነገር ኢትዮጵያ የብዙ ጀግኖች እናት መሆን እንዳማራት፣ ማማርም ብቻ አይደለም፣ ቅሪትም እንደያዘች የሚናገር ነው፡፡ አገራችን ትክበድ ትውለድልን! የተወለዱትም ይባረኩላት!

  1. የጠመዱን ኃይሎች እኛን እያበረቱን/እያገዙን እንደሆነ ልብ ብላችኋል!?

በሕዝቦች የተከበበ መንግሥት በኢትዮጵያ የመኖሩን እውነታ ናላቸው ማየት ስቶት፣ ‹‹የሽግግር መንግሥት አውጀናል›› አሉ የተባሉት ሰዎች ሰሚም ጠያቂም አጥተው፣ በእውነታና በቀን ቅዠት መካከል ያለው ልዩነት ተቀላቅሎባቸው ሜዳ ለሜዳ ለብቻ እንደ መለፍለፍ ያለ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ (አንዴ የኬንያው ራይላ ኦዲንጋ እንዲህ ‹‹ነካ›› አድርጎት አየር ላይ በዓለ-ሹመት ፈፅሞ ነበር፡፡ ደግነቱ እሱ በቶሎ ወደ ልቦናው ተመለሰ፡፡ የእኛዎቹም ፈጣሪ ጤናቸውን መልሶላቸው ሕዝባዊ የለውጥ ዥረታችንን እንዲቀላቀሉ እንመኛለን)፡፡ የሕወሓት ጦረኞችና ተቀጥላቸው ሸኔ አንዳችም ፖለቲካ ያልተረፋቸውና በኢትዮጵያ ሕዝብ የተተፉ ሳፊ ወንጀለኞች መሆናቸውን፣ አሜሪካና የምዕራብ መንግሥታት ከእነ ሚዲያዎቻቸውም ሆኑ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ነን ባዮች ሊሸሽጓቸው በማይችሉት ደረጃ ዕርቃናቸውን ወጥተዋል፡፡ ሕወሓቶች የኢትዮጵያ መንግሥትን የተናጠል ተኩስ ማድረግን ለግፍ ድግስ ተጠቅመው በአማራና በአፋር ሲቪል ሕዝብ ላይ የፈጸሙት (የማተረማመስ፣ የዘረፋና የውድመት፣ ሕዝብ የማፈናቀል፣ ሰላማዊ ሰዎችንና ሕፃናትን በጭፍን የመረፍረፍ) ወንጀል እንዳላዩ በማለፍ እንደምን ሊደበቅ!! የሕወሓት-ሸኔ ወንጀለኞችን በሚያወግዝ ሠልፍ ላይ አንድ ተራ ሰው ሲናገር እንደ ሰማሁት ‹‹ሸኔ›› እና የሕወሓት አሸባሪዎች ነካክተው አንድነታችንንና መተሳሰባችንን አጠናከሩልን ያለው እውነት ነበር፡፡ በግፋቸው የዋሉልን ውለታ ግን ከዚህም በላይ ነው፡፡ እዚያም እዚያም እያሸበሩ ትርምስ በትርምስ፣ መፈናቀል በመፈናቀል ሊያደርጉን፣ በዝርፊያ/በውድመትና በርሸና ሊበቀሉን ባካሄዱት ባለብዙ አቅጣጫ ዘመቻ፣ ለመከላከያ ኃይላችን ደጀን የመሆን አቅማችንን አባዙት! የአገር ዘብነታችንን ሕዝባዊ ወታደርና ሕዝባዊ የደኅንነት/የፀጥታ መረብ እስከ መሆን ድረስ አንተረከኩት፡፡

የአሜሪካና የአውሮፓ ውስን መንግሥታት ከእነ ሚዲያዎቻቸው፣ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ዓለም አቀፍ ተቋማት ነን ባዮች በኢትዮጵያ ለደረሱ ሰብዓዊ ጥቃቶችና ጉስቁልናዎች እኩል ዓይንና እኩል ድምፅ የሌላቸው ጭራሹን አንዱን አጡዘው ሌላውን እንዳልደረሰ በዝምታ የሚዘሉ መሆናቸው፣ ዓላማቸው ፖለቲካዊ መሆኑን ማጋለጡ ከጊዜ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ አሜሪካና ምዕራባዊ አጋሮቻቸው ሰው አገር ድረስ ተሻግረው ‹‹መሪያችሁ ወንጀለኛ ነው፣ ወይ ስጡን ወይ ራሳችን የገባበት ገብተን ለፍርድ እናቀርበዋለን›› እያሉ ጦር እስከ ማዝመት ድረስ አይደረግ የሚያደርጉ ሆነው ሳለ፣ እኛን ግን በገዛ አገራችን ውስጥ የአገሪቱን መከላከያ ኃይል ትልቅ ዕዝ ቦጭቆና አኮላሸቶ አገር የመውረር ከፍተኛ ክህደት የፈጸመን ቡድን፣ ይህም ሳይበቃው የትግራይን ሕፃናትና ሲቪሎች ወደ ጦርነት የመማገድ ግፍ የሠራ፣ በተጎራባች አካባቢዎች ላይ እየዘመተም ከጦር ወንጀልና ከጅምላ ጥቃት አንስቶ እስከ ተራ ዘራፊነት የሰፉ ነውሮችን እያካሄደ ያለ ባለብዙ ወንጀልን አሳዳችሁ ይዛችሁ ለፍርድ አታቅርቡ  (ተኩስ አቁማችሁ ተደራደሩ፣ የወንጀል ወንጀሎችን የፈጸመ ቡድን በአካባቢ ገዥነት እንዲቀጥል ፍቀዱ) ሲሉን የግፈኞች ለፍርድ መቅረብ ጉዳያቸው እንዳልሆነ፣ ፍትሕን ማውለብለብ ለእነሱ ይጠቅመናል ሲሉ የሚይዙት፣ አይጠቅመንም ሲሉ የሚረግጡት የፖለቲካ መሣሪያቸው እንደሆነ ራሳቸውን በራሳቸው ያጋለጡበት ነው፡፡ ከእኛም የሚፈለገው ይህንን ቅሌታቸውን በተደራጀ የሰነድ ማስረጃ ለዓለም ማጋለጥ እንጂ፣ እዚያም እዚያም እየዘለሉ መቀበጣጠር አይደለም፡፡ የአሜሪካ መንግሥትና ምዕራባዊ አበሮቹ እየሠሩ ያሉትን ነውረኛ ተግባር በውጭ ያሉ የኢትዮጵያ ልጆች በብዙ ግንባር ለዓለም እያጋለጡ መንግሥታቱ በሕዝባቸው ፊት እንዲሳጡ፣ የኢትዮጵያን ሀቅ የሚያስተጋቡ ምዕራባዊ የኢትዮጵያ ተቆርቋሪዎችና ለእውነት የታመኑ ጋዜጠኞች እንዲጨምሩ፣ የእነ አሜሪካ ተባባሪዎች እንዲቀንሱ፣ እንዲያም ሲል የአሜሪካ መንግሥት የሥራ አስፈጻሚዎችን አቋም የሚያቃና ጫና ከውስጥ እንዲመጣበት ለማድረግ እየሠሩ ነው፡፡ እስካሁን በውጭ ያሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ ልጆችና ሌሎች ወዳጆቻችን እየሠሩ ባሉት ሥራ የተጠራቀመው የተሰሚነት መሻሻልም ግፋ በለው የሚያሰኝ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትና የውስጥ ልሂቃን ይህንን ነው ማገዝና በመረጃ መመገብ ያለባቸው፡፡

የአገራችን መንግሥታዊና የግል ሚዲያዎችም ማትኮር ያለባቸው ይህንን ዘርፈ ብዙ ውጤት በማስገኘትና የትግራይ ሕዝብን የህሊና ሐርነት በማጎልበት ዒላማዎች ላይ ባነጣጠሩ ስል ሥራዎች ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የእነ አሜሪካን ‹‹ታሪካዊ ጠላትነት›› ሳያውጅ ያወጀ ይመስል አሰሱን ገሰሱን ሁሉ እየቃረሙ ለፕሮፓጋንዳ ማዋል ይጎዳን እንደሁ እንጂ አይጠቅመንም፡፡ የ16ኛ/የ17ኛ ክፍለ ዘመን አስተሳሰብ ያለው ዘረኛ ‹‹ምሁር›› ያቀረበውን ‹‹አፍሪካን በድህነት፣ በትርምስና በአቅመ ቢስነት ቀይዶ ጥሬ ዕቃቸውን በርካሽ መምጠጥ አለብን›› የሚል ፋሺስታዊ ዲስኩር የዛሬ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ምዕራባዊ የሐሳብ መሐንዲሶችና መንግሥታት አቋም ይመስል ደጋግሞ በመገናኛ ብዙኃን ማቅረብና ማባዘትስ ምን የሚሉት ነው? ዕውቀት ማስፋት ወይስ ማደናቆር? የኢትዮጵያ መንግሥት ወዳጅ ማበራከቱና ያሉትን ወዳጅነቶች ተንከባክቦ በየፈርጁ አቅም የማጎልበት ተግባር ማካሄዱ አበጀህ የሚባል ነው፡፡ ይህንን መዘገብም የሚጠበቅ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ‹እንትና› የሚባል አገር ‹‹ዜሮ ‹ኮንፍሊክት› ፖሊሲ ያለው… ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ብዙ የምትማረው …›› እያሉ ቅቤ መጥበስን ምን አመጣው? የዚህ ዓይነት ቀረጥ ክፈሉ ተብለናል ወይስ ቅቤ ጠባሽነት ደማችን ውስጥ ገብቷል?

ከተማሩ አንዳንድ አገር ወዳዶቻችን የምንሰማው በቅጡ ያልታሰበበት ንግግርም የሚገርም ነው፡፡ የእነ ቬነዙዌላንና የፊሊፒኖችን አምባገነኖች ጠቅሶ ‹‹ምን ሆኑ እነሱ?›› የሚል ድርደራ፣ እነሱ ለእኛ በምሳሌ አስረጂነት የሚበቁ ሆነው ነው? በተለይ ቬነዝዌላ ምን ያልሆነችው አለ? ‹‹እከሌ ምን ሆነ?›› የሚል አካሄድ እኮ የሶሪያው በሽር አላሳድ ምን ሆነ እስከ ማለት ሊወስደን ይችላል፡፡ ከሞላ ጎደል መላው ኅብረተሰባችን፣ መንግሥትና አብዛኛው ተቃዋሚ አንድ ላይ የገጠሙበት የእኛ እውነታ ከእነ ቬነዙዌላ እውነታ ጋር አይመሳሰልም፡፡ እኛ አገር የማዳንን ተግባር ፌዴራላዊ ዴሞክራሲን እውነተኛ መሠረት ከማስያዝ ተልዕኮ ጋር ያጣመርን ነን፡፡ በዚህ ላይ ራስን በራስ የማጥፋት ‹‹ግጥሚያ›› የያዙት ሕወሓቶች ከሚተኩሱት ጥይታቸው የተሻለ ዋጋ ለትግራይ ሕዝብ ደም እንደማይሰጡት ወለል እንደ ማለቱ፣ በግፍ ወንጀሎች እንደ መብከታቸውና ኃይላቸው በመመናመን ጎዳና ውስጥ እንደ መሆኑ፣ እነዚህን ወንጀለኞች በፍጥነት አሽመድምዶ የትግራይን ሕዝብ ከጦረኞቹ መንጋጋ የማላቀቅ ትልቁ ተግባር በእጃችን ያለ ያህል ነው፡፡

  1. የትግራይ ሕዝብ ሆይ! የሕወሓት ጦረኞች እንድትተፋቸው እየተማፀኑህ ነው!

ኢትዮጵያን ማዳን ሙሉ የሚሆነው የትግራይን ሕዝብ ማዳን ሲቻል ብቻ ነው፡፡ የሕወሓት ጦረኛ አሸባሪዎች ትግራይ ላይ ተተክለው እያሉ ኢትዮጵያ ሰላም አታገኝም፡፡ የአገርም የብሔርም ተቆርቋሪነት የተሰለበባቸው እነዚህ ከሐዲዎች ትግራይ ላይ ነገሡ ማለት፣ ኢትዮጵያ ጠላቶቿ ሁሉ በጉያዋ የጦር ሠፈር እንዲያቋቁሙ ፈቀደች ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መቀጠልና ሰላም ማግኘት ከሕወሓት ጦረኞች ጋር አብሮ ሊኖር የማይችል ነገር ሆኗል ማለት ደግሞ፣ የትግራይ ሕዝብ ሰላምና ልማትም የህልም እንጀራ ይሆናል ማለት ነው፡፡

በዛሬው ጊዜ ይህንን ሀቅ ለመረዳት የትግራይ ሕዝብ ዕውን አንቂ ትሻለህ?! የሕወሓት ጦረኞች ያለ ደምና ያለ በቀል መኖር እንደማይችሉ እነሱ ራሳቸው በተግባር እየተናዘዙልህ እኮ ነው!! ሕፃናትህን እየማገዱ፣ በአጎራባች ወገኖችህ በአፋርና በአማራ ላይ የዘመቱት ለአንተ ሰላምንና ብልፅግናን ወይም መሬት በጆንያ ጭነው ሊያመጡልህ እንዳልነበረ፣ ለበቀል የዘመቱበት የአፋርና የአማራ ሕዝብ በቁጣ ተንጨርጭሮ በአንተ ላይ እንዲዘምትና አንተን በማስፈጀት እነ አሜሪካ ለእነሱ እንዲደርሱላቸው መዘየዳቸው እንደነበር ለማጤን አስረጅ ያስፈልግሃል!?

ትግራይ እንደ ጅግጅጋና ድሬዳዋ ለባህር በር ቅርብ (ያውም በሁለት በኩል ለጂቡቲና ለኤርትራ ወደቦች) እንደ መሆኗ፣ ምርጥ የኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ የኢንዱስትሪ ልማት ማዕከል የመሆን ዕድል ያላት አካባቢ እንደሆነች ግልጽ ነው፡፡ የውጭ ጠላት አደግዳጊ ሆነው ያረፉት የሕወሓት ጦረኞች ይህንን ዕድል አንቀው ነው በደምህ የሚታጠቡት፡፡ ከዚህ በላይ ምን እስኪያደርጉህ ትጠብቃለህ!! ሕዝባዊነቱን በቅርብ ከምታቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር ሆነህ የነጠቁህን በዴሞክራሲያዊ ነፃነት ራስህን በራስህ የማስተዳደር መብት፣ የነጠቁህን የሰላምና የግስጋሴ መናኸሪያ የመሆን ዕድል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ንጠቃቸው!! እነዚህ ግፈኞች በየአካባቢው ሰርጎ በመግባት ሽብርና ትርምስ የመፍጠር ጣዕረ ሞታዊ መንፈራፈር ውስጥ በሚገኙበት ሁኔታ ውስጥ ግብረ አበራቸውን ከደህነኛው መለየት አስቸጋሪ  ነውና፣ በየትም ያለህ ትግራዊ ሁሉ ከኢትዮጵያ ወገኖችህ ጋር በፀረ ሽብሩ ንቁ ትግል ውስጥ ግባ! በሕወሓት አባልነት ውስጥ የቆያችሁም ሁሉ ከአናታችሁ የተቀመጡትን የሽብር ራሶች በመክዳት ከትግራይ ሕዝብ ጋር መቆማችሁን አስመስክሩ! በአሸባሪው የውጊያ ሥምሪት ውስጥ ያላችሁም፣ እየሸሻችሁና እጅ እየሰጣችሁ የትርምስና የጦረኝነት መጠናቀቅ አካል ሁኑ!!

  1. የትግራይ ሕዝብ ሆይ! በዴሞክራሲያዊ ነፃነት የሰላምና የልማት ኑሮ ውስጥ የመግባት ዕድልህ የአንተን ውሳኔ የሚጠባበቅ ነው!!

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ደምና ሽብር የለመደባቸውን የሕወሓት ጦረኞች እያራወጠ በሌላ ድል ትግራይ ውስጥ ቢዘልቅ እንኳ፣ ከእነሱ አፈና ለመላቀቅ አንተ ሆ ብለህ እስካልተነሳህ ድሉም፣ የአንተ ኑሮም እየፈጩ ጥሬ ከመሆን ፈቀቅ አይልም፡፡ ለሰላምና ለአዲስ ሕይወት ቆርጠህ ከተነሳህ ግን በመከላከያ ሠራዊት ታግዘህ፣ ያመንካቸውንና ከራስህ የወጡ ሕዝባዊ የደኅንነትና የፀጥታ ዘቦች አቁመህ፣ ከታች እስከ ላይ አንተው የመረጥካቸውና አንተው የምትቆጣጠራቸው ሰዎች የተዋቀሩበት ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም፣ የአፈና መዋቅር ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሚናቸውን እንዲለዩ እያደረክና እያፀዳህ ቋሚ አስተዳደርህን ለመገንባት የሚያሹትን ሁኔታዎች መደልደል ትችላለህ፡፡ አንዴ እዚህ ቆራጥ ዕርምጃ ውስጥ ከገባህ ወደ ኋላ መመለስም ሆነ ዳግም ድንግዝግዝ ውስጥ መግባት ብሎ ነገር አይኖርም፡፡ የምዕራባውያን የሕወሓት ጦረኞችን የደገፈ ጫጫታና ኢትዮጵያንና ኤርትራን በማዕቀብ የማነቅ ጥረት ሁሉ እምሽክሽኩ ይወጣል፡፡ ሕዝብን ማረን ማለትና እጅ መስጠት ሞታችን ያሉ የሕወሓት ጦረኞች ትጥቅ ትግል እንሞክራለን ብለው በረሃ ቢገቡ እንኳ ዕድሜ አይኖራቸውም፡፡ ምክንያቱም ሕወሓቶች የገነዙት ሁለገብ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴህና ልማትህ ነፍስ ይዘራል፡፡ ነፍስ ዘርቶም ድህነት በሠለጠነበት ሕይወትህ ላይ ከወረት የዘለለ ለውጥ ማምጣት እስከቻለ ድረስ በረሃ ገብተው ሊተኩሱብህ የሚሞክሩ ርዝራዥ ጦረኞች  መክስማቸው አይቀሬ ነው፡፡

የማወራው መላምት ሳይሆን ሊጨበጥ ስለሚችል የሕይወት ለውጥ ነው፡፡ ስለትግራይ የሞቀ የኢኮኖሚ ሕይወትና ልማት ሳወራ፣ ትግራይን ከመሀል አድርገው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ስለተገናኙበት የኢኮኖሚና የልማት ተራክቦ ማውራቴ ነው፡፡

  1. ፕሮፓጋንዳ መንፋቴ ይሆን??

የማወራለት ይህ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ እኔ ከኪሴ ያወጣሁት ነገር አይደለም፡፡ የኤርትራ መዳከም የኢትዮጵያ መዳከምም እንደሆነ፣ የኢትዮጵያም መዳከምና መበታተን ለኤርትራ ጉዳት እንደሆነ፣ የሁለቱ ፀበኛ መሆንም ለሁለቱም ኪሳራ ለሌሎች ግን ፌሽታቸው እንደሆነ፣ የአፍሪካ ቀንድ ኑሯችን እየቆነጠጠም እየገረፈም ፍርጥ አድርጎ ሲነግረን ቆይቷል፡፡ ሁለታችንም በስተኋላ እውነቱን በተግባር አምነን ተቀብለናል፡፡ የመደጋገፍ ረሃብና ናፍቆታችን በመግደርደር የማይደበቅ ሆኗል፡፡ ሕወሓት የእኔ ንግሥ ካልቀጠለ ኢትዮጵያን ልመንጭር ብሎ ሲያምስ የሠጉልን፣ በኋላም የክህደት ወረራ ሲፈጸም አለንላችሁ ያሉን፣ በዓለም አደባባይም አብረውን የተዋደቁትም የታሪክና የሥጋ ዘመዳቸው ስለሆንን ብቻ ሳይሆን፣ የየበኩል ህልውናችንና ልማታችን እርስ በርስ ተፈላላጊ መሆኑን የማወቅና ለራስ የመድረስ ኃላፊነትን የመወጣት ጉዳይ ነው፡፡

ግንዛቤውና የራስ ለራስ ያህል ኃላፊነቱ የሁለት በኩል ነው፡፡ እኛ መንግሥትን ፈርቶና አፍ ዘግቶ መኖር እንደማንሻ ለእነሱም ይህንን አንመኝም፡፡ ነገር ግን የሕወሓት ጦረኞች ሲያደቡበት የነበረውን  የመሪ ግድያ፣ የመፈንቅለ መንግሥት ሴራም ሆነ ወረራ አንመኝላቸውም፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ድግስ ተባባሪም አንሆንም፡፡ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት አሳቢ ነን ባይ ምዕራባውያን በማዕቀብና በሥውር ሴራ አንቀው እናመጣለን ለሚሉት ‹‹ለውጥም›› ፍዝ ተመልካች አንሆንም፡፡ እነሱ ለዴሞክራሲ መቋቋምና ለሰብዓዊ መብት መከበር መድኃኒት አዛዥም ሆነ የምስክር ወረቀት ሰጪ መሆን እንደማይችሉ ባመሳቀሏቸው አገሮች መከራ ተምረናል፡፡ በዛሬው ጊዜ በምዕራብ ጣልቃ ገብነትና ሴራ ይቅርና ከውስጥ በመጣ አመፅና ግልበጣ ወደ ተሻለ ለውጥ ለመሻገር መሞከር ኪሳራ የበዛበት የሎተሪ ቁማር ውስጥ መግባት መሆኑን የብዙ አገሮች ልምድ መስክሮልናል፡፡ የእኛ ለስላሳ የተባለው የመሪ ለውጥ እንኳ በኋላ ስንት ጠንቀኛ ቀውሶች ተጎልጉለውበታል፡፡ ስለሆነም እንኳን በቅዋሜ ግፊት መሪ ሲለወጥ ይቅርና በምርጫ ውጤት መሪ ሲቀየር እንኳ ‹‹ምን ይከተል ይሆን?›› ብለን መሥጋታችን አይቀርም፡፡ በእኛ የደረሰው ትርምስ እነሱን እንዲጎበኛቸው አንሻም፡፡ የእኛ ፖለቲከኞች ለአገርና ለለውጥ ተባብረው መሥራታቸውን እንደምንሻው ሁሉ፣ የኤርትራም ገዥ ቡድንና ከእሱ ውጪ ያሉ ምሁራንም ሆኑ ተቃዋሚዎች አንድ ላይ እንዲተባበሩና ለአገራቸው እንዲበረቱ እንመኛለን፡፡ ተቀራርበውና ተደራድረው አሁን ያለውን ከበረሃ ትግል ጀምሮ እስካሁን ያለውን መሪ እንደ ነፃነት አንጋፋ ባለውለታ አክብረው ለቀውስ ባልተጋለጠ መልክ፣ ያወጣናል ያሉትን የዴሞክራሲ ጉዞ በተመጠነ ደረጃ ቢጀምሩ እንኳ እኔ ተመስገን የምል ይመስለኛል፡፡

ለእኛም ለእነሱም በዴሞክራሲ ጉዞ ውስጥ ስለመሆን አለመሆናችን ወሳኞቹ መስካሪዎቻችን ሕዝቦቻችን ናቸው፡፡ የየጉዟችንን ሥልቶች ሕዝቦቻችን እሰይ ብለው ካፀደቁትና ከተመሙበት የውጭ ኃይሎች ሚዛን ትርፍ ነገር ነው፡፡ ዛሬ ያለው ዓለማዊ ሁኔታ ይህንን ያህል ድረስ፣ አንዳችን ለሌላችን እንድንሳሳና እንድንጠነቀቅ ግድ ይለናል፡፡ ዝምድናና ህልውናችን እጅጉን እንደሚያፈላልገን ሁሉ፣ ፍትሐዊ መጠቃቀምን ውሉ ያደረገ መተሳሳብ ዝምድናችንን እንደሚያዘልቅና እንደሚያጠናክር ከገባን፣ ቀሪው ሥራ ዕዳው ገብስ ነው፡፡ የፕሮፌሰር ተከሰተ ነጋሽን ግድርድር አልባ ሀቀኝነት አነሰም በዛ ለመቀበል ደፍረን፣ ለሁለታችንም አገሮችና ሕዝቦች የጋራ ሕይወት፣ ዕድገትና ጥንካሬ አዛላቂ የሆነውን የተራክቦ ቅንብር በጋራ ምሁራኖቻችን አስጠንቶ ለየመንግሥታቶቻችን ማቅረብና የሚሆነውን እንደሚሆን ማድረግ ነው፡፡

በእርግጥም መንግሥቶቻችንና ዘመዳሞቹ ሕዝቦቻችን በጋራ የፈቀዱት ይሆናል! በሁለቱም አገሮቻችን የኢኮኖሚ መነቃቃትና ልማት የሚያረብብበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ተስፋ አደርጋለሁ!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...