Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በታሸገ ውኃ ላይ ኤክሳይስ ታክስ መጣል የለበትም›› ጌትነት በላይ (ኢንጂነር)፣ የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ፣ የለስላሳ መጠጥ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪዎች ኢንዱስትሪ ማኅበር ቦርድ ፕሬዚዳንት

የተፈጥሮ ውኃን በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊነት ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ አላቂ ሀብት ነው ተብሎ የሚታመነውን ውኃ በአግባቡና በቁጠባ መጠቀም ካልተቻለ ወደፊት እጥረት ይፈጠራል የሚል ሥጋትም አለ፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የውኃ ሀብት አላት ቢባልም፣ በአግባቡ መጠቀም ካልተቻለ የችግሩ ሰላባ ትሆናለች የሚሉ ምልከታዎች እየተንፀባረቁ ነው፡፡ በከፍተኛ ደረጃ ውኃን ዋነኛ ግብዓት አድርገው የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች የውኃ እጥረት የሚያጋጥማቸው ወቅት አለ፡፡ ይህ ጉዳይ ዝም ከተባለና ውኃን ቆጥቦ በመጠቀም በጋራም ሆነ በግል መሥራት ካልተቻለ፣ እ.ኤ.አ. በ2030 የውኃ እጥረት ሊያጋጥም ይችላል የሚል በጥናት ላይ የተመሠረተ ትንታኔ ይቀርባል፡፡ ይህ ጉዳይ ኢትዮጵያንም የሚመለከት በመሆኑ ውኃን ዋነኛ ግብዓት አድርገው የሚጠቀሙ እንደ የታሸጉ ውኃ አምራቾች፣ የለስላሳ መጠጥ አምራቾች፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪዎች፣ የቢራ አምራቾች፣ የአልኮልና የወይን አምራቾች ከውኃ እጥረት፣ ብክነትና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው በማመን አንድ ኅብረት እስከ መፍጠር ደርሰዋል፡፡ ይህ ኅብረት ውኃን በአግባቡ ለመጠቀም ከተለያ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሥራት ሥጋቱን ለመቀነስ እንዲቻል ይሠራል ተብሏል፡፡ ባለፈው ሳምንት የተመሠረተውን ኅብረት በመፍጠር ዋነኛ ድርሻ የነበረው ኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ፣ የለስላሳ መጠጥ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪዎች ኢንዱስትሪ አምራቾች ማኅበር ተጠቃሽ ነው፡፡ ዳዊት ታዬ የታሸገ ውኃ ምርትን ሥጋት እየሆነ ከመጣው ውኃ እጥረት፣ እንዲሁም የማኅበሩን እንቅስቃሴ በተመለከተ የማኅበሩን ቦርድ ፕሬዚዳንት ጌትነት በላይ (ኢንጂነር) አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበራችሁ በአብዛኛው የታሸገ ውኃ አምራቾችን በአባልነት ይዞ የተቋቋመ ነው፡፡ አጠቃላይ የሥራ ክንውኑ እንዴት ይታያል?

ኢንጂነር ጌትነት፡- በአሁኑ ወቅት የታሸገ ውኃ አምራቾች ቁጥር ከ106 በላይ ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከ86 በላይ የሚሆኑ አባሎቻችን ናቸው፡፡ ማኅበራችን በዘርፉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን እየሠራ ነው፡፡ ይህንንም በተግባር እየፈጸምን ነው ብለን እናምናለን፡፡ ለምሳሌ በእስራኤል አገር ማኅበራት ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው፡፡ የተለያዩ የፖሊሲ ጉዳዮች ሲቀረፁ ማኅበራት ሳይሳተፉበትና ሳያዩት አይፀድቅም፡፡ የእኛም ማኅበር ልክ በእስራኤል እንደሚገኙት ማኅበራት ፖሊሲ ውስጥ ገብቶ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆንና መንግሥትንም ሆነ አምራቹን በማገዝ መሥራት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ጠንካራ ቦርድ አለን ብለንም እናምናለን፡፡ እንደ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ካሉ መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ፡፡ እነሱ እንዲያውም ተፈታተኑን እያሉ ነው፡፡ እኛም መስተካከል ይገባዋል በምንላቸው ጉዳዮች ላይ የተጠና ነገር አቅርበን እንፈታተናለን፡፡  

ሪፖርተር፡- በፖሊሲ ቀረፃ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ጭምር ነው የምንሠራው የምትሉት እንዴት ነው? ከዚህ ዕሳቤ አንፃር መሆን አለበት ብላችሁ ያመናችሁበትን ነገር ወደ ተግባር ለመለወጥ ምን ያህል ሠርታችሁበታል? እንደተባለው መንግሥትን በመፈተን የሠራችሁት ሥራ ምንድነው? እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችል ነገር አለ?

ኢንጂነር ጌትነት፡- አንድ፣ ሁለት ምሳሌ ልጠቅስልህ እችላለሁ፡፡ ከዚህ ቀደም የታሸጉ የውኃ ምርቶች ክዳን ላይ የፕላስቲክ መሸፈኛ ይደረግ ነበር፡፡ አሁን እኛ ባቀረብነው ሐሳብ መሠረት በመንግሥት ደረጃ ታምኖበት እንዲቀር ማድረጋችን አንዱ ነው፡፡ ይህ የፕላስቲክ መሸፈኛ አካባቢን ይበክል ነበር፡፡ እኛም የሚያስከትለውን ብክለት በመመልከትና የውጭ አገር ተሞክሮዎችን በመውሰድ በመንግሥት ደረጃ እንዲታይ አድርገን፣ ይህንን መሸፈኛ አምራቾች እንዳይጠቀሙበት አድርገናል፡፡ ይህም ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር ሆነን ተፅዕኖ ፈጥረን እንዲቀርና እንዲፀድቅ ያደረግነው ነው፡፡ ውሳኔው ሕጋዊ እንዲሆንም ከሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ይህንን ሽፋን አምራቾች እንዳይጠቀሙ የሚያመለክት ትዕዛዝ እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ ሌላ ምሳሌ ካስፈለገ ደግሞ ከኤክሳይስ ታክስ ጋር ተያይዞ የሠራነው ነው፡፡ ይህም የኤክሳይስ ታክስ አዋጁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሊፀድቅ ሲል በውኃ ላይ የተጣለው ኤክሳይስ ታክስ አግባብ አለመሆኑን በመጥቀስ አዋጁ ተሻሽሎ እንዲቀረፅ አድርገናል፡፡ ምክንያቱም ውኃ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነው፣ መሠረታዊ ነው፡፡ እንዴት ኤክሳይስ ታክስ ትጥሉበታላችሁ ብለን በተወሰነ ደረጃ የታክስ መጠኑን አስቀንሰናል፡፡ አሁንም በዚህ ኤክሳይስ ታክስ ጉዳይ ገና ሥራ ይቀረናል፡፡ ይህንንም ዳር ለማድረስ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ለኤክሳይስ ታክስ ቀሪ ሥራ አለን የምትሉት ምንድነው?

ኢንጂነር ጌትነት፡- በታሸገ ውኃ ላይ የሚጣለው ኤክሳይስ ታክስ ዜሮ ፐርሰንት መሆን አለበት እንላለን፡፡ ምክንያቱም ውኃ ቅንጦት አይደለም፡፡ መንግሥት በገንዘብ ሚኒስቴር ያጠኑ ሰዎች አካባቢ ስለምታቆሽሹ የሚል መከራከሪያ ይቀርብበት ነበር፡፡ አሁን ግን ይህ አመለካከት እየተቀየረ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን በየአካባቢው ብትሄድ አንድ ጥቅም ላይ የዋለ የፕላስቲከ መያዣ አታይም፡፡ መያዣውን በመሰብሰብ ተመልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በተሠራው ሥራ እየመጣ ያለ ለውጥ ነው፡፡ የሥራ ዕድልም ፈጥሯል፡፡ እኛ ትምህርት እንሰጣለን፣ ድጋፍ እናደርግላቸዋለን፡፡ አሁን የሚጣል ነገር የለም፡፡ ይህ ከአካባቢ ጥበቃ ጋር የምንሠራው ነው፡፡ የውኃ ሀብት ጥበቃ ማለት አንዱ ከአካባቢ ላይ መሥራት ነው፡፡ ማኅበራዊ ገጽታን ወይም ደግሞ ማኅበረሰቡን መደገፍ ነው፡፡ ስለዚህ እኛ በተለይ በአካባቢ ጥበቃ ላይ ስንሠራ፣ መንግሥትም ታክሱን ዜሮ ያደርጋል ወደሚል አቅጣጫ እንዲሄድ በዚህ ላይ እየሠራ ነው፡፡ ስለዚህ በፈጠርነው ተፅዕኖ የኤክሳይስ ታክስ ከአሥር በመቶ ወደ አምስት በመቶ እንዲወርድ ማድረጋችን አንድ ጉዳይ ሆኖ፣ አሁን ደግሞ ይህ ዜሮ ፐርሰንት እንዲሆን እየሠራን ነው፡፡ እንዲህ ካለው በተጨባጭ በሚታይ ተግባር ማኅበሩ ተፅዕኖ ፈጣሪነቱን እያሳየ ነው፡፡ ወደፊትም እንዲህ ባለው ሥራው ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከታሸገ ውኃ ምርት ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተግዳሮቶች አሉ ይባላል፡፡ በተለይ አንዱ የውኃ እጥረት ሊኖር ይችላል የሚል ሥጋት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የታሸገ ውኃ እጅግ ውድ ነው ይባላልና የታሸገ ውኃ ለምን ውድ ሆነ?

ኢንጂነር ጌትነት፡- ዘርፉ ብዙ ተግዳሮቶች አሉበት፡፡ አንደኛው የዘርፉ ችግር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ ለምርቱ የሚያስፈልጉት ጥሬ ዕቃዎች ከውጭ የሚገቡ ናቸው፡፡ ኪት፣ ላስቲኩና አጠቃላይ የውኃ ማሸጊያዎቹ በሙሉ ከውጭ የሚመጡ ናቸው፡፡ እዚህ ላይ ሁሉም ሊገነዘብ የሚገባው ውኃ ተወደደ የሚያስብለውም ፓኬጁ ነው፡፡ ውኃውን ነፃ ነው ብለህ ብትቆጥረው መያዣው ውድ መሆኑ ዋጋው ከፍ እንዲል ያደርገዋል፡፡ መያዣውን ውድ የሚያደርገው ደግሞ ጥሬ ዕቃውን ከግዳጅ ምርት ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምር ደግሞ የመያዣ ምርት ዋጋ አብሮ ይጨመራል፡፡ በዚህ ላይ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አለ፡፡ በዚያ ሳቢያ የታሸገ ውኃ ምርት እጥረትም ያጋጥማል፡፡ ምክንያቱም ውኃ ቢኖርህም ማሸጊያው ከሌለ ምርቱን አምርተህ ማውጣት አትችልም፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ለዚህ ዘርፍ ቅድሚያ መስጠት አለበት የሚል እምነት ያለን፡፡ ውኃ መሠረታዊ ከምንላቸቸው የሰው ልጅ ፍላጎቶች አንዱ ነው፡፡ ሌላው የዘርፉ ችግር ከኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ መብራት ሲቆራረጥ ምርት ማስተጓጉል ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር ይበላሽብናል፡፡ ለውኃው ማሸጊያ የምንጠቀምባቸው ጥሬ ዕቃዎች ፕላስቲክ ነክ ስለሆኑ፣ መብራት ሲቋረጥ ብዙ ምርት ከጥቅም ውጪ ይሆናል፡፡ ይህንን ለማካካስ ደግሞ የሚወጣው ወጪ ብዙ ነው፡፡ ሦስተኛው ደግሞ ውኃ ላይ ግንዛቤ ካለመሠራቱ ጋር ተያይዞ ያለው ክፍተት ነው፡፡ መንግሥት በንፁህ ውኃ አጠቃቀም ላይ ግንዛቤ መሥራት አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ብዙ ሰው ንፁህ ያልሆነ ውኃ ይጠጣል፣ ነገ ኩላሊት ይታመማል፣ በተያያዥ በሽታ ይያዛል፡፡ ይህም በመሆኑ ለመድኃኒት የሚያወጣውን ወጪ ከፍተኛ ያደርገዋል፡፡ መንግሥት ግንዛቤ ፈጥሮ ሁሉም ነው ውኃ መጣጣት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- እርግጥ ነው ሁሉም ሰው ንፁህ ውኃ መጠጣት አለበት፡፡ አንዳንዶች ወይም ጥቂቶች አንድ ሊትር ውኃ ምናልባት አሥር ብር ከፍለው ሊጠጡ ይችላሉ፡፡ አብዛኛው የኅበረተሰብ ክፍል ግን አንድ ሊትር ውኃ በአሥር ብር ገዝቶ መጠቀም አይችልም፡፡ ይህ በመሆኑ የታሸገ ውኃ የሚጠቀሙት ጥቂቶች ናቸው፡፡ በአጭሩ የታሸገ ውኃ በጣም ውድ ነው፡፡ እርግጥ ለምርቱ ማሸጊያ የጥሬ ቃ ከውጭ የሚገባ ስለሆነ ዋጋውን በማስወደዱ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን የሚሸጥበት ዋጋ የተጋነነ ነው ብለው የሚሞግቱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል አንድ ወቅት ዋጋ ቀንሳችሁ መልሳችሁ የመጨመራችሁስ ምክንያት ምንድነው?

ኢንጂነር ጌትነት፡- ልክ ነህ፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ የማሸጊያ ዋጋ ውድ ስለሆነ ነው የውኃ ዋጋ ውድ ነው የሚል አመለካከት እንዲኖር ደረገው፡፡ ከማሸጊያ ዕቃ መወደድ ባሻገር ዕቃዎች ሲገቡ ደግሞ ለዕቃዎች የሚከፈሉ የተለያዩ ታክሶች አሉ፡፡ ይህም ዋጋው ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ መንግሥት ታክሶችን ቢያነሳ አምራቾች በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ኤክሳይስ ታክስ እኮ ከኅብረተሰቡ የምንሰበስበው ከሽያጭ 10 በመቶ ነው፡፡ ይህ በጣም ብዙ ነው፡፡ ይህ ተነሳ ማለት የዋጋ ቅናሽ ይኖራል ማለት ነው፡፡ አዎ እንደጠቀስከው ዋጋ የቀነስንባቸው ወቅቶች አሉ፡፡  የውኃ የመሸጫ ዋጋን ቀንሰን ነበር፡፡ ይህ ሲሆን የውኃ ክዳን ላይ ይታይ የነበረው የማሸጊያ ፕላስቲክ ወይም ልባስ እንዲቀር ሲደረግ ዋጋ ቀንሰናል፡፡ ኤክሳይስ ታክስ ሲቀንስም ዋጋ ቀንሰናል፡፡ አሁን ግን የማሸጊያ ዕቃዎች ዋጋ ጨመረ፣ የዶላር ምንዛሪም ጨመረ፣ የነዳጅ ዋጋም ጨመረ፣ ስለዚህ የታሸገ ውኃ መሸጫ ላይም የዋጋ ለውጥ ተደረገ፡፡ ስለዚህ መንግሥት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን እያየ ታክሱንም መቀነስ አለበት፡፡ እንደ ዘይትና እንደ ሌሎች ከውጭ የሚመጡ ምርቶች ላይ እንደሚደርገው ውኃ ላይም የታክስ ቅናሽ ማድረግ አለበት፡፡ ቢያንስ ታክሱን ቢያነሳ ወይም ቢቀንሰው እኛ በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ የምንችልበት ዕድል አለ፡፡ አንድ ጥናት እንዳመለከተው በኢትዮጵያ በቀን የሚጠጣው የታሸገ ውኃ መጠን ሰባት ሚሊዮን ሊትር አካባቢ ነው፡፡ 110 ሚሊዮን ሕዝብ ያለበት አገር ይህ ይሸጣል የተባለው መጠን በጣም ትንሽ ነው፡፡ ነገር ግን አሁን ምርት ላይ ያሉ ውኃ ፋብሪካዎች የቀን የማምረት አቅማቸው 30 ሚሊዮን ሊትር ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው አሁን ባለን አቅም ቢያንስ በቀን 15 ሚሊዮን ሕዝብ ሁለት ሊትር መጠጣት ይችላል፡፡ የምርት ችግር የለም፡፡ ነገር ግን አሁን የዋጋ ጦርነት ተጀምሯል፡፡ እንዲያውም በአብዛኛው ተከስሮ ነው የሚሸጠው፡፡ የታሸገ ውኃ አዋጭ እየሆነ ነው ማለት አይቻልም ኪሳራ ላይ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- እርግጥ ኪሳራ ላይ ናቸው? ለምን? የዋጋ ጦርነቱንስ ምን አመጣው?

ኢንጂነር ጌትነት፡- ምክንያቱም አሁን ገበያው ውስጥ የማይንቀሳቀስ ኃይል ስላለና አምራቹ ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል ስላለበት ቀንሶ ይሸጣል፡፡ ለዚህም ነው ዘርፉን መንግሥት ማበረታታት አለበት የምንለው፡፡ መንግሥት ታክስ ቢቀንስለና ሌላም ማበረታቻ ቢያደርግ፣ በተለይ ከውጭ ምንዛሪ ጋር ተያይዞ ያለባቸው ችግር እንዲፈታ ቢደረግ ዋጋው ተመጣጣኝ ይሆናል፣ አምራቹም አይጎዳም፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያሉት የታሸገ ውኃ አምራቾች ምርት ከበቂ በላይ ነው ማለት ይቻላል? ወይም ከፍላጎት በላይ ሊያመርቱ የሚችሉ የውኃ ማምረቻዎች አሉ ማለት ነው? ይህ ከሆነ ገበያው ጤናማ ነው ማለት ይቻላል?

ኢንጂነር ጌትነት፡- አዎ፡፡ አሁን ያለው ፍላጎት ቢጨምር አምራቾቹ መስመር ዘርግተው ምርታቸውን ማሳደግ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ ፍላጎት እንዳይጨምር ካደረገው አንዱ በውኃ ላይ በቂ ግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ አለመሠራቱ ነው፡፡ ኅብረተሰቡ አንድ ሊትር ውኃ አሥር ብር መግዛት ሳይችል ቀርቶ ንፁህ ውኃ መጠቀም ባለመቻሉ ምክንያት ለሚያገኘው በሽታ ከፍተኛ ወጪ ያወጣል፡፡ ይህ መታወቅ አለበት፡፡ ውኃ እንደ ሌላው ምግብ መገዛት አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ሁሉም አካላት የገንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት አለባቸው፡፡    

ሪፖርተር፡- አሁን ካለው ፍላጎት በላይ የታሸገ የውኃ ምርት ካለ ምርቱን ወደ ውጭ ለመላክ ተሞክሯል? አንድ ወቅት የታሸገ ውኃ ወደ ውጭ መላክ ተጀምሮ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡

ኢንጂነር ጌትነት፡- አዎ ተጀምሮ ነበር፡፡ ወደ ጂቡቲ፣ ሶማሌላንድና የመሳሰሉ አገሮች መላክ ተጀምሮ ነበር፡፡ ጂቡቲ እኮ ከፈረንሣይም ታስመጣለች፡፡ ከእኛ ብትወስድ ይቀርባታል፡፡ ነገር ግን ችግር አለ፡፡ አሁን የኢትዮጵያ መንግሥት ይፈቅዳል፡፡ ነገር ግን እዚያ ያለውን ኤጀንት መያዣ ይጠይቃል፡፡ አሁን ማኅበራት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን እዚያ ያለውን ኤጀንት ማለፍ እንችላለን ወይ የሚለውን በቀጣይ የምንሠራበት ይሆናል፡፡ ውኃችንም ንፁህ ስለሆነ የሚፈለግ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ማኅበራችሁ ዋነኛ ተዋንያን የሆነበትና ከውኃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ አንድ ኅብረት ሳምንት ፈጥራችኋል፡፡ ውኃን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጠቀሙ የመጠጥ ኢንዱስትሪዎች ኅብረት ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነትም በማድረግ ምሥረታው ተካሂዷል፡፡ ለዚህም አንዱ መነሻችሁ የውኃ እጥረት ያጋጥማል የሚል ሥጋት ነው፡፡ ሥጋቱ እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር ጌትነት፡- የዓለማችን ሁለት ሦስተኛው ውኃ ነው፡፡ ግን ለመጠጥ ጥቅም ላይ የሚውለው 0.002 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ይህንን ውኃ በሚገባ ካልተጠቀምንበት ያልቃል፡፡ ውኃ ከጉድጓድ ነው የምንወስደው፡፡ ከአገራችን ሁኔታ አንፃርም ብዙዎቹ የውኃ አምራቾች በመጋቢትና ሚያዝያ ወር የውኃ እጥረት እየገጠማቸው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ምልክት ነው፡፡ በዓለም ደረጃም ይህ ሥጋት አለ፡፡ ስለዚህ እጥረቱ እንዳይባባስ ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል፣ ውኃን መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ውኃን መልሰን መጠቀም አለብን፡፡ ስለዚህ ይህንን ሥጋት ከግምት በማስገባት ወኃን በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ጋር በዚህ ላይ ለመሥራት ኅብረቱ ተፈጥሯል፡፡ ተነሳሽነቱ የዓለም ባንክ ነው ያመጣው፡፡ ምንም እንኳን ውኃ ቢኖራችሁም፣ ውስን ሀብት ነው፣ ፍላጎት ደግሞ እየጨመረ ስለሚሄድ እ.ኤ.አ. 2030 ላይ ትቸገራላችሁ ነው የሚሉት፡፡ P4ጂ (Partnership for Green Growth and Global Goals 2030) ከሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር የሚሠራ ነው፡፡ አረንጓዴ ኢኮኖሚ እናድርግ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ዓላማ እንፍጠር ብለው ተነሳሽነቱን አመጡ፡፡ ይህ ጉዳይ በዋናነት እኛን ስለሚመለከት እኛን እንደ ዋና አስተባባሪ አድርገው እንዲህ ዓይነቱ ጥምረት ተፈጠረ፡፡ ይህንን በዚህ እንቅስቃሴ ውስጥ የዓለም ባንክ፣ ወተር ኤይድና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ገብተውበት አንድ ላይ እየሠራን ነው፡፡ ዛሬም ፋውንዴሽኑን ፈጥረን በአምራቹ ጀመርነው እንጂ ይህ የውኃ ጉዳይ ወደ ቤታችን በመምጣት ያንኳኳል፡፡ አሁን ቤታችን እጃችንን ስንታጠብ ውኃውን ትደፋዋለህ፡፡ ይህንን የምንደፋውን ለመፀዳጃ ቤት መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ ስለዚህ አብዛኛው ውኃ ይባክናል፡፡ ስለዚህ ከጥቅም ውጪ የሚሆነውን ውኃ መልሰን መጠቀም አለብን፡፡ መቆጠብ አለብን፡፡ ውኃን በጥንቃቄ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለማድረግ በጋራ መሥራት ይገባል፡፡   

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት በተለይ እንደ እናንተ ሉ የውኃ አምራቾች ውኃ ለማግኘት ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ ጉድጓድ መቆፈር ግድ እየሆነባቸው ነው እየተባለ ነው፡፡ አሁን በተወሰነ ሜትር ርቀት ውኃ ማግኘት እየከበደ መሆኑም ተገልጿል፡፡ ይህ ደግሞ ውኃ ለማግኘት የሚጠይቀውን ወጪ ይጨምራል የሚል ትንታኔም ይሰጥበታል፡፡ በእርግጥ እንዲህ ለውን ችግር እየተመለከታችሁ ነው?

ኢንጂነር ጌትነት፡- እሱን እኮ ነው የምልህ፡፡ ዝናቡ ሄዶ ሄዶ ወደ ሚያዝያ አካባቢ ሁሉም ውኃ አምራቾች የሚያነሱት ነገር አለ፡፡ የውኃ እጥረት ያጋጥመናል ይላሉ፡፡ ስለዚህ ውኃችንን በትክክል መጠቀም አለብን፡፡ ይህን ለመጠቀም ደግሞ እነዚህን ሦስት ስትራቴጂዎች መጠቀም አለብን፡፡ መቆጠብ፣ መልሶ መጠቀምና እንዳይባክን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ውኃን ዋነኛ ግብዓት አድርገው የሚጠቀሙ የውኃ አምራቾች፣ የፍራፍሬ ጭማቂ አምራቾች፣ የቢራና የሌሎች መጠጦች አምራቾች በውኃ አጠቃቀም ላይ የተፈጠረው ኅብረት ጠቀሜታ እንዴት ይገለጻል?

ኢንጂነር ጌትነት፡- ኅብረቱ እነዚህን አምራቾች ፈንድ እያደረጉ እንዲሠሩ ማድረግ ነው፡፡ ውኃን መልሶ ለመጠቀም መሠረተ ልማት ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ የዓለም ባንክና 4ጂ ፈንድ ያደርጋሉ፡፡ በጋራ እንሠራለን፣ እኛ ደግሞ እናስፈጽማለን፡፡፡ በዚህም አምራቾች ውኃ ቆጥበው እንዲጠቀሙ ግንዛቤ እንፈጥራለን፡፡ ውኃ እንዳይባክን ምን እናድርግ? የባከነ ውኃ ካለ ደግሞ ያንን መልሰን እንዴት እንጠቀም? በሚለው ላይ መሥራት ነው፡፡ ውኃን መልሶ መጠቀም ደግሞ የጉድጓድ ውኃ እንዳይቀንስ ያደርጋል፡፡ ከወዲሁ እ.ኤ.አ. 2030ን ማሰብ አለብን፡፡ ከ2030 በኋላ ችግር ሊገጥመን ስለሚችል ከአሁኑ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም በጥናት ላይ ተመሥርተን እንሠራበታለን፡፡ ኅብረቱ የራሱ ቦርድ ይኖረዋል፣ ጽሕፈት ቤት ይኖረዋል፣ ወደፊት ሁሉንም የመጠጥ ኢንዱስትሪ የያዘ ማኅበርም ወደ መመሥረት የሚሄድም ይሆናል፡፡ በጋራ በምንሠራባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ እንድንሠራ ያደርገናል፡፡  

ሪፖርተር፡- የታሸገ ውኃ ዋጋን የተመለከተ ሌላ ጥያቄ ላስታውስዎና ኤክሳይስ ታክሱን እንዳሰባችሁት ዜሮ ፐርሰንት ቢሆን ዋጋ ትቀንሳላችሁ?

ኢንጂነር ጌትነት፡- አዎ፡፡ ከዚህም ቀደም እኮ ቀንሰናል፡፡ ኤክሳይስ ታክስ ወደ አሥር በመቶ ሲወርድ ከ58 እስከ 60 ብር ሸይጥ የነበረ የአንድ ደርዘን የውኃ ማከፋፈያ ዋጋ ወደ 52 ብር ወርዶ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እነዚህ 106 የታሸገ ውኃ አምራቾች በቀን ምን ያህል ሊትር ውኃ ያመርታሉ?

ኢንጂነር ጌትነት፡- በቀን 30 ሚሊዮን ሊትር የማምረት አቅም አላቸው፡፡ አንዳንዶቹ ግን በተለያየ ምክንያት ከገበያ የወጡ አሉ፡፡ አሁን ግን ፍላጎቱን መሠረት አድርገው የሚያመርቱ በመሆናቸው በቀን ወደ ሰባት ሚሊዮን ሊትር ሊያመርቱ ይችላል፡፡ ገበያው ከመጣም ከፍ ሊል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን ያሉት አምራቾች በቀን 30 ሚሊዮን ሊትር የማምረት አቅም አላቸው እየተባለ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የሚያመርቱት ከአቅማቸው እጅግ ወርደው ከሆነ ለምን ተጨማሪ የውኃ ማምረቻዎች ይከፈታሉ? አሁንም እኮ ገበያ ውስጥ ለመግባት የሚፈልጉ አሉ፡፡ ከአቅም በላይ ምርት ካለ እዚህ ዘርፍ ውስጥ ለምን ይገባል?

ኢንጂነር ጌትነት፡- ካለማወቅ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንድ አጥኚዎች ዘርፉ አትራፊ ነው ብለው ስለሚያቀርቡ ሊሆን ይችላል፡፡ አሁን የውኃ ዘርፍ በቂ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁን የውኃ ማምረቻ ከመክፈት ሌላ የቢዝነስ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ቢደርጉ ይሻላል፡፡ ውኃ አትራፊ ነው ብለው ስህተት ሠርተናል ያሉ አሉ፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት 17 ያህል ገብተው ከገበያው ወጥተዋል፡፡ ስለዚህ ያበቃ ቢዝነስ ውስጥ መግባት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ አንዳንድ አጥኚዎች የታሸገ ውኃ ቢዝነስ ገንዘብ ማተም ነው ይሏቸዋል፡፡ ግን ውሸት ነው፡፡ ውኃ ዝም ብለህ አውጥተህ የምትሸጠው አይደለም፡፡ ጥሬ ዕቃው ከውጭ ነው የሚመጣው፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደ እናንተ ያሉ በተለያዩ ዘርፎች ላይ የተደራጁ ማኅበራት ሚና ምን መሆን አለበት ብለው ያምናሉ? ከመንግሥት ጋር ሊኖራቸው የሚችለው ግንኙነትስ?

ኢንጂነር ጌትነት፡- መንግሥት እያንዳንዱን አምራች ከሚያገኝ ከማኅበራት ጋር መሥራት አለበት፡፡ 106 ድርጅቶችን ከማግኘት ከማኅበር ቦርድ አባላት ጋር ብታነጋግር ውጤት ይኖረዋል፡፡ ለፖሊሲ ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናሉ፡፡ የፖሊሲ ተፅዕኖ ማለት በአሉታዊ ሳይሆን በአዎንታዊ ተፅዕኖ ማድረግ ነው፡፡ አሁን አንዳንድ ፖሊሲዎች ለመረዳት የሚያዳግቱ ናቸው፡፡ ይወጣሉ ግን ችግር ይኖራቸዋል፡፡ ወይም የተሳሳቱ ይሆናሉ፡፡ እንዲህ ከሚሆን ከሚመለከታቸው ማኅበራት ሐሳብ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ይህ ማለት ግን የእኛን ብቻ ይውሰዱ ማለት አይደለም፡፡ የእኛን ግብዓት በመውሰድ መንግሥት የተሻለ ፖሊሲና ስትራቴጂ ካወጣ ኢኮኖሚው ያድጋል፣ አገር ታድጋለች፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከማኅበራት ጋር እጅ ለእጅ ሆኖ መሥራት አለበት፡፡ ምክንያቱም ማኅበራት የሚሠሩት የመንግሥትን ጥቅም ያስጠብቃል፣ የአምራቹንም ጥቅም ያስከብራል፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁን ካለው ከፍተኛ የዋጋ ንረት ጋር በተያያዘ ገበያ ላይ የገጠማችሁ ችግር አለ? በተለይ የዋጋ ንረቱ ብዙውን የኅብረተሰብ ክፍል እየተፈታተነ ነው፡፡ የመግዛት አቅምም ተደክሟል፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ኅብረተሰቡ መግዛት የሚፈልገው በጣም መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን ነው፡፡ የታሸገ ውኃ ለመግዛት ላይገፋፋ ይችላልና ከዚህ አንፃር የዋጋ ንረቱ በእናንተ ገበያ ላይ ተፅዕኖ አላሳደረገም?

ኢንጂነር ጌትነት፡- ተፅዕኖው አለ፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ብዙ ሰዎች የታሸገ ውኃ ይጠጣሉ፡፡  ኢኮኖሚውን የተረጋጋ ማድረግም ይጠይቃል፡፡ ዶላር ሲጨምር ሁሉ ነገር ይጨምራል፡፡ ከዶላር ጋር ያልተያዙ ምርቶች ላይ ሳይቀር ነጋዴዎች ዝም ብለው ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ ስለዚህ በኢኮኖሚው ላይ በመሥራት ገበያውን ማረጋጋት ወሳኝ ነው፡፡ ለዚህ እኮ ነው የዋጋ ንረቱ አሁን ማስተናገድ አይቻልም የምንለው፡፡ እኛ የዋጋ ንረት ባለበት ወቅት ዋጋ ብንጨምር የምናገኘው ትርፍ የለም፡፡ ግን ቁጥጥር ቢደረግና በተለይ መሠረታዊ በሚባሉ ምርቶች ላይ ታክስ ቢቀንስ ዋጋ አይጨምርም፡፡ ኅብረተሰቡም በተመጣጣኝ ዋጋ ይገዛል፡፡ መንግሥት ታክስ ሲጨምር ግን አምራቹም ይጨምራል፡፡ ይህ ሲሆን ሸማቹ ለመግዛት ይቸገራል፡፡

ሪፖርተር፡- በእናንተ ዘርፍ ይህ ታይቷል?

ኢንጂነር ጌትነት፡- አዎ እሱንም ዓይተናል፡፡ በመሠረታዊ ምርቶች ላይ ያለው ጫናው ይቀንስ የምንለው ለዚህ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ጉራጌን በክላስተር ለመጨፍለቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚቃወም ጎጎት ፓርቲ አስታወቀ

ለጉራጌ ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበር እንደሚታገል የሚናገረው አዲሱ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...

‹‹ኢኮኖሚው ላይ የሚታዩ ውጫዊ ጫናዎችን ለመቀልበስ የፖሊሲ ሪፎርሞች ያስፈልጋሉ›› ዓለም ባንክ

በዓለም ደረጃ ከተፈጠረው የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ፣ በኢትዮጵያ ውጫዊ...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...