Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከፍተኛ ውኃ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች በውኃ ዘርፍ አብሮ ለሥራት ጥምረት መሠረቱ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፍተኛ ውኃ የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ከውኃ እጥረት ጋር በተያያዘ ሊያጋጥሟቸው የሚችሉ ችግሮችን ለመከላከልና በዘርፉ በጋራ ለመሥራት ጥምረት በይፋ መሠረቱ፡፡

ጥምረቱን የመሠረቱት ከፍተኛ ውኃ የሚጠቀሙት የታሸገ ውኃ፣ የለስላሳ መጠጥ፣ የጭማቂ፣ የቢራና የሌሎች የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች ናቸው፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በይፋ የተመሠረተው ጥምረት፣ በውኃና ወኃ ነክ ምርት ላይ የተሰማሩ ፋብሪካዎች የፋብሪካዎቹ ዋና ጥሬ የሆነውን ውኃ በአግባቡ የመጠቀም አስፈላጊነት ላይ በመግባባት ለዚሁ ጉዳይ የሚሠራ ጥምረት አቋቁመዋል፡፡

‹‹በተደራጀ ጥረት ውኃን መቆጠብ፣ ብክለትን መቆጣጠር›› በሚል መሪ ቃል የተመሠረተው ጥምረት፣ ከ100 በላይ የዘርፉ አምራቾች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ እንዲሁም በዘርፉ በምርምርና ድጋፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችና ግለሰቦች በተሳተፉበት ጥምረቱን የሚመሩ የቦርድ አባላትም መርጧል፡፡

ጥምረቱ በኢንዱስትሪዎች ውኃ አጠቃቀም፣ ከኢንዱስትሪ በሚለቀቁ ፍሳሾች አወጋገድ፣ ከማኅበረሰቡ ጋር በሚኖር ግንኙነትና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ፕሮጀክቶች ቀርፆ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ከመንግሥት ጋርም በቅርበትና በቅንጅት ይሠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጥምረቱ እንዲፈጠር ካስገደዱ ምክንያቶች አንዱ አብዛኞቹ ፋብሪካዎች ውኃን የሚያገኙት ከከርሰ ምድር ወይም በቁፋሮ በመሆኑ አሁን ላይ እየታየ ያለው የውኃ እጥረት ወደፊት እየጎላ ስለሚሄድ ይህንን ሥጋት ከግምት በማስገባት በጋራ መሥራቱ ተገቢ በመሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ፣ የለስላሳ መጠጥ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪያዎች አምራቾች ኢንዱስትሪ ማኅበር ቦርድ ፕሬዚዳንት ኢንጂነር ጌትነት በላይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የውኃ አጠቃቀም ላይ በርትቶ መሥራት ካልተቻለ ወደፊት ችግር ሊገጥም ይችላል፡፡ ብዙ የውኃ አምራቾች መጋቢትና ሚያዝያ ላይ የውኃ እጥረት እያጋጠማቸው ስለሆነ ይህ ጉዳይ አሳሳቢ በመሆኑ በጥምረት መሥራቱ አዋጭ ነው፡፡

ፒ4ጂ ፓርትነርሺፕ ፎር ግሪን ግሮውዝ ኤንድ ዘ ግሎባል ጎልስ 2030 የሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት አገር ውስጥ ከሚገኙ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ውኃን አስመልክቶ በኢትዮጵያ በዓይነቱ የመጀመርያ የሆነ የአምራች ኢንዱስትሪ ትብብር ማዕቀፍ እንዲቋቋም እየሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ኢንጂነር ጌትነት፣ ጥምረቱ የተፈጥሮ ውኃን በግብዓትነት በሰፊው የሚጠቀሙ አምራች ኢንዱስትሪዎችን ያካተተ መሆኑንና በዋናነትም የታሸጉ ውኃ አምራቾች፣ የለስላሳ አምራቾች፣ አትክልትና ፍራፍሬ አቀነባባሪዎች፣ እንዲሁም የአልኮልና የዋይን የውኃን አምራቾችን የሚያጠቃልል ይሆናል ብለዋል፡፡

ጥምረቱን ለመፍጠር ከተዘጋጀው ሰነድ መረዳት እንደተቻለው፣ የማኅበረሰቡ ውኃ ፍጆታ ከማደጉ አኳያ ለውኃ ያለው ሽሚያ በዚያው ልክ እየጨመረ ስለሚሄድ ውኃን ከማስተዳደር አንፃር አቅርቦትን ከማሳደግ በተጨማሪ የውኃ ፍላጎትን መቆጣጠር ወይም በቁጠባና በኃላፊነት መጠቀም የግድ ነው፡፡  

በዚህ አሊያንስ ምሥረታ ላይ የተገኙት የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በርካታ ወንዞች ያሏት መሆኑን ገልጸው፣ አብኞቹም በተለያየ መጠን ውኃ የሚይዙና ጥቅም ላይ ለማዋል የሚመቹ ናቸው ብለዋል፡፡

ነገር ግን አገሪቷ ያላት የከርሰ ምድር ውኃ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ያለው እውነታ በመሆኑም ሕዝቡ ከከርሰ ምድርም ሆነ ከወንዞች ውኃ ሀብት እንዲጠቀም በቂና አካታች የውኃ አጠቃቀም አስተዳደር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የንግዱ ማኅበረሰብ ውኃን በኃላፊነት መጠቀም ወሳኝ ስለመሆኑም የገለጹት ሚኒስትሩ፣ የግሉ ዘርፍ በውኃ ጉዳይ ላይ መሰባሰቡ በመንግሥትም በበጎ የሚታይ እንደሆነና የንግዱ ማኅበረሰብ በራሱ በኩል ያለውን ኃላፊነት ከተወጣ መንግሥት የፖሊሲ፣ የአስተዳደርና የማበረታቻ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ስለመሆኑም አረጋግጠዋል፡፡

አያይዘውም ሚኒስቴራቸው የግሉ ዘርፍ በውኃ ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሳተፍ ማድረጉንና ይህ የግልና የመንግሥት ትብብር በውኃ ዘርፍ ላይ የተጋረጡትን ኢኮኖሚዊና አካባቢያዊ ፈተናዎች ለመመለስ እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ የጋራ ችግር የሆነውን የውኃ አጠቃቀም ፈተና ለመወጣት ኩባንያዎች ጥምረት መፍጠራቸው ለዘርፉ አዋጭ ስለመሆኑ በመግለጽ፣ ጥምረቱ እንደ ኢንተርፕራይዝ፣ እንደ አገልግሎት ሰጪና እንደ አካባቢ ሁኔታ ሊንቀሳቀስ ይችላል፣ ይህ መሆኑ የተለያዩ ፍላጎቶችን አመጣጥኖ ምላሽ ለመስጠት ያስችላልም ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጥምረቱ በአካባቢ ጥበቃ፣ በሥነ ምግባር እንዲሁም የበጎ ፈቃድ እሴትን በማጠናከር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ማረጋገጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር በበኩላቸው የተናገሩት፣ ለሕይወት ወሳኝ የሆነውን የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም እንዲህ ያሉ የቢዝነስ ተቋማት በጥምረት መመሥረት ከፍተኛ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ነው፡፡

በኢትዮጵያ የመጀመርያ በሚሆነው በዚህ ጥምረት ፋብሪካዎች ተደራጅተው መንቀሳቀሳቸውም ከውኃ ጋር የተያያዙ ግቦችን ለማሳካት መንገድ የሚከፍት መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

በጥምረቱ ምሥረታ ላይ የኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ አምራቾች ማኅበር በቦታው በክብር እንግድነት ለተገኙት ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዕውቅና ይገባቸዋል ብሎ ሽልማት አበርክቷል፡፡

ማኅበሩ ለሚኒስትሩ እንዲህ ባለው መድረክ ዕውቅና የሰጣቸው ስለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለውን እውነታና የኢትዮጵያ አቋም በዓለም አቀፍ መድረክ እንዲታወቅ ላበረከቱት ውጤታማ ሥራና ሁለተኛውን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በስኬት እንዲጠናቀቅ በማድረግ ለነበራቸው አስተዋጽኦ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ውኃ ተጠቃላች በመሆን ከሚጠቀሱት ውስጥ የታሸገ ውኃ አምራቾች በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ በዚህ ዘርፍ 106 ፋብሪካዎች አሉ፡፡ አትክልትና ፍራፍሬ ለማቀነባበር የሚሠሩ 33 ፋብሪካዎች፣ አሥር ብራንድ ፋብሪካዎች፣ 31 የአልኮል መጠጥ ፋብሪካዎች፣ አምስት ወይን አምራቾችና አምስት የለስላሳ መጠጥ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ በዚህ ሳምንት የተፈጠውም ጥምረት እነዚህን ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች