Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቀው የኑሮ ውድነት

በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እየተደረገ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ እንደ አገር ከገጠመን ችግር ጎን ለጎን ወቅታዊው የዋጋ ንረትም ሌላው ፈተናችን መሆን ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ዛሬ በአገር አቀፍ ደረጃ የገጠመን የዋጋ ንረት ከዚሁ ጦርነት ጋር የተያያዘም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ጦርነቱ ለዋጋ ንረቱ መባባስ አንድ ምክንያት ቢሆንም፣ ሌሎች በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አገር እንዳትረጋጋ መሀል ሆኖ ኢኮኖሚዊ ጦርነት በመክፈት የሕዝብን ምሬት ለመጨመር የሚደረጉ ሸፍጦችንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከሰሞኑ በመንግሥት ደረጃ እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች ወቅታዊ የዋጋ ንረቱን ሊያረጋጉ የሚችሉ ቢሆንም፣ ችግሩን ከሥሩ ለመንቀል ወይም ተፅዕኖውን ለመቀነስ አሁንም ብዙ መሠራት አለበት፡፡

ሆን ተብሎ የሚፈጸሙ ኢኮኖሚያዊ ሸፍጦችን መከላከል የኑሮ ውድነቱን ለማርገብ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ሰንኮፉን በመንቀል የተረጋጋ የገበያ ሥርዓት ለመፍጠር እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀምበት የሚገባም ነው፡፡

በብዙ ምክንያቶች የአገራችን የግብይት ሥርዓት በእጅጉ የተበለሻሸ ነው፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ ከኢኮኖሚው አንፃር አገር እያደሙ ያሉ ኢኮኖሚያዊ ሸፍጦችን ለመከላከል ከሚደረግ ወቅታዊ ጥረት ጎን ለጎን ሕገወጥ ተግባራት እንዳያንሠራራ፣ በኔትዎርክ የሚደረግ ዝርፊያ እንዲቆምና በረባው ባልረባው ምክንያት የዋጋ ግሽበትን የሚፈጥሩ ሕገወጥ ተግባራትን ሁሉ ለመቆጣጠር ጠንከር ያለ አሠራር መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ እየሰማን እንዳለነው የተወሰኑ ቡድኖች ገበያውን ተቆጣጥረው እንደፈለጉ በማሽከርከር ለዋጋ ንረት ምክንያት መሆናቸው ሲታወቅ፣ በመንግሥት የሚወሰደው ዕርምጃ ጊዜያዊ ሳይሆን ዘለቄታውንም ያሰበ መሆን አለበት፡፡ አሁን እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎች የመጨረሻ ግብ መሆንም አለባቸው፡፡

ለሕገወጥ ተግባራቱ መበራከት ጤናማ የገበያ ሥርዓት ያለመኖሩና የቁጥጥር ሥልቱ ደካማ መሆን ይጠቀሳሉ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሠራር በተለየ የመቆጣጠሪያ ሥልትን በመቅረፅ ከሕገወጥ ቡድኖች ቀድሞ መገኘትን ይጠይቃል፡፡

እንዲህ ያለውን አሠራር ለመዘርጋት ብርቱ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ላይ እየገነነ የመጣው የዋጋ ንረት ከዚህም በላይ እንዳይሻገርና በመንግሥት እየተሠራ ያለው ሥራ ውጤቱ እንዲታይ ማድረግ ግድ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው፣ መንግሥት ብዙ የውጭ ምንዛሪ በማውጣት የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል የሚደጉማቸው መሠረታዊ ምርቶች በአግባቡ እንዲሠራጩ መደረግ አለበት፡፡ ይህ የወቅቱን የዋጋ ንረት ለማርገብ ያግዛል፡፡

ዘይት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጥቶበት እንዲገባ ይደረጋል፡፡ ዋጋውን ለማረጋጋት ተብሎ ታክሱ እንዲቀንስ መደረጉም ይታወቃል፡፡ ዘይቱ ገበያውን ሊያረጋጋ የሚችለው ግን ሥርጭቱ በአግባቡ ሲከናወን ብቻ ነው፡፡ እንደ ዘይት ሁሉ በተመሳሳይ መንገድ ከውጭ ወደ አገር እየገባ ያለው ስንዴ ምርቱን ለማስገባት ከተከፈለው መስዋዕትነት ባልተናነሰ የሥርጭት ሒደቱን በማስተዋል ለሌብነት ተጋላጭ እንዳይሆን ማድረግ እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡ ገበያን ያረጋጋሉ ተብለው በመንግሥት ድጎማ የሚመጡ ምርቶችም ሆኑ ሌሎች ላይ ሥርጭቱ ላይ ጠንካራ ቁጥጥር መተግበር ወቅታዊውን ችግር ለመሻገር ጠቃሚ ይሆናል፡፡  

የምርት እጥረት በሌለበት ሁኔታ ዋጋ ሲቆለል፣ ገበያው ሲተረማመስ የማየታችን አንዱ ምክንያት ገበያ ለማረጋጋትና እጥረትን ለመቅረፍ ተብለው የሚቀርቡ ምርቶች በአግባቡ አለመሠራጨታቸው ነው፡፡ የዋጋ ንረቱን በማባባስ የራሳቸው የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳላቸው የታየ በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ ሌላው መጠቀስ ያለበት ብርቱ ጉዳይ ሸማቾችም ቢሆኑ እንዲህ ያሉ ምርቶችን በአግባቡ መጠቀም የሚኖርባቸው መሆኑ ነው፡፡

አገር በአንድ ላይ እየተፈተነ ባለበት ሰዓት አገር መታደግ የሚቻለው ካልተገቡ ተግባራት በመቆጠብ ጭምር መሆኑን በደንብ ልንረዳ ይገባል፡፡ እንዲህ ባለው ወቅት ጨዋ ሸማች ሆኖ መገኘትም ያስፈልጋል፡፡ በሸማቾች ማኅበራት የሚከፋፈሉ መሠረታዊ የሚባሉ እንደ ዘይት፣ ዱቄትና ስኳር ያሉ ምርቶችን የሚገዙ ጥቂት የማይባሉ ሸማቾች እዚያው አየር በአየር በመሸጥ የተወሰነ ጥቅም ለማግኘት የሚፈጽም ግብይት ተፅዕኖ እንዳለው ማወቅ ያስፈልጋል፡፡

ሸማቾች ለራሳቸው እንዲጠቀሙበት የተሰጣቸውን ዘይት 100 እና 150 ብር አትርፈው መሸጣቸውን እንጂ ቀጣይ ጉዳቱን አይገነዘቡትም፡፡ ከእነርሱ ምርቱን የተረከቡ ደግሞ የራሳቸውን ትርፍ አክለው የሚሸጡ በመሆኑ የዋጋ ንረቱ ምን ያህል እያፋፋሙ እንደሆነ አይገነዘቡም፡፡

የሸማቾች ሠራተኞች የታማኝነት ጉዳይም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምርቱን በአግባቡ ትክክለኛው ተጠቃሚ ጋር ለማደረስ ከሚደረገው ጥረት ባሻገር በልዩ ሁኔታ ገበያ ለማረጋጋት የሚመጡ ምርቶች ከተመደበላቸው የመሸጫ ቦታዎች ውጪ እንዳይሸጡ ማድረግ አንድ መፍትሔ ይሆናል፡፡

ከሸማቾች ማኅበር በቀጥታ ለሸማቾች የተሰጠ ዘይት ለምን ሱቅ ውስጥ ሲሸጥ ዝም ይባላል፡፡ ያውም ዋጋው በእጅጉ ተጋንኖ የመሸጡ አንዱ ምክንያትም ይኼው ከሸማቾች የተገዛው ዘይት ምርት ለነጋዴ በመቀባበሉ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችም እንደቀላል ማየት የለብንም፡፡ አሁን ገበያውን ለማረጋጋትና ከችግር ለመውጣት ከታሰበ የንግድ ሰንሰለቱ ላይ የመፍትሔ አማራጮችን ሁሉ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት