በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት ኃይል መካከል የነበረው ልዩነት እያበጠ ሄዶ ጦርነት ከቀሰቀሰበት ጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. አንስቶ፣ ጉዳዩ የዓለም ኃያላን አገሮችን ትኩረት የሳበ ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ ሆኗል።
ጉዳዩ የኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተ ፖለቲካዊ አለመግባባት የወለደው መጣጣል ቢሆንም ቅሉ፣ ኢትዮጵያ የምትገኝበት ቀጣና ባለው ስትራቴጂካዊ ፋይዳ ምክንያት የውስጥ ቀውሱ የዓለም ኃያል የሚባሉትን አገሮች ትኩረት ከመሳብ አልፎ የተፅዕኖ ፉክክር ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል።
የትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰበት ጥቅምት 2013 ዓ.ም. አንስቶ እስከ ነሐሴ ወር ድረስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታ ምክር ቤት፣ በትግራይ ክልል ቀውስ ላይ ስምንት ስብሰባዎችን አድርጓል።
የዓለም ኃያላን አገሮች የሚፎካከሩበትን የትግራይ ክልል ቀውስ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ግልጽና ኦፊሳላዊ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ አሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች ጥረት ቢያደርጉም፣ እስከ ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ድረስ ኦፊሴላዊ አጀንዳ መሆን ሳይችል በሌሎቹ የፀጥታው ምክር ቤት ኃያላኖች በተለይም በሩሲያና በቻይና በዋናነት ውድቅ ሲደረግ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ከጥቅምት ወር አንስቶ እስከ ሰኔ ወር ድረስ የፀጥታው ምክር ቤት ሌሎች ጉዳዮች በሚል አጀንዳ ሥር የትግራይ ክልል ቀውስን በተመለከተ ኦፊሴላዊ ያልሆኑ ስድስት ውይይቶችን አድርጓል። በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ግን የፀጥታ ምክር ቤቱ ኦፊሴላዊ አጀንዳ አድርጎ ተወያይቶበታል።
ይሁን እንጂ በዚህ ውይይት ላይም ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት የያዙት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የሆኑት ሩሲያና ቻይና፣ እንዲሁም ህንድና ሌሎች ተለዋጭ መቀመጫ ያላቸው አገሮች ለአብነትም የአፍሪካ አኅጉርን የወከሉት ሦስቱ የአፍሪካ አገሮች የትግራይ ክልል ቀውስ የኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ጉዳይ እንጂ፣ ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ሥጋት ባለመሆኑ ከጀንዳ ሊሆን አይገባም በማለት በማጣጣላቸው፣ አሜሪካና አጋሮቿ የሆኑት የአውሮፓ አገሮች ውጥናቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
የትግራይ ፖለቲካ ቀውስ በዚህ መንገድ በፀጥታው ምክር ቤት አጀንዳ ማድረግ ያልቻሉት ኃያላኖቹ አገሮች በጦርነቱ ምክንያት እየደረሰ ያለውን ኢሰብዓዊ ጥሰትና ሰብዓዊ ቀውስ፣ መሠረታዊ የክርክር ጭብጥ አድርገው ጉዳዩ ወደ በምክር ቤቱ ተንጠልጥሎ እንዲገባና እንዲቆይ አድርገውታል።
ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. በነበረው የፀጥታ ምክር ቤት መድረክ ላይም ‹‹የትግራይ ክልል ቀውስ ሰላምና ደኅንነት በአፍሪካ›› በሚል አጀንዳ ቀርቦ ሁለት ሰዓት ገደማ የፈጀ ውይይት ተደርጎበታል።
ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ስብሰባዎች ሁሉ ባለፈው ሳምንት የተካሄደው የፀጥታው ምክር ቤት ስብሰባም በተመሳሳይ የኃያላን አገሮች ፖለቲካዊ የበላይነት ለመያዝ ያደረጉበት ፍጥጫ ሆኖ ታይቷል። ይሁን እንጂ የትግራይ ክልል ቀውስ መፍትሔ እንዲያገኝና እንዲያበቃ ፍላጎት ያላቸው አገሮች ፖለቲካዊ አቋምም የተንፀባረቀበት ነበር ማለት ይቻላል።
ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደው ስብሰባ እንዲጠራ አጀንዳ ያስያዙት አገሮች ከዚህ ቀደምም በጉዳዩ ላይ የጋራ የሚመስል አልያም ተመሳሳይ አቋም ሲያራምዱ የነበሩት ናቸው። እነዚህም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ፣ ጣሊያንና አይርላንድ ናቸው።
በዚህ ስብሰባ ላይ የፀጥታው ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የሆነችው ህንድን ጨምሮ፣ ሩሲያና ቻይና በሰብዓዊነት ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን አጥብቀው ተቃውመዋል።
እነዚህ አገሮች ጣልቃ ገብነቱን አጥብቀው ቢቃወሙም በትግራይ ክልልም ሆነ ከዚህ ጋር በየተያያዘ፣ በአማራና በአፋር ክልል የተከሰቱ ሰብዓዊ ጥሰቶችን እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውሶችን አውግዘዋል።
በሐሙሱ የፀጥታ ምክር ቤቱ ስብሰባ ላይም እንደ ቀደሙት ስብሰባዎች የኢትዮጵያ መንግሥትን ለመከላከል ጠንከር ያሉ ሙግት ያሰሙት አገሮች ዋነኞቹ አገሮች ቻይና፣ ሩሲያና ህንድ ናቸው።
በዚህ ስብሰባ ላይ የቻይና መንግሥትን አቋም ያቀረቡት በተመድ የቻይና መንግሥት አምባሳደር፣ በሰብዓዊ ቀውስ ምክንያትና በሰብዓዊነት ስም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን የቻይና መንግሥት አጥብቆ እንደሚያወግዝ ተናግረዋል።
‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የገጠመውን የውስጥ ችግር የመፍታት ዕውቀትም ሆነ ችሎታ እንዳለው ቻይና በፅኑ ታምናለች፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር አለበት፣ ቻይናም ታከብራለች፤›› ብለዋል።
በኢትዮጵያ ለተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ዓለም ዓቀፍ የተራድኦ ድርጅቶችም ለዓለም አቀፍ መርሆች ተገዝተውና የአገሪቱን ሕግ አክብረው እንዲንቀሳቀሰ ጠይቀዋል።
በማከልም፣ ‹‹በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የሚወሰድ የተናጠል ማዕቀብ ከዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መርህዎችና ልማዶች ያፈነገጠ ጣልቃ ገብነት ነው። ችግሩን የሚያወሳስብ እንጂ መፍትሔ የማይሰጥ ድርጊት በመሆኑ ተገቢነት የለውም፤›› በማለት አጣጥለዋል።
ከቻይና ጋር ተመሳሳይ አቋም ያራመደችው ሩሲያ በተመድ አምባሳደሯ በኩል ባደረገችው ንግግር ለኢትዮጵያ መንግሥት ያደላና የሕወሓትን የኃይል ድርጊት የሚያወግዝ አቋም አንፀባርቃለች።
ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይደርስ ከትግራይ ክልል ወጥተው ግጭት በመቀስቀስና መተላለፊያ ኮሪደሩን የዘጉት የሕወሓት ኃይሎች እንደሆኑ፣ ከዚህም አልፈው የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ኮሪደር የሆነውን የጂቡቲ ወደብ አገናኝ የተሽከርካሪ መንገድና የባቡር መስመር ለመቆጣጠርና ለመዝጋት ሙከራ ማድረጋቸውን በመግለጽ ሩሲያ ኮንናለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ ለመፍታት የተናጠል ተኩስ ቢያደርግም ሌላኛው ወገን የአጠፋ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፣ ጦርነቱን ከትግራይ ክልል ወደ አጎራባች ክልሎች እያስፋፋ እንደሚገኝ በመጥቀስ ሩሲያ በሕወሓት ላይ ጣቷን ቀስራለች።
‹‹ሌላው ዓለም የሰሜን ኢትዮጵያን ሰብዓዊ ቀውስ ለፖለቲካ ትግል መጠቀሚያ ከማድረግ ይቆጠብ፣ ለችግሩ የመጀመርያ መፍትሔ ይህ ነው፤›› ብላለች።
ለተፈጠረው ቀውስ መፍትሔው የፖለቲካ ውይይት ቢሆንም፣ ይህ ውይይትም ከውጭ መጫን እንደሌለበትና ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሊተው እንደሚገባም ተከራክራለች።
የሰላም ጥረቱ ባለቤትነት ለኢትዮጵያ እንዲተው ነገር ግን በዚህ ውስጥ የአፍሪካ ኅብረትና የአኅጉሪቱ አገሮች፣ እንዲሁም የተመድ ዋና ጸሐፊ የዕገዛ ሚና ቢያደርጉ የምትቀበለው መሆኑን አስታውቃለች።
‹‹ቀውሱን ለመፍታት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የተናጠል ማዕቀብ በማድረግ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ አገሮች ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል፤›› ያለችው ሩሲያ፣ የተናጠል ማዕቀብ በተመድ የሚደረገውን የሰላም ጥረት እንደሚጎዳና የኢትዮጵያንም ችግር ከማወሳሰብ ውጪ ፋይዳ እንደማይኖረው አሳስባለች።
የፀጥታው ምክር ቤት የአሜሪካና የአጋሮቿን የእንግሊዝና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች ፖለቲካዊ ፍላጎት በመቃረን የቆሙት ዋነኞቹ አገሮች ሩሲያና ቻይና ቢሆኑም፣ እነዚህ አገሮችም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን የቆሙበት ምክንያት ጥልቅ ፍቅር ነው ማለት አይደለም።
እነዚህ አገሮች ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን የቆሙት የዓለም የፖለቲካ ሚዛንን ለመጠበቅና ቀጣናዊ ፖለቲካውን በመያዝም የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ማሳካት፣ ኢሰብዓዊ ጥሰትን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ውይይት ወደ ፀጥታው ምክር ቤት እንዳይቀርብ በማድረግ ራሳቸውን ከመሰል ጫናዎች ለመከላከል የያዙት አቋም እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
በዚህ የኃያላን መድረክና ፍጥጫ መካከል የሆኑ አቋም ያራመዱት የአፍሪካ አኅጉር ተወካይ ሆነው የምክር ቤቱን ተለዋጭ መቀመጫ የያዙት ሦስት አገሮች ናቸው።
የእነዚህ አገሮች አቋም በኬንያው የተመድ አምባሳደር በኩል የቀረበ ሲሆን፣ ይኸውም ችግሩን ከመሠረቱ ለመመልከት የሞከረ፣ የአጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሔውንም ለይቶ ያመላከተ ነበር።
በኢትዮጵያ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች የሚታዩት ግጭቶች የብሔር ማንነትን መሠረት አድርገው የሚያጠነጥኑ መሆናቸውን መረዳት እንደሚያስፈልግ፣ አገሪቱን ለመሰል ግጭቶች የዳረጋትም ብሔርን መሠረት ያደረገው የፖለቲካ አደረጃጀቷ እንደሆነ የኬንያው ተወካይ ባቀረቡት የአፍሪካ አኅጉርን የሚወክል አቋም አንፀባርቀዋል።
‹‹አሁን በኢትዮጵያ የሚስተዋለው አለመረጋጋት የአገሪቱን መፃዒ ዕጣ ፈንታ ለመወሰን ተብለው የሚቀርቡ የሚቃረኑ ሕልሞች ግጭት ውጤት ነው፤›› ብለዋል።
በብሔር ማንነት ላይ የተዋቀረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥሪት አደገኛ እንደሆነ የገለጹት የኬንያው አምባሳደር፣ ይህ አደረጃጀት የፖለቲካ ልዩነቶችን አቻችሎ ለመሸከም እንደማይችል፣ ከዚያ ይልቅ የፖለቲካ ልዩነቶች በቀላሉ ወደ ፖለቲካ ግጭት እንዲያመሩ መንገድ የሚከፍት እንደሆነ ገልጸዋል።
በመሆኑም አሁን በኢትዮጵያ ያለው ግጭት መሠረታዊ መንስዔውን ለይቶ መፍትሔ ካልተገኘ በስተቀር፣ የባሰ ፖለቲካዊ ቀውስ ሊከሰት እንደሚችል በሥጋት አስረድተዋል።
ግጭቱን ለመፍታት በአፍሪካ ኅብረት ሥር የተቀመጡ የግጭት መፍቻ እሴቶችና ዘዴዎች በፍጥነት ወደ ተግባር መግባት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
‹‹በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ለማስቆም በፍጥነት ጥቅም ላይ መዋል የሚገባው መሣሪያ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ደኅንነት መዋቅር ውስጥ የተቀመጡ ዘዴዎች ናቸው። ከእነዚህ መሣሪያዎች ውስጥ በቅድሚያ ጥቅም ላይ መዋል ያለበትም የኅብረቱ አባል አገሮች በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ እንዲገባ ኅብረቱን መጠየቅ ነው፤›› ብለዋል።
የአፍሪካ ቀንድ ቀውሶችን ለመፍታት የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ኮሚሽነር ከሰሞኑ የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መሾማቸውን በማስታወስ፣ ሁሉም የዓለም መንግሥታት ኦባሳንጆ የሚጀምሩትን አጠቃላይ ጥረት በተለይም የኢትዮጵያን ቀውስ አስመልክቶ ለሚያደረጉት ጥረት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ይህ የሰላም ጥረት ዕውን እንዲሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ማንኛውንም ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ገደቦችን እንዲያነሳ ጠይቀዋል።
አሁን ባለው ግጭት ምክንያት ያልተገቡ ጥሰቶች ተከስተው እንኳን ቢሆን፣ ወደዚህ የግጭት ሁኔታ ያመሩት ቅቡልነት ያላቸው የፖለቲካ ቅራኔዎች መሆናቸውን ተገንዝቦ የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያልፋቸውና ውይይት ላይ ለተመሠረተ ፖለቲካዊ መፍትሔ በሩን እንዲከፍት ጠይቀዋል።
ለዚህም ሲባል በመጪው መስከረም 2014 ዓ.ም. የሚመሠረተው የኢትዮጵያ ፓርላማ፣ ቀደም ሲል አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ፍረጃውን እንዲያነሳ ጠይቀዋል።
ሲቪል ሰዎችን በጦርነቱ እንዲሳተፉ ጥሪ ማድረግና መመልመል ብሔራዊ ስሜትን ከመፍጠር አኳያ ፋይዳ ያለው ቢሆንም እንኳን፣ በጥንቃቄ ካልተያዘ ወደ ሌላ መንገድ ሊያመራ የሚችል አደገኛ አካሄድ መሆኑንም አሳስበዋል።
ሕወሓት ከአማራና ከአፋር ክልሎች ለቆ እንዲወጣ የጠየቁ ሲሆን፣ ሌሎች የታጠቁ ኃይሎችን ለግጭት ከማስተባበር ድርጊቱም እንዲቆጠብ አሳስበዋል። ግጭቱን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲስፋፋ መግፋት የፖለቲካ ልዩነቶች እንዳይታረቁ የማድረግና አጠቃላይ ችግሩንም የሚያወሳስብ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በተለየ መንገድ ባስቀመጡት የአፍሪካ አኅጉር አቋም፣ ‹‹ሕወሓት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ነፃነትና ሉዓላዊ የግዛት አንድነት በሚጎዳ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፍ ከሆነ፣ ሁሉም የአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ድርጊቱን ለመከላከል የሚገደዱ እንደሆነ መጠራጠር የለብንም፤›› ሲሉ የኬንያው አምባሳደር አሳስበዋል።
በማከልም የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣና ምንም ዓይነት የተናጠል ማዕቀብ በኢትዮጵያ ላይ ከመጣል መንግሥታት ሊቆጠቡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአፍሪካ ኅብረትን ሚና ሁሉም የፀጥታው ምክር ቤት ደግፈው የተቀበሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ የተመድ መልዕክተኛ ታዬ አፅቀ ሥላሴ (አምባሳደር) በኩል ከሁሉም መልካም ዕሳቤ ካላቸው የውጭ አጋሮች ጋር የኢትዮጵያ መንግሥት ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።
‹‹የእኛ ፍላጎት ሰላም ነው። ነገር ግን የሕወሓት ኃይል በኢትዮጵያና በሰላም መካከል ላይ ቆመብን፤›› ሲሉ አምባሳደሩ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ያረጋገጡት አምባሳደሩ፣ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ በውክልና ለመወሰን ሉዓላዊነቷን ጥሶ ጣልቃ የሚገባ ኃይልን የሚቀበል ነፍስ በኢትዮጵያ ምድር እንደሌለ አስረግጠው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረትን ሚና ሁሉም የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ደግፈው የተቀበሉ ቢሆንም፣ የምክር ቤቱ ውይይት መጠናቀቅን ተከትሎ ሕወሓት ባወጣው መግለጫ ግን የአፍሪካ ኅብረትን በማጣጣልና በመወረፍ የተቋሙን አደራደሪነት እንደማይቀበል ገልጿል።
ድርድር የሚካሄድ ከሆነ ሕወሓት የሚቀበላቸው ገለልተኛ አደራደሪ መሆን ያለባቸው አገሮች ግብፅ፣ ሱዳን፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ አየርላንድ፣ ተመድ፣ የአውሮፓ ኅብረት ናቸው፡፡