Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በተሻሻለው የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ሲቃኙ

በሐረጐት አብርሃ

የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የተቋቋመበትን አዋጅ ለአራተኛ ጊዜ በአዋጅ ቁጥር 1236/2021 አሻሽሏል፡፡ ከአሁን በፊት በመጀመርያው ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 235/1993፣ ዳግመኛም በአዋጅ ቁጥር 433/1997፣ እንደገና በማሻሻያ በአዋጅ ቁጥር 883/2007 ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ማቋቋሚያ አዋጆች በየደረጃው እየተሻሻሉ እንዲሄዱ የየራሳቸው ምክንያቶች ቢኖሯቸውም፣ በዋናነት የሚጠቀሱ ግን የግልጽነትና የተጠያቂነት መርሆችን በሥነ ምግባር ግንባታ፣ በሙስና መከላከል፣ በሙስና ምርመራና ክስ ሥራዎች አጉልቶ ለማውጣት፣ ግልጽነት የሚጎላቸው ድንጋጌዎች ካሉ ለማሻሻል፣ በአዋጁ ያልተሸፈኑ የሥነ ምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል ሥራዎችን ለማካተት፣ የኮሚሽኑ ሥልጣንና ተግባር ከሌሎች የወንጀል ሕጎች ጋር በማጣጣም ተግባራዊ እንዲሆን ታሳቢ በማድረግ ሥራ ላይ ውለው የነበሩ አዋጆች  ናቸው፡፡

በ2013 ዓ.ም. ተሻሽሎ የወጣው አዲሱ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1236/2013 ተሻሽሎ እንዲወጣ ያደረጉት መሠረታዊ ሁኔታዎች አሉት፡፡ አንደኛውና ዋነኛው ምክንያት ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በኮሚሽኑ ሥልጣን ሥር የነበሩትን የምርመራና  የዓቃቤ ሕግ ሥራዎች ወደ ፖሊስና ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞ በኮሚሸኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ነው፡፡ በተለይም በአሠራር ሥርዓት ጥናት የተገኙ ክፍተቶችና የአስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራዎች በነበረው ማቋቋሚያ አዋጅ ተፈጻሚነትና ተጠያቂነት ማረጋገጥ አስቸጋሪ አድርጎት በመቆየቱ ይህን ሊያጠናክር የሚያስችል አዋጅ ማውጣት ያስፈለገበት ምክንያት አለ፡፡ ከዚህ ባሻገር በተለያዩ አዋጆች ለኮሚሽኑ ተሰጥተው የነበሩት ተግባርና ኃላፊነቶችን በአንድ አዋጅ አሰባስቦ ለማውጣት ኮሚሽኑ ሙስናን በተመለከተ በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚኖረውን የማስተባበርና የመምራት ሚና በግልጽ ለማመላከት ከሌሎች ተቋማት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በአዲስ ዕሳቤ ቃኝቶ ለማውጣት ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የኮሚሽኑ ተቋማዊ አሠራርና ነፃነት ለማረጋገጥ የሚያግዙ ድንጋጌዎችም በአዋጁ ትልቅ ትኩረት አግኝተዋል፡፡ 

ከሁሉም በላይ ግን በዚህ አዋጅ ትልቅ ትኩረት ካገኙ ጉዳዮች አንዱ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ሲያነሱዋቸው የነበሩ መሠረታዊ ችግሮች መፍትሔ በዝርዝር ያስቀመጠ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ይህን አዲስ አዋጅ ከመውጣቱ በፊት በደንብ አማካይነት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 144/2000 የሚመሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ነገር ግን ደንቡ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በሥነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲያመጡ በተሟላ ሁኔታ የሚደግፍ አልነበረም፡፡ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ሲነሱ ቆይቷል፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ችግሩን ከሥሩ የሚፈቱ ድንጋጌዎች በአዲሱ አዋጁ እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡ በአዋጁ መሠረት ዝርዘር ማስፈጸሚያ መመርያ ተዘጋጅቶ ሥራ ላይ ውላል፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማም አዋጁና አዋጁን ተከትሎ የወጣውን መመርያ ይዘዋቸው የመጡት አዳዲስ ዕሳቤዎች/ድንጋጌዎች ለማሳየት፣ በዚህ መሠረት በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት ተቋማትና ባለድርሻ አካላት የአዋጁን መንፈስ በግልጽ ተረድተው የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በአግባቡ እንዲያደራጁ ድጋፍ እንዲሰጡ፣ እንዲሁም የመከታተያ ክፍሎች ከማደራጀት አኳያ በአንዳንድ ተቋማት የተስተዋሉ አሉታዊ ዕሳቤዎች እንዲታረሙ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግም ታስቦ ነው፡፡ አዋጁና አዋጁን ተከትሎ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች አሠራርና አደረጃጀት ለመወሰን የወጣው መመርያ ይዟቸው የመጣው አዳዲስ ዕሳቤዎች ብዙ ቢሆኑም ለአንባቢያን ግንዛቤ ይረዳ ዘንድ ዋና ዋናዎቹ ብቻ እንደሚከተለው እንዳስሳቸዋለን፡፡

የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ሰፊ ኃላፊነትና ተግባር የተሰጣቸው መሆኑ

የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 144/2000 ሲቋቋሙ ተሰጥቷቸው የነበሩ ኃላፊነቶች አሁን በአዲሱ አዋጅ ከተሰጣቸው ሚና አንፃር ሰፊ ልዩነት አለው፡፡ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት በደንቡ የነበራቸው ሚና በሥነ ምግባር ዙሪያ የተቋሙ የበላይ ኃላፊ አማካሪ ሚና ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ማለት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች የማማከር ሚና ብቻ እንጂ ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ዋና ዋና ተግባራትን አካተው ራሳቸውም ውሳኔ እየሰጡ እንዲሄዱ የሚያስችል አልነበረም፡፡ የሚያቀርቧቸው ምክሮች ወይም ውሳኔዎች ተቀባይነት ባያገኙ በቀጣይ ሊወሰዱ የሚገባቸው ጉዳዮች የሚያመላክት አልነበረም፡፡  በነበረው ደንብ የሥነ ምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል ተግባራትና ኃላፊነቶች ውስን ናቸው፡፡ የነበሩት በአብዛኛው ለግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ሰፊ ትኩረት ሰጥተው የነበሩ እንጂ በደንቡ መካተት የነበረባቸው፣ ነገር ግን የተተዉ ዋና ዋና ሥራዎች ሲሠሩ አልነበሩም፡፡ ቢሠሩም በኮሚሽኑ ውክልና ሲሰጣቸው ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ የተቋማት ሠራተኞችና አመራሮች ሀብት መመዝገብና አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራ መሥራት ወዘተ. ለእነሱ የተሰጠ ኃላፊነት አልነበረም፡፡ በአዲሱ አዋጁ ቁጥር 1236/2013 እና አዋጁን ተከትሎ የወጣውን የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች አደረጃጀትና አሠራር ለመወሰን የወጣውን መመርያ ቁጥር 20/2013 እነዚህና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ያስቻለ ነው፡፡ ደንቡን በመመርያ ቁጥር 20/2013 ሲሻር ብዙ ዕሳቤዎች አካቶ ይዞ እንዲወጣ ተደርገዋል፡፡ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ከነበራቸው የአማካሪ ሚና በተጨማሪ ለኮሚሽኑ የተሰጡ ተግባርና ኃላፊነቶች ከሞላ ጎደል ለእነዚህ አካላት እንዲሰጣቸው ተደርገዋል፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 20 ላይ ያለው አገላለጽ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በተቋሞቻቸው የሥነ ምግባር ግንባታና የሙስና መከላከል ሥራዎች በባለቤትነት የሚያስተባብሩ የሥራ ክፍሎች ሆነው እንደሚደራጁ ይገልጻል፡፡ ከዚህ አገላለጽ መረዳት የሚቻለው ከላይ ያነሳናቸውንና ከአሁን በፊት በደንቡ ያልተገለጹ ተግባራት ማለትም የሀብት መዝጋቢ መረጃ የማደራጀት፣ ሀብት መመዝገብ፣ አስቸኳይ የሙስና መከላከል ሥራዎችና በተቋም ደረጃ የጥቅም ግጭት ተግባራት መለየት ወዘተ. የመሳሰሉ ሥራዎች በአዲሱ መመርያ ውስጥ ተጨማሪ ተግባርና ኃላፊነቶች ሆነው ተካተዋል፡፡ ካለፈው ሰፋ ያለ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ሲሠራቸው የነበሩትን ሥራዎች እንዲሠሩ በስፋት ጎልብተዋል፡፡ የሥነ ምግባር መኰንኖች በቀን ስምንት ሰዓት የሚያሠራ ሥራ የላቸውም የሚል ከአንድ አንድ ቅንነት የሚጎላቸውን ባለሥልጣናት የሚነሳውን ትችት በመሠረቱ የሚቀይር ሲሆን፣ በተግባር እየታየ ያለውም የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ከኮሚሽኑ የማይተናነስ ሥራ እየሠሩ መሆናቸውን መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም በአዋጁ እንደ አዲስ ዕሳቤ የተወሰደው ጉዳይ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ተግባርና ኃላፊነታቸው በማስፋት በተቋም ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ የፀረ ሙስና ሥራ በእያንዳንዱ ተቋም ዋና ሆኖ እንዲሄድ በሚያስችል መልኩ የተቃኘ ነው፡፡

የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች የአሠራር ነፃነት የሚያረጋግጥ መሆኑ

ሌላ በዚህ አዋጅ አዲስ ዕሳቤ ሆነው የመጣው የመከታተያ ክፍሎች የተጠሪነት ችግሮች መፍታት ነው፡፡ የተጠሪነት ጉዳይ የሥራ ግንኙነት ለማሳለጥ ተብሎ ብቻ የሚታሰብ ጉዳይ አይደለም፡፡ ተጠሪነት በፀረ ሙስና ትግሉ ከሚኖር አደረጃጀትና አሠራር ነፃነት አንፃር ቀጥታ ግንኙነትና ከፍተኛ ጥቅም ያለው ጉዳይ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ስምምነት (ኮንቬንሽን) እንዲሁም በፀረ ሙስና ተቋማት አደረጃጀትና ነፃነት አንፃር ጥናት ያደረጉ አካላት ከሚያነሱት ጉዳዮች አንዱ ለፀረ ሙስና ተቋማት (የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ጨምሮ) በሕግ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በብቃትና በታማኝነት እንዲወጡ ከተፈለገ ያልተገደበ የአሠራር ነፃነት መኖር ወሳኝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በየተቋሙ የሚገኙ መከታተያ ክፍሎች ተጠሪነታቸው ለኮሚሽኑ እንዲሆኑ የተደረገው ከኮሚሽኑ የሚኖራቸው ግንኙነት ጠንካራ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን ከማንኛውም አካል ሊመጣ የሚችል ተፅዕኖ ወይም ጉዳት ጭምር ለመከላከል አስፈላጊ ስለሆነ ነው፡፡

ቀደም ሲል የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ለተቋማት አመራሮች ተጠሪ በመሆናቸው የሚጠበቅባቸው ሚና ሲወጡ አልነበረም፡፡ ሲወጡ የነበሩ ጥቂት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎቹም ከተፅዕኖ ነፃ አልነበሩም፡፡ እንዲያውም ከፍተኛ በደልና መፈናቀል የደረሳቸው የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ የተሻለ አደረጃጃት፣ የሰው ኃይልና በጀት ተመድቦላቸው እንዳይሠሩ የተጠሪነት ጉዳይ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በየተቋማቱ ከሚገኙ የኦዲት ክፍሎች ጋር ስናነፃፅራቸው  ውጤቱ የተለያየ ነው፡፡ በመሆኑም የተጠሪነት ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ሆኖ ሲነሳ የነበረና ፈጣን መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ በመሆኑ በአዲሱ አዋጅ ቁጥር 1236/2013 አንቀፅ መሠረት የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የልማት ድርጅቶችና ሕዝባዊ ድርጅቶች የሥነ ምግባር መኰንኖች ተጠሪነታቸው ለኮሚሽኑ እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በዚህ መሠረት ኮሚሽኑ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች የማደራጀት፣ የመመደብ፣ የማዘዋወርና  የማሰናበት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ቅርንጫፍ ላይ የሚሠሩ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ተጠሪነታቸው ለዋናው ተቋም የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል እንዲሆን ተደርገዋል፡፡ ይህ በመሆኑ አዋጁ እጃቸውን አስረዝመው መከታተያ ክፍሎችን ሲኮረኩሙ የነበሩ ባለሥልጣናት ወይም ተቋማት አደብ እንዲገዙና መከታተያ ክፍሎች ሊደርሱ የሚችሉ ማናቸውም ተፅዕኖዎች እንዲከላከል ያስችላል፡፡ በዚያው ልክ ሥራቸውንና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የማይወጡ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በሚኖሩበት ወቅትም ኮሚሽኑ በቅርበት ተከታትሎ ፈጣን የማስተካከያ ዕርምት ዕርምጃ ለመውሰድ ዕድል ይፈጥርለታል፡፡

የሥነ  ምግባር  መከታተያ  ክፍሎች  አደረጃጃት  ዘላቂ  መፍትሔ  እንዲያገኝ

ያስቻለ መሆኑ

በዚህ አዋጅ ትኩረት ተሰጥቷቸው ከታዩ ጉዳዮች አንዱ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች አደረጀጃት ችግርን የመፍታት ዕሳቤ ነው፡፡ ቀደም ሲል በነበረው ደንብ በእያንዳንዱ ተቋም ካለው ሥራ ስፋት አንፃር ሊኖር የሚገባ አደረጃጃትና የሰው ኃይል የማይመልስ ነው የነበረው፡፡ የአሁን ግን ተቋማት ያላቸውን የሥራ ስፋት የሙስና ተጋላጭነትና የሰው ሀብት ብዛት በሚገባ ታይቶ ከዳይሬክቶሬት እስከ ባለሙያ ደረጃ ድረስ እንዲያደራጁ ይፈቅዳል፡፡ በቢሊዮን ብር የሚሆን ሀብት እያስተዳደሩና እያንቀሳቀሱ  አንድ ባለሙያ ለመመደብ እንኳን ሲያቅማሙ የነበሩትን ተቋማት አሁን ኮሚሽኑ መዝኖና ገምግሞ ለተቋሙ የሚመጥን አደረጃጀት በመፍጠር የሰው ኃይል ተመድቦላቸው ጥሩ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡ የሚደራጁ የሥነ ምግባር መከታተያ የሥራ  ደረጃቸው በግልጽ በዓላማ ፈጻሚ ደረጃ እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ይህም የተደረገበት ዋና ምክንያት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ጠንካራ ባለሙያና አመራር ተመድቦላቸው ውጤታማ ሥራ እንዲሠሩ እንጂ ከአሁን በፊት በየወሩ እየለቀቀ በሚሄድ የሥነ ምግባር መኰንን እዚህ ግባ የሚባል ሥራ መሥራት አይቻልም፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ አብዛኛዎቹ ተቋማት አዋጁን ተከትሎ ያደራጁ ሲሆን፣ አንዳንድ ተቋማት ግን የአዋጁ ግልጽ ድንጋጌ በሚቃረን መልኩ የሥራ ደረጃው ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ሊፈቅድ ይገባል፡፡ የሥራ ደረጃ የመወሰን ሥልጣን የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን እንጂ የፀረ ሙስና ኮሚሽን  ሥልጣን አይደለም፡፡ ሲቪል ሰርቪስ ዘዋሪ (ሰርኩላር) ሊያስተላለፍልን ይገባል፡፡ ከአሠራርና መርህ ጋር ይጋጫል ወዘተ. የሚሉ አግባብ ባልሆኑ ምክንያቶች በአንዳንድ ተቋማት ተቃውሞ እየተነሱ ይገኛል፡፡ እንዲያውም ከዚህም አልፎ በተቋሙ እንዲሠራ ኮሚሽኑ የመደበው የሥነ ምግባር መኮንን አልቀበልም ብሎ ቢሮ እንዳይገባ የቢሮ ቁልፍ የቀሙ ተቋማት እንዳሉ ተስተውሏል፡፡ በመሠረቱ በዓላማ ፈጻሚ ደረጃ እንዲሆን በአገሪቱ ሕግ የማውጣት ትልቅ ሥልጣን ያለውን ፓርላማ አስፈላጊነቱ አምኖ፣ ተወያይቶና ፈቅዶ በአዋጅ እንዲካተት ያደረገ አካል መቃወም በራሱ የሕግ መሠረት የለውም፡፡

የግልጽነት ጥያቄዎች ከተነሱ ሥርዓቱን ተከትሎ ኮሚሽኑ ማብራሪያ መጠየቅ እንጂ ፓርላማ ያወጣውን ሕግ አልተገብርም ብሎ ከሕግ በላይ መሆን አይቻልም፡፡ በኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ በተሰጠው ሥልጣን ላይ ሲቪል ሰርቪስ ሆነ ሌላ ተቋም ጥያቄ ማንሳት አይችልም፡፡ በአዋጆች መካከል ተቃርኖ ቢኖር እንኳ በቅርብ ጊዜ የወጣው አዋጅ ተፈጻሚነት እንዳለው ይታወቃል፡፡ እስካሁን ባለኝ መረጃ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በራሱ ይህን አደረጃጀት የተቃወመ አልመሰለኝም፡፡ እንዲያውም  በአዋጅ መሠረት የራሱ የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍል በዓላማ ፈጻሚ ደረጃ አደራጅቷል፡፡ ይህ ሆኖ እያለ ተቋማት በዓላማ ፈጻሚ ደረጃ እንዲያደራጁ ሲጠየቁ ፈቃደኛ አለመሆን ከሲቪል ሰርቪስ አዋጅ ወይም ሥልጣን ጋር የሚያያዝ ሆኖ ሳይሆን ለፀረ ሙስና ትግሉ ተባባሪና ቁርጠኛ አለመሆን ነው፡፡ ለፀረ ሙስና ትግሉ ተባባሪ አለመሆን ደግሞ በአዋጁ አንቀጽ 22 ተጠያቂነት እንዳለው በግልጽ ተቀምጧል፡፡ እርግጥ ነው በዓላማ ፈጻሚ ከፍተኛ ደረጃ ሲባል፣ አንዳንድ የሥራ ደረጃዎች የተለየ ብቃት ወይም ስታንዳርድ የሚጠይቁ ሲሆኑ የእነዚህን ሙያዊ ስታንዳርዶች/መርሆዎች ሳይነካ አጣጥሞ በዓላማ ፈጻሚ ደረጃ መመደብ የሚቻልበት ሁኔታ አለ፡፡

በመሆኑም ተቋማት የአዋጁንና አዋጅን ለማስፈጸም ተብሎ የወጣውን መመርያ በአግባቡ ተረድተው ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው፡፡ ሥራው ካለው ውስብስብና ለአላስፈላጊ ተፅዕኖዎች ከመጋለጥ አንፃር እንዲሁም መከታተያ ክፍሎች አሁን ከተሸከሙት ተግባርና ኃላፊነት ስፋት አንፃር በዓላማ ፈጻሚ ደረጃ መደራጀታቸው ያንሳቸው እንደሆነ እንጂ የሚበዛባቸው አይደለም፡፡ ከዚህ ውጭ በጣም ጥቂት ተቋማት ከዓላማ ፈጻሚ ደረጃ ወርደው የሥራ ደረጃ ለመስጠት ወይም መከታተያ እንዳይመደብ የሚያደርጉትን ግፊት ከአዋጁ መርህና ከሞራል አንፃር ትክክል አይደለም፡፡ ተቋማት የፀረ ሙስና ትግሉ የጋራ ሥራ መሆኑን ተረድተው ከኮሚሽኑ ጋር ተግባብተው መሥራት አለባቸው፡፡ ከዚህ አልፎ አዋጁንና ሌሎች የፀረ ሙስና ሕጎች ለመጣስ ሙከራ የሚያደርጉ ተቋማት ወይም የተቋማት አመራሮች ሲኖሩ ልክ አንደ ሀብት ምዝገባ አልመዘገብክም ተብለው እንደተጠየቁ ሁሉ ለማደራጀት ፈቃደኛ አይደለንም የሚሉ ተቋማት ካሉ ኮሚሽኑ በሕግ ሊጠይቃቸው ይገባል፡፡ በሚሊዮን ሙስና የሚቸበቸብበትና የሀብት ብክነት በሚታይበት አገር ውስጥ የዓላማ ፈጻሚ ደረጃ አላደራጅም ብሎ አታካራ መግባት የህሊና ተጠያቂነት እንዳለባቸው ማስገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኮሚሽኑም በዚህ ረገድ አዋጁን ጠበቅ አድርጎ ማስፈጸም ይጠበቅበታል፡፡

ሲጠቃለል በዚህ አዋጅና መመርያ መሠረት የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች ከማጠናከር አኳያ የተወሰደው ዕርምጃ፣ በእያንዳንዱ ተቋም ጠንካራ ትናንሽ የፀረ ሙስና ተቋማት ማደራጀት የሚያስችል ሥርዓት ተፈጥሯል ተብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ማደራጀት ብቻ ግን በቂ አይደለም፡፡ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት እነዚህን አደረጃጀቶች በሕዝብና  በሕግ የተሰጣቸውን ተልዕኮ እንዲያሳኩና ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ  ሁላችንም ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል እላለሁ፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን! ሰላም ለአገራችን!  

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የኮሚሽኑ ሳይሆን የግል ምልከታቸው ነው፡፡ ጸሐፊው በፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር ግንባታና የኅብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ዳይሬክተር ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡ 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles