Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

አደራ!

ሰላም! ሰላም! እነሆብሶትወልደንብሶት እያረጀን መሆናችን ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጠሩ። ይገርማል ዓመታትም እንደ ዘንድሮ ሸሚዝ ኮሌታ ቶሎ ያልቃሉ ለካ? እያሉ ጎረቤቶቼ ሲያወኩ የሰማ አንድ መንገደኛ፣ “ምን የሸሚዝ ኮሌታ ብቻ፣ የሞባይል ካርዱ አይብስም እንዴ…” ሲላቸው ውካታቸው ቀነሰ። “እውነትም ገና ከመሞላቱ እልም የሚለው የሞባይል ካርድና የወር አስቤዛችን ጉዳይ ገና ስንት ጉድ አለበት…” ሲል ሌላው፣እኔማ የኑሮ ውድነት አሠቃየን ማለት በለመደው አፋችን፣ ከዘመናት ችግራችን ለመላቀቅ መፍትሔ ለምን እንዳጣን አለመነጋገራችን ይገርመኛል…” የሚለው ታዳጊ ወጣት መሆኑ አስደነገጠኝ፡፡ ሰላም ቢሰፍን እኮ አዲሱ ትውልድ ነባሩን መፈጠሩን የሚያስጠላ ሞጋች ጥያቄ እያቀረበ፣ ለምን ከድህነት ጋር እየኖረ እርስ በርሱ ደግሞ እንደሚጋደል ትንፋሽ ያሳጣው ነበር፡፡ ለማይረባ ነገር የምናባክነው ጉልበታችንና ዕውቀታችን ባክኖ የቀረው ለምን መባል ያለበት ይመስለኛል፡፡ ይኼን ጊዜ ነው እንግዲህ እኛ ማን ነን? የምንፈልገው ምንድነው? እየተባባልን ካልተነጋገርንና ለጋራ ጉዳያችን በአንድነት መሠለፍ ካልቻልን ዓለም እንደሚንቀን መረዳት ያለብን፡፡ ተባብረን ታሪክ ስንሠራ ብዙ እንደሚባልልን የዓድዋው ድል ምስክር ነው፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት አገሬ በቢቢሲ፣ሲኤንኤን፣አልጄዚራ፣ፍራንስ 24ኒውዮርክ ታይምስ የድህነትና የጦርነት መዘባበቻ ስትሆን ይነደኛል፡፡ ያንገበግበኛል ብል ይቀለኛል!

በሌላ በኩል ያው የወትሮ ነገራችን እንደተጠበቀ ነው። ያለ ችሎታና ጠጥቶ በማሽከርከር ወገን መፍጀትና ንብረት ማውደም፣ ከመጠን በላይ በሆነ ራስ ወዳድነት ዋጋ መቆለል፣ ባልተረጋገጠ ወሬ አገር ማሸበር የገንዘብን የመግዛት አቅም መቅኖ ማሳጣት፣ የመኖሪያ ቤት ኪራይ በመጨመር ወገንን መጉዳት፣ የሚሠራን እያዋከቡ ሕገወጥነትን ማበረታታት፣ ያለ ጉቦ አልሠራም ማለት፣ ፍቅርንና መተሳሰብን ትቶ ጠላትነት ላይ መበርታትና የመሳሰሉት አብረውን አሉ። በነገራችን ላይ አብዛኞቹ የማውቃቸው ወዳጆቼ ካላንደር የሚዘጋቸው ብሔራዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓሎች ቅዳሜና እሑድ ላይ ሲያርፉ አይወዱም። የአዘቦት ቀን ላይ ሲያርፉ ግን ስሜቱ ልዩ ነው። ሥራ የለም የተባለ ቀን ሰነፉ ቅልጥ ያለ አርበኛ ይሆናል። እንዲያውም እንደ ምሁሩባሻዬ ልጅ ሰላማዊ የፖለቲካ ትንተና ከሆነ፣ ሥራ ጠልቶ ሀብት መመኘት የሰነፎች ሙያ ነው፡፡ “ራስን በሥራ ማሳደግና ለአገር መከታ መሆን የሚቻለው በጥረት ነው ሲባል የማይመስላቸው ብዙ ናቸው፡፡ ለምን ብትለኝ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የተለመደው በአቋራጭ በሌብነት መክበር ስለተለመደ ነው…” ሲለኝ ችግሩ ይገባኛል፡፡ ባይገባኝስ የት እደርሳለሁ!

መቼም አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስብላሉ።አንዳንድ ነገሮች ብዙ ያስገርሙኛል…› እንዲል ጥላሁን ገሠሠ። እናማ የሥራ ቀን ለበለጠ አገራዊ ዓላማ ዋለ ስንባል ጮቤ መርገጥ ሲኖርብን፣ ከግል ጥቅማችን አንፃር የአገርን ጉዳይ ስንቃኝ ግርም ይላል። መቼም ሰው ሥረ መሠረቱ ልጅነቱም አይደል? በቀደም ዕለት ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣የአንድ ሙሉ ሰው አባቱ የወለደው ሳይሆን ልጅነቱ ነው…ስላለው ዶስቶቪስኪ የሚባል የሩሲያ ጸሐፊ ሲያጫውተኝ ነበር። እሱ ምሁራዊ አተያዩን ከማስረጃ ጋር እያቀናበረ ሲያጫውተኝ እኔ የማስበው ልጅነቴን ነበር። አንዳንዴ ዛሬያችሁ ግራ ሲያጋባችሁ፣ እኔ እንዲህ ነኝ? ኧረ ማን ነኝ? ስትሉ ዝም ብላችሁ ወደ አስተዳደጋችሁ ዘመን ተመለሱ እመኑኝ መልሱ ያለው እዚያ ውስጥ ነው። ማንነት ላይ ያለ ችግር ግራ አጋብቶ ስንቱን ሲያዛንፈው እያያችሁ አይደል? “ራስን ወይም የተጠለሉበትን ቡድን ከአገር ማስበለጥ ውስጥ የሚገባው እኮ፣ በተወላገደ ማንነትና በተበላሸ ሰብዕና መሆኑን በአገር ላይ ከተነሱ ምግባረ ብልሹ ሌቦችና የታሪካዊ ጠላቶች ተላላኪዎች ድርጊት መረዳት ይቻላል…” የሚለኝ ምሁሩ ወዳጄ አባባል ነገሮችን ሙሉ ያደርግልኛል፡፡ ክብረት ይስጥልኝ!

ታዲያ ምነው ሥራው ላይ ከመረባረብ በወሬና በአሉባልታ ተጠምደን እየዋልን መፍትሔ ከየት እናግኝ? የሚል ጥያቄ ያላችሁ ወሬውን ረግጣችሁ የመውጣት መብት አላችሁ። መልስ አልባ ሆኜ ብቻ ሳይሆን ዶስቶቪስኪ በሕይወት ስለሌለ ጭምር እንጂ፣ ቢያንስ እሱን ለማጠያየቅ መሞከሬ አይቀርም ነበር። እና ልጅነታችንን ስናጠና ትምህርት ቤት አርፍዶ የመግባት የአብዛኞቻችን አባዜ ትዝ ሲለኝ፣ ዛሬ ከረፋዱ አምስት ሰዓትሥራ አስኪያጁ ገና አልገቡምየሚባለው ነገር ውሉ ይገባኛል። ሠልፉና የሰንደቅ ዓላማ መስቀል ሥነ ሥርዓቱን አድምቀን ስናበቃ፣ አንደኛው ክፍለ ጊዜ ላይ የተሰጠንን የክፍል ሥራ በገዛ ስንፍናችን ወደ ሦስት ቀን የቤት ሥራነት ስንቀይረው ያደግን ልጆችን ሳስብ ዛሬ ስለአገር ክብር፣ ዕድገትና ልማት ደንታ በማጣታችን የቆለልነው ዕዳ እየታሰበኝ ተጠያቂነታችን ይታሰበኛል። ታዲያ እኛ ማን ነን ማለት አይገባም ትላላችሁ? በሚገባ እንጂ!

ለግርግርና ለሆታ ቅድሚያ በመስጠት ለሐሜትና ለአሉባልታ ትኩረት መድበን ስንጓዝ ብቻ እንጀራ እንደሚወጣልን እየነገሩ ያሳደጉንን ወላጆች የታዘዝን እኛ፣ ለሠርግና ለድግሱ የምንጨነቀውን ያህል ለፍቺው አለማሰባችን ምን ይገርማል? ተፈጥሮ ያላደለንን አብሾና ሥራ ሥር እየጋቱ ለአንደኝነት፣ ኮሌጅ ለመበጠስ፣ በልጦና ይዞ ለመገኘት ካሳደጉን ወላጆቻችን የተገኘን እኛ፣ ዛሬ ከተማውን ተቆጣጥረን ወንበዴውንና ጨካኙን ብንረሳው ምን ያስተቻል? እውነት አይደለም? “በመበላለጥ የኑሮ ብልኃት የተቃኘ ልጅነት…” አለኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ በቀደም ዶፍ ዘንቦ ከአንዱ ታዛ ተጠልለን ጎርፉ እስኪጎድል ቆመን ስናወራ። “…በመበላለጥ የተቃኘ ልጅነት በጉልምስና ዘመን እያነጣጠቀ፣ አገር ከመበጥበጥ ሌላ ውጤቱ ምን ሊሆን ኖሯል?” ሲለኝ፣ምን እኔን ትጠይቀኛለህ?” አልኩት አስፋልቱ ላይ የሚፈነጨውን ጎርፍ እያየሁ፡፡ጎርፍ ያመጣሽ እንደሁ ልጠብቅ ወንዙንብዬ ለማንጠግቦሽ ያፏጨሁበትን ዘመን እያስታወስኩ። አሁንማ ጊዜው ነጉዶም ትዝታው ይወዘውዘኛል፡፡ እኔን አይባልም እንዴ?

ይኼን ጊዜ አንድ ወፈፌ ዶፉ እላዩ ላይ እየወረደ በጉያው ሦስት አራት  የጫት እንጨቶች ሸጉጦ፣ጎርፉ ሳይጎድል አሥር ብር ስጡኝ…አለን። ዝም ስንለውስለጎርፉ?” ብሎ ደገመው። የባሻዬ ልጅ አሥር ብር አውጥቶ ሰጠው። በቆመበት ቁጢጥ ብሎ ብሯን አጣጠፋት። አጥፎ አጥፎ ሲያቃናት ጀልባ ሆነች።እኔን አልቀናኝም እስኪ አንቺ ሞክሪው…ብሎ አንሳፈፋት። የባሻዬ ልጅ ተናዶአንተ! ወንጀል እኮ ነው…” እያለ የሚያደርገው ሲጠፋው ወፈፌው፣ለምን እኔን አላልክም?” አለው። የባሻዬ ልጅ ግራ ገባው።እኔም እኮ ሥጋና ነፍስ ያለኝ የምራመድ ወንጀል ነኝ። ሲለምኑብኝ ለምን ዝም አልክ? ዋጋዬን ሲከለክሉኝ፣ ግዴታዬና መብቴ ላይ ሲጫወቱ፣ በድህነት ሲያጎሳቁሉኝ፣ የትም ሲጥሉኝና መልሰው ስሜን ብቻ እያነሱ በጥጋብ ሲሳከሩብኝ ለምን ዝም አልክ? አገሬን በጦር እየወጉና በእሳት እያቃጠሉ ደሃውን እየገደሉ መድረሻ ሲያሳጡት ለምን ብለህ አልተነሳህም?” ቢለው ምን ይበል? ራስን መጠየቅ መቼ ለመድንና? ጉድ እኮ ነው ጎበዝ!

በቀደም አንድ ደንበኛዬ የንብረት ሽያጭ መቼ እንደሚጀመር ሊጠይቀኝ አግኝቶኝ ትኩር ብሎ የጣት ቀለበቴን እየተመለከተ፣ትዳር እንዴት ነው?” ብሎ ጠየቀኝ። ‹‹አሸወይና ነው፣ ወርቅ ሚስት አለችኝ…አልኩት። አንዳንዴ ከጥያቄው በፊት የተዘጋጁ መልሶች ችግር ይፈጥራሉ እኮ። ለካስ ዕድሜው ከእኔ ከጎልማሳው የማያንሰው ደንበኛዬ አራተኛ ጣት ባዶ ኖሯል። ምን ብዬ ጨዋታዬን ልቀጥል።ይገርምሃል ከጓደኞቼ መሀል ሳላገባ የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ…አለኝ፡፡ግድ የለም ሁሉም በጊዜው ይሆናልብዬ ሌላ የተዘጋጀ መልስ ከመመለስ ለጥቂት ተረፍኩ፡፡ አንዳንዱ  ባለማግባቱ የሚበሳጨውን ያህል ሌላ በምንም ሲበሳጭ አላየሁማ፡፡ምነው አልክ?” አልኩት ብዙም እንዳልደነቀኝ ሆኜ፡፡ዕድሜ ለጓደኞቼ መማሪያ ሆኑኛ፡፡ አንድ ሁለቱ ይሻላሉ እንጂ የሰባቱ ኑሮ ሲኦል በለው። ነጋ ጠባ ጭቅጭቅ ነው። ዘመኑ እንደምታየው ስለእኩልነት የሰበከውን ያህል ስለአንተ ትብስ አንቺ አይሰብክም። እናም እኔ ይኼን እያየሁ ምን ተማምኜ ላግባ? ያውስ በመሸበት ማደር በቀለለበት ዘመን?” ሲለኝ ከልቤ አዘንኩ። እንዴት ነው ነገሩ? ተነጋግሮ ችግርን መፍታት ብርቅ በሆነበት አገር ውስጥ ሆነን ትዳራችን ቀርቶ ችግኙስ እንዴት ይፀድቃል ጎበዝ? እስኪ እንነጋገር!

የድለላውን ሳይሆን የማማከር መሰል ሥራዬን ጨራርሼ ኮሚሽኔን ተቀብዬ ከደንበኛዬ ከተለያየን በኋላ፣ ከአዛውንቱ ባሻዬ ጋር ስንጫወት ይኼው ደንበኛዬ ያለኝን ብነግራቸው፣ አንገታቸውን ወዝወዝ አድርገውዋ!ብለው ቀሩ።ምነው?” ስላቸው፣ያለ ሙያቸውና ፍጥረታቸው ገብተው የተደናገሩ ከበሮ መቺዎችን እያየ ስንቱ ከበሮውን ትራስ አደረገው? ስንቱ ዛሬ ታይተው በነጋታው በፈረሱ ትዳሮች ውጥኑ ፈረሰ? ለአገር ለወገኑ ስንት ዓላማና ዕቅድ ያለው ከእሱ በፊት የነበሩትን እያየ ስንቱ ሀሞቱ ፈሰሰ? ስንቱ እሳት ጭሮ ከሰላማዊ ትግል ሸሸ? ስንቱ ሕይወትን ተፀየፈ?” ሲሉኝ አዝማቹን እየደጋገምኩ አጀብኳቸው።እባብ ያየ በልብጥ በረየእንደሚባለው የእኛ ሰው ግን በስንቱ ይንገፈገፋል? ያም ሆነ ይህደፋርና ጭስ መውጫ አያጣምእንደሚባለው፣ አንዳንድ ነገሮቻችንን ደፍረን ከላያችን ላይ ፈንቅለን መጣል አለብን፡፡ እየተንገፈገፍንማ መኖር የለብንም፡፡ አይመስላችሁም? አዎ ይመስለናል!

በሉ መሰነባበቻችን ደርሷል። እኔና የባሻዬ ልጅ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪያችን ጎራ ብለን አንድ አንድ ማለት ጀምረናል።ያም ሲያማ ያም ሲያማ፣ ወገኔ ለእኔ ብለህ ስማይላል በሚስረቀረቅ ድምፁ የሙዚቃው ንጉሥ። አንዱ ከመቀመጫው ተነስቶ፣30 ዓመታት ምን ተሠራ? መንገድ፣ ግድብ፣ የጋራ መኖሪያ ቤት፣ ወዘተ፣ ወዘተ፡፡ በእርግጥ ብዙ ለውጥ አየን ማለት አይቻልም፡፡ ጥያቄውመንገዱን እየፈነጨበት ያለው ማነው ነው? እስቲ መልስ ወዲህ በሉ…”  ሲል የግሮሰሪዋ ታዳሚዎች በአንድ ድምፅሌባው!” ብለው አስተጋቡ። ድንግጥ አልኩ። ሌላው ተነስቶ፣ብሶትን ቀብረን መልሰን ብሶት የምናምጥ ከሆነ፣ ለምን አንደኛችንን ድምፃችንን አዘግተን አንገላገልም?” ሲል ሰው አውካካ። ደግሞ ሌላው ተነስቶ፣ማሳሰቢያ አለኝ!” አለ።በልሲባልሳቃችሁን በቁጥጥር ሥር አውላችሁ ሳቁ ለማለት ነው። ምናልባት ከጣራ በላይ ስትስቁፊውዝተቃጥሎ ሳምንት መብራት እንዳይጠፋ፣ አመሠግናለሁ…ብሎ ገና ሳይቀመጥ ሌላ ሳቅ። እኔ በመገረምና ግራ በመጋባት ድባቡን አስተውላለሁ። ሁሉም ተቺ ነው። ሁሉም ጥያቄ አለው። ሁሉም አንደበቱ ለነገርና ለሒስ የሰላ ነው። እንዲያው ከዚህ ልማድ መቼ ይሆን የምንገላገለው? አይታወቅም!

 እኛስ ማን ነን? ሌባው የገዛ ዘመዴ፣ የገዛ ወገኔ፣ አብሬው የጠጣሁት፣ አብሬው የበላሁት አይዞህ አትፍራ ምን አባቱ ያልኩት አይደለም እንዴ?’ የሚል አንድ እንኳ የለም። ኋላ ውሎ አድሮ ለባሻዬ ትዝብቴን ስነግራቸው፣ንጉሥ ዳዊት ራሱን በአምላኩ ፊት ሲያይ ምን አለ መሰለህ?” አሉኝ፡፡ምን አለ?” ስላቸው “‘እኔስ ማን ነኝ? ቤቴስ ምንድነው?’ ነው ያለው፡፡ አየህጠቢብ ሰው ዓይኖቹ በገዛ መንገዱ ላይ ናቸውያለንን ጠቢቡ ሰለሞንን የወለደው እንግዲህ እሱ ነበር…አሉኝ። አላልኳችሁም? ዛሬያችሁ ላይ ጥያቄ ካላችሁ ልጅነታችሁን መርምሩት አላልኳችሁም? ታዲያ ተጠያቂው ማን ነው ጎበዝ? ጠያቂውስ? ‘ኧረ እኛስ ማን ነን? ጥያቄያችንስ የማን ነው?!’ ብለን ተለያየን፡፡ራስን የማወቅ ዘመን ያድርግልንብለዋል ባሻዬ። አሜን አትሉም? እንዲህም ሲሉ ጨምረዋል፡፡ ‹‹የተከላችሁትን ችግኝ ተንከባከቡ፣ ስትንከባከቡም ራሳችሁን ጠይቁ፣ ማን ነኝ? ወዴትስ ነው የምሄደው በሉ፡፡ አደራ የተተከለው የሚበቅለው ንፁህ ልቦና ሲኖር ነው…›› ብለዋል አዛውንቱ ባሻዬ፡፡ ከአጉል መካሪ የጠቢብ ተግሳጽ እንዲሉ አደራ ማለትስ አሁን ነው፡፡ መልካም ሰንበት

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት