Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየጥበቡ ጎታ መሐመድ አወል ሳላህ

የጥበቡ ጎታ መሐመድ አወል ሳላህ

ቀን:

ከ1980ዎቹ አጋማሽ ወዲህ እስከ የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ዋዜማ ድረስ በዓለማዊው የሙዚቃ መድረክ በወሎ አማርኛ ዘዬ ይበልጥ ይታወቅ ነበር፡፡ ከቀዳሚ የሙዚቃ ሥራዎቹ ውስጥ የመጀመርያው ረድፍ ላይ የሚደረደሩት ‹‹ከመከም››፣ ‹‹ንገሽ ባካላቴ›› እና ‹‹ነይ ድጌ›› ናቸው፡፡ በዘፈነውና የብዙኃኑን ቀልብ ከሳበበት አንዱ ነይ ድጌ ቅፅል ስሙ እንዲሆንለትም አድርጓል፡፡

ድምፀ መረዋው መሐመድ አወል ሳላህ በባለለዛ ቅላፄው ከአድማጭ ጆሮ ካደረሳቸው ሥራዎቹ መካከል ለአልበም (ካሴት) ከበቁት ሰምበል ገላ፣ ልሁን ደና፣ ቦረና ነው ቤቷ፣ ባለእንሶስላዋ፣ ንቦዬ፣ ወለባዬ፣ ዞማዬ፣ ኢትዮጵያ፣ ያለው ገለል ይጠቀሳሉ፡፡

ያለሙዚቃ መሣሪያ በመድረክም ሆነ በምሽት ክበቦች በማቀንቀን ረገድ ከተሳካላቸው አንዱ መሐመድ አወል ሳላህ ነው፡፡ ከያኒው መሐመድ አወል በቀድሞው የምድር ጦር ሠራዊት በኤርትራ በነበረው የ18ኛ ተራራ ክፍለ ጦር ባልደረባ ሆኖ አገራዊ ግዳጁን ሙዚቃን በማጥናት ጭምር መወጣቱ በገጸ ታሪኩ ተመልክቷል፡፡

የሚሌኒየሙ ዋዜማ ማለትም 2000 ዓም (ዓመት) መሐመድ አወል አዲስ የሕይወት መስመር የተለመበት ዓመት ነበር፡፡ ወደ እስላማዊ መንፈሳዊ እንጉርጉሮ የተሸጋገረበት ዘመን፡፡

‹‹ነሺዳ›› ተብሎ የሚጠራው እስላማዊ ተመስጧዊ እንጉርጉሮን የጀመረበት የአዲስ ቃና ስልት ተከትሎ የዘለቀበት ሆኗል፡፡

መንፈሳዊ ሕይወትን አጥብቆ በመያዝ ለእምነቱ ተከታዮች መንፈሳዊ ሕይወት የሚያገለግሉ ሦስት አልበሞችንና ነጠላ ነሺዳዎችን አበርክቷል፡፡ በሙንሺድነት ሕይወቱ በአልበሞቹ ከተካተቱት ውስጥ፡- የለኝ በጎ ሥራ፣ መሐመድ ተብዬ፣ እመስገጃሽ ላይ ታገሺ፣ ውዴታ እስከ ጀነት ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹ዑማ ኔትዎርክ›› ስለመሐመድ አወል ሳላህ ሥራዎች ከገለጸው ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡

‹‹ሥራዎቹ እስላማዊ ሥርዓት ላይ ያተኮሩ ምክሮች፣ በነፍስ ቅኝት የተበጁ የተውበትና የምልሰት እንጉርጉሮዎች፣ የጊዜን ዓውድ የሚቃኙ ታላላቅ የእስላም ባለሟሎችን ሰብእናዎች የሚያወድሱ፣ አላህንና መልዕክተኛውን የሚያልቁ የተስፋና የብሥራት የአይዟችሁ ባይነት ሐሳቦች ተላብሰዋል፡፡››

ዑማ ኔትወርክ ሐቲቱን ይቀጥላል፡፡ ‹‹የመሐመድ አወል ሳላህ እንጉርጉሮ ነሺዳዎች ለነፍስ የሚሰጡት ንግርት እልፍ ነው፡፡ ተዘክረው አያበቁም፡፡ ከሕይወትና ከእውነት ጋር በስውር ስፌት ተገምደዋል፡፡ …የዘመንን ምስቅልቅልን አይቶ አያልፍም ከዘመን እኩይ ድባብ እንድንሸሽ ያባብለናል፡፡››

በያኔው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት በደሴ ከተማ አራዳ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር፣ በ1958 ዓም ከእናቱ ከወ/ሮ ሰዓዲያ ሰዒድ አህመድና ከአባቱ ሐጂ ሳላህ አሕመድ የተወለደው መሐመድ አወል፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን በወ/ሮ ስሂን ትምህርት ቤት አጠናቋል፡፡ በውትድርና ተቀጥሮ አስመራ ከገባ በኋላ በሙዚቀኛነትም አገልግሎት መስጠቱ ይወሳል፡፡

ከጦሩ ከተሰናበተ በኋላ ወደ ሳውዲ ዓረቢያ በማቅናት ለሰባት ዓመታት ቆይቷል፡፡ ወደ አዲስ አበባ እንደተመለሰም በሳውዲ የቀጠለውን የሙዚቃ ሕይወት እስከ 2000 ዓ.ም. አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡

የሕይወቱን የመጨረሻዎቹ 13 ዓመታት በመንፈሳዊ ዐውድ የቃኘው መሐመድ አወል ሳላህ፣ ለረዥም ጊዜ ከርሱ ጋር በቆየው የልብ ሕመም ምክንያት ነሐሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. በ55 ዓመቱ አርፏል፡፡ ሥርዓተ ቀብሩም በማግስቱ በኮልፌ የሙስሊም መካነ መቃብር ተፈጽሟል፡፡ ሙንሺድ መሐመድ አወል ሳላህ ባለትዳርና የስድስት ልጆች አባት ነበረ፡፡

ነፍስ ኄር መሐመድ አወል በ‹‹መሐመድ ተብዬ›› እንጉርጉሮው፡-

‹‹ሕይወት ትርጉም አለው

ትርጉም ከተሰጠው

ሕይወት ጣዕም አለው

አላህ ሲያሰምረው›› ያለው እዚህ ላይ ለጥቅሰት ይበቃል፡፡

ሚንበር ቲቪ ስለ ሙንሺድ መሐመድ አወል ሳላህ የሰጠው ምስክርነት እነሆ፡፡

‹‹መሐመድ አወል ሳላህ የማኅበራዊ ግንኙነት፣ የሥርዓተ ጾታና ሌሎች የሥነ ምግባር ዝንፈቶችን የሚያርቁ፣ ልዕለ ኃያል ሐሳብ ያነገቡ በርካታ የእንጉርጉሮ ጸጋዎችን ሰጥቶናል፡፡ ሲሰጥ አልሰሰተም፡፡ አለመሰሰቱን በሚንበር ቲቪ በሚተላለፈው አፍላ የነሺዳና የእንጉርጉሮ ባለተሰጥዖዎችን የሚያወዳድረው ዳና ከዋክብት ላይ በትጋት ሲያሳይ ቆይቷል፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...