በቶኪዮ 2020 ፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያ በትዕግስት ገዛኸኝ አማካይነት አገኘች፡፡ የአፍሪካ ሻምፒዮኗ ትዕግስት፣ ቅዳሜ ነሐሴ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው በጭላንጭል የሚያዩ የ1500ሜ ሩጫ፣ የራሷን ምርጥ ሰዓት 4:23.24 በማስመዝገብ ነው ለፓራሊምፒክ አሸናፊነት የበቃችው፡፡ ትዕግስትን ተከትላ በ2ኛነት የገባችው አሜሪካዊቷ ሊዛ ኮሮሶ ስትሆን፣ ቱኒዝያዊቷ ሶማያ ቡሰይድ በ3ኛነት አጠናቃለች፡፡ ኢትዮጵያ አራተኛው ቀን ላይ በደረሰው 16ኛው የበጋ ፓራሊምፒክስ ጨዋታ የደረጃ ሰንጠረዥ በትዕግስት ወርቅ 35ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
በሌላ ዜና በዚሁ የፓራሊምፒክ ጨዋታ የእጅ ጉዳት ባላቸው የ1500 ሜትር ፍፃሜ ገመቹ አመኑ 5ኛ ወጥቷል፡፡ አመኑ ያስመዘገበው ጊዜ 03:56:04 የግሉ ምርጥ ሰዓት ነው። ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ የወጡት ሩሲያዊው ኢራማቹክ አሌክሳንደር፣ ቡልጋሪያዊው ስቶያኖቭ ሪስቲያን እና ዑጋንዳዊው ኢሞንግ ዴቪድ ናቸው፡፡