Sunday, February 5, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሸማቾች መብት ተቆርቋሪዎች ማኅበር ተቋቋመ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ጊዜ እየከፋ የመጣውን የዋጋ ንረት መነሻ በማድረግ፣ የሸማቾች መብት ተቆርቋሪዎች ማኅበር ተቋቋመ፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪዎች ማኅበር›› በሚል ስያሜ የተቋቋመው ቦርድ መር አገር በቀል ድርጅት መሥራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቁምላቸው አበበ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ በተለያየ መንገድ የንግድ እንቅስቃሴን የተመለከቱ ዘገባዎች በተለያዩ የኅትመት ደርጅቶች ሲያቀርቡ እንደቆዩ አስታውሰዋል፡፡  እነዚህን ዘገባዎች ተከትሎ ከሚያቀርቧቸው ምክረ ሐሳቦች አንዱ የሸማቾችን መብት የሚያስከብር ማኅበር ወይም ድርጅት ሊኖር ይገባል የሚለው ምክረ ሐሳብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አብዛኛው ከሸማቾች መብት ጋር የተገናኘው ጥያቄ ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ ስለሸማቹ  የሚቀርብ ጥያቄ ማስተጋባት እንቅስቃሴ በስፋት ሳይስተዋል እንደቆየ አቶ ቁምላቸው አስረድተዋል፡፡

ከላይ የተነሱትን ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ ሊነሱ ይገባል ከሚል መነሻ ማኅበሩን ለማቋቋም እንደተነሱ ያስታወቁት የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ማኅበሩ መሥራች፣ ፈቃድ ለማግኘት ግን የአዲስ አበባ ሸማቾች ማኅበር የሚል ተቋም መቋቋሙን መረዳታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሆኖም ችግሩ አገር አቀፍ በመሆኑ፣ በግንቦት 2013 ዓ.ም. ከሲቪል ማኅበራት ኤጀንሲ ተገቢውን ፈቃድ በማግኘት የኢትዮጵያ ሸማቾች መብት ተቆርቋሪዎች ማኅበር በሚል ስያሜ ማኅበሩ መመሥረቱን አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተስተዋለ ያለው የኑሮ ውድነት ባለፉት ሦስት ዓመታት ብቻ የመጣ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ቁምላቸው፣ ባለፉት 50 ዓመታት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮች ድምር ውጤት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ አገሪቱ ትከተል ከነበረው የኮሙዩኒዝም ርዕዮት ዓለም ወዲህ የነበረው ማኅበራዊ መስተጋብር እየሳሳ በመምጣቱ መተዛዘን እየጠፋ፣ ግለኝነት፣ ስስት፣ አንዱን ጥሎ የማለፍና በአቋራጭ የመክበር እንቅስቃሴዎች መስፋፋቱን አቶ ቁምላቸው ያስረዳሉ፡፡

ከ1984 ዓ.ም. ወዲህ አዲስ የመንግሥት ለውጥ ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ መንግሥት በኢንዶመንት ስም ባቋቋማቸው ድርጅቶች አማካይነት የ40 ዓመታት ፍኖታ ካርታ በማዘጋጀት፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚ 40 በመቶ የመቆጣጠር ዓላማን ያነገበ አካሄድን ሲከተል እንደቆየ ያስታወቁት አቶ ቁምላቸው፣ እነዚህ ድርጅቶች ግባቸውም ሰፊውን ኅብረተሰብ ለመጥቀም ሳይሆን የአገሪቱን ኢኮኖሚ መቆጣጠር ማለትም የፖለቲካና የማኅበራዊ እንቅስቃሴን መቆጣጠር ነው የሚል ዓላማን ያነገበ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዚህም  ምክንያት የአገሪቱ ገበያ እንደተናጋ ያስታወሱት አቶ ቁምላቸው፣ የባንክ ብድር የሚሰጥበት መንገድ፣ ብር የዋጋ ግሽበትን ታሳቢ ሳያደርግና ሌሎች የኢኮኖሚና ፊስካል ፖሊሲዎችን ታሳቢ ሳያደርግ ሲታተም እንደቆየ ይናገራሉ፡፡

‹‹ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ከአገሪቱ አቅም በላይ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውና የአገሪቱ የገንዘብ የመግዛት አቅም እያሽቆለቆለ መምጣቱ፣ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበትና የዋግ ንረትን አስከትሎ አሁን ላለንበት ደረጃ አድርሶናል፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በኬላዎች የሚደረገው ፍተሻ የላላ በመሆኑ ምክንያት፣ በኮንትሮባንድ የሚመጡ ዕቃዎች ቀጥታ ወደ ገበያ በመግባት ሲፈጠር የነበረው ቀውስ በዚህ ወቅት ለተፈጠረው ምስቅልቅል የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበት ተጠቃሾቹ ጉዳዮች እንደሆኑ ማኅበሩ ያምናል ብለዋል፡፡

ኢኮኖሚና ገበያ በራሱ ሰላምናና መረጋጋትን የሚፈልግ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ቁምላቸው ግጭት፣ ጦርነትና ሽብር በአንድ አገር ውስጥ ካሉ ገበያና ኢኮኖሚ እንደሚታመሙ አስታውቀዋል፡፡

የሸማቾች መብት ተቆርቋሪ ማኅበር ዋነኛ ዓላማ ሸማቾች ምርትን፣ ሸቀጥን ወይም አገልግሎትን ለትርፍ ሳይሆን ለፍጆታ የሚገዙ እንደሆነ ገልጸው፣ በዚህ ረገድ ሁሉም ሕዝብ ሸማች ነው ለማለት እንደሚቻል፣ አንድ ቦታ ላይ ቸርቻሪ የሆነው ሌላ ቦታ ሸማች ሆኖ እንደሚገኝ ልብ ሊባል ይገባል ይላሉ፡፡

ሸማቹ ገበያን ለማረጋጋት፣ በኢኮኖሚ ላይ ወሳኝ ሚና ለመጫወት፣ የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ትልቅ ሚና እንዳለው፣ ሚና ብቻም ሳይሆን ገበያን እስከ መወሰን የሚያስችል ጉልበትም አለው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ይህ ጉልበት በተለያየ መንገድ ሊገለጽ እንደሚችልና የፖሊሲ ሐሰቦችን በማመንጨትና ግፊት በማድረግ፣ ምርትን ከተባለው ዋጋ ለሽያጭ በሚቀርብበት ወቅት በተባለው ዋጋ ላለመግዛት በማመፅና በገበያ ሕግ እንዲመራ በማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ሸማቾች በሰው ሠራሽ ገበያ ሳይሆን በገበያ ሕግ እንዲመራ ለማድረግ የሚያስችል መብት እንዳላቸው ግልጽ ቢሆንም፣ አብዛኛው ሸማች ግን ይህን አያውቅም ብለዋል፡፡

በነፃ ገበያ ስም ስድ የተለቀቀውን ገበያ ሥርዓት ማስያዝ አንዱ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነ ያሳሰቡት አቶ ቁምላቸው፣ የፖለቲካ ውሳኔ የሚመስል በጥቂት ነጋዴዎች ላይ የሚወሰደው ዕርምጃ ብቻውን ዘላቂ ለውጥ እንደማያመጣና ከሁሉ ነገር በላይ የመንግሥት ቀዳሚ ሥራ ሊሆን የሚገባው የግብይት ሥርዓቱን ማስተካከል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ መንግሥት ፍላጎትና ቁርጠኝነት ካለው ይህን ጉዳይ የሚመለከተው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማን አስመጪና አምራች፣ ማን አከፋፋይ መሆኑን ጠንቅቆ እንደማወቁና የግብይት ሰንሰለቱን ከዋናው ቦታ እስከ ታች ገበያ ድረስ ያለውን ሒደት እንደመረዳቱ፣ ይህ ቁርጠኝነት አለው ወይ የሚለው ጉዳይ መሠረታዊ ጥያቄ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ያስረዳሉ፡፡

የግብይት ሥርዓቱ ተፅዕኖ በአቅርቦትና በፍላጎት፣ እንዲሁም ወረርሽኝ በኮሮና ተስተጓጉሏል የሚለው ጉዳይ ብዙም አሳማኝ እንዳልሆነ ያስረዱት አቶ ቁምላቸው፣ ያለው ተፅዕኖ የሚካድ ባይሆንም ዋነኛው ተፅዕኖ ፈጣሪው ጉዳይ የግብይት ሥርዓቱ ብልሹ መሆን እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ይህንን የግብይት ሥርዓት ሳይስተካካል መንግሥት በድጎማ ዘይት፣ ስኳርና የመሳሰሉትን የምግብ ፍጆታ ሸቀጦች ቢያመጣ የኅብረተሰቡን ችግር እንደማይፈታ ይናገራሉ፡፡

በድጎማ ከሚመጣው ሸቀጥ 70 በመቶው ለነጋዴዎች መቅረቡ ለሸማቹ የማያስብ የንግድ ማኅበረሰብ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ተገቢ እንዳልሆነ የገለጹት አቶ ቁምላቸው፣ ቢቻል በድጎማ የሚመጡ ሸቀጦችን ሙሉ በሙሉ ለሸማቾችና ለክልሎች ማከፋፈል፣ ካልተቻለም የክፍፍል ምጣኔውን ማስተካከል እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡

በሌሎች አገሮች እንደሚደረገው የትርፍ ህዳግ የሚባለው ጉዳይ በኢትዮጵያም ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት ማኅበሩ ያስታወቀ ሲሆን፣ በሚገባ ተጠንቶ በመጀመርያ በመሠረታዊ ሸቀጦችና ምርቶች የትርፍ ህዳግ ሊኖር እንደሚገባ ተመላክቷል፡፡

ረዥም ሒደቶችን በማለፍ በግንቦት ወር ፈቃዱን እንዳገኘ ያስታወቀው ማኅበሩ፣ በተለይ አንገብጋቢውን የኑሮ ውድነት በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ደብዳቤዎችን እንዳስገባ ገልጾ፣ ሆኖም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በኩል ምላሽ እንዳልተገኘ አስታውቋል፡፡

ከሸማቾች ማቋቋሚያ አዋጅ በአንቀጽ 25  ላይ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶችን ዋጋ ስለመወሰን ይገልጽና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ፣ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዋጋ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡ መሠረታዊ የንግድ ዕቃዎችና አገልግሎቶች ላይ ያደረገውን ጥናት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ በማስፈቀድ ዝርዝራቸውንና ዋጋዎቻቸውን በሕዝብ ማስታወቂያ ላይ ሊያወጣ እንደሚችል ያስረዳል፡፡ ዋጋው በመንግሥት ተወስኖ በሕዝብ ማስታወቂያ የተገለጸን መሠረታዊ የንግድ ዕቃ ወይም አገልግሎት ከተወሰነው ዋጋ በላይ መሸጥ፣ ወይም ለመሸጥ መሞከር የተከለከለ መሆኑን  እንዲሁ አዋጁ ያስረዳል፡፡

ምንም እንኳን በአዋጁ ላይ የሠፈረው ለሸማቾች መብት የቀረበውን ጉዳይ በዝርዝር ቢያስረዳም የተለያዩ የኢኮኖሚ ምሁራን እንደሚገልጹት፣ የሸማቾችን መብት በማስከበር ረገድ የሚንቀሳቀሱ አካላት እምብዛም አለመኖራቸው፣ ቢኖሩም በተገቢው መጠን ባለመንቀሳቀሳቸው ሸማቾች በየጊዜው በሚያጋጥማቸው ጭማሪ ምክንያት የኑሮ ውድነትን ለመጋፈጥ መገደዳቸውን ያስረዳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች