Saturday, June 15, 2024

የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ለአገር አይበጅም!

ኢትዮጵያ በታሪኳ እጅግ የገዘፈ የሰብዕና ባለቤት የሆኑ ልጆቿን በተለያዩ ዘመናት ዓይታለች፡፡ በጦር ሜዳ ሕይወታቸውን ከገበሩላት፣ ደማቸውን ካፈሰሱላትና አጥንታቸውን ከከሰከሱላት በተጨማሪ፣ በተለያዩ መስኮች ስሟን ያስጠሩ ጀግኖች ልጆች ነበሯት፡፡ ዛሬም እንደሚኖሩ ምንም ጥርጥር የለም፡፡ በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ከልጆቿ ብዙ ነገሮች ትፈልጋለች፡፡ አስተማማኝ ሰላም፣ በሕግ የበላይነት ሥር የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትና ፍትሐዊ የሆነ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን መሻቶች ዕውን ለማድረግ ግን፣ በተለይ በምሁርነትና በልሂቅነት ካባ ውስጥ የተሸፈኑ ወገኖች ሰከን ማለት አለባቸው፡፡ ይህ ስክነት የሚያስፈልገው አገርን ወደ ቀውስ ከሚያንደረድሩ አላስፈላጊ ድርጊቶች ለመታቀብ ብቻ ሳይሆን፣ በሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተሳትፎና ይሁንታ ሰላሟና ደኅንነቷ አስተማማኝ የሆነ አገር ለመገንባት ጭምር ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ አገርን የማያስቀድም የፖለቲካ ዓላማም ሆነ አጀንዳ እንዳይኖር የሚታገሉ ምሁራንና ልሂቃን ማስፈለጋቸው አያጠራጥርም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሀቀኝነት፣ ቅንነትና ሰብዓዊነት ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን ሳያሟሉ በሸፍጥና በሴራ ፖለቲካ በሕዝብ ስም መነገድ የለየለት ቁማርተኝነት ነው፡፡ አገር ከባድ ችግር ውስጥ ሆና የመፍትሔ ያለህ ሲባል የሚያዋጣውንና የሚያዛልቀውን መንገድ ማመላከት ሲገባ፣ ቀውስ የሚያባብስና ኢትዮጵያዊያንን የሚነጣጥል ድርጊት ውስጥ መገኘት ተገቢ አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያ አይበጃትምና፡፡ 

በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሠልጥነናል የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ምሁራንና ልሂቃን ደሃ አገር ውስጥ መኖራቸውን እስኪረሱ ድረስ፣ ማኅበራዊ የትስስር ገጾች ውስጥ መሽገው አገር ሊያፈርሱ የሚችሉ ቅስቀሳዎች ውስጥ ተሰማርተዋል፡፡ ስሜታውያንን በጭፍን በመንዳት ግጭት እየቀሰቀሱ ለንፁኃን ሞትና መፈናቀል ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ በተማሩት ሙያ አገር ማሳደግና በሕግ የበላይነት የሚመራ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ዕገዛ ማድረግ ሲጠበቅባቸው፣ እነሱ ግን ጎራ ለይተው ምስኪኑን ሕዝብ በማንነትና በእምነት ጭምር ለማፋጀት አቅላቸውን ስተዋል፡፡ በኃይለኞች አፈና ምክንያት ድምፃቸው ጠፍቶ የነበሩት ሳይቀሩ፣ የነፃነትን ዋጋ በአግባቡ መረዳት አቅቷቸዋል፡፡ ነፃነትን ለአምባገነንነት ገጸ በረከት የሚያቀርቡ ድርጊቶች ውስጥ ተዘፍቀዋል፡፡ ከንቱ ፉከራ ውስጥ ሆነው መደማመጥን አጥፍተዋል፡፡ ከጦርነት በመለስ ሌሎች አማራጮች የሌሉ ይመስል፣ ነጋ ጠባ የጦርነት ነጋሪት ይጎስማሉ፡፡ እነዚህ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች የዴሞክራሲን መሠረታዊ ጽንሰ ሐሳቦች እየተጋፉ፣ ኢትዮጵያን ወደ ገደሉ ጠርዝ እየገፉ ለማፈራረስ እያመቻቹ ነው፡፡ በሸፍጥና በሴራ ፖለቲካ አገር ሲፈርስ እንጂ ሲገነባ ታይቶ አይታወቅም፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አደገኛ ድርጊት መታቀብ ይገባል፡፡

‹የምትለብሰው የላት የምትከናነበው አማራት›› እንደሚባለው፣ በአሁኑ ጊዜ በድህነትና በኋላቀርነት በምትማቅቅ አገር ውስጥ ተማርን ባዮች ማገናዘብ አቅቷቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ከገባችበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት መረባረብ ሲያዋጣ፣ የጎሳ አጥር ውስጥ ሆነው በገሃድ የሚቃዡ ምሁራን ተብዬዎች እንደ እንጉዳይ ፈልተዋል፡፡ ኢትዮጵያ እጀግ በጣም ሰፊ ለም መሬት፣ አመቺ የሆነ የአየር ንብረትና ጠንካራ ወጣት የሰው ኃይል ይዛ ትራባለች፡፡ የአፍሪካ የውኃ ማማ ሆና ትጠማለች፡፡ የገዘፈ ታሪክ ባለቤት ሆና የአገሮች ጭራ ናት፡፡ አሁንም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት ተመጣጣኝ ምግብ ስለማያገኙ ይቀነጭራሉ ወይም ይሞታሉ፡፡ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ካሉት በታች፣ ከሞቱት በላይ ሆነው ከአንገፍጋፊ ድህነት ጋር ይኖራሉ፡፡ ሚሊዮኖች መጠለያ አልባ ናቸው፡፡ በከተሞች በሚያሳፍር ሁኔታ የከተማ ነዋሪዎች የትራንስፖርት፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክና የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን የሚያገኙት በኋላቀር አሠራሮች ነው፡፡ አዲስ አበባን ጨምሮ ብዙዎች ከተሞች የቆሻሻ መጣያ ናቸው፡፡ የደሃ ደሃ አገር ታቅፎ እንደ ደላቸው አገሮች ግጭት በመቀስቀስ መተራመስ ትዝብት ላይ ይጥላል፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ ጦርነት ውስጥ ተገብቶ  ንፁኃን ሲያልቁና ሲፈናቀሉ ምሬቱ ከባድ ነው፡፡ ይህ አደገኛ ድርጊት በፍጥነት ሊቆም ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ ከትናንት የተሻለ ሥርዓት ተገንብቶ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ በሰላምና በነፃነት እንዲኖሩ፣ በሸፍጥና በሴራ ፖለቲካ መቆመር ሲያበቃ ነው፡፡ በመቀጠል ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት፣ በሕግ የበላይነት የሚያምንና ተግባራዊ የሚያደርግ መንግሥታዊ ሥርዓት መመሥረት ሲቻል ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች መልክ እየያዙ መጠናከር ሲቻል፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አንፀባራቂ አገር መሆን ትችላለች፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን ከራስ በፊት ለአገር የሚሉ ምሁራንና ልሂቃን በአደባባይ በርክተው መታየት አለባቸው፡፡ በአደባባይ ሰላምን እየደሰኮሩ ውስጥ ውስጡን ሴራ መጎንጎን ደግሞ ለአገር ጥፋት እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡ በዚህ ዓይነት ድርጊት የተካኑ በሚፈጥሩት ችግር በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ  ወገኖች መፈናቀላቸውና በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን መገደላቸው ከቶውንም ሊረሳ አይገባም፡፡ በግጭት ነጋዴዎች አማካይነት እየደረሰ ያለው ፈተና የአገርን ካስማና ማገር እየነቃቀለ መሆኑን መዘንጋትም ተገቢ አይደለም፡፡ የአንድን ቡድን ፍላጎት ለመጫን ብቻ ሲባል የሚደረገው ትንቅንቅ፣ አገርን ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንደከተተ የታወቀ ነው፡፡ አገር አፍራሽ ድርጊት ውስጥ የተሰማሩ ኃይሎች ሊበቃቸው ይገባል፡፡ 

በዚህ ወሳኝ ወቅት በአገር ጉዳይ ላይ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ውይይቱ ግን ገንቢና ሁሉንም ወገን ማዕከል ሲያደርግ መደማመጥ ይለመዳል፡፡ መደማመጥ ሲኖር ልዩነትን ይዞ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር አዳጋች አይሆንም፡፡ ከዚህ ቀደም መነጋገርና መደማመጥ ባለመቻሉ ምክንያት በርካታ ወርቃማ ዕድሎች አምልጠዋል፡፡ እነዚያ ዕድሎች ባይመክኑ ኖሮ ሞት፣ ሥቃይ፣ እስራትና ስደት የበርካታ ኢትዮጵያውያን ዕጣ ፈንታ አይሆኑም ነበር፡፡ የሕግ የበላይነት እየተደረመሰ አምባገነንነት አይፈነጭም ነበር፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱ ዜጎች በገዛ አገራቸው ባይተዋር አይሆኑም ነበር፡፡ ላባቸውን እያንጠባጠቡ የሚሠሩ ሚሊዮኖች እየደኸዩ፣ ከዘራፊ ባለሥልጣናት ጋር የተወዳጁ ጥቂት ቅንጡዎች ሚሊየነሮች አይሆኑም ነበር፡፡ ሕገወጥነት በሕጋዊነት ላይ የበላይ መሆን የቻለው የሕግ የበላይነት በመደርመሱ ነው፡፡ ከዚህ መሰሉ የሰቆቃ ታሪክ ውስጥ በመውጣት ኢትዮጵያን የሰላም፣ የነፃነት፣ የብልፅግናና የዴሞክራሲ አምባ ማድረግ ይቻላል፡፡ የሚቻለው ግን ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ብቻ ዕድሉን በማመቻቸት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ከተቻለ ሰላም በምድሪቱ ላይ ይናኛል፡፡ ሰላም እንዲኖር ደግሞ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ልዩነቶቻቸውን አክብረው በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ ከሸፍጥና ከሴራ ፖለቲካ የሚገኘው ውድቀት ብቻ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ሰላም የሚገኘው ግን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሰላማዊ ሲሆኑ ብቻ ነው፡፡ አንደኛው ወገን ሰላም ለማስፈን ሲታገል፣ ሌላው ወገን በየሥርቻው እሳት የሚጭር ከሆነ በወንፊት ውኃ መቅዳት ነው የሚሆነው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በመግራት ወደ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ዓውድ ውስጥ መግባት የሚቻለው፣ ሁሉም ምሁራንና ልሂቃን ከሸፍጥና ከሴራ ሲፀዱ ነው፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ባለህበት እርገጥ ፖለቲካ ያተረፈው ሞት፣ እስር፣ ሥቃይና ስደት ብቻ ነው፡፡ ይህንን አሳፋሪና ኋላቀር ፖለቲካ በመተው ሥልጡን ፖለቲካ ማራመድ የሚበጀው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓት መገንባት ነው፡፡ የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ውጤቱ አገር ማፍረስ ነው፡፡ ሁሉንም ወገኖች የሚያግባባ ዴሞክራሲያው ሥርዓት ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሕ ይገኙበታል፡፡ ለፀብና ለመተናነቅ በር አይከፍትም፡፡ ሁሉም ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ይከበራሉ፡፡ በፖለቲካው መስክ ከሚያስፈልጉ ዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች መካከል አንዱ ሰላም ስለሆነ፣ ሰላም ሲሰፍን የሚፈለገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት አስተማማኝ ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ስለዚህም ምሁራንና ልሂቃን ከሸፍጥና ከሴራ ፖለቲካ ይታቀቡ፡፡ ለአገር አይበጅምና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...

የ‹‹ክብር ዶክትሬት›› ዲግሪ ጉዳይ

በንጉሥ ወዳጅነው ‹‹የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ግልጽ የሆነ መመርያ እስኪወጣ ድረስ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባለሥልጣናት የሚቀስሙት ልምድ በጥናት ይታገዝ!

ሰሞኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የተመራ የከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ልዑክ፣ ከሲንጋፖር ጉብኝት መልስ በሁለት ክፍሎች በቴሌቪዥን የተገኘውን ልምድ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ለአገር...

የዘመኑ ትውልድ ለአገሩ ያለውን ፋይዳ ይመርምር!

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ኢትዮጵያን የሚያስፈልጓት ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ከብዙዎቹ በጣም ጥቂቱን አንስተን ብንነጋገርባቸው ይጠቅሙ ይሆናል እንጂ አይጎዱም፡፡ ኢትዮጵያም ሆነች ብዙኃኑ ሕዝቧ ያስፈልጓቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ...

ከግጭት አዙሪት ውስጥ የሚወጣው በሰጥቶ መቀበል መርህ ነው!

የኢትዮጵያን ሰላም፣ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅሞች ማዕከል በማድረግ መነጋገር ሲቻል ለጠብ የሚጋብዙ ምክንያቶች አይኖሩም፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ክንውኖች በሙሉ ከጥፋት የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም፡፡ በኢትዮጵያ ዘርፈ...