በአገሪቱ የንግድ ሥራ ትምህርት ፈር ቀዳጅ የሆነውን የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት (ኮሜርስ) ከይዞታው ለማንሳት የተላለፈውን ውሳኔ፣ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በድጋሚ ሊያጤኑት እንደሚገባ ተመከረ፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት 17ኛውን ዓመታዊ አገር አቀፍ የምርምር ጥናት ሲምፖዚየም፣ ቅዳሜ ነሐሴ 22 እና 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በንግድ ሥራ ኮሌጅ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አከናውኗል፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ የተለያዩ ከቢዝነስ ኢንዱስትሪው ጋር በተገናኘ የተሠሩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ከጥናቱ ጎን ለጎን የንግድ ሥራ ትምህርት ቤቱ ከየት ተነስቶ የት ደረሰ? አሁንስ የገጠመው ተግዳሮት ምንድነው? በሚሉ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይት ቀርቧል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከሳምንታት በፊት በተለምዶ ሠንጋ ተራ በሚባለው አካባቢ ያለው የአዲስ አበባ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንዱ አካል እንደሆነ አስታውሶ፣ መንግሥት አካባቢውን ለልዩ አገልግሎት ማለትም የአገሪቱን የፋይናንስ ማዕከል አድርጎ እያደረጀ በመሆኑ፣ በንግድ ሥራ ትምህርት ቤቱ የሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ውስጥ ተጠቃለውና አንድ ላይ በመዋቀር እንዲሠራ መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ከይዞታው ጋር የተገናኘው ጉዳይ መንግሥት በሚያስቀምጠው አቅጣጫ መሠረት የሚስተናገድ እንደሆነ ያስታወቀው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ መቼ ይፈርሳል? ምን ይሆናል? የሚለው በሒደት የሚታወቅ እንደሆነና በቀጣይ በመንግሥት አቅጣጫ መሠረት እንቅስቃሴው የሚቀጥል እንደሆነ መገለጹ አይዘነጋም፡፡
ባለፈው ቅዳሜ የተካሄደውን የፓናል ውይይት የመሩት የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ኃላፊ ወርቁ መኮንን (ዶ/ር) ባቀረቡት የመነሻ ጥናት እንዳስታወቁት፣ ትምህርት ቤቱ የአገር ቅርስ ነው፡፡ ብዙ ተማሪዎች የወጡበትና አሁንም እየተማሩ የሚገኙበት ተቋም እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ በአገር ውስጥ ያለ ቁጥር አንድ የቢዝነስ ተቋም እንደ መሆኑ መጠን፣ በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መነሻ ሐሳብ ወይም ካሪኩለም የሚሰጥ እንደሆነ ያመላከቱት ኃላፊው፣ ይህንን አበርክቶ ያደረገ ትምህርት ቤት ከቦታው እንዲነሳ ማድረግ ምናልባት ፖሊሲ አውጪዎች ሳይገነዘቡት የወሰኑት ጉዳይ ነው ለማለት የሚያስደፍር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ኃላፊው ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ምናልባት ቦታውን የፈለጉት አካላት ለውሳኔ የዳረጋቸው ምክንያት ራሱን ለቻለ ጥሩ ነገር ነው ተብሎ ይታሰባል ብለው ይሆናል፡፡ ሆኖም ይቋቋማል ተብሎ ከታሰበው አገልግሎት ይልቅ ትምህርት ቤቱ በቦታው ላይ መቆየቱ፣ ከዚያ በላይ ይጠቅማል ብሎ ለፖሊሲ አውጪዎች ማስገንዘብ ከራሱ ከንግድ ሥራ ትምህር ቤት የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡
በዚህ ወቅት ትምህርት ለፖሊሲ አውጪዎች ግንዛቤ የመስጠት እንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ ያስታወቁት ወርቁ (ዶ/ር)፣ በደፈናው እነዚህ ተቋማት ልክ አይደሉም ብሎ መነሳት ሳይሆን ግንዛቤ በማስጨበጥ ላይ ያተኮሩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የሚመለከታቸው አካላት በተዘጋጀው የውይይት ፎረም ላይ ይገኛሉ በማለት የተጋበዙ ቢሆንም አንዳቸውም ሊመጡ አልቻሉም ያሉት ኃላፊው፣ በአንድ በኩል የሚታየው ነገር ተወስኗልና ውሳኔን መቀልበስ አይቻልም ወይም በዚያ ላይ መከራከር አይቻልም የሚል ስሜት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ለአንድ አገር ዓላማ እስከተሠለፈ ድረስ በጉዳዩ ላይ መወያየት ይጠበቅበታል ብለው፣ በዚህ ወቅት የትምህርት ቤቱ ማኅበረሰብ የሚፈልገው ጉዳይ ቢኖር በግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎች የሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን እንዲገነዘቡትና ውሳኔያቸውን በድጋሚ እንዲያጤኑ ማድረግ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ከተመሠረተበት ከ1935 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርተ ተቋማት ታሪክ የራሱ የሆነ ድርሻ የተወጣ እንደሆነ በፓናል ውይይቱ ወቅት የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ሁለቱንም ፆታዎች በንግድ ነክ ትምህርቶች አሰባጥሮ በማስተማር ረገድ፣ በውጭ አገር ዜጎች ኃላፊነት ሥር የነበረውን አብዛኛውን የትምህርት ተቋማት አስተዳደር ወደ ኢትዮያውያን አስተዳደራዊ አሠራር በማስተካከል የራሱን ሚና እንደተጫወተ ተጠቅሷል፡፡
ኮሌጁ ባለፉት 80 ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የተማረ የሰው ኃይል አፍርቷል ያሉት ወርቁ (ዶ/ር)፣ ሲጀመር በአሥራዎቹ አኃዞች የነበሩትን ተማሪዎች ቁጥር በዚህ ወቅት በሺዎች ቤት ለማድረስ እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የፈጠራ ውጤትን በአገሪቱ ከማሳየት አኳያ የአማርኛ ታይፕ ለመጀመርያ ጊዜ የተፈለሰፈበት ተቋም እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በዚህም በአገልግሎት ሰጪ ቢሮዎች የነበረውን የጽሑፍ ተግባቦት እንቅስቃሴ በቀጥታ በአገሪቱ ቋንቋ እንዲሰጥ ማስቻሉን፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሚከናወኑ ችግር ፈቺ ምርምሮችና ጥናቶች ከሚያቀርቡ ተመራማሪዎች መካከል የኮሜርስ ተማራማሪዎች ተጠቃሾቹ እንደሆኑ ተመላክቷል፡፡
የንግድ ሥራ ትምህርት ቤቱ ከአጀማመሩ የሚሰጣቸው ትምህርቶች ገበያውን መሠረት አድርገው የሚቀረፁ እንደነበሩ የተወሳ ሲሆን፣ ሆኖም ትምህርት ቤቱ ሲቋቋም ጀምሮ በተለያዩ አካላት በተለይም አስተዳደር ላይ ባሉ ሰዎች ስለትምህርት ቤቱ የዕውቅና አረዳድ ችግር እንደነበረና በተለይም የንግድ ቸርቻሪዎችን ለማፍራት የተቋቋመ ትምህርት ቤት ነው ብሎ የማሰብ ዝንባሌ መኖሩን ወርቁ (ዶ/ር) አስታውሰዋል፡፡ አሁንም 80 ዓመት ያገለገለን ተቋም ለማፍረስ መዘጋጀት ከአረዳድ ክፍተት የሚመነጭ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡
ትምህርት ቤቱ ገበያ ተኮር የሆኑ ካሪኩለሞችን በመቅረፅ የገበያውን ፍላጎት በማጣጣም አስፈላጊ ክህሎት ያላቸውን ዜጎች የሚፈሩበት ተቋም ሆኖ ሳለ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ረገድ ያለውን አስተዋጽኦ በግልጽ ካለመረዳት በመንግሥት አካላት ገቺ ሁኔታዎች እየገጠሙት እንደሆነ ፓናሊስቶቹ አመላክተዋል፡፡ ሁሉም ፖሊሲ አውጪዎችና የመንግሥት አካላት ትምህርት ቤቱ በአገሪቱ ያለውን አስተዋጽኦ በመመልከት፣ የተሻለ የውሳኔ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባቸውም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል፡፡
የማርኬቲንግ ማኔጅመንት መምህርና አማካሪ አቶ መቅደላ መኩሪያ በፓናል ውይይቱ ወቅት ሲያስረዱ፣ ትምህርት ቤቱ ገበያውን በማየት ገበያው ውስጥ ምን ክፍተቶች አሉ? የሚለውን በመለየት የተለያዩ የትምህርት ክፍሎችን እንደሚቀርፅ፣ በሌላ በኩል አገሪቱ ከምትገኝበት ነባራዊ ሁኔታ በዘለለ በቀጣዮቹ ጊዜያት በአገሪቱ ሁኔታ ምን ሊፈለግ ይችላል? የሚለውን ፍላጎት በማየት ተፈላጊውን የትምህርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡
የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ካለበት ቦታ ቢነሳ ምን ሊፈጠር ይችላል የሚለው ሲታሰብ፣ አንድ በተቋሙ የሚማር ተማሪን ተስፋ እንደማደብዘዝ ይቆጠራል ያሉት አቶ መቅደላ፣ ይህም በአቅራቢያው ያሉ የፋይንስ ተቋማትን እየተመለከተ ራሱን የሚያዘጋጅበትን ጉዳይ እንደሚያስብና ከኢንዱስትሪው አንፃር የንግድ ሥራ ትምህርት ቤቱ የሚገኘው በትክክለኛ ቦታ እንደሆነ ገልጸው፣ ይህ በመሆኑም የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስሩን በይበልጥ ለማጠናከር የሚረዳ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
በ1910 ዓ.ም. የኢትዮ ጅቡቲ የባቡር መስመር ተጠናቆ አዲስ አበባ ሲደርስና ማዕከሉን ለገሃር ሲያደርግ የኢትዮጵያ ብሎም የአዲስ አበባ የንግድና የኢኮኖሚና ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በተለምዶ ለገሀርና በዚህ ወቅት የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ወደ የሚገኝበት አካባቢ እንዳዘነበለ በፓናል ውይይቱ ወቅት የተነሳ ሲሆን፣ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤትም የዚህ ስበት አካል ወይም ማዕከል ለመሆን በቅቷል ተብሏል፡፡
ለዚህ ሐሳብ ማሳያ ከሆኑት ነገሮች መካከል የአገሪቱ ዋና ዋና አገልግሎት ሰጪ የንግድና የፋይናንስ ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤቶች የተገነቡት በተቋሙ ዙሪያ እንደሆነ፣ ለአብነትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵየ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትና ሌሎችም እንደሚጠቀሱ፣ ሒደቱ ቀጥሎም የኢትዮጵያ መድን ድርጅትና የጉዞ ወኪሎች፣ ሆቴሎችና በቅርቡ ደግሞ የተለያዩ ባንኮችና የንግድ ዋና መሥሪያ ቤቶች ግንባታ ገቢር እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡ ለእነዚህ ተቋማት ዋነኛ የሠለጠነ ሰው ኃይል አቅራቢ የንግድ ሥራ ትምህር ቤት መሆኑ የተቋሙን ማዕከልነት የሚያጎላው እንደሆነ፣ በፓናል ውይይቱ ወቅት የተነሳ ጉዳይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ ያሉት የንግድ ባንኮች በሚያቀርቡት የሊዝ መሬት ፕሮፖዛል መሠረት፣ በተለምዶ ሠንጋ ተራና አካባቢው ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መሬትን በወቅታዊ የሊዝ ዋጋ መሠረት መሬት ማቅረብ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ለፋይናንስ ተቋማቱ የሚቀርበው መሬት ትክክለኛ ሥፍራና መጠነ ስፋት የከተማ አስተዳደሩና ተቋማቱ በሚያደርጉት የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት እንደሚሆን ከዚህ ቀደም የተጠቀሰ ሲሆን፣ መንግሥት አካባቢውን የፋይናንስ ተቋማት መናኸሪያ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ በተደጋጋሚ ጊዜ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
የሠንጋ ተራ አካባቢ በአገሪቱ ውስጥ ትልልቅ የሆኑት የፋይናንስ ማዕከላት መገኛ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በዚህ ወቅት ብቻ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ዘመን ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ አዋሽ ኢንሹራንስ፣ ኒያላ ኢንሹራንስ፣ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ ንብ ባንክ፣ ኅብረት ባንክ፣ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክና ሌሎች ተቋማት ዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውንና ለተለያዩ አገልግሎት የሚጠቀሙባቸውን ሕንፃዎች እየተገነቡበት ነው፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ስለመፍረሱ በጽሑፍ የደረሰ ምንም ዓይነት ነገር እንደሌለ ወርቁ (ዶ/ር) አስታውሰው፣ ነገር ግን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጠራው ስብሰባ ትምህርት ቤቱ አሁን ካለበት ቦታ ተነስቶ ወደ ሌላ ቦታ እንደሚዘዋወር እንደተገለጸ ተናግረዋል፡፡
ሪፖርተር በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው እንቅስቃሴ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ዋና ዳይሬክተርን በተደጋጋሚ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም፣ ስልክ ባለመነሳቱ ምክንያት የቢሮውን ምላሽ ማካተት አልተቻለም።