የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) ለ2022 ኳታር ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን አርብ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ያደርጋል፡፡ የብሔራዊ ቡድኑ 23 ተጫዋቾች የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታቸውን ለማድረግ ማክሰኞ ነሐሴ 25 ቀን ወደ ስፍራው አቅንቷል፡፡
በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድኖች ጋር ተደልድሏል፡፡
ዝግጅቱን ከነሐሴ 4 ቀን ጀምሮ በአዳማና በባህርዳር ሲያደርግ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ፣ ከዑጋንዳና ሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድኖች ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርጓል፡፡
በአጠቃላይ 28 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን ሲያደርግ የቆየው ብሔራዊ ቡድኑ፣ አምስት ተጫዋቾችን ቀንሷል፡፡ ከቀናት በፊት የመጨረሻ ተመራጮችን ይፋ ያደረገው አሠልጣኝ ውበቱ፣ ባህር ዳር ላይ ከዑጋንዳ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገው 2ለ1 በረቱበት ዕለት የፋሲል ከነማው ሱራፌል ዳኛቸው፣ የኢትዮጵያ ቡናው ዊሊያም ሰለሞን፣ የባህር ዳር ከተማው ፍጹም ዓለሙ፣ የድሬዳዋው ከነማ ፍሬው ጌታሁንና በዛብህ መለዮ በፈጸሙት የዲሲፕሊን ግድፈት ከቡድኑ ውጪ ሆነዋል፡፡
ዋሊያዎቹ አርብ የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ካደረጉ በኋላ ጳጉሜን 2 ቀን በባህር ዳር ስታዲየም ዚምባቡዌን ያስተናግዳሉ፡፡
ከስምንት ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ የተመለሰው ብሔራዊ ቡድኑ በጥሩ መነቃቃት ላይ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ ከተጋጣሚው ጋና ጋር ተመሳሳይ በሆነ አየር ንብረት ባለበት አዳማና ባህር ዳር ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር ብሔራዊ ቡድኑ በቂ ዝግጅት እንዲያደርግ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ተሰናድቶለታል፡፡
ከዚህ ቀደም እምብዛም የወዳጅነት ጨዋታ ማግኘት ብርቁ የነበረው ብሔራዊ ቡድኑ፣ አሁን ላይ በጥቂቱም ቢሆን የተለያዩ አገሮች እየጋበዘ ይገኛል፡፡ ይኼም ቡድኑ ያለበትን ክፍተት ለመመልከት እንደሚረዳው ዕሙን ነው፡፡
ዋሊያዎቹ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ኅዳር ወር ላይ ካጠናቀቁ በኋላ፣ ለካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ በቅርቡ በወጣው የምድብ ድልድል ኢትዮጵያ በምድብ አንድ ከአዘጋጇ ካሜሮን፣ ቡርኪና ፋሶና ኬፕ ቨርዴ ጋር መደልደሏ ይታወሳል፡፡