Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየአርኖ ሚሼል ዳባዲ ምስክርነትና የወቅቱ የብሔር ፖለቲካ (ክፍል ሁለት)

የአርኖ ሚሼል ዳባዲ ምስክርነትና የወቅቱ የብሔር ፖለቲካ (ክፍል ሁለት)

ቀን:

በመታሰቢያ መላከ ሕይወት

አሚዳ ስለአህመድ ግራኝ የተወልን መረጃ

‹‹በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ አንድ አህመድ የሚባል ስመ ጥር ፈረሰኛ ለዚህ አነስተኛ የሐረር ገዥ አደረለት፡፡ ትንሽ ጊዜ ቆየና ጥቂት ጓደኞቹን ያስከትልና ወደ ገጠሩ ወጣ በማለት በገዛ ጌታው ላይ ይሸፍታል፡፡ በዚያው እያለ ኃላፊ መንገደኞችንና ነጋዴዎችን አልፎ አልፎ ትንንሽ መንደሮችን መዝረፍ ይጀምራል፡፡ ቀስ በቀስ ተከታዩ እየበዛ ሄደ፡፡ ያደረሰባቸውን በደል ለመበቀል የገጠሩ ነዋሪዎች ይነሱብኛል ብሎ በመሥጋት፣ ከነበረበት ሥፍራ ራቅ ያለ ቦታ ሲሄድ የንጉሠ ነገሥቱ ግዛት ድንበር ላይ ይደርሳል፡፡ ሳያሰብ በድንገት ጦርነት በመክፈት የሸዋውን መርዕድ አዝማች በተደጋጋሚ ውጊያ ድል ነሳ፡፡ ግዛት ለማስከበር መጥቶ የነበረው መርዕድ አዝማች መሸነፍ ብቻ ሳይሆን ከብዙ ሠራዊት ጋር በጦርነቱ ላይ ሕይወቱን አጣ፡፡

- Advertisement -

‹‹እያንዳንዱን ውጊያ እያሸነፈ በመጣ ቁጥር የአህመድ ጦር እየተበራከተ መጣ፡፡ ሸዋን ለመከላከል ንጉሠ ነገሥቱ ጦር ይልካል፡፡ አሁንም ቀኙ ለአህመድ ሆነና የሸዋውን ጦር አዝማች የሆነውን ራስ ገድሎ በማሸነፍ ድል ተቀዳጀ፡፡ ለዘመቻው ትርጉም ለመስጠት ሲል የሃይማኖት ድባብ ሰጠውና ሙስሊም ወገኖችን በአንድ ሰንደቅ ዓላማ  ሥር ለማሠለፍ ቻለ፡፡ ቀጥሎም በዓረብ ባህል መሠረት ‹ኢማም› የሚለውን ማዕረግ ስም ለራሱ ሰጠ፡፡ ኢማም ማለት የሃይማኖት አጋር እንደ ማለት ነው፡፡ ክርስቲያኖች ደግሞ ‹ግራኝ› እያሉ ይጠሩት ነበር፡፡  

‹‹በዚህ ዓነት አህመድ ግራኝ ወራሪውን በመቀጠል ከአፄው ተልከው የዘመቱትን ሁሉ ተራ በተራ አሸነፋቸው፡፡ በመጨረሻ ንጉሠ ነገሥቱ ራሱ ጦሩን ይዞ ሊገጥመው መጣ፡፡ አህመድ ግራኝ በታላቅ ጦርነት የአፄውን ሠራዊት ለማሸነፍ በቃ፡፡ ንጉሡ በሽሽት ሲያፈገፍግ አህመድ ግራኝ ዱካ በዱካ እየተከተለ ያሳድደው ጀመር፡፡ ከአንዱ ግዛት ድንበር ወደ ሌላው እየገሰገሰ ንጉሡን ሲያባርር እግረ መንገዱን ደግሞ እስልምናን ተቀብለው፣ በነብይ ለማመን ፈቃደኛ ያልሆኑትን ክርስቲያኖች እያረደ አብያተ ክርስቲያናትን ያቃጥል ነበር፡፡

በጦርነቱ ተሸንፎ የተዳከመው ክርስቲያኑን የኢትዮጵያን ንጉሥ ለመርዳት ጀግኖች ፖርቹጋሎች ተልከው መጡና በበጌምድር ውስጥ በተደረገ ታላቅ ጦርነት ድል አድርገው አህመድ ግራኝ ሞተ፡፡ የአፄው መንግሥትም እንደገና አንሰራርቶ ሊነሳ ቻለ፤›› (መጽ 1) ገጽ 93፡፡

ግራኝ አህመድ ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩት መሪ አፄ ልብነ ድንግል የነበሩ ሲሆን፣ በግራኝ መሐመድ በደረሰባቸው ተደጋጋሚ ሽንፈት ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን፣ ከእሳቸው በመቀጠል ወደ ሥልጣን የመጣው ወጣቱ ገላውዲዮስ የካቲት 28 ቀን 1535 ዓ.ም በተደረገ ጦርነት አህመድ ግራኝ በመገደሉ ለአሥራ አምስት ዓመታት ሲካሄድ የነበረው ኢትዮጵያን እስላማዊት የማድረግ ትግል ዕልባት አገኘ፡፡ አህመድ ግራኝ ከመሞቱ በፊት ኢትዮጵያን አገሬ ብሎ ደምቢያ ከተማ ላይ ከትሞ ተደላድሎ ይኖር ነበር፡፡ ከሞተ በኋላ ሠራዊቱ በየአቅጣጫው ተበትኖ ሽሽቱን ተያያዘው፡፡ ከድል በኋላ የኢትዮጵያ ክርስቲያናዊ ሥርወ መንግሥት ወደነበረበት ተመለሰ፡፡

አሚዳ ስለሰለሞናዊ ሥርወ መንግሥት የሰጠን መረጃ

በኢትዮጵያ በሰፊው የሚነገረው አፈ ታሪክ መሳይ ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፣ የይሁዳን መንግሥት ልትጎበኝ የሄደችው ንግሥት ሳባ ከንጉሥ ሰለሞን ምኒልክ የተባለ ልጅ ወለደች፡፡ ይህ ልጅ ለአቅመ አዳም በደረሰ ጊዜ አባቱን ጠይቆ እንዲመጣ ትልከዋለች፡፡ ንጉሡ ከዙፋኑ ወርዶ፣ መኳንንቶቹን መስሎ፣ አብሯቸው ይቀመጥና ከመኳንንቶቹ አንዱን ደግሞ ‹ልብሰ መንግሥቱን› አልብሶ ዙፋኑ ላይ ያስቀምጠዋል፡፡ እናቱ ከአባቱ ከንጉሥ ሰለሞን የተቀበለችውን ቀለበት መልሶ እንዲሰጠው ለወጣቱ ልዑል ሰጥታው ነበርና ወደ ዙፋኑ ተጠጋና እንደ ደንቡ በትኅትና ዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ሰው እጅ ከነሳ በኋላ ቀና ብሎ ቢያየው መልኩ እናቱ እንደነገረችው አልመስል አለው፡፡

ከዚያም የተቀመጡትን መኳንንቶች በዓይኑ ሲያማትር እናቱ በአዕምሮ የቀረፀችበትን ምሥል የያዘ ሰው ያያል፡፡ ከዚያም ያላንዳች ማመንታት ተጠግቶ የእናቱን ቀለበት ይሰጠዋል፡፡ ከዚያ የነበሩ ሁሉ በሁኔታው በጣም ይደነቃሉ፡፡ ሰለሞንም እጅግ ደስ ብሎት ተመልሶ ዙፋኑ ላይ ይቀመጥና ልጁን ይመርቀዋል፣ የሚያምር ልብስ ያለብሱታል፣ ወዲያውም ንጉሡ ኃላፊነትና ሥራ ይሰጠዋል፡፡ ወጣቱ ኢትዮጵያዊ ልዑል አባቱን በጣም ስለሚመስል በሄደበት ሁሉ የይሁዳ ሕዝብ ንጉሥ ሰለሞንን ይመስላቸው ነበር፡፡ የወጣት ልጁን ብልህነት የተገነዘበው ሰለሞን ሁኔታው ስላላማረው ወጣቱን ልዑል መልሶ ወደ እናቱ ሸኘው፡፡

ሲሄድም በአገሩ ካሉ ታላላቅ ቤተሰቦች የአንዳንዶቹን የክብር ልጆች፣ እንዲሁም ከአሥራ ሁለት የይሁዳ ነገዶች አንዳንድ ተወካይ መርጦ አብረውት እንዲሄዱ ይሰጠዋል፡፡ ይህን ያደረገው በይሁዳና በኢትዮጵያ ነገሥታት መካከል ያለው ቁርኝትና ትስስር ዘለዓለማዊ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡

ወጣቱ ልዑል ይህ ብቻ አልበቃውም፣ የንጉሥ አባቱን አገር የሚያስታውሰው ልዩ ማስታወሻ ይዞ መሄድ አሰበ፡፡ ለዚህም አብረውት ለመሄድ የተነሱትን ባለሟሎች ትብብር በመጠየቅ በመጠባበቂያ ድንኳን በሌዋውያን ይጠበቅ የነበረውን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት ሰርቀው ይሄዳሉ፡፡ እነዚህን በሃይማኖታቸው ፍቅር ልባቸው የነደደ ‹‹ሰራቂዎች›› ለመርዳት የፈለገ ይመስል ያልታሰበ ዓውሎ ንፋስ ተነስቶ የይሁዳን ሰዎች ያዋክባቸዋል፡፡ በአጋጣሚው ተጠቅመው የሸመጠጡት ምኒልክና ባልደረቦቹ እንደሚሉት ዓውሎ ንፋስ ብቻ ሳይሆን፣ ቀይ ባህር ደርሰው መርከብ ላይ እስኪሳፈሩ ደመና እየከለላቸው ነው የተጓዙት፡፡ እዚያ ሲደርሱ ይጠብቃቸው በነበረው መርከብ በፍጥነት ተሳፍረው በመሄድ አገራቸው ገቡ (መጽ 1) ገጽ 84 – 85፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ ኢትዮጵያ በነበረው ረዥም ቆይታ በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ጥንታዊ ታሪክ ላይ ጭምር ሰፊ ጥናትና ምርምር ያደርግ እንደነበር ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ ያስረዳል፡፡ ምናልባትም አርኖ ሚሼል ዳባዲ ያደረገውን የኢትዮጵያን ኃያልነት የሚገልጸው ጥናት በርካታ ወራሪዎች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም፡፡ ኢትዮጵያ በመሳፍንት ዘመን በየቦታው በተለያዩ ገዥዎች ሥር የምትተዳደር ቢሆንም፣ ይህ ሁኔታ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ አውሮፓውያንም በዚያን ወቅት በትንንሽ የመንደር መንግሥታት ይገዙ ነበር፡፡ ጀርመኖች ከ30 በላይ በሆኑ ትንንሽ መንግሥታት፣ ጣሊያኖችም በበርካታ የመንደር መንግሥት ተከፋፍለው የቆዩበት ዘመን ነበር፡፡ ነገር ግን በኋላ ቅኝ ግዛታቸውን ለማስፋፋት እንዲመቻቸው ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት መመሥረት የግድ እንዳለባቸው ስለተረዱ፣ ወደ አንድ መንግሥትነት በመቀየር የቅኝ ግዛት የማስፋፋት ሥራቸውን በስፋት ተያያዙት፡፡ ከዚህ በመቀጠል እንግሊዞች ኢትዮጵያ በወቅቱ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራት ይሠሩት የነበረውን ሸፍጥ አርኖ ሚሼል ዳባዲ በሚከተለው ሁኔታ ይገልጽልናል፡፡ 

እንግሊዞች የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይጠናከር በወቀቱ ይሠሩት የነበረው ሴራ

‹‹እንግሊዞች ዓለምን በመውረርና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ፣ ከዚያም የእነሱን ማንነት ለማስፋፋት በሠሩት እጅግ ብልህነት የተሞላው ተግባር ዛሬ እንግሊዝኛ ቋንቋ የዓለም ቋንቋ ለመሆን ችሏል፡፡ እንግሊዞች ፊት ለፊት ተዋግተው ጦርነት ያሸነፉበት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ዘዴና ብልኃትን ነው የሚጠቀሙ፣ ወይም ደግሞ ቅኝ የያዙትን አገር ዜጎች ውትድርና ያሠለጥኑና ሌሎች ሰዎች ለእነሱ ጥቅም እንዲሞቱላቸው ያደርጋሉ እንጂ፣ እነሱ መቼም የራሳቸውን ዜጋ ለአደጋ አያጋልጡም (ግድ ካልሆነባቸው በቀር)፡፡››

አርኖ ሚሼል ዳባዲ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ላይ ከቆየ በኋላ በምፅዋ በኩል አድርጎ ወደ የመን፣ ከዚያ ወደ በርበራና ታጁራ (ጂቡቲ) ተጉዞ ነበር በዚያን ወቅት የመን የእንግዞች ቅኝ ግዛት ነበረች፡፡ በመሳፍንቱ ዘመን ለነጋዴዎች የምትመች መዳረሻ ሸዋ የነበረች ሲሆን፣ ንጉሥ ሳህለ ሥላሴ የወቅቱ ንጉሥ ነበሩ፡፡ ጂቡቲ ደግሞ በሡልጣን ትመራ የነበረች ወደብ ነበረች፡፡ እንግሊዞች ምንም ዓይነት ሸቀጣ ሸቀጥ ወደ መሀል ኢትዮጵያ እንዳይገባና ኢትዮጵያ ከውጭ ከሚመጡ እንግዶች ጋር ግንኙነት እንዳታደርግ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጉ ነበር፡፡

አርኖ ሚሼል ዳባዲ መጽሐፍ አንድ ገጽ 438 ላይ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹በርበራ የኤደን አገረ ገዥ የካፒቴን ይሄይስ ተላካሊ የነበረው ሼር ማርክ ከዚህ ተነስተን የምንሄድበትን ቦታ እንዳያውቅ ብዙ ጥረን ነበር፡፡ ነገር ግን ታጁራ እንደምንሄድ እንደሰማ ወዲያውኑ ለጌታው ለካፒቴን ይሄይስ ልኮባቸው ኖሯል፡፡ እሳቸውም ካፒቴን ክርስቶፈር መርከቡን ይዞ ቀድሞን በፍጥነት ታጁራ እንዲገባ ያዙታል፡፡ የታዘዘው መሄድ ብቻ ሳይሆን የእኛን እዚያ መግባት ነዋሪዎቹ እንዲቃወሙ ማነሳሳት ነበር፡፡ ካፒቴን ይሄይስ ነገሩን ሁሉ አብርደን፣ ከሡልጣኑ ጋር ተስማምተን እንደተቀመጥን ሲሰማ በንዴት ጦፈ፡፡ በተቻለ መጠን ጉዟችን እንዳይሳካና የምንቆይበት ጊዜ አስቸጋሪ እንዲሆን ተግተው ከመሥራት አሁንም አላረፉም፡፡ ለምሳሌ ከውጭ የሚመጣ ምግብ ነጋዴዎች እንዳይሸጡልን ነጋዴዎችን አዘዋል፡፡

ከዚያ በባሰ ወደ አገር ውስጥ የሚሄድ ቅፍለት (Caravan) እኛን አስከትሎ ወደ ሸዋ የሄደ እንደሆነ፣ የእንግሊዝ የንግድ መርቦች ከታጁራ ጋር የሚያደርጉን የንግድ ልውውጥ እስከ ጭራሹ እንደሚያቆሙና ለመሸጥ የሚመጡ ባሪያዎችን እንድሚወርሱ በመግዛት ያስፈራሩ ጀመር፡፡ በአርኖ ሚሼል ዳባዲ የመጀመርያው መጽሐፍ ወደ መጨረሻው አካባቢ እንግሊዞች ለጂቡቲው ሡልጣን በርካታ ማባበያዎችን እየሰጡ የፈለጉትን እንዲፈጽምላቸው ተግተው ይሠሩ ነበር፡፡ ማንኛውንም የንግድ መርከብ ወደ ሸዋ የሚሄድ ሸቀጥ እንዳያራግፍ ኃይል ሁሉ በመጠቀም ያስቆሙ ነበር፡፡

በጣም የሚገርመው ከዛሬ 180 ዓመት ገደማ እንግሊዞችና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ በዚህ መልኩ ጫና ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ አሜሪካኖች የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲፈርስና አገሪቱ ወደ ትንንሽ ፍርስራሽ መንግሥታት እንድትለወጥ እያደረጉት ያለውን ጥረት ስንመለከት፣ አገራችን ኢትዮጵያ ሁሌም በፈተና ውስጥ የኖረች አገር መሆኗን እንገነዘባለን፡፡ በተጨማሪም ከምኒልክ በኋላ ኢትዮጵያ ደረጃውን የጠበቀ የማዕከላዊ መንግሥት መሪ ማግኘት ባለመቻሏ የአገራችንን ፈተና እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡  

በአገረ መንግሥት ምሥረታና የማስቀጠል ሒደት እጅግ ፈታኝ ተግባር ቢሆንም፣ በዓለማችን ይህንን ፈታኝ ሒደት አልፈው ጠንካራ መንግሥት፣ ጠንካራ ኢኮኖሚና ጠንካራ ወታደራዊ ኃይል የገነቡ በርካታ መንግሥታት አሉ፡፡ የኢትዮጵያን አገረ መንግሥት ግንባታ ፈታኝ የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ደግሞ ኢትዮጵያ ለምታ፣ በልፅጋና ጠንካራ የጥቁር ሕዝቦች ሥልጣኔ ከገነባች ምዕራባውዊ ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች (የአፍሪካ) ምሳሌ ትሆናለች፡፡ ሌሎች አፍሪካ አገሮች ውስጥ ያለንን ጥቅም ማስጠበቅ ያቅተናል ብለው ስለሚምኑ በኢትዮጵያ ላይ የሚደርጉትን ጫና አጠናክረው መቀጠላቸው አይቀርም፡፡ ለዚህ ነው ጠንካራ መንግሥት መሥርተን፣ አንድነታችንን አስጠብቀን ወደፊት መጓዝ ያለብን፡፡

አሚዳ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቦታዎች ባሳለፏቸው ጊዜያት ከነገረን ነገር አንዱ የዱር እንስሳት አንበሳ፣ ዝሆን፣ ሚዳቋና ከርከሮ የመሳሰሉ በርካታ እንስሳት ከኤርትራ ጀምሮ እስከ ጎጃም ወሎ ድረስ እንደነበሩ ነው፡፡ እንዲያውም በእሱ አገላለጽ የዱር እንስሳት የሚርመሰመሱበት ቦታ ነው እያለ የገለጸው፡፡ ነገር ግን በሚያሳዝን ሁኔታ እነዚህ እንስሳት (በአጉል አውሬ የማደን ጀብደኝነት) ድራሻቸው ጠፍቷል፡፡ አሚዳ አልፎ አልፎ እሱም ድኩላዎችን በማደን ለምግብ ይጠቀም እንደነበር ነግሮናል፡፡

ሌላው አሚዳ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተራራዎች በቆየባቸው ጊዜያት ከሁሉም መሳፍንቶች ጋር እጅግ የቀረበ ግንኙነት ነበረው፡፡ ከንጉሥ ሳህለ ሥላሴ በስተቀር ከደጃች ውቤ፣ ከደጃች ጎሹ፣ ከደጃች ራስ ዓሊ ጋር ግንኙነቱን የሚገልጸው አብሮ በመብላት አብሮ የዕረፍት ጊዜን በማሳለፍና አብሮ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ ጭምር ነበር፡፡ ከነገሥታቱ ጋር በነበረው ቆይታ ስለአውሮፓ ሥልጣኑ የሚያውቀውን በርካታ ሳይንሳዊ ዕውቀቶች ነገሥታቱን አስተምሯቸዋል፡፡

ፈረንሣዮች በኢትዮጵያ ታሪክ የፈጸሙት መጥፎ ተግባር መኖሩን አላውቅም፡፡ አሚዳ ብቻ ሳይሆን በምኒልክ ዘመን ወደ ሐረር መጥቶ የነበረው ታዋቂው የሥነ ጽሑፍ ሊቀ አርተር ራምቦ ለምኒልክ የጦር መሣሪያ በመሸጥ የአፄ ምኒልክ ጦር እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ባለውለታችን ነው፡፡ የአርተር ራምቦ መኖሪያ ቤት በጥሩ ሁኔታ ተይዞ በሐረር ከተማ ውስጥ አሁን የሙዚየም አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡

አሚዳ በመጀመርው መጽሐፉ ስለሐረሪዎች እንዲህ ብሎ ነበር (መጽ 1) ገጽ 426፡፡ ‹‹ወደ ሐረር ግዛት እስካሁን አንድም አውሮፓዊ ገብቶ አያውቅም፡፡ እንደሚወራው በዚያ የሚኖሩት አክራሪ ሙስሊሞች ስለሆኑ ማንም ክርስቲያን ወደዚያ ከመጣ ወዲያውኑ ይገሉታል አሉ፡፡ እኛ ግን በእርግጥ እንዲህ ያለ አደጋ ካለ በፀባይ እናልፈዋን ብለን አስበናል፡፡ ነገር ግን በኤደን አገር ገዥ በእኛ ላይ የተወሰደው የማሳደድ ዕርምጃ ወሬው ገና ድሮ ሐረር ደርሷል ተብሎ ተነገረን፡፡ እኛ ያሰብነው ሳይታሰብ ሹልክ ብለን ለመሄድ ነበር፤››፡፡

በዚያን ዘመን መረጃ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የሚዘዋወረው በነጋዴዎች ነበር፡፡ ቅፍለት (Caravan) እየነዱ፣ ሰብሰብ ብለው የሚጓዙ ነጋዴዎች ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለምን ሥልጣኔ እንዲበለፅግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ መረጃ ብቻ ሳይሆን ከቦታ ቦታ የሚያዘዋውሩ አዳዲስ የተመረቱ ምርቶችን ራቅ ባለ ቦታ ወስዶ በመሸጥ መንግሥታት እንዲጠናከሩ፣ በተለያዩ ገዥዎች መካከል የኃይል መቀራረብ እንዲኖር በማድረግ ተግባር ላይ ትልቅ ተግባር አበርክተዋል፡፡  

አርተር ራምቦ ይህንን ተግባር በመፈጸሙ ምናልባት ዓድዋ ላይ ለተገኘው ድል የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ይቻላል፡፡  በመሳንፍንቱ ዘመንም ሸዋ የንግድና የኢትዮጵያ ማዕከል እንደነበረች አሚዳ የነገረን ነገር አለ፡፡ (በመጽ 1) ገጽ 436 ላይ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ከባህር ጉዟችን ሌላ በየብስ ለሚያደርጉት የንግድ ልውውጥ ዋናው የመገበያያ ቦታቸው ሸዋ ነው፡፡ ወረሂመኑ ወደሚገኘው የአርጎባ ገበያ አዘውትረው ቢሄዱም አልፈው ወደ ጎንደር የሚዘልቁት በጣም ጥቂት ናቸው፤››፡፡

ይህ አባባል የሚገልጽልን ነጋዴዎች ወደ ሸዋ የሚደርጉት ተደጋጋሚ ጉዞና የንግድ እንቅስቃሴ ከሌሎቹ የመሳፍንት ግዛች ሸዋ በተሻለ መንገድ እንዲጠናከር፣ በኋላ በአፄ ምኒልክ የተመሠረተው ጠንካራው የማዕከላዊ መንግሥት እንዲመሠረት የበኩለን አስተዋጽኦ እንዳደረጉ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የግድ መጠቀስ ካለበት ጉዳይ አንዱ በአሁኑ ወቅት አገራችንን እያተራመሳት ያለው የብሔር ፖለቲካ በአሚዳ ጥናታዊ ሥራዎች ውስጥ ምንም ዓይነት ታሪካዊ መሠረት እንደሌለው ነው፡፡ አሚዳ ያጠናው ኢትዮጵያ በቆየባቸው ጊዜያት የተከናወነውን ብቻ ሳይሆን፣ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ታሪክን ጭምር ነበር፡፡ በቆይታው በከፍተኛ ፍጥነት አማርኛ ቋንቋ አቀላጥፎ ይናገር የነበረ በመሆኑ ያለ ችግር መረጃ መሰብሰብ ችሎ ነበር፡፡

በድንገት ያለ ምንም ሳይንሳዊ ጥናት በ1983 ዓ.ም. የተጀመረው የብሔር መንግሥት የመመሥረት ቅዠት ይኼው እስካሁን እያተራመሰን ቀጠለ እንጂ፣ ማንም ሰው ወይም ቡድን በምን ዓይነት ሁኔታ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ፍኖተ ካርታ ያዘጋጀ የለም፡፡ እንዲያው ብቻ እስኪ ልሞክረው እየተባለ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎቻችንን ሕይወት በየጊዜው እየቀጠፈ ነው፡፡

አሁን የትግራይ ክልልና የአማራ ክልል የይገባኛል እያሉ ጦር የተማዘዙበት የወልቃት ምድር በዚህ ጽሐፉ ውስጥ በዚያን ወቅት ምን ይመስል እንደነበረ በመጠኑ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ የበለጠ መረጃ ለማግኘት ደግሞ መጽሐፉን አንብቡት፡፡ እንደሚታወቀው ሕገ መንግሥቱ መሬትን ለክልሎች ስለሰጠ ነው በዚህ ደረጃ እየተናቆርን ያለነው፡፡ መሆን የነበረበት ሁሉም መሬት የመላው ኢትዮጵውያን ሆኖ፣ ሕግና ሥርዓት ተዘርግቶለት ሁሉም በሚመቸው ቦታ መኖር የሚችልበትን ሥርዓት ዘርግተን መራመድ ስንችል ብቻ ነው እውነተኛ ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው፡፡ ከዚህ በፊት ደጋግሜ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት ‹‹የብሔር መሬት የለም››፡፡ መሬት ለፍጡራን ሁሉ በጋራ እንድንጠቀምበት የተሰጠችን ፀጋ ነች፡፡ ሰዎች፣ እንስሳት፣ ዕፅዋትና የተለያዩ ነፍሳት በጋራ ሥርዓት ዘርግተን ልንጠቀምባት የሚገባ ንብረታችን እንጂ የማንም ቡድን ንብረት የሆነ መሬት የለም፡፡ የአሚዳ ጥናታዊ ሥራ ብቻ ሳይሆን በርካታ የውጭ አገር አሳሾች ያጠኗቸውን ሥራዎች ብንመረምር የምናገኘው እውነታ ተቀራራቢ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው በአሚዳ ጥናት ውስጥ የተካተቱ፣ አሁን በጭራሽ ስማቸውንና ቋንቋቸውን የማናውቀው በርካታ ብሔረሰቦች በዚያን ወቅት ነበሩ፣ በመጽሐፉ በተደጋጋሚ ብዙ ቦታ ተጠቅሷል፡፡

በተመሳሳይ አሁን ማደግ የተሳናቸው ቋንቋዎች ከእነ ብሔራቸው ማንነት በሚቀጥሉት ከ50 እስከ 100 ዓመት ጊዜ መጥፋታቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም ማንም እንዲያድጉ እየተንከባከባቸው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ትግርኛ ተናጋሪዎች ለማንነታቸውና ለቋንቋቸው ልዩ ፍቅር አላቸው፡፡ ነገር ግን ሥልጣን ላይ በነበሩበት 27 ዓመትና አሁንም ቋንቋው ምንም ዓይነት ዕድገት አላስመዘገበም፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ትግራይ ክልል ለስድስት ዓመት ተዘዋውሬ መሥራት በቻልኩበት ወቅት፣ አንዱም የትግራይ ከተማ ውስጥ መጻሕፍት ቤት አላየሁም፡፡ በክልሉ የማንበብ ባህል ብዙም አልዳበረም፡፡ ካላነበቡና ካልጻፉ ደግሞ የማንነት ቋንቋም አይበለፅግም፡፡

ማንነት በጠመንጃ አፈሙዝ አያድግም፣ አይበለፅግም፡፡ ማንነት ተጠብቆ የሚያድገው ወይም የሚበለፅገው በዘርፉ ሰፊ ሥራ ሲሠራ ብቻ ነው፡፡ የመሳፍንቱ ዘመን ኢትዮጵያን አሚዳ በጥልቀት እንድናየው አስችሎናል፡፡ በዘመኑ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች በገዥዎች ከፍተኛ በደል ይደርስባቸው ነበር፡፡ ከፍተኛ ግብር እንዲገብሩ ይደረግ ነበር፡፡ በተጨማሪ ወታደሮች ምርቶቻቸውን ቤት እየገቡ ዘረፋ ያካሂዱ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ የምኒልክ ዘመን እስኪመጣና ሕግና ሥርዓት በማዕከላዊ መንግሥት መመሥረት እስከቻለበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎ ነበር፡፡ አገር የመመሥረት ሒደት እጅግ እልህ አስጨራሽ  ነው፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ሒደት አልፋ ተመሥርታ ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን ደግሞ በመፍረስ ሒደት ላይ ነን፡፡ በታሪካችን ማዕከላዊ መንግሥት በዚህ ደረጃ አቅመ ቢስና ልፍስፍስ የሆንበት ጊዜ ተመዝግቦ አያውቅም፡፡

የድሮ ታሪካችን በአመዛኙ ለግዛት ከተደረጉ ትግሎች በስተቀር፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለጋራ ዓላማ መቆም ተቸግሮ አያውቅም፡፡ ለምሳሌ በአቶ ይልማ ደሬሳ የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ስለንግሥት ሰብለ ወንጌል እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፡፡ ‹‹ንግሥት ሰብለ ወንጌል የአፄ ገላውዲዮስ እናት ስትሆን፣ ትውልዷ ትግራይ ነው፡፡ በመሐመድ ግራኝ ወረራ ዘመን ከአፄ ልብነ ድንግል ሞት በኋሏ ልጇ ገላውዲዮስ ገና በ20 ዓመቱ የነገሠ ሲሆን፣ ንግሥት ሰብለ ወንጌል የሐማሴንና ሌሎች የሰሜን ሰዎችን በማስተባበር ልጇ ገላዲውዲዮስ በአህመድ ግራኝ ላይ አንፀባራቂ ድል እንዲቀዳጅ ያስቻለች ታላቅ ሴት ነች፤›› ይላል፡፡

በአሥራ ስድተኛው ክፍለ ዘመን የነበረው ኢትዮጵያዊነት ይህንን ይመስላል፡፡ አሁንስ? በአሁኑ ጊዜ ከሕወሓት ጋር በሰሜኑ የአገራችን ክፍል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ጊዜ የወሰደው በሕወሓት ጥንካሬ ሳይሆን፣ በማዕከላዊ መንግሥት ደካማነት ነው፡፡ መንግሥት መወሰድ የሚገባቸውን ዕርምጃዎች ወቅቱን ጠብቆ መውሰድ ባለመቻሉ የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ ወይም ሕወሓት ይህን ሁሉ መወራጨት ሊያደርግ የቻለው፡፡ ምዕራባውያን ደግሞ በአንድ አገር ስንጥቅ ሲፈጠር በዚያ ክፍተት ውስጥ ገብተው የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም ይሯሯጣሉ፡፡ ከእኛ የሚጠበቀው ተግባር በተቻለ በአገር ውስጥ ስንጥቅ እንዳይፈጠር ተግቶ መሥራት ነው፡፡ አሜሪካኖች በታሪካቸው አሸባሪ ከተባለ ድርጅት ጋር ሲተባበሩ ይህ የመጀመርያ ነው፡፡ እንኳን እነሱ ከአሸባሪ ጋር ሊሠሩ ይቅርና ለምሳሌ ሱዳን ኦሳማ ቢላደንን ደብቀሻል፣ ከአሸባሪ ጋር አብረሽ እየሠራሽ ነው ብለው በማዕቀብ ፍዳዋን ለብዙ ዓመታት አሳይተዋታል፡፡ ከሕወሓት ጋር የሚሠሩት አሜሪካኖች ሕወሓትን ለፍላጎታቸው ማስፈጸሚያ እንደ መጠቀሚያ አደረጉት እንጂ፣ ለሕወሓቶች ዓላማ ተጨንቀው አይደለም፡፡ በመጨረሻም ይህ ጽሐፍ በጋዜጣና በመጽሔት ያሳተምኩት መቶኛ ጽሑፌ መሆኑን በድጋሚ አንባቢያን ዕውቅና እንዲሰጡኝ በአክብሮት በመጠየቅ ለዛሬ እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...