Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ግራ የገባ ነገር!

ከመገናኛ በቀበና በኩል ወደ አራዶቹ ሠፈር ፒያሳ ልንጓዝ ነው። በአፍታ ሰመመን ውስጥ የአኗኗራችን ጉዳይ ጠምዶ ይዞናል። ሆዱን ባር ባር የሚለው፣ የተከፋው፣ ደስታ ሰቅዞ የያዘው፣ ተፈጥሮ ላይ አመፃ የሚቃጣው፣ በአጠቃላይ ሁሉም በጥድፊያ ሰበብ ከውስጥ ሐሳቡ በተቃርኖ ይጓዛል። ሁሉንም ችግር ታቅፈን ምንም የማይመስለን ሆነን ስንታይ ማስመሰላችን አይታይም። ‹‹አይ መፈጠር! አይ መኖር እቴ!›› ይላል አንዱ ግራ የገባው። በመሆንና ባለመሆን ሥሌት ውስጥ ሁሉም ውጤቱን ሊሰበስብ፣ የዘራውን ሊያጭድ፣ አንዳንዴም የተሰፈረለትን ሊቀበል በፍርኃት ጎዳና ላይ እየተጓዘ ይጠባበቃል። ነገር ግን ተፈጥሮ የመምረጥን ነፃ ፈቃድ ባትቸረን ኖሮ፣ በዚህ ሁሉ አዋኪ ነገር መሀል ምን ይውጠን ነበር? የተንጠለጠሉ ተስፋዎች በጥያቄ ማዕበል እየተናጡ ነገን እንድናይ ይገፉናል። ዘንድሮ የሚደግፍና ከኋላ የሚገፋ ባይመናመን ኖሮ እኮ ብዙ እንጓዝ ነበር። ዘመን አይሽሬ ሀሜት፣ ክፋትና ምቀኝነት በቁም አስሮን የሌላውንም የራሳችንንም በረከት ይቀማናል። በግሳፄና በምክር የማይከስሙ ባህሪዎቻችን እየበዙ ብዙ ያስተዛዝቡናል። ትዝብትና ጎዳና መቼ ተለያይተው ያውቁና!

በአካባቢው እንደ ጉዳዩ ዓይነት የሚብከነከው ብዙ ነው። ከዚያ መሀል ነው ረዥም ርቀት ተጓዡ አንገቱን ታክሲ ውስጥ የሚያስገባው። ወያላው በጓደኞቹ ተከቦ ያሻውን ወሬ እያነሳና እየጣለ ይጣራል። ምናለበት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት የማይረሱ ቢበዙልን? ‹‹አገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን እኔ ምን አደረግኩላት ብለህ ጠይቅ›› የሚል ጥቅስ ከፊት ለፊታችን ተለጥፎ ያዩ ሁለት ተሳፋሪዎች ጨዋታ ጀመሩ። ‹‹አሁን አንተ ለዚህች አገር ምን አደረግክላት?›› ይለዋል አንደኛው። ያኛው ይመልሳል፣ ‹‹ቀድሞ ነገር አንድ ነገር ለማድረግስ ቢሆን ዝም ተብሎ መሰለህ? እኔ እኮ ምናለበት እንዲህ ያለውን ጥቅስ ስንረዳ እንደ ወረደ ባይሆን? አይ የትምህርት ጥራት መውረድ። ፈቃድ ሲኖርህ እኮ ነው አንድ ነገር የምታደርገው…›› ብሎ ይመልስለታል። ‹‹ለአገር በጎ ነገር ለማድረግ ደግሞ ፈቃድ ካልተሰጠ አይሆንም ተባለ እንዴ?›› ብሎ በተባራሪ ወሬውን የሰማ ይጠይቃል። ‹‹አዎ!›› አለ ስለፈቃድ ያነሳው ተሳፋሪ በስላቅ። ‹‹ሰው ባለመደማመጥ ቁምነገሩን ከአሰስ ገሰሱ መለየት ትቷል ጃል…›› ይላል። አንዱ ታዛቢ፣ ‹‹እንዴ! በፈቃድ ወረፋ ተይዘን ለመኖር ፈቃድ እንዳያስፈልገን እንጂ ሌላውስ ሌላ ነው…›› ሲል ለጨዋታ የተነሳ መሆኑ ተነገረው። ‹‹እና ለአገር አስተዋጽኦ ለማበርከት ምን ቢያስመርርህ ነው እንዲያ የምትለው?›› ብሎ ወደ ሁለቱ የወሬው ጀማሪዎች አፈጠጠ። ተጀመረ ማለት ነው!

‹‹ወንድሜ እዚህ አገር ስንዝር ለመራመድ ግንብ ማፍረስ እንደሚጠበቅብህ አልነግርህም። ላያችን ላይ የሚሾሙብን እኛን ማገልገል ሳይሆን ዓላማቸው የሚመስለው እኛ እንድናገለግላቸው ነው። ማን ፈልጎ ይሰንፋል? ማን መማር ይጠላል? ማን ማትረፍ ይንቃል? ግን ሁሉንም እንዳይሆን የሚያደርገው አጥር ነው። በዚህ መሀል እኔ ለአገሬ ምን አደረግኩላት ብዬ ላስብ ወይስ እንዴት ብዬ በልቼ ልደር?›› ሲል ብዙም ሊከራከረው የፈለገ አልነበረም። በልቶ ለማደር ማሰብም እንደ አስተዋጽኦ ይቆጠር ይሆን? ምን ይታወቃል ጊዜው የኑሮ ውድነት ነው እኮ፡፡ የአገር ነገር ሲነሳ ሁሌም ቢሆን መመሰጥ አይጠፋም። ሁሉም በየራሱ ህሊና ጅረት ግራ ቀኝ እያየ አንዳንዴም ፊት ለፊት፣ ብቻ በዝምታ ያስባል። ኑሮ አንዳንዴ እንደሚታክተን አዕምሮን ማሰብ ቢታክተው ከተማችን የዕብዶች መናኸሪያ መሆኗ ባላጠያየቀ ነበር። ‹‹አይ አንቺ አገር መቼ ይሆን በልቶ ማደር ልጆችሽን በሐሳብ አዙሪት እየናጠ መድፋቱን የሚተዋቸው?›› እያሉ አንድ አዛውንት ተሳፋሪ ሲገቡ፣ የተነጋገርንበትን ሳይሰሙ እንዲያ ማለታቸው እያስገረመን ተመለከትናቸው። ለካ ከመንገዱ ዳር ምንም እህል ባለመቅመሱ ምክንያት በቁመቱ ልክ የተጋደመ ስኳር በሽተኛ ዓይተው ኖሯል። በሽተኛውን ቀና አድርገው የሚጠጣ ነገር ለመጋት የሚሞክሩ መንገደኞች ይረባረባሉ። ‹‹ምናለበት ከውድቀት በፊት ብንረባረብ?›› ቢል አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹እውነት ነው፣ ይኼኔ አንድ ጉርሻ ማግኘት ባይችል ነው…›› ብሎ አጠገቡ ያለው መለሰ። አመላችን ሆኖ ካለቀ መድረስ ይቀናናል። ‹‹አቅርቡኝ ጠይቁኝ ብዬ ስለፈልፍ ሰሚ ስላጣሁኝ፣ በድኔን አትንኩት ስሞት አትቅበሩኝ…›› ያለው ማን ነበር? እንጃ!

ታክሲዋ ስትሞላ ፈጠን የሚለው ልጅ እግር ወያላ ሲሮጥ መጣ። በሩን እየዘጋ ሾፌሩን ‹‹ሳበው!›› አለው። ሾፌሩ ይኼኔ የሆነ የዘነጋው ነገር ትዝ ብሎት፣ ‹‹እንዴ አንተ ልጅ መንጃ ፈቃድህን እንዴት እያደረግክ ነው?›› ብሎ ጠየቀው። ሁላችንም የሚመልሰውን ልንሰማ ጆሯችንን አሰገግን። ‹‹እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ በርካታ ተፈታኝ አለ ብለው ከሦስት ወር በኋላ ቀጠሩኝ። አይገርምህም ግን? እኔማ አንዳንዴ መስመሩ ‹‹ክራውድድ›› ሲሆን የዚህ ሁሉ ሰው መንፈስ ጭምር እንጂ፣ የምናየው መኪና ሁሉ አልተላለፍ ብሎ አይመስለኝም…›› አለው። ‹‹ዘንድሮ እኮ መኪና ማለት ጫማ በለው፣ ቅንጦትነቱ ድሮ ቀረ። እናንተን ተማምነን ታዲያ ልንኖር ነው?›› ሲል አንድ ተሳፋሪ ተንኮለኛው ወያላ፣ ‹‹ከጫማም የቻይና ጫማ የሚባል አለ፣ መኪና ሁሉ መኪና አይደለም…›› ሲለው፣ ‹‹ወይ ጉድ! እያቃጠለንም ተራምደናል እንኳን መንዳት…›› ሲለው ማጉረምረም ተሰማ። በቻይና አትምጡብን!

ታክሲያችን በሰፊው አስፋልት ላይ ጉዞ ስትጀምር፣ ‹‹አቤት! አቤት! መቼም ይኼ መሠረተ ልማት እንዲህ ሁሉም ቦታ ሲያልቅ ማየት ደስ ሲል…›› አለ አንድ ጎልማሳ ተሳፋሪ የመንገዱን ግራና ቀኝ እያየ። ‹‹መንገድ ሲሠራ ያስቸግራል እንጂ ሲያልቅ ያምራል…›› አለ አብሮት የተቀመጠው ተሳፋሪ። ‹‹ታዲያስ! ቤት ሲሠሩት አሳር አብልቶ አይደል? ሲኖሩበት ግን ልዩ ነው…›› አለ ጎልማሳው። በጎልማሳው አስተያየት ብዙ ሰው የከፋው መሰለ። ‹‹ምነው፣ ምነው ደህና ረስተነው የነበረውን ነገር ባታስታውሰን?›› አለች አንዲት ሴት። ‹‹እንዴት?›› ቢላት ጎልማሳው? ‹‹የቤት ጉዳይን ነዋ፣ ባለፈው ሰሞን አከራዬ ልቀቂ ብሎኝ ትናንት ባለሁለት ክፍል ኮንዶሚኒየም ቤት አገኘሁ። አሁን ሄጄ ዋጋ ብነጋገር 15,000 ብር አይሉኝ መሰላችሁ? ኧረ የጉድ ዘመን!›› ብላ እንባ ተናነቃት። ከአስፋልት እስከ መኝታ ቤታችን ቅሬታችን በዝቷል። ዕድገት አይሉት ፈሊጥ የቅሬታ ሰሚዎቻችን የማንገዳደረው መልስ ሆኗል። ‹‹እና ምን ተሻለሽ?›› ቢላት አጠገቧ የተቀመጠው ወጣት ‹‹እንዴ! ምነው ወንድሜ ምን ተሻለን በል እንጂ? ‹የአንዱ ቤት መቃጠል ለሌላው ሙቀትና ብርሃን ነው› ያሉትን የአገርህን ጸሐፊ አታውቃቸውም? ለነገሩ የዘንድሮ ልጆች ከአገራችሁ ይልቅ የባዕድ አጨብጫቢ መሆን ትወዳላችሁ…›› ብለው አዛውንቱ በንዴት ተናገሩ። በመንገድ አድርገን ስለቤት አውርተን በአገር ምርትና በአገር ሰው ስለመኩራት እስክናወራ ታክሲያችን ጉዞዋ እንደ ቀጠለ ነው። መቼ ቆሞ ያውቅና!

 ‹‹ወራጅ!›› አለ አንድ መንገድ ላይ የገባ ተሳፋሪ። ታክሲዋ ልታወርደው ስትቆም፣ ‹‹ወይ ጉድ!›› ይባባላሉ ከኋላ የተቀመጡት ተሳፋሪዎች። ‹‹ሰው ምነው እንዲህ ሐሞቱ ፈሰሰ? ከእዚች እዚች ለመሄድ ነው የገባው?›› ሲለው አንደኛው፣ ‹‹በቃ በዓመት አንዴ ታላቁ ሩጫን ትሮጣለህ በየዕለቱ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ሰው ታወራለህ…›› ቢለው ሳቅን። መቀላለዳቸው ቀጠለ። ‹‹ለመሆኑ አንተ ያልሮጥከው ኑሮ ራሱ ታላቅ ሩጫ ነው ብለህ ነው?›› አለው ጮክ ብሎ። ‹‹ታዲያስ! ከዘንድሮ ኑሮ በበለጠ ምን ታላቅ ሩጫ ይኖራል? በልቶ ለማደር 10 ሺሕ ማይልስ የሚማስን ሰው 10 ኪሎ ሜትር ብርቅ አይሆንበትም…›› ብሎ በነገር ነካ አደረገው። ታዲያ ቀልድ መሆኑን ሁለቱም ለማሳወቅ ትከሻቸውን ቸብ ቸብ ይደራረጋሉ። ‹‹ይሁንና ግን መሮጥ ነበረብህ። ሩጫህ ግን አገርን ለማሳደግ እንጂ እንደ ወንበዴ ለማፍረስ አይደለም…›› አለው ድንገት የጨዋታውን ፍሬ ነገር ወደ ፖለቲካ እያሸጋገረ። ‹‹አይ ያንተ ነገር፣ አገር አልሚና አገር አፍራሽ መለየት ያቃተው ፈረንጅ ጣልቃ እየገባ ካልተረባረብንማ ሞተናል…›› አለው። ነገሩ ጠጥሯል!

ታክሲያችን ቀበናን አልፋ ግንፍሌን ተሻግራ ወደ ወወክማ አቅጣጫ ስታመራ አራት ኪሎ መድረሳችንን አወቅነው፡፡ አራት ኪሎ የመንግሥት መቀመጫ በመሆኗ ሁሌም ስሟ ከምንም ነገር በላይ ገዝፎ ይታወቃል፡፡ በስተግራ በኩል የፓርላማው ሕንፃ ኹነኛ ምልክት የሆነው ሰዓት ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ‹‹ምነው የፓርላማው ወሬ ጠፋሳ?›› አሉ አዛውንቱ፡፡ አጠገባቸው የተቀመጠው ጎረምሳ፣ ‹‹አዲሱ ፓርላማ የሚሰየመው በመስከረም መጨረሻ አይደለም ወይ?›› አላቸው፡፡ አዛውንቱ ራሳቸውን እየነቀነቁ፣ ‹‹የለም! ወጣቱ ጥያቄዬ አልገባህም…›› አሉት፡፡ ወያላው ጣልቃ ገብቶ፣ ‹‹ታዲያ በደንብ አስረድተው ይጠይቁ እንጂ?›› አላቸው፡፡ አዛውንቱ ሳቅ እያሉ፣ ‹‹ጥያቄዬማ አዲሱ ፓርላማ እስኪሰየም ድረስ እረፍት ላይ ያለው ፓርላማ አባላት ምን እየሠሩ ነው?›› ሲሉ፣ ወያላው በበኩሉ እየሳቀ፣ ‹‹ምናልባት ጦር ግንባር ዘምተው እንዳይሆን…›› ብሎ ‹‹መጨረሻ!›› ሲለን እየተሳሳቅን ወደ ጉዳያችን ተበታተንን፡፡ እውነት ዘምተው ይሆን እንዴ? ወይስ ዘመቻ መኖሩን አልሰሙም? ግራ የገባ ነገር! መልካም ሰንበት!

 

 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት