‹‹የያዝነው ጉዳይ የለም የነበሩትን ጥያቄዎች በአግባቡ መልሰናል›› ፓርላማ
ከአንድ ዓመት በፊት ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከእስያ አገሮች ተገዝተው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ 637 ተሽከርካሪዎች በኤክሳይስ ታክስ አዋጅ አፈጻጸም ምክንያት አስመጪዎች ስላልደረሷቸው ፓርላማው በመመርያ መፍትሔ ይስጠን አሉ፡፡
በተሻሻለው 1186/2012 የኤክሳስ ታክስ አዋጅ መሠረት ባገለገሉ ተሽከርካሪዎች ላይ፣ እንደ አገልግሎት ዘመናቸውና ሥሪታቸው መጠን እስከ 500 በመቶ ኤክሳይስ ታክስ መጣሉ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ አዋጁ በፀደቀበት ዓመት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በመከሰቱና ተሽከርካሪዎቹን ወደ አገር ለማስገባት የዓለም የንግድ ሁኔታና እንቅስቃሴ በመገደቡ፣ አገር ውስጥ ገብተው ለባለቤቶቹ ይተላለፋሉ ተብለው የነበሩ ተሽከርካሪዎች ለባለቤቶቹ አለመድረሳቸውን የኢትዮጵያ ተሽከርካሪ አስመጪዎች ማኅበር አስታውቋል፡፡
ከ1,200 በላይ አባላት እንዳሉት ያስታወቀው ማኅበሩ ሐሙስ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ጉዳዩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፣ በየካቲት 2012 ዓ.ም. እንደ ገና ተሻሽሎ በወጣው የኤክሳይስ ሕግ ከነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ቢተገበርም፣ ቀድመው የታዘዙት ተሽከርካሪዎች በኮቪድ-19 ምክንያት ሊገቡ እንዳልቻሉ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ መሐመድ አህመዴ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም ተሽከርካሪዎቹ ነባሩ ሕግ እየተተገበረ በነበረበት ወቅት የተገዙ በመሆናቸው፣ በአዲሱ አዋጅ ሊተገበርብን አይገባም በሚል ማኅበሩ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለገቢዎች ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለጉዳዩ በማስረዳት መፍትሔ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም፣ መፍትሔ ማግኘት እንዳልቻሉ ፕሬዚዳንቱ አስረድተዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴርና የገቢዎች ሚኒስቴር ጉዳዩን የተቀበሉት ቢሆንም፣ በወቅቱ በዓለም ላይ በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለተፈጠረው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ ችግር፣ የአዋጁ አፈጻጸም ላይ ጊዜ ማራዘሚያ ወይም መመርያ በማውጣት ያለሥራ ከአንድ ዓመት በላይ ለቆሙት ተሽከርካሪዎች ፓርላማው መፍትሔ ይስጥ ብለዋል፡፡
በአማካይ አጠቃላይ ዋጋቸው ከ350 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመቱ የተነገረላቸው ተሽከርካሪዎች ለባለቤቶቻቸው ባለመድረሳቸው ከፍተኛ የገንዘብ ኪሳራ እንደደረሰባቸው፣ ንብረት አስይዘው የወሰዱትን የባንክ ብድር መመለስ አለመቻላቸውን፣ የአንዳንዶች የቤተሰብ ሕይወት ቀውስ ውስጥ በመግባቱ ሳቢያ ትዳር እየፈረሰ እንደሆነ አቶ መሐመድ አክለው ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ጉዳዩ በዋነኝነት ይመለከተዋል የተባለውንና በስንብት ላይ ያለውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ለወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁን ደውሎላቸው፣ ከተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ በኋላ ስልካቸውን ቢያነሱም፣ ‹‹የያዝነው ጉዳይ የለም፣ የነበሩትን ጥያቄዎች በአግባቡ መልሰናል፤›› ሲሉ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡