Thursday, March 23, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ፖሊሲ ተሻሽሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ተሰማ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የቆየው የግብርና ፖሊሲ ተሻሽሎ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡ ተሰማ፡፡

መረጃው የተሰማው የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ሥዩም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ፣ ሐሙስ ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጡ ነው፡፡

የግብርናውን ዘርፍ ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ያደርጋል የተባለለት ይህ አዲስ የግብርና ፖሊሲ፣ በማክሮ ኢኮኖሚ አጥኝዎች ተጠንቶና ተግምግሞ፣ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲፀድቅ መላኩን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ከሁለት ዓመት በፊት በሥራ ላይ ባዋለው አገር በቀል የኢኮኖሚክ ሪፎረም አማካይነት ‹‹አንድም መሬት ሳይታረስ ማደር የለበትም›› ተብሎ ዘመናዊ መስኖ በማስፋፋት ዕቅድ አማካይነት፣ የአገር ውስጥ ምርትን በማሳደግ መንግሥት ከውጭ የሚያስገባውን የስንዴ ምርት ሙሉ ለሙሉ ለማቆም ማስታወቁ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ምንም እንኳ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የግብርና ምርቶች ጭማሪ ቢያሳዩም አገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የሰሜኑ ግጭት፣ የአንበጣ መንጋና ሌሎች ችግሮች ምክንያት በአገር ዉስጥ የሸቀጦች የአቅርቦት እጥረት ማጋጠሙን  እዮብ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ለ2014 ዓ.ም. በጀት የሚውል የአሥር ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ግዥ እያካሄደ መሆኑን ሚኒስቴር ዴኤታው ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ከውጭና ከአገር ውስጥ አምራቾች የ53 ሚሊዮን ሊትር ዘይት ግዥ በመፈጸም ለአገር ውስጥ ፍጆታ እንደሚቀርብ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት በቀጣይ በአገር ውስጥ መመረት እየቻሉ የዋጋ ንረት ሊያመጡ የሚችሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ ጠንከር ያለ ማስተካከያ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የኢኮኖሚክ ማሻሻያ ኢኮኖሚው በተሻለ ቁመና ላይ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ፣ አገሪቱ የተፈራውን ያህል እንዳታሽቆለቁል እንዳደረጋት ገልጸዋል፡፡

‹‹በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚው አስገራሚ አፈጻጸም ላይ ነው ብንል የተጋነነ አይሆንም፤›› ብለዋል፡፡

ለአብነትም የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በቀደሙት ዓመታት ኪሳራ ያስመዘግቡ የነበሩ ቢሆንም፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግን አንድም የልማት ድርጅት ኪሳራ እንዳልደረሰበት ተናግረዋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ በ2014 ዓ.ም. አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ተቋማትን መልሶ በማደራጀት፣ ኃላፊነት የተሞላበትና የቢሮክራሲ ማነቆ እንዳይኖርባቸው በጥብቅ እየተሠራ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ መንግሥት ይመሠርታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ብልፅግና ፓርቲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከተወዳዳረባቸው 436 የፓርላማ መቀመጫዎች ውስጥ፣  መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን 410 ያህሉን ማግኘቱ ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች