Sunday, February 5, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

እየባሰበት ያለው የኑሮ ውድነት ትኩረት ይሻል!

የኢኮኖሚው ነገር ሲነሳ አሁን ዋነኛው አንገብጋቢ ጉዳይ ለሕዝብ ጭንቅ የሆነው የኑሮ ውድነት ነው፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሰበብ ስድ የተደረገው የግብይት ሥርዓት ፈር ካልያዘ፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን የተቆጣጠሩ ኃይሎች አገሪቱን ቀውስ ውስጥ እንደሚከቷት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ከአጠቃላይ አገራዊ የምርት ስብጥር አኳያ የአንበሳውን ድርሻ የሚይዙት የፍጆታ ምርቶች የዋጋ ግሽበት በተጠና መንገድ እንዲረግብ ካልተደረገ፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለከፋ ችግር መጋለጡ አይቀርም፡፡ መንግሥት ለማስተንፈሻ ሲል የሚወስዳቸው እንደ የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪን ለተወሰነ ጊዜ ማስቆም፣ በነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግና የመሳሰሉት ጊዜያዊ ዕርምጃዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከወዲሁ መታሰብ ያለበት ዘላቂው መፍትሔ ሊሆን ይገባል፡፡ በአብዛኛው በአገር ውስጥ የሚመረቱ የፍጆታ ምርቶች በውጭ ምንዛሪ ከውጭ የገቡ ይመስል፣ የዋጋ ግሽበቱ መረን ተለቆ እንደ ሰደድ እሳት ሲስፋፋ የንግድ መደብር ማሸግና ፈቃድ መንጠቅ መፍትሔ አይደለም፡፡ በመጀመሪያ በአገር ውስጥ የፍጆታ ምርቶች ተትረፍርፈው እንዲመረቱ የሚያስችል ፖሊሲና ስትራቴጂ ያስፈልጋል፡፡ በመቀጠል የአቅርቦት መስመሩን አንቀው ከያዙት ኃይሎችና ከደላሎች ነፃ ማውጣት ይገባል፡፡ መንግሥት ጉድለቱን ለመሸፈን ሲል እያተመ ገበያ ውስጥ የሚረጨው ገንዘብ የዋጋ ግሽበት እያባባሰ ስለሆነ፣ በከፍተኛ መጠን መቀነስ አለበት፡፡ የብር የመግዛት አቅም መዳከሙና የጥቁር ገበያው ሽሚያ ፈር አለመያዙ ከባድ ጉዳት እያደረሰ ስለሆነ፣ መንግሥት በጥናት ላይ የተመሠረተ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መቅረፅ ይጠበቅበታል፡፡ የገቢና የወጪ ንግድ ሚዛን እንዲጠበቅ የአገር ውስጥ ምርት ላይ መረባረብ ተገቢ ነው፡፡ ኢኮኖሚው በሥርዓት እንዲመራ ካልተደረገ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ እሳት የሚለበልበው የኑሮ ውድነት ሰላባ ሆኖ፣ አገሪቱ ለሁከትና ለትርምስ ትዳረጋለች፡፡

ኢትዮጵያ ከተሠራባት እንኳን ለራሷ ለአፍሪካም ትተርፋለች ሲባል ቀልድ አይደለም፡፡ በሁሉም መስክ የሚሠሩ ከተከበሩ ሥራ ፈጣሪዎች ይበዛሉ፣ ሀብት ይትረፈረፋል፣ ድህነት በእርግጥም ታሪክ ይሆናል፡፡ አሁን እንደሚታየው መሬትን በብሔር እየተደራጁ መውረር፣ የባንክ ብድርና የውጭ ምንዛሪ ማግበስበስ፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድል ያለ ገደብ በመጠቀም መክበርና ሥነ ምግባር በጎደለው ሁኔታ መበልፀግ መቆም አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የሌቦችና የዘራፊዎች ሲሳይ እየሆነች ዕድገት አይታሰብም፡፡ የኑሮ ውድነቱን ከሚያባብሱ መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል በግልጽ የሚታወቁ የተደራጁ ኃይሎች ማንንም ሳይፈሩ ምርቶችን መደበቅ፣ ዋጋ መቆለልና ማንም አይናገረንም በማለት ኢኮኖሚውን ማነቃቸው ይጠቀሳሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለአከፋፋይ በ300 ብር ያቀረበው ምርት፣ ሸማቹ ዘንድ ሲደርስ ከ700 ብር በላይ የሚያወጣው በምን ምክንያት ነው? አምራቹ በበርካታ ውጣ ውረድ ውስጥ ያመረተው ሲሚንቶ በአከፋፋዩና በቸርቻሪው ታግቶ በደላላ አስተናባሪነት ለሸማቹ በውድ ዋጋ ሲቀርብ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የማንን ጎፈሬ እያበጠረ ነው? ገበያ ውስጥ ጣልቃ ገብቶ ዋጋ መወሰን ባይኖርበትም፣ እንዲህ ያለውን መረን የወጣ ብልሹ አሠራር ማስወገድ ካልቻለ ፋይዳው ምንድነው? የሕዝብ ጩኸት ሲበረታ እየተደናበሩ የንግድ መደብር ማሸግና ፈቃድ መንጠቅ ላይ ከመረባረብና የበለጠ ቀውስ ከመፍጠር፣ ሥርዓት ባለው መንገድ ኃላፊነትን መወጣት የመንግሥት ኃላፊነትም ግዴታም ነው፡፡

ኢኮኖሚውን ከገባበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት የተለያዩ ተግባራት ይከናወናሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የማይክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት መፍጠር፣ ጥብቅ የሆነ የገንዘብና የበጀት ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ፣ ለአበዳሪዎች አስተማማኝ ደንበኛ መሆን የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት፣ ከኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥትን ተዋናይነት የሚቀንሱ ትክክለኛ ዕርምጃዎችን መውሰድ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በአስተማማኝ መሳብ፣ በአጭርና በረዥም ጊዜ ሒደት የሚከናወን ትክክለኛ የፕራይቬታይዜሽን ሥርዓት መዘርጋት፣ ቅጥ ያጣ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርና ተጠያቂነት የሌለበት የብድር አሰጣጥን ፈር ማስያዝ፣ የብር ምንዛሪ ተመን ማስተካከያን ጥንቃቄ በተሞላበት ሥርዓት ማከናወን፣ የብልሹው የግብይት ሥርዓት ውጤት የሆነውን የዋጋ ግሽበት መግታትና የመሳሰሉት ተግባራት የግድ ናቸው፡፡ እነዚህ ተግባራት ደግሞ ከፍተኛ የሆነ ትጋት ይጠይቃሉ፡፡ የውጭ እጅ ጠምዛዦች ወሳኝ የሚባሉ የልማት ድርጅቶችን በፕራይቬታይዜሽን ስም ጠራርገው እንዳይወስዱ፣ የመንግሥትን የኢንቨስትመንት ድርሻ በመቀነስ ስም አትራፊ የሚባሉ ተቋማትን እንዳይነጥቁና ባዶ እንዳያስቀሩ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ የውጭ ብድር ጫና እንዲቃለል ከአበዳሪዎች ጋር መልካም ግንኙነት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ሥራ ፈጠራም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሠራበት ይገባል፡፡ ለወጣቶች ሥራ ፈጠራ እየተባለ ያለ ዕቅድ የሚከናወኑ ድርጊቶች ቆመው፣ ተቋማዊ አሠራር መስፈን አለበት፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከገባበት አዘቅት የሚወጣው በእሳት ማጥፋት ዓይነት አሠራር አይደለም፡፡

በንግድና በኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማሩ ወገኖች ከሸፍጥ የፀዳ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ችግር ያለባት አገር ናት፡፡ ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው በትክክለኛው መንገድ ሲሠራ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለቁጥር የሚያታክቱ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ናት፡፡ የሚያነሳሳው ከተገኘ ሠርቶ ተዓምር መፍጠር የሚችል ጠንካራ ሕዝብ አላት፡፡ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ከዕውቀትና ከጉልበት ጋር በማቀናጀትና ዘመናዊ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም፣ በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማቀላጠፍ የግድ ማጭበርበርና ተራ ሌብነት ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ከአቋራጩ የአየር በአየር መንታፊነት ውስጥ በመውጣት፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሥራ ለመጀመር መነሳት የግድ ይላል፡፡ የንግድና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራትን በማጠናከርና ጠንካራሥነ ምግባር መመርያ በማውጣት፣ ከኋላ ቀርና ልማዳዊ አሠራር ውስጥ በፍጥነት መውጣት ተገቢ ነው፡፡ ግብርመሰወርና ከተራሚዛን ማጭበርበር ሌብነት በመላቀቅ፣ ለሥራ ፈጠራና ለጤናማ የንግድ ውድድር መስፈን አስተዋጽኦ ማበርከት የግድ ይላል፡፡ ለአገር አንዳች የረባ ነገር ሳያበረክቱ መሬት፣ የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪና የመሳሰሉ ጥቅማ ጥቅሞች ካላገኘን እያሉ ትርምስ መፍጠር አሳፋሪ ነው፡፡ ይልቁንም ከውጭ የሚመጡ የፍጆታ ምርቶችን በአገር ውስጥ ለመተካት ታጥቀው መነሳት ይገባቸዋል፡፡ አገርን ከመዝረፍ አገርን ማልማት ይለመድ፡፡ መንግሥት ደግሞ በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ የትርፍ ህዳግ የሚወስን ሕግ በመደንገግ፣ የንግዱ ማኅበረሰብ ዘረፋ ከሚመስለው ትርፍ ማግበስበስ ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ሃያኛው ክፍለ ዘመን ከዝነኞቹ የዓለም ኢኮኖሚ ሊቃውንት ቀድመው የምጣኔ ሀብት ጥልቅ ትንታኔ በመስጠታቸው የሚታወቁት ሊቁ ነጋድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ፣ ‹‹አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያ›› እና ‹‹መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር›› በተባሉ ርዕሶች በወጡ ዝነኛ ጽሑፎቻቸው ለዚህ ትውልድ ጭምር የሚሆን ምክረ ሐሳብ ትተው አልፈዋል፡፡ በበርካታ የመስኩ ምሁራን ሳይቀር ከፍተኛ አክብሮት የተቸራቸው ጠቢቡ ገብረ ሕይወት፣ ሕዝብ ወይም መንግሥት አገር ለማልማትና ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ ለመፍጠር እንዴት ሊሳካላቸው እንደሚችሉ፣ ወይም ውድቀት እንደሚያጋጥማቸው በዝርዝር አሥፍረዋል፡፡ ለምጣኔ ሀብት ዕድገት ቁልፍ ብለው ካወሱዋቸው መሠረታዊ ጉዳዮች መካከል ዕውቀት፣ ክህሎት፣ ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና ቴክኒካዊ የለውጥ ዕርምጃ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹…አዕምሮ የሌለው ሕዝብ ሥራት የለውም፣ ሥራት የሌለው ሕዝብም የደለደለ ኃይል የለውም፡፡ የኃይል ምንጭ ሥራት ነው እንጂ፣ የሠራዊት ብዛት አይደለም፡፡ ሥራት ከሌለው ሰፊ መንግሥት ይልቅ፣ በሕግ የምትተደዳር ትንሽ ከተማ ሞያ ትሠራለች…›› ሲሉ በዘመኑ የአጻጻፍ ሥልት፣ መንግሥት የሚባለው ተቋም በሥርዓት አገር ማስተዳደር እንዳለበት በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ሰሚ ባለመገኘቱ ግን ኢትዮጵያ እሳቸው ካለፉ በኋላም ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ፣ የሐሳብና የቁሳዊ ድህነት አረንቋ ውስጥ እንደ ተዘፈቀች አለች፡፡ አሁንም ሕዝቧ በምግብ ራሱን መቻል አቅቶት በድህነት ይማቅቃል፡፡ ከሚስተዋለው ፖለቲካዊ ቀውስ በላይ የኑሮ ውድነቱ ቀውስ የእያንዳንዱን ዜጋ በራፍ እያንኳኳ ነው፡፡ እየባሰበት ላለው የኑሮ ውድነት ትኩረት መስጠት የግድ መሆን አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

ከውጭ ይገቡ የነበሩ 38 ዓይነት ምርቶች እንዳይገቡ ዕግድ ተጣለ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 38 ከውጪ የሚገቡ ምርቶች ላይ ዕገዳ...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና የመንግሥት ውዝግብ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት...

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ምሥረታ ዝግጅቶችና ከገበያው የሚጠበቁ ዕድሎች

ኢትዮጵያ ከ50 ዓመት በኋላ ዳግም የምታስጀምረውን የካፒታል ገበያ ዘመኑን...

አዲሱ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ቀዳሚ ጉዳዮች ይፋ አደረጉ

አዲሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ትኩረት አድርገው የሚሠሩባቸውን ቀዳሚ...

መንግሥት የደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ድንበር ጥሰው የሚያደርሱትን ጥቃት እንዲያስቆም ተጠየቀ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ...

አዲስ ሲኖዶስ አቋቁመዋል በተባሉና በኦሮሚያ መንግሥት ላይ ክስ ለመመሥረት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ከገባችበት አረንቋ ውስጥ በፍጥነት ትውጣ!

የአገር ህልውና ከሕዝብ ሰላምና ደኅንነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ አገር ሰላም ውላ ማደር የምትችለው ደግሞ የሕዝብ ደኅንነት አስተማማኝ ሲሆን ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት በአገር ህልውና...

የፈተናው ውጤት የፖለቲካው ዝቅጠት ማሳያ ነው!

በ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከአጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 3.3 በመቶ ያህሉ ብቻ ማለፋቸው፣ የአገሪቱን የትምህርት ጥራት ደረጃ በሚገባ ያመላከተ መስተዋት እንደሆነ አድርጎ መቀበል ተገቢ ነው፡፡...

የምግብ ችግር አገራዊ ሥጋት ስለደቀነ ፈጣን ዕርምጃ ይወሰድ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሰው ልጆችን አቅም በብርቱ እየፈተኑ ያሉ በርካታ ችግሮች አሉ፡፡ ከችግሮቹ ብዛት የተነሳ አንዱን ከሌላው ለማስቀደም የማይቻልበት ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የምግብና የሰላም...