የሞባይል ባንክ አገልግሎት ለመጀመር ከመንግሥት ጋር እየተነጋገረ ነው
ከስድስት ወራት በኋላ ሥራ የሚጀምረው ሳፋሪኮም በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2023 የራሱን የመሠረተ ልማት ግንባታ እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡
ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን የቴሌኮም ፈቃድ ጨረታ አሸንፎ ወደ ሥራ ለመግባት ዝግጅት እያደረገ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2022 ለኢትዮጵያውያን ሁለተኛ የሆነውን የቴሌኮም አገልግሎት ያስጀምራል፡፡
ኩባንያው በአገር ውስጥ ሊያስጀምረው ያሰበውን አገልግሎትና ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ፣ ዓርብ ነሐሴ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በመግለጫው ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሳፋሪኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር ሶውስ፣ ምንም እንኳን ኩባንያውን ሥራ ለማስጀመር አሁን በሥራ ላይ ያለውን የኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማት የሚጠቀሙ ቢሆንም፣ ከአንድ ዓመት በኋላ የራሱን መሠረተ ልማት የማልማት ዕቅድ እንዳለው አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮምን መሠረተ ልማት ለመጠቀም የሚያስችለውን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ውይይት እያደረገ መሆኑን አቶ አንዋር ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ እንደ አዲስ ለማልማት የታሰበውንም ሆነ አሁን በሥራ ላይ ያለውን መሠረተ ልማት በጋራ መጠቀም እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ኩባንያው በሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት 8.5 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ያቀደ ሲሆን፣ በየዓመቱ 300 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ የኔትወርኪንግና የአይሲቲ ሥራዎችን እንደሚያከናውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሠራተኛ ቅጥር እንደጀመረ ጠቁመው፣ ኩባንያው በመጪው ዓመት 1,000 ኢትዮጵያውያን ለመቅጠር ማቀዱንም ገልጸዋል፡፡
‹‹እተካሄደ ያለው የሥራ ቅጥር ለኢትዮጵያ ሕዝብ መጪውን ጊዜ ዲጂታል ለማድረግ የገባነውን ቃል ለማሳካት እንዲያስችለን ታስቦበት የተዘጋጀ ነው፤›› ሲሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በየዓመቱ 150 አዳዲስ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን በመቅጠር፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለንግድ ዘርፍ እንቅስቃሴ አስፈላጊ የሆኑ ክህሎቶችን መቅሰም የሚችሉበት ሰፊ የአመራር ሥልጠና ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ ኩባንያው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ለማስጀመር ከብሔራዊ ባንክና ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ውይይት እያደረገ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል ሁኔታዎች ሲመቻቹና መመርያዎች ሥራ ለማስጀመር ግልጽ ሆነው ሲቀርቡ ሥራ ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
በሳፋሪኮም ስም የተመዘገበው ‹‹ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያ›› የተሰኘው ጥምረት በዘርፉ አሉ የሚባሉ ዓለም አቀፍ ስመ ጥር የቴሌኮም ኩባንያዎችንና ተቋማትን በቅንጅት የያዘ ነው፡፡ እነሱም ሳፋሪኮም፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ቮዳፎን ግሩፕ፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽንና ሲዲሲ ግሩፕ ናቸው።
የኢትዮጵያ መንግሥት የሞባይል ባንክ አገልግሎት ዘርፉን ለኢትዮ ቴሌኮምና ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች ብቻ መፍቀዱ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህ ዘርፍ በሒደት ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ሊደረግ እንደሚችል ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከጥቂት ወራቶች በፊት አስታውቀዋል፡፡