በኢትዮጵያ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት የጋራ ምክር ቤት መሠረቱ፡፡
በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሴቶች የጋራ ምክር ቤት የመሠረቱት ዓርብ ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፣ የምክር ቤቱ መመሥረት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ እንዲሠሩ እንደሚያግዝ ተጠቁሟል።
የጋራ ምክር ቤቱ መሥራችና ሥራ አስፈጻሚ አባል ነቢሐ መሐመድ እንደተናገሩት፣ በቅርቡ በተካሄደው ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ላይ በዕጩነት ከቀረቡ 9,505 ተወዳዳሪዎች መካከል የሴቶች ቁጥር 1,987 ብቻ ነው።
ይህ አኃዝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ ረገድ ሰፊ ክፍተት እንዳለባቸው የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም የሴቶችን የፖለቲካ መስክ ተሳትፎና አመራር ሰጪነት ለማሳደግ ሁለንተናዊ ጥረት የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ የጋራ ምክር ቤቱ መመሥረቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡
ፓርቲዎች አባላት ሲመለምሉ ሴት ዕጩዎችን በሥራ አስፈጻሚነት የኃላፊነት ዕርከን የማምጣት ተግባራትን ማከናወን እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመው፣ የጋራ ምክር ቤቱ ሴቶች በተለይም በፖለቲካው መስክ ተሳትፏቸው የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመታገል የሚያስችል ዕድል እንደሚከፍትላቸው ያላቸውን እምነት አውስተዋል።
በምክር ቤቱ በአባልነትም ይሁን በሌሎች መስኮች መሳተፍ የሚችሉት በአገሪቱ ሕጋዊ ምዝገባ አካሂደው የሚንቀሳቀሱ 53 የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት ብቻ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ በአገሪቱ በሕጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴት አባላት በግለሰብ ደረጃ የሚሳተፉበትና በፖለቲካው መድረክ እጅግ አነስተኛ የሆነውን የሴቶች ተሳትፎን ክፍተት ለመሙላት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት፣ በምሥረታው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ተናግረዋል።