Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትሽልማት የጎረፉለት የኦሊምፒከ አትሌቲክስ ቡድን

ሽልማት የጎረፉለት የኦሊምፒከ አትሌቲክስ ቡድን

ቀን:

በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ላይ የሚካፈሉ አትሌቶችን ባስመዘገቡት ውጤት መሠረት መሸለም ከተጀመረ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ እ.ኤ.አ 1960 የሮም ኦሊምፒክ ጨዋታ ጀምሮ፣ በተለያዩ ሻምፒዮናዎች ላይ ተሳትፎ የሚመጣን ብሔራዊ ቡድን እንደ ቡድኑ ውጤት ሽልማት ይበረከትለታል፡፡

ሽልማቱም እንደየዘመኑ ቢለይም፣ ሹመት (ማዕረግ መስጠት)፣ መኖሪያ ቤት፣ መሬት፣ መኪናና የገንዘብ ሽልማቶች የተለመዱ ናቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር የወርቅ ሜዳሊያ እንዲሁ ከሽልማት ዝርዝሮች ውስጥ ይካተታል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ ሻምፒዮናዎች ላይ ሲሳተፉ ይነስም ይብዛም ሽልማት ይበረከትላቸዋል፡፡ በተለይ በእግር ኳሱም እንዲሁም በአትሌቲክስ ስፖርት ላይ ተሳትፎ አድርገው አመርቂ ውጤት ላመጡ የሚከናወን ቢሆንም፣ በኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ የተሳተፈ ቡድን ግን የሚደረግለት ሽልማት ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

- Advertisement -

በተለይ ባለፉት ሁለትና ሦስት ኦሊምፒኮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ የቻሉ አትሌቶች የመሬት ሽልማት ተብርክቶላቸው፣ መሬቱንም ለኢንቨስትመንት በማዋል ፍሬ ማፍራት ችለዋል፡፡

በዘንድሮ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በርካታ ሽልማቶች እየተበረከቱለት ይገኛል፡፡ ምንም እንኳን ቡድኑ በአንፃራዊ መልኩ ዝቅተኛ ውጤት ቢያጠናቅቅም፣ ለነገውም ተምሳሌት ይሆን ዘንድ በሽልማት ተንበሽብሿል፡፡

ገና ከቶኪዮ በተመለሰ ማግስት በኦሊምፒኩ ላይ ሜዳሊያ ማምጣት የቻሉትን አትሌቶች መሬት መሸለም የጀመረው የደቡብ ብሔሮች በሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ነበር፡፡ በዚህም መሠረት የደቡብ ክልል ለሰለሞን ባረጋ በወልቂጤ ከተማ 10 ሺሕ ካሬ ሜትር፣ እንዲሁም ለለሜቻ ግርማ፣ ጉዳፍ ፀጋይና ለተሰንበት ግደይ በፈለጉበት የክልሉ ከተማ የአንድ ሺሕ ካሬ ሜትር መሬት መስጠቱን አስታውቋል፡፡ ከመሬቱ ባሻገርም የብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በብሔራዊ ቤተ መንግሥት የታደመው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ አትሌቲክስ ቡድን እንደየደረጃው ከዘጠኝ ሚሊዮን ብር በላይ ተሸልሟል፡፡

በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ወደ ቶኪዮ ያቀናውን ልዑካን ቡድን አባላትን ያካተተ ሲሆን፣ በተለይ ሜዳሊያ ያመጡ አትሌቶች ከፍተኛውን ሽልማት ማግኘት ችለዋል፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ማምጣት የቻለው ሰለሞን ባረጋ ሦስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቶዮታ መኪና እና 50 ግራም የወርቅ ሜዳሊያ ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተቀብሏል፡፡

የ3000 ሺሕ ሜትር መሰናክል የብር ሜዳልያ ያስገኘው ለሜቻ ግርማ 1.5 ሚሊዮን ብር፣ የሴቶች 10,000 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ባለድሏ ለተሰንበት ግደይና የ5000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ጉዳፍ ፀጋይእያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሚሊዮን ብር ተሸልመዋል፡፡ በኦሊምፒኩ ለተሳተፉ ሁሉም አትሌቶች 50,000 ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

በተለያዩ ርቀቶች ላይ መሳተፍ የቻሉ ዲፕሎማ ማግኘት የቻሉ አትሌቶች ከ200 ሺሕ ብር እስከ 150 ሺሕ ብር ድረስ ሲሸለሙ፣ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ በቴኳንዶ ስፖርት መወከል የቻለው ሰለሞን ቱፋ 150 ሺሕ ብር ተሸላሚ መሆን ችሏል፡፡

  ከዚህም ባሻገር ወርቅ ላስገኘ ዋና አሠልጣኝ 300 ሺሕ ብር እንዲሁም ለምክትል አሠልጣኝ 200 ሺሕ ብር ሲሸለሙ፣ የብር ሜዳልያ ላስገኘ አሠልጣኝ 200 ሺሕ ብር እና የነሐስ ሜዳልያ ማስገኘት ለቻሉም ለእያንዳዳቸው 70,000 ብር ሽልማት አግኝተዋል፡፡

የኦሊምፒክ ቡድኑ ከቀናት በፊት በኦሊምፒክ ኮሚቴና በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አማካይነት የገንዘብና የዕውቅና ሽልማት ተበርክቶለታል፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ወርቅ ላመጣ 2.2 ብር ሽልማት፣ ብር ላስገኘ 1.5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የነሐስ ሜዳሊያ ላገኙ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 1.2 ሚሊዮን ብር ሽልማት አበርክቷል፡፡ ሽልማቱ አሠልጣኞችን ሳይቀር ያካተተ ሲሆን በቶኪዮ ኦሊምፒክ በእግር ኳስ ዳኝነት የተሳተፈው ባምላክ ተሰማም 50 ሺሕ ብር አግኝቷል፡፡

በአንፃሩ ውዝግብ የማይለየው የኦሊምፒክ ኮሚቴው በቶኪዮ ኦሊምፒክ በቴኳንዶ የወከለውን ሰለሞን ቱፋን ከሽልማትና ምሥጋና ውጪ ማድረጉ በርካቶችን አነጋግሯል፡፡ ስፖርተኛውም በፌስቡክ ገጹ ላይ ‹‹አገሬ የእንጀራ እናት ሆነችብኝ ›› ሲል ቅሬታውን አስፍሯል፡፡

ሰለሞን የኦሊምፒክ ኮሚቴ የምሥጋናና የሽልማት መርሐ ግብር ላይ እንኳን ሊሸልመኝ ይቅርና ለተሳትፎዬ ስሜን እንኳን ጠርቶ አላመሰገነኝም ሲል ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ለአትሌቶች እንደየደረጃቸው ከአንድ ሚሊዮን እስከ 300 ሺሕ ብር ድረስ ሸልሟል፡፡ ለአሠልጣኞች ከ50 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ ብር ሸልሟል፡፡

በቶኪዮ ኢሊምፒክ የተመዘገበውን ውጤት ተመልክቶ በርካታ ሐሳቦች ሲነሱ ቆይተዋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ከቶኪዮ ከተመለሰ በኋላ ስለ ቆይታውና ስለአጠቃላይ ውጤቱ በተመለከተ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ሁለቱም ተቋማት ለውጤቱ መጥፋት ምክንያት ያሉትን በጋዜጣዊ መግለጫው ቢያብራሩም እርስ በርስ መወቃቀሳቸውን ቀጥለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የኦሊምፒክ ቡድኑ ወደ አገር ቤት መመለሱን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ሪፖርት አንደሚጠብቁ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በነበረው የሽልማትና የዕውቅና መርሐ ግብር ላይ በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት የኢትዮጵያ ኢሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዳግም መዋቀር እንዳለበት ያመለከተ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

በቶኪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት በተመለከተ የሚመለከተው አካል በጥልቀት ማየት እንዳለበትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...