Monday, July 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በነሐሴ አጋማሽ ከወልቂጤ ወደ አዲስ አበባ ለመጓዝ አይሱዙ የሚባለው ቅጥቅጥ መለስተኛ አውቶቡስ ውስጥ ተሳፍሬያለሁ፡፡ አውቶቡሱ ሞልቶ ጉዞ ጀመርን፡፡ አጠገቤ በረባ ባልረባው የሚነጫነጭ አንድ ጎልማሳ ተቀምጧል፡፡ ይህ በ30ዎቹ የዕድሜ መጨረሻ ላይ የሚገኝ የሚመስል ጎልማሳ የሞባይል ስልኩን ደጋግሞ እየደወለ ከሚያናግራቸው ሰዎች ጋር በብስጭት ይነጋገራል፡፡ ከስልኩ መለስ ሲል ደግሞ የአውቶቡሱ ሾፌርና ረዳቱ በሚነጋገሩት ይናደዳል፡፡ አንዴ አውቶቡሱ ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎችን ሌላ ጊዜ ደግሞ በመስኮት ወደ ውጭ እያየ ‹‹ኤጭ›› እያለ ይቁነጠነጣል፡፡ እኔ ደግሞ በሰውየው አኳኋን ግራ ተጋብቼ አየዋለሁ፡፡ እሱ ግን ለአፍታም ከቁብ አልቆጠረኝም፡፡

ሾፌሩ የተለያዩ ሙዚቃዎችን እየመረጠ ከቆየ በኋላ የአንድ የዘመኑን ድምፃዊ ሙዚቃ ከፍላሹ ላይ ለቀቀው፡፡ ‹‹ካልጠፋ ዘፈን ይኼንን ታመጣለህ እንዴ? ስንትና ስንት ዘፈኖች እያሉ ይኼ እንዴት ይመረጣል?›› እያለ ሾፌሩን ሲነተርከው የሾፌሩ ረዳት ጀርባውን ሰጥቶት፣ ‹‹ወንድም የአውቶቡሱ የጉዞ ዘፈን የሚመረጠው በሾፌሩ እንጂ እንደ መጠጥ ቤት በተስተናጋጆች ምርጫ አይደለም…›› እያለ ምላሽ ሰጠው፡፡ ሌሎችም ከዚህ ዘፋኝ በላይ ማን ይምጣለት እያሉ ጨመሩበት፡፡ አውቶቡሱም መጓዙን ቀጠለ፡፡ ሙዚቃውም እንዲሁ፡፡

በረዳቱና በሌሎቹ አስተያየቶች ያልተደሰተው ጎልማሳ፣ ‹‹በቤታችሁ አውቃችሁ ሞታችኋል፡፡ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ሒሩት በቀለ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ነፃነት መለሰ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ አረጋኸኝ ወራሽ…›› እያለ የበርካታ ድምፃውያንን ስሞች ከዘረዘረ በኋላ፣ ‹‹እነዚህን የመሳሰሉ ድንቆች በተፈጠሩባት አገር እንዴት የአንድ ሰው ዘፈን ብቻ ያደነቁረናል? አሁን ደግሞ ኦሮሚኛ ከጉራጊኛ፣ አማርኛ ከደቡብ፣ ሶማሊኛ ከአፋርና ከሌሎችም ጋር አሪፍ ተደርገው በሚሠሩበት ዘመን የምን አንድ ዘፋኝ ላይ መንጠልጠል ነው? ታክሲ ውስጥ፣ ሻይ ቤት፣ ሆቴል ውስጥ፣ ሺሻ ቤት፣ ጫት ተራ፣ ድድ ማስጫ… አንድ ነገር ብቻ…›› እያለ ተብሰከሰከ፡፡

በዚህ መሀል ተንጠራርቼ፣ ‹‹ወንድም የብዙኃኑ ምርጫ ከሆነ አናሳዎች ለብዙኃን መገዛት አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ በየትም ቦታ የሚደረግ አሠራር ነው፡፡ ስለዚህ ተረጋጋ፤›› በማለት ሐሳቤን ጣል አደረግኩለት፡፡ ሰውየው ወደ እኔ ዞር ብሎ ካየኝ በኋላ፣ ‹‹እኔን የሰለቸኝ እኮ አንተ በምትለው ዓይነት እንተዳደር የሚባለው ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ እዚህ አውቶቡስ ውስጥ ያለው ሰው በሙሉ ይህ ሙዚቃ ይመቸኛል ቢል ለእኔ አይስማማኝም፡፡ ሌላው ቀርቶ የአገሪቱ ሕዝብ በሙሉ ቀይ ቀለም እንወዳለን ቢል የእኔ ምርጫ ሰማያዊ ነው፡፡ ስለዚህ ብዙኃኑ የተቀበለውን አናሳው ሳይወድ በግድ መቀበል አለበት የሚለው አይስማማኝም፤›› ብሎ ፊቱን ወደ መስኮቱ መለሰ፡፡

የሁለታችንን ውይይት ሲያዳምጡ ከነበሩት መካከል አንዱ በዓይኑ ጠቀስ አደረገኝ፡፡ እኔ ደግሞ በግንባሬ ምንድነው በማለት ጠየቅኩት፡፡ ወረቀት ላይ የሆነ ነገር ጫር ጫር አድርጎ፣ ‹‹ወፈፍ ያደርገዋል፣ መለስ እስኪልለት ዝም በለው፤›› የሚል መልዕክት አሳየኝ፡፡ የሰውየውን ምክር ተቀብዬ እኔም ዝም አልኩ፡፡ አውቶቡሱ ወሊሶ ደርሶ ሲቆም አንዳንድ ተሳፋሪዎችን ተከትዬ ወረድኩ፡፡ መንገዱ ዳር ቆሜ ግራ ቀኙን ሳማትር አጠገቤ የነበረው ጎልማሳ መጥቶ ቆመ፡፡ እሱም እንደ እኔ ዙሪያ ገባውን ማየት ጀመረ፡፡

በዚህ መሀል፣ ‹‹የእኔ ወንድም ሥራህ ምንድነው?›› በማለት ጠየቀኝ፡፡ ‹‹መምህር ነኝ፤›› አልኩት፡፡ ‹‹የዕውቀት አባት መምህር ነህ ለካ? እኔ ደግሞ ወይ ነጋዴ፣ ወይ ካድሬ፣ ወይ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጸሐፊ መስለኸኝ ነበር፡፡ መምህር ከሆንክማ ብዙ ነገር እነግርሃለሁ፤›› ብሎኝ ወደ አውቶቡሱ በፍጥነት ተመለሰ፡፡ ቆየት ብሎ ወደ መቀመጫዬ ስመጣ እግሩ ሥር ካኖረው አነስተኛ ሻንጣ ውስጥ አንድ አጀንዳ ሲያወጣ ነበር፡፡

ጉዞአችንን እንደጀመርን፣ ‹‹መምህር ይህንን ተመልከት፤›› ብሎ አጀንዳውን ሰጠኝ፡፡ አጀንዳው በተለያዩ ጽሑፎችና ግጥሞች ዳር እስከ ዳር ሞልቷል፡፡ በአረንጓዴ፣ በጥቁር፣ በሰማያዊና በቀይ ብዕሮች የተከተቡ ናቸው፡፡ ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ ከ1967 ዓ.ም. እስከ 1971 ዓ.ም. ድረስ የተጻፉ ናቸው፡፡ ‹‹ይኼ የማን ነው?›› አልኩት፡፡ ፍዝዝ ብሎ እያየኝ፣ ‹‹የአባቴ ማስታወሻ ነው፤›› ሲለኝ ከዓይኖቹ የእንባ ዘለላዎች ተዘረገፉ፡፡ ዓይኖቹን ጠራርጎ ከተረጋጋ በኋላ፣ ‹‹ፍቅር፣ ደግነት፣ ክፋትና ሰይጣናዊ ድርጊቶች የሞሉበት ማስታወሻ ነው…›› እያለኝ አንገቱን ደፍቶ ማልቀስ ጀመረ፡፡

አጀንዳው ውስጥ የተጻፉትን አለፍ አለፍ እያልኩ እየገላለጥኩ ሳይ ጸሐፊው ምጡቅ የሆነ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ የነበረ ሰው ይመስላል፡፡ የግጥሞቹ ውበትና ቤት አመታት፣ የጽሑፎቹ ዓረፍተ ነገር አሰካክና የሚያስተላልፉት ላቅ ያለ መልዕክት አስገራሚ ነው፡፡ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ሁነቶች ተነስቶ ስለነበረው ሕዝባዊ እንቅስቃሴና ስለተፈጸመው የግፍ ድርጊት፣ በአጫጭር ግጥሞችና በአጫጭር ማስታወሻዎች የሠፈሩት መልዕክቶች የዚህን ዘመን መጻሕፍት ያስንቃሉ፡፡ ‹‹ለመሆኑ አጀንዳውን ምን ልታደርገው ነው?›› አልኩት አዲስ አበባ ስንቃረብ፡፡ ‹‹አቃጥለዋለሁ!›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡

በአጀንዳው ውስጥ የሠፈሩትን ነገሮች የዚህ ዘመን ትውልድ ማንበብ ስላለበት፣ ‹‹እባክህ እንዳለ ቢታተም እኮ ለአገር ጠቃሚ ነው፤›› ስለው ከት ብሎ ሳቀብኝ፡፡ ‹‹ኧረ እባክህ መምህር አትቀልድ፡፡ ይኼ በኮሜዲና በለብ ለብ ሙዚቃ አቅሉን የሚስት ትውልድ ለዚህ ዓይነት ቁም ነገር ነገር የለውም፡፡ በዚህ ማስታወሻ ምክንያት ራሴን ስቼ እንዳበደ አማኑኤል ሆስፒታል የገባሁት እኮ ቁም ነገር በማይገባቸው ከንቱዎች ምክንያት ነው፤›› ብሎኝ አጀንዳውን ቀማኝ፡፡ ቢቸግረኝ፣ ‹‹ኧረ እባክህ ተለመነኝ…›› እያልኩ ስማፀነው፣ ‹‹እኔን ከምትለምን እንቶ ፈንቶ ላይ ተጥዶ የሚውለውን የፌስቡክ አብዮተኛ ወደ ቁምነገር አምጣው…›› ብሎኝ አውቶቡሱ ሲቆም ጥሎኝ ፈረጠጠ፡፡ ስንት የሚገርሙ ታሪኮች የታጨቁበትና እስካሁን ያልሰማሁዋቸው ጉዶች የተዘረዘሩበት አጀንዳን ይዞ ከአጠገቤ ብን ያለው ጎልማሳ ጉዳይ እየከነከነኝ አለሁ፡፡ ስንትና ስንት የኅትመት ብርሃን ያላዩ ጉዶቻችን በከንቱ ቀርተው ይሆን? በሕይወት እያሉ የሚገርሙ ታሪኮቻችንን በግል የሚተርኩልን አስገራሚ ሰዎችን ከማለፋቸው በፊት ለሕዝቡ እንዲቀርቡ ካልተደረጉ ምን ይሻል ይሆን? ኧረ ጎበዝ በየቦታው ስንት ጉድ አለ እናስብበት፡፡

(መምህር ገረመው አብዛ፣ ከወልቂጤ)

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሚዲያው በሕዝብ የህሊና ችሎት ከተዳኘ በቂ ነው!

መሰንበቻውን ድንገት ሳይታሰብ ያለ ማስጠንቀቂያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

የባህር በር ጉዳይ

በታምሩ ወንድም አገኘሁ ድሮ ድሮ ገና ልጅ ሆኜ ፊደል እንደቆጠርኩ...

አገሩ ፖለቲካዊ ስክነትና መደማማጥ ያስፈልገዋል

በንጉሥ ወዳጀነው    ኢትዮጵያ የሁላችንም የጋራ ቤት ነች፡፡ ‹‹ጥያቄዬ ተመለሰልኝ››፣...

የመንግሥት የሰብዓዊ መብት ተቋም ለምን የመንግሥት ሚዲያን ማስተማር አቃተው

በገነት ዓለሙ የአገራችን የ2016 የበጀት ዓመት መሰናበቻና የአዲሱ የ2017 በጀት...