Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉይህስ አያስቅም!

ይህስ አያስቅም!

ቀን:

በሁሴን አዳል መሐመድ (ዶ/ር)

የሚከተለውን በሁለት ስንኞች የተቋጠረ ግጥም ለጽሑፉ መግቢያ አድርጌ የተጠቀምኩት በምክንያት ሲሆን፣ ግጥሙ ያዘለውን መልዕክትና በዚህ ርዕስ ለምን መጻፍ እንዳስፈለገኝ ከጽሑፉ ይዘት መረዳት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህን ጽሑፍ በጥሞና እንዲያነቡ ውድ አንባቢያንን በትህትና እጋብዛለሁ፡፡

‹‹ያሳዝናል እንጂ ይህስ አያስቅም፣

- Advertisement -

በሰው ተመስሎ ዝንጀሮ ጫት ሲቅም››

ጫት በኅብረተሰቡ ዘንድ ዕውቅና ካገኙ ባህላዊ ዕፅዋት (Cultural Plants) መካከል አንዱ ሲሆን፣ በአንፃሩ በሱስ አምጪነት የሚታወቅ ዕፅዋት ነው፡፡ ቀደም ባለው ዘመን በአገራችን ጫት የሚቅሙ ሰዎች በዕድሜ የገፉና ለፀሎት የተገቡ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ፣ ዱአ የሚቀመጡ ሰዎች እንጂ የማንኛውም ወጣት አልነበረም፡፡ ጫት የሚቃምበት ዓላማ፣ ወቅት፣ ቦታውና ሰው ጭምር ተመርጦ በሥርዓትና በጧሄራ ይፈጸም ነበር፡፡ በድሮ ጊዜ ጫት ለቀለብ፣ ለመዝናኛና ጊዜ ማሳለፊያ ተብሎ ፈፅሞ አይቃምም፡፡ ባህላዊ የቤተሰብ አስተዳደር ሥርዓታችን ጠንካራና ጤናማ ስለነበር ጫት መቃም ለወጣቶች ከተከለከሉ ማኅበረሰባዊ ድንጋጌዎች መካከል አንዱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ማንም ሰው የዕድሜ፣ የፆታም ሆነ የሌሎች ሁኔታዎች ገደብ ሳይደረግበት በዘፈቀደ የትም ሆኖ ጫት ይቅማል፡፡ አንዳንድ ሰዎች ጫት ለምን እንደሚቅሙ ሲጠየቁ ጊዜ ለማሳለፍ፣ ድብርት ለማባረር፣ ደስታ ለማግኘት፣ ቀልብን ሰብስቦ ሥራን በጥሞና ለማከናወን፣ ወዘተ የሚሉ የማይመስሉ ምክንያቶችን ይዘረዝራሉ፡፡

ሰዎች በጫት ሱስ መጠመዳቸውን፣ ብሎም ለጤንነትና ለኑሮ ጉዳት መጋለጣቸውን የሚረዱት ጊዜ ካለፈና ሰለባ ከሆኑ በኋላ ነው፡፡ ግን ምን ያደርጋል፡፡ ‹‹ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ›› ይሆንባቸዋል፡፡ የጫት ሱሳቸው ጣሪያ ነክቶ፣ ነሁልለው ከሥራ፣ ከኑሮና ከትምህርት ገበታ ተፈናቅለው እርባነ ቢስ ሆነው የቀሩትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ የአባቶች ሁነኛ የዱአ መሣሪያ ተደርጎ ይወሰድ የነበረው የተከበረው ዕፅ፣ ይኼው ዛሬ የማንም ሰው በተለይም የወጣቶች ጊዜ ማሳለፊያና መቦዘኛ ተራ ቅጠል መሆኑ ያሳዝናል፡፡ በዚህም ምክንያት ለጫቱና ከጫት ጋር ተያያዥ ለሆነው ነባር ባህልና ትውፊት ጭምር ያለን ዕይታ ተዛብቶ ሁለቱም ተያይዘው ገደል ሲገቡ ተቀምጠን እያየን ነው፡፡

ከዚህ የውድቀት አዘቅት ውስጥ የገባነው ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ በፈጸምነው ታሪካዊ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ለምሳሌ ከግንቦት 1983 ዓ.ም. በፊት በደሴ ከተማ ለረዥም ዘመን ሁለት የጫት መሸጫ ጣቢያዎች ብቻ የነበሩ መሆኑን በአስረጂነት እጠቅሳለሁ፡፡ እነዚህም ቦታዎች የሚገኙት ‹‹ሙጋድ›› እና ‹‹ዓረብ ገንዳ›› አካባቢ ብቻ ነበሩ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በደሴ ከተማ የጫት ማከፋፈያና መሸጫ ጣቢያዎች ቁጥር የትየለሌ ነው፡፡ የዚህ ውጤትና አንድምታ ምን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ጫት ሱስ አስያዥ የሆኑ ‹‹ከቲን›› እና ‹‹ካቴኖን›› የሚባሉ ቅመሞች ያሉት መሆኑ፣ የጤንነትና የመልካም ሥነ ምግባር ጠንቅነቱ እየታወቀ መጥቷል፡፡ የጫት ዋጋ እንዲሁ ዕለት ከዕለት እየጨመረ በመሄድ፣ ዋጋው ለደሃው የኅብረተሰብ ክፍል ጭራሽ ሊቀመስ የማይችል የቤተሰብ ድህነት አባባሽ መንስዔ ሆኗል፡፡ ከሚያስከትለው የጤንነት ጉዳት በመነሳት አንዳንድ አገሮች ጫት መቃምም ሆነ ማዘዋወር ክልከላ አድርገዋል፡፡ አውሮፓዊቷ አገር እንግሊዝ ጫትን በሕግ መሠረት ቅጣት የሚያስቀጣ አንደኛ ደረጃ ‹አፍዝ አደንግዝ› በማለት በአገሯ ፓርላማ ደንግጋለች፡፡ በእኛ አገር ግን ጫት ወደ ውጭ ከሚላኩ የግብርና ምርቶች ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ፣ በተለይም በምሥራቁ የአገራችን ክፍል ድንበር አቋርጦ በኮንትሮባንድ መልክ ጭምር የሚላክ አንዱ የውጭ ንግድ የግብርና ምርት ሆኗል፡፡ ከሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ጥቅም ይሁን ወይም ከመዘንጋት የተነሳ በአገራችን በጫት ላይ የረባ ገደብ አልተጣለም፡፡ በአንድ ወቅት የአማራ ክልል መንግሥት በጫት ምርት ላይ ተፅዕኖ ለማድረግና ጫትን ከገበሬዎች ማሳ እስከ ማጥፋት የሚደርስ ገደብ ለመጣል እንደሞከረ አስታውሳለሁ፡፡ አንዳንድ ገበሬዎችም በማሳቸው ላይ ያለውን ጫት በመንቀል አስወግደው፣ በሌሎች ሰብሎች ለመተካት መነሳሳታቸውን ጭምር ሲናገሩ አዳምጬ ነበር፡፡

ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ከትግራይ በስተቀር በጫት ላይ ጠንካራ አቋም ወስዶ የነበረ ሌላ ክልል ስለመኖሩ አላውቅም፡፡ አሁን ጦር ሜዳ ለሚላኩ ወጣቶች ይሰጣል ከሚባለው አነቃቂ ዕፅ በስተቀር፣ ከለውጡ በፊት የትግራይ ክልል የጫት ንግድንም ሆነ መቃምን ያበረታታ ነበር የሚል አልሰማሁም፡፡ እንዲያውም ወደ ትግራይ ጫት በኮንትሮባንድ እንጂ በግልጽ አይገባም ይባል ነበር፡፡ በሌሎች ክልሎች ልቅ የተደረገው ጫት መቃም በትግራይ ለባለሥልጣናት ካልሆነ በስተቀር፣ ለሌላው የኅብረተሰብ ክፍል ዝግ ነበር ይባላል፡፡ የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጫት መቃምን ለወጣቱ ዝግ አድርጎ የነበረው ክልሉን የሚረከቡ የነገዎቹ አገር ተረካቢ ወጣቶች፣ ጫት ይዘው በያገኙበት ቦታ በቦዘኔነት እንዳይቀመጡ በሥነ ምግባር ለማረቅ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ በጊዜው ሌሎች ክልሎች የትግራይን ልምድ ባለመጋራት የተሞኙ ይመስላል፡፡

ጫት የሚያስከትለውን ጉዳት በጥሞና ካላዩ ክልሎች አንዱ አማራ ክልል ነው፡፡ ክልሉ የጫት አጠቃቀም ባህላዊ መሠረቱን ሳይለቅ እንዲቀጥል የሚያስችል ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ፣ ችግሩን በቸልታ ከማየት አልፎ ተርፎ ለችግሩ ተቋማዊ ድጋፍ ሰጥቷል፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው በመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከተቀመጡ ሰዎች መካከል በጫት ኃይል የሚንቀሳቀሱ መንኮራኩሮችና የጫት ሱስ ተጠቂዎች መገኘታቸው ነው፡፡ ወደ ኃላፊነት ቦታ የመምጫው አንዱ መንገድ የጫት መንገድ መሆኑን ለወጣቱ ትውልድ በሞዴልነት ለማስተማር ግንባር ቀደም ሥፍራ አላቸው፡፡ የዚህ መንስዔ በትጥቅ ትግል ወቅት ጦርነትን በሱስ አምጪ ቅመሞች ጭምር በመጠቀም መንግሥትን የጣሉ ሰዎችና የእነሱ ደቀ መዝሙሮች የሕዝብ አስተዳደር መዋቅሩን ስለተቆጣጠሩት የመጣ ችግር ይመስለኛል፡፡ በጫት ሱስ ችግር ውስጥ የተዘፈቀ ሰው ሌላውን ከጫት አረንቋ መንጥቆ ማውጣት አይችልም፡፡ ይህም ሲባል የጫት ጓደኛ ያልሆኑ ሰዎች በመካከላቸው የሉም ማለት አይደለም፡፡ ወደ ሕዝባዊ ኃላፊነት ቦታ የሚመጣ ሰው የጫት ሱስን ጨምሮ ከማንኛውም ዓይነት ደባል ሱስ የፀዳ  መሆን አለበት ለማለት ያህል ነው፡፡

በአማራ ክልል በሰፊው ይነገሩ የነበሩ ሁለት ጓደኛሞች ቀልድ መሰል ሀቆች እሰማ ነበር፡፡ ግን ቀልዶች አይደሉም፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ባህር ዳር ለስብሰባ በሄዱ ወቅት ማረፊያ ቦታቸው ድረስ የባህር ዳር ጫት እንዲመጣላቸው ጠይቀው፣ በወቅቱ የነበረው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጫት እንደማይቅም ሲነግራቸው፣ ‹‹ለካ መፍዙዝ የሆንከው ጫት ስለማትቅም ነው፤›› እንዳሉት ይነገራል፡፡ ይኼው አሉሽ፣ አሉሽ እስከ ታች መዋቅሩ ደርሶ አብዛኛው ወቅትያ ሁሉ ‹‹ጫት መቃምስ እንደ እሳቸው፤›› እያለ ጫት ቃሚ ሆነ ይባላል፡፡ እሳቸው ካሉበት የኃላፊነት ቦታ አንፃር ይኼን አይሉም እንዳልል፣ ከአንደበታቸው ወጥቶ እኔው ራሴ በጆሮዬ የሰማሁት ብዙ ብዙ ጉድ እንዳላምን አላደረገኝም፡፡

በአንድ ወቅት በፓርላማ ጉባዔ ላይ፣ ‹‹ሰርቀው እስካልተያዙ ድረስ ሌብነትም ሥራ ነው፤›› ያሉት አይረሳኝም፡፡ ደግሞ ሌላ ጊዜ፣ ‹‹የአክሱም ሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው?›› ብለው ሲዘባርቁ ሰምቻቼዋለሁ፣ እናንተም ሰምታችሁ ይሆናል፡፡ በየመንግሥት መዋቅሩ የተሰገሰገው ወቅትያ ሁሉ ወጣቱን ከጫት የሚያርቅ ሳይሆን፣ ስቦ ከጫት ጋር የሚያገናኝ ማግኔት እንዲሆን ይህ የከፍተኛው የፖለቲካ አመራር ሥነ ምግባርና መሪ ንግግር ለችግሩ መሠረት ሆኖ ያገለገለ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ሀቅ ደግሞ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እያልን የምንበጠረቅበት ሰነድ ረቂቅ ላይ በሐረር ከተማና በሌሎችም የተወሰኑ የአገራችን አካባቢዎች ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ተጠብቆ፣ ፈርሸው ጫት እየቃሙ ይወያዩበት ተብሎ ይኼው መደረጉ ነው፡፡ ለጫት መቃም በዚህ ደረጃ መንግሥታዊ ድጋፍ ማድረግ ወጣቱ ትውልድ ለጉዳዩ ከፍተኛ ግምት እንዲሰጥ እንደ መቀስቀስ ይቆጠራል፡፡

ጫት መቃምን ከእምነት አንፃር ለያይቶ ማየት ቢያስቸግርም፣ በተለይ በወሎ ሙስሊም ማኅበረሰብ ዘንድ ጫት የክብር ቦታ አለው፡፡ በጽሑፉ መግቢያ ላይ የተቋጠረው ስንኝ የሼህ ሁሴን ጅብሪል ስለመሆኑ ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ገደማ በፊት የአባቴ ጓደኛና ገበር የነበሩት አቶ ዘነበ መሐመድ ሲናገሩ ከሰማሁት የማስታውሰው ነው፡፡ ሼህ ሁሴን ጅብሪል ከስመ ጥሩው መምህር አካለ ወልድ ጋር እስከ ንጉሥ ሚካኤል ዘመን መጨረሻ የኖሩ፣ ሁለቱም ለቤተ መንግሥትና በየግላቸው ለሚከተሉት የሃይማኖት ተቋም ቀረቤታ የነበራቸው ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ ሼህ ሁሴን ጅብሪል የመጪውን ዘመን ሁኔታ የተነበዩና በትውልድ ቅብብሎሽ እየታወሰ የመጣውን ግጥም በመንዙማ መልክ የተረኩ ወልይ ስለመሆናቸው ብዙ ይባልላቸዋል፡፡ ስለጫት ተናገሩት የተባለው ትንቢት ውጤቱ አሁን በተጨባጭ እየታየ ነው፡፡

ለተቀደሰ ዓላማ በተቆጠበ ሁኔታ ይውል የነበረው ጫት ዛሬ ማንም ሰው በሚውልበት የትም ቦታ ሁሉ ያለ ኃፍረትና ፍርኃት ሲያሞሰካው ይውላል፡፡ ‹‹. . . በሰው ተመስሎ ዝንጀሮ ጫት ሲቅም›› የሚለው አገላለጽ የዝንጀሮን ጫት ቃሚነት የሚገልጽ ሳይሆን፣ ማንም ተራ ሰው በተለይም በወጣትነት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሰው መቃም የማይገባውን ጫት የሚቅምበት ዘመን ወደፊት እንደሚመጣ ቀድመው መተንበያቸውን ያሳብቃል፡፡ ዕድሜ ፈቅዶለት፣ እዚህ ዘመን ላይ ደርሶ፣ ይህን ጉድ ማየት ከማሳዘን አልፎ የሚያስለቅስ እንጂ የሚያስደስት ተግባር አለመሆኑን በቅሬታ መልክ የገለጹበት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ አሁን ያሉ አባቶችና ወላጆች ወጣቱን ትውልድ ከጫት ተራ መንጥቀው ለማውጣትና በምክር ለመመለስ ዓይነተኛ ምሳሌ ሆኖ ሊያገለግላቸው ይችላል፡፡

ነገር ግን ከሁሉም በላይ ችግር የሆነው ጉዳይ ጫትንና ወሎዬነትን እያዛመዱ፣ የአማራ ሕዝብን ለመከፋፈል ያግዛል ከሚል ማዕዘን በመነሳት የሚደሰኩሩ አንዳንድ ፌስቡከኞች አልፎ አልፎ መከሰታቸው ነው፡፡ የወሎ ወጣት በህልውና ዘመቻው ላይ በገፍ ወጥቶ ከመሳተፍ አለመሳተፍ ጋር በማያያዝ፣ በተለይም የደሴ ወጣት በየመጠጥ ቤቱና የኳስ ጨዋታ ማሳያ ቤቶች ጫት ሲቅም ይውላል የሚል መስቃ አዘል አስተያየት ይጻፋል፡፡ ትችቱ ምናልባት ወጣቱ በእልህ እንደ ተርብ ግው ብሎ ወደ ህልውና ዘመቻው እንዲሄድ ቁጭት ውስጥ ለማስገባት በማሰብ ይመስለኛል፡፡ ነገሩ በጎ ጎን ያለው ትችት ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ጫት በመቃም ላይ የተጠመደው የወሎ ወጣት ብቻ አስመስሎ ማቅረብ ግምት ያስወስዳል፡፡ የወሎ ወጣት ከሌላው የኢትዮጵያ ወጣት ተለይቶ ዳተኛ በመሆን የህልውና ዘመቻው የእኔ ዘመቻ አይደለም ስለማለቱም መረጃ የለም፡፡ ይልቁንም ዘመቻውን ለመቀላቀል የሚያስችለውን ሥልጠና በመውሰድ ወደ ማሠልጠኛ ማዕከላት በገፍ እየተመመ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ የወሎ ወጣት የጦርነቱ እቶን እሳት ከሚነድበት የጦር አውድማ ውስጥ ስለሚገኝ ሳይወድ በግድ በላቀ ሁኔታ የጦርነቱ ተሳታፊ ነው፣ እየሆነም ነው፡፡

የወሎ ወጣት ከሌላው አካባቢ ወጣት በተለየ መልኩ የጫት ሱስ አነሁልሎት ወይም ጫት ከህልውና ዘመቻው ብሶበት በዚህ ታሪካዊ ክንውን ላይ አሻራውን ለማስቀመጥ አልተዘጋጀም የሚል የፌስቡክ ወሬ በገጻቸው ላይ ጽፈው በማስነበብ፣ ለወሎ ወጣት ያልተገባ ስም መስጠቱ ወጣቱን ቅር እንዳያሰኝ እሠጋለሁ፡፡ ምንም እንኳ ነገሩ ፌስቡክ [ፌዝ ቡክ] ቢሆንም፣ ማንም ሰው በኃላፊነት መጻፍ እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ትውልዱን ከጫት ቃሚነት ልናወጣው የምንችለው የወጣቱን ክብር በማራከስ ሳይሆን፣ በማስተማርና ተቋማዊ አሠራር በመፍጠር ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ወሎ በጦርነት ቀጣና ውስጥ እንደ መግባቱ መጠን፣ ወጣቱ በአሁኑ ወቅት መዋል ያለበት  የጫት፣ የመጠጥና የኳስ ጨዋታ ማሳያ ቤቶች ሳይሆኑ ጦርነቱን በድል ለመወጣት በሚያስችሉ ቦታዎችና ግዳጆች ላይ እንደሆነ ቅስቀሳ ማድረግና የግዳጅ የሥራ ድርሻና የግዳጅ ቀጣና መስጠት የዘመቻ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊነትና ተግባር ነው፡፡ የህልውና ዘመቻውን ሊያደናቅፍ ይችላል ተብሎ በሚገመት ማንኛውም ጉዳይ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ ውሳኔዎችንና ዕርምጃዎችን መውሰድ ይገባል፡፡

በኢትዮጵያ የታሪክ መዝገብ የወሎን ስም ያስጠሩ በርካታ ስመ ጥር ወጣቶች ነበሩ፡፡ ግን ጫት በመቃም አልነበረም፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የወሎ አባቶችና እናቶች ገድልም የሚያኮራና ከፍ ያለ ቦታ ያለው መሆኑን ከታሪክ ማኅደር መረዳት ይቻላል፡፡ አሁን ያሉትም የወሎ ወጣቶች የአባቶቻቸውና የእናቶቻቸው ልጆች ናቸው፡፡ ወጣቱን ከማይገባው የጫት መቃም አባዜ ቀስ በቀስ አውጥቶ ኅብረተሰቡን ወደ ቀድሞው ባህላዊ የጫት ሥሪትና ትውፊት ከፍታ ሊመልስ የሚችል ተቋማዊ አሠራር ወደፊት መዘርጋት ይቻላል፡፡

የቱሪዝም መስህብ የሆነውን የጫት ባህላችንንና ትውፊታችንን ከወደቀበት አዘቅት በማንሳት ወደ ቀድሞው ከፍታ ለመመለስ በየደረጃው መሠራት የሚኖርባቸው ተቋማዊ ሥራዎች አሉ፡፡ ቱባ ባህላችንን ለማስቀጠል በሚደረግ ጥረት ውስጥ ከላይ በተገለጸው መሠረት የሕግና አስተዳደራዊ ማዕቀፍ በማዘጋጀት ከማዕከል እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ የሚዘረጉ ሥራዎችን ነድፎ ክፍተቱን ወደፊት መዝጋት ይቻላል፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅት ፈታኝና ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት ‹‹ያሳዝናል እንጂ ይህስ አያስቅም፣ በሰው ተመስሎ ዝንጀሮ ጫት ሲቅም›› የሚለው የሼህ ሁሴን ጅብሪል ትንቢት ያዘለውን ጥልቅ መልዕክት በመገንዘብ፣ ጫት መቃም ከወቅቱ የአገራችን ችግር ጋር አብሮ የሚሄድ ተግባር ባለመሆኑ፣ የግል አመሉን ከሁኔታው ጋር በማስተካከል ከታሪክ ተጠያቂነትና ውርደት ራሱን የማይጠብቅ ወሎዬ ወጣት ይኖራል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ‹‹ኮሶን ለደራ ይጠጡታል›› እንዲሉ የጫት አመል ያለበት ወሎዬ ወጣት ራሱን ከጫት ተራ አውጥቶ ከሌሎች ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ተሠልፎ መላ ትኩረቱን በህልውና ዘመቻው ላይ በማድረግ፣ የአያት ቅድመ አያቶቹን ገድል በመድገም ታሪክን ማስቀጠል እንደሚጠበቅበት ሊገነዘብ ይገባዋል፡፡ ጫት ለመቃምም ቢሆን የአገርና የነፃነት ባለቤት መሆን ግድ ይላል! ኢትዮጵያ በክብር ለዘለዓለም ትኑር!፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...