Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየጋራ ትልሞችን ያወቀ ርብርብ ያስፈልገናል!

የጋራ ትልሞችን ያወቀ ርብርብ ያስፈልገናል!

ቀን:

በበቀለ ሹሜ

ሀ) 1. የአፍሪካ ኅብረት አሁን ባለበት ደረጃ የአኅጉሩ አገሮች ባላቸው ቀጣናዊ ስብስብ ውስጥ ግጭትን፣ ሽብርን፣ ወታደራዊ ግልበጣዎችንና መቆራረሶችን እየተከላከሉ/እያመከኑ የተደጋገፈ ልማትንና ዕድገትን የሚመግብ ሰላም እንዲያጎለብቱ በማገዝ ላይ አትኩሮ እስካልሠራ ድረስ፣ በየቀጣናውም ውስጥ ለየቀጣናቸውና ለአኅጉራቸው የግስጋሴ አርዓያና የትብብር አቅም የሚሆኑ አገሮች እየተበራከቱ እስካልፈኩ ድረስ፣ የአፍሪካ ኅብረት ከጌታ አገሮች የንዋይ ጥገኝነትና ጫና ተላቆ በነፃነትና በፅናት ለአኅጉሩ የሚበጀውን ማድረግ አይቻለውም፡፡

የአፍሪካዊያንን ችግሮች በአፍሪካውያን የመፍታት ፍላጎቱም በቀጥታና በተዘዋዋሪ ወደ ጌታ አገሮች ከማንጋጠጥ አይወጣም፡፡ አፍሪካም የኃያላን ጣልቃ ገብነት ሜዳ መሆኗ አይቋረጥም፡፡ አኅጉራዊ አገር የመሆን ዕቅዱም የማይጨበጥ ቅዠት ከመሆን አይዘልም፡፡ የአፍሪካ ቀንድ የተደጋገፈ የልማትና የሰላም ግንባታ ጥረትም ከዚህ አኳያ ነው መታየት ያለበት፡፡ የእኛን ቀጣና የጋራ ልማትና የሰላም መጎልበት የአኅጉራችን መጎልበት መሆኑን የአፍሪካ ኅብረት በፅኑ ሊያምንበት ይገባል፡፡ እስካመነ ድረስም ሱዳን የተጀመረ የድንበር ድርድርንና የኢትዮጵያን ባልንጀርነት ረግጣ በኃይል መሬት ማስፋቷንና ኢትዮጵያን የሚያምሱ ቡድኖች ማሠልጠኛና ማኮብኮቢያ መሆኗን በፍዝነት ማየት ጥፋት ይሆንበታል፡፡

ወደ ፋሽስታዊ አሸባሪነት ያሽቆለቆለው ሕወሓት የማተራመስ ደባ የሠራውና እየሠራ ያለው በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ላይ ሳይሆን በቀጣናውም ላይ ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ መከላከያም ውስጥ ያለነው እኛው ነን›› እስከ ማለት ድረስ ኢትዮጵያን ሸጦ፣ ሱዳን በኃይል ድንበር እንድታሰፋ ያደፋፈረው ሕወሓት መሆኑ ከዚህ ቀደም በይፋ ተነግሯል፡፡ ሰላም አማሹ ሕወሓት የኢትዮጵያን የሰሜን ዕዝ በሸፍጥና በጨካኝ ጥቃት ጠልፎ ውጊያ የከፈተውም፣ በኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሳይሆን በኤርትራ ላይም ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ አገሮችን ለጋራ ሰላምና ልማት ያደረገችውን የማስተባበር ጥረት በክፉ ዓላማ ተርጉሞ ለእነ አሜሪካ ሚስጥራዊ ስብቀት በመፈጸም ይኼው ቡድን ይታማል፡፡ የእነሱን ግራ ቀኝ የማይል ድጋፍ ሊያገኝ የቻለውም ቀጣናውን የማመስ፣ ኢትዮጵያን የመቆራረስና ኤርትራን የመሰልቀጥ ፕሮጀክቱ የእሱም የእነሱም ጥቅም መሆኑን በሸረኛ ስብቀቱ በማሳመኑ ስለመሆኑም ሐሜቱ ይፈነጥቃል፡፡

ምዕራባውያኑ በዚህ ቡድን የጦር ወንጀሎችና የሰብዕና ወንጀሎች ላይ ዓይናቸውን ጨፍነው ኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ የንክሻ ጩኸት የሚያካሂዱት፣ ለሕወሓትና ለሽብር ሸሪኮቹ ተገንና አሠልጣኝ ከሆነችው ሱዳን ጋር አዲስ ፍቅር የያዙት፣ በደራሽ ሰብዓዊ ዕርዳታ ረገድ ለትግራይ ሕዝብ ‹‹በማሰብ›› እንቅልፍ አጣን የሚሉትን ሩቡን ያህል እንኳ፣ ሕወሓትና ሸሪኮቹ ላፈናቀሏቸው መከረኞች መቆርቆር የተሳናቸው በፖለቲካዊ ሥሌት ምክንያት ነው፡፡

ሕወሓት የተባለ በ‹ዘር› ጥላቻ፣ በቂምና በበቀል የሰከረ ጦረኛ ቡድን፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በትግራይ ገዥነት ቢቀመጥም ሆነ የተነጠለች ትግራይ ገዥ ለመሆን ቢችል ክፍለ-አኅጉራዊው አካባቢ ፈጽሞ ሰላም አያገኝም፡፡ የኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብና የህዳሴ ግድብን የተመለከተው የሦስትዮሽ ድርድር በሰላም ለመጠናቀቅ የተሻለ ዕድል የሚያገኘው ይህ ቡድን ከተወገደ ብቻ መሆኑ ገሃድ የወጣ እውነት ነው፡፡ የአፍሪካ ኅብረት ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ንቁ ደጋፊ ባይሆን እንኳ፣ የምዕራባዊያንን ሰላም የማያመጣ ጫና መቃወም አይበዛበትም፡፡

2. ኢትዮጵያ የዚህን ጦረኛ ቡድን የመዋጋት አቅም አንክታ ጀሌዎቹን ወደ ሰላም መሳብ ከቻለች ስኬቱ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሰላምና ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣናውም ሰላም ትርጉሙ ከትልቅም ትልቅ ነው፡፡ ይህ ቡድን በሸሩ፣ ሕዝብን በብሔርነቱ በጠመደ ጥላቻው፣ በበቀለኝነቱና በደም ጥማቱ ምክንያት እንደ መንግሥት ቆሞ ሰላምን፣ ፍትሕንና መብትን ማስተዳደር እንደማይችል ትናንትናም ዛሬም በተግባር አረጋግጧል፡፡ ሕወሓት ምን ያህል ፀረ ሕዝብ፣ የቂምና የውድመት ኃይል እንደሆነ ለማሳየት ብዙ ሰነድ ማገላበጥ አይኖርብንም፡፡ ሐምሌና ነሐሴ 2013 ዓ.ም. በአፋርና በአማራ ዘልቆ የሠራውን የግፍ ጉድ በምሥልና በሰው ምስክር መዘክዘክ ብቻውን ከበቂ በላይ ነው፡፡

ግፍ ቀለቡ ሕወሓት አፋርና አማራ የዘመተው ዘርፎ፣ አውድሞ፣ ገድሎ፣ ደፍሮና አፈናቅሎ ሕዝብን ውርደት ለማከናነብ ብቻ አልነበረም፡፡ በአፋርና በአማራ ውስጥ (በሌሎች ሥፍራዎችም ጭምር) ያሉ የትግራይ ልጆችን እየበላ ትግራይ ድረስ የሚዘልቅ ጭፍን በቀል እንዲቀጣጠልና ምዕራባውያን ጭፍን ፍጅትን ‹‹በማስቆም›› ቀዳዳ እንዲደርሱለት ለማድረግ ነበር፡፡ በዚህም ሥሌቱ ሕወሓት ለቡድናዊ ትርፉ የማይሸጠው ነገር እንደሌለ ደጋግሞ አረጋግጧል፡፡ የትግራይ ልጆችንና ሕዝብን በጭፍን አሳጭዶ፣ እሱ በምዕራባዊ ደጋፊነት በደም የጨቀየ ሥልጣኑን ሊያተርፍ!! የዚህ ቡድን የሰይጣን ቁራጭነት እስከዚህ ድረስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት ይህንን ቡድን ‹‹አሸባሪ›› ብሎ መፈረጁ የቡድኑን የከፋ ባህርይ የመቀደስ ያህል ‹ደግነት› ያሳየ ነው፡፡ ቡድኑ አማራ ውስጥ የሠራውን ያዩ እናት ለዚህ ቡድን ያገኙለት ስም ‹‹አረመኔ! ፋሺስት!›› የሚል ነው፡፡ በእርግጥም ሕወሓትና ሸኔ የፋሺስት ቁራጮች ናቸው፡፡ ሁለቱን ያስተባበራቸውም ይኼው ባህርያቸው ነው፡፡ የሸኔና የሕወሓት ቅንጅት ይፋ ከመሆኑ በፊት ሸኔዎች ሲያካሂዱት የነበረው ጭፍጨፋና ግድያ የሕወሓትም ነበር፡፡ ኅብረታቸው ይፋ ከወጣም በኋላ በኦሮሚያ ወለጋ በነሐሴ 2013 ዓ.ም. ውስጥ የተካሄደውን የ200 ገደማ ሰዎች ጭፍጨፋንም ሕወሓቶች ይጋሩታል፡፡ በወንጀሉ ማግሥት ሸኔ፣ ‹‹የለሁበትም በገለልተኛ ወገን ይጣራ፤›› ማለቱም ሕወሓቶች እንዲለፍፍ የሰጡት የኢትዮጵያ ሕዝቦችን ጠንካራ አንድነት በጥርጣሬ የማልፈስፈስ ጊዜ ያለፈበት ተንኮል መሆኑ ነው፡፡

የሕወሓት ጦረኛ በቀለኞች በቅርብ ወረራቸው ያሳዩት የመግደል፣ የመዝረፍ፣ የማጋዝና፣ ማጋዝ ያቃታቸውን የማውደም ድርጊት ሥር የሰደደ ባህርያቸው ነው፡፡ ሸፋፍነን ትተነው እንጂ በ1980ዎች ወደ አዲስ አበባ ሲገሰግሱ ባረፉባቸው ሥፍራዎች ውስጥም ሆነ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ እንደ ወታደራዊ ጣቢያ በተጠቀሙባቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ያላካሄዱት ዘረፋ፣ እየሰባበሩ እሳት ያልማገዷቸው የቢሮ ቁሳቁሶች አልነበሩም፡፡ ቢሮዎችና አዳራሾች ሳይቀር ለእዳሪ መውጫ የዋሉበት ሁኔታም ነበር፡፡

ዛሬ ከብት እስከ መግደል ድረስ በቀል አስክሮት ያየነው ይህ ቡድን፣ በትግራይ ሕዝብ ተተፍቶ የተንሳፈፈበት ሁኔታ ውስጥ ከገባ በትግራይ ውስጥ ብቻ ሲሠራው የኖረው የግፍ መዓት ቢጎለጎል ማስጫ አይበቃውም፡፡ ግፉ ብዙ ጎልጓይ እንደሚያገኝ ሁሉ፣ የትግራይ ሕዝብ የነፃነት አየርን እየተነፈሰ የልማት ፀሐይን ማየት የሚጀምረው ወዲያው ነው፡፡ ይህ ቡድን ከተወገደ የኢትዮ ኤርትራ ሕዝቦች ፍትሐዊ ግንኙነትም ሕይወት አግኝቶ ለመላወስ ጊዜ አይፈጅበትም፡፡ ይህ ቡድን ከተወገደ፣ የሱዳንና የአገራችን የድንበር ጣጣም ሆነ የሦስትዮሹ ድርድር በሰላም እንዲያልቅ የማይናወጥ ቁርጠኛነት እንዳለን፣ ከየትኞቹም ጎረቤቶቻችን ጋር የመጋጨት ፍላጎት እንደሌለን፣ እስካሁን በያዝነው አቋምም የራሳችንን ጥቅም ያህል ለሱዳንና ለግብፅ ፍትሐዊ ጥቅም ታማኝ ሆነን መቆየታችንን፣ ፀብ ናፋቂ ያልሆነ ይህ አቋማችን የኢትዮጵያን ለውጥና የሱዳንን ለውጥ የሚያግዝ ብቻ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና የጋራ ልማት የሳሳ መሆኑን የአፍሪካና የዓለም ማኅበረሰብ እንዲያውቅልን ማድረግ ይቀለናል፡፡ የሱዳንና የግብፅ መንግሥታት ከያዙት የፀብና ኢትዮጵያን የመጉዳት መንገድ እንዲመለሱ የማይናቅ ሰላማዊ ተፅዕኖ ማድረግ እንችላለን፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ በመክፈቻና በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ብዙ ዓይነት እንግዶች ሊጋበዙ የሚችሉበት አገራዊ ጉባዔያችን ጥሩ አጋጣሚ ይሆናል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ተግባሮች መቃናት ውስጥ የአገር ወዳድ ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች ኅብረትና የኅብረታቸው የጋራ መርሐ ግብር መያዝ መቻል እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡    

ለ) 3. በጋራ መርሐ ግብር መተባበር እስከ መቼ?

እስካሁን በፖለቲካ ሰላማችን ውስጥ ለደረሰው ቀውስና ላቆሳሰለን ጨካኝ በቀል ሁሉ ተጠያቂዎቹ እኛው መሆናችንና እኛው ለእኛው ጠላት ሆነን የውጭ ቀበኛ በራሳችን ላይ መጋበዛችን ቁጭታችን ለመሆን በቅቶ ከሆነ፣ እንዲህ ያለው ገመና እንዳያዳግመንና ኢትዮጵያ ወልዳ ያስተማረቻቸው ልጆቿ እንብላሽ እንዳይሏት፣ እሷም ማሳደግ እንደጠፋባት ድመት እንዳትቀረጥፋቸው በማስቻል ረገድ ከሕወሓት መነቀል በኋላም ብዙ የኅብረት ሥራ አለብን፡፡ አንዳንዶችን እንጠቃቅስ፡፡

  • የተጠቃሁ ባይነት ልማደኛ ሆነን በደል በወረንጦ ከመፈለግ መመለስ፣ የጥላቻና የበቀል ስሜትን በዕርቅና በፍትሐዊ ግንኙነት ግንባታ ማጠብ፣ ጥፋተኞችን በምን ልበቀል ከማለት ይልቅ በፍትሕ ላይ ማተኮር፣ ቀንደኛ ወንጀለኞችን የመፋረድ ሥራን ለጀሌዎች ሰፊ የይቅርታ ዕድል ከመስጠት ጋር ማዛመድ፣ ብሎም ቁስል የሚያሽሩ፣ መተሳሰብንና የእኩልነት ስሜትን የሚያጎለብቱ ሥራዎችን መሥራት፣
  • ከፖለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት አንስቶ ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ እስከሚሰማራ ኢንቨስትመንት ድረስ፣ ተገለልኩ/ተበለጥኩ ለሚል ቅሬታ የሚያጋልጡ መንገዶችን መሸሽ (ኅብረ ብሔራዊ ቅንብርን ማዳበር)፣
  • የትኛውም ማኅበረሰብ በሌላው እንዲዋጥ አለመሥራት፣ በማኅበረሰቦች መሀል የሚፈጠረውን አዝግሞታዊ (ተፈጥሯዊ) መላላስ ግን ለመግታት አለመተናነቅ፣
  • በአንድ ራስ ገዝ ውስጥ የሌላ ራስ ገዝ ደሴት ወይም ኤምባሲ መሰል ነገር አጥሮ ለማስቀመጥና ከሩቅ ጣልቃ እየገቡ ነገር ለማቡካት አለመሥራት፣
  • በአጠቃላይ ሐሰተኛ ‹‹ንቃት››ን፣ ማናህሎኝ ባይነትን፣ ጠምዛዛነትንና መሰሪነትን፣ ነገር እያጫጫሱ መጠማመድን፣ ቅሬታ እያመቁ ማጠራቀምን፣ አጠራቅሞም በዱላና በባሩድ ለመፍታት መሞከርን ፖለቲካችን ለአዲሱ ትውልዳችን እንዳያወርስ፣ በዚህ ፋንታ በትኩሱ ዕንከኖችንና ችግሮችን እየተቹ/እያጋለጡ፣ በጥሞናም እየተነጋገሩ የማስወገድ ልምምድን እንዲያስተላልፍ መሥራት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

አንዳንዶቹ ነገሮች ሽግግራዊ ዓይነት መፍትሔ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ዘላቂ ዕድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ ሁሉም ግን ፖለቲከኞቻችን ከለመደባቸው አነቋቋሪ አስተሳሰብና የግንኙነት ባይ ለመላቀቅ እስካልጣሩና መልካም ምሳሌ እስካልሆኑ ድረስ፣ የአዲስ ትውልዳችንን እነፃ ማጎሳቆላቸውና ለሰላማችን ሥጋት መሆናቸው አይቀርም፡፡ የምሁራኖቻችንና የፖለቲከኞቻችን የጋራ ዕቅድ ነድፎ መሥራት፣ ለአሁናችንም ለወደፊታችንም እጅግ አስፈላጊነቱ የሚደቀነው እዚህ ላይ ነው፡፡

እስከ ዛሬ ከመግለጫና የአገር ወዳድነት ስሜትን ከመጋራት ባለፈ፣ በተወሰኑ ዒላማዎች ላይ ባነጣጠረ የኅብረት ሥራ አለመጠመዳቸው ውድ ዕድልን ያባከነ ነበር፡፡ ሲሆን፣ ሲሆን የአገር ልጆች በውስጥና በውጭ አገር ለተያያዙት የአርበኝነት ተጋድሎ መንገድ ጠራጊ፣ አነሳሽና ምሪት ሰጪ መሆን የሚገባቸው እነሱ ነበሩ፡፡ ይህ ባይሆንላቸውም ግን፣ ተባብሮ መታገልን ከእነሱ ለመቅሰም ቀስቃሽ እስኪመጣ መጠበቅ አይኖርባቸውም፡፡

  • የፀረ ሽብርና የፀረ አገር ብተና ትግል፣
  • ምዕራባዊያን በኢትዮጵያና በኤርትራ ላይ የከፈቱትን ሉዓላዊነትን የተዳፈረ ጫናና ዘመቻ የማዳከም ትግል፣
  • የታላቁ ህዳሴ ግድብን የሚመለከተው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት ውስጥ ዕልባት እንዲያገኝና የኢትዮ ሱዳን የድንበር ውዝግብ ያለ ግጭት እንዲያልቅ የሚያግዝ አኅጉራዊናለም አቀፋዊ ድጋፍን የማበራከት ትግል፣
  • በኢትዮጵያ አፍራሾች ላይ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቶርቅና ሰላም መገንባት፣ አያይዞም በመልሶ ግንባታናኢኮኖሚ ልማት ማንሰራራት ላይ መጠመድ፣
  • በዴሞክራሲ ግንባታ ውስጥ ንቅዘትን/ልሽቀትን እንደሥርዓት ያሸነፈ የመልካም አስተዳደርና አገልግሎት ባህል እንዲሰፍን መዋደቅ፣   

እነዚህ የአገር ወዳድ ምሁራንና ፖለቲከኞች የርብርብ መገናኛዎች መሆን ይችላሉ፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ህልውና ነክ እንደ መሆናቸውም፣ ‹‹ቡድኔን በተመለከተ ምላሽ የሚሹ ጥያቄዎች አሉኝ›› የሚል ቅድመ ሁኔታ በፖለቲካ ቡድኖች በኩል ሊነሳባቸው አይገባም፡፡ የርብርቡን አንገብጋቢነት እስከተረዳን ድረስም ከዚህ የርብርብ ተግባር በላይ ቡድናዊ ጉዳያችንን ያለ ማስቀደም ኃላፊነት ውስጥ መግባታችን ነው፡፡ በሌላ አነጋገር በምርጫ አማካይነት የምናደርገው “የመጣጣል” ፉክክር በርብርብ የጋራ ተልዕኳችን ግቢ ውስጥ የሚካሄድ መሆኑ ነው፡፡ የዚህ ዓይነት መግባባት ያለበት የአብሮ መሥራት ኅብረት ቢያንስ ለአሥር ዓመታት ያህል የሚያስፈልገን ይመስለኛል፡፡

በተረፈ ተጋድሏችን ከባሩድ ገና ያልተገላገለ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ምሥራች በመላ ኅብረተሰቧና ልጆቿ መነቃነቅ መበሰር ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ በዲያቢሎስ ቁራጮቹ ሕወሓትና ሸኔ ብትደማም፣ እነዚህ ቡድኖች ፖለቲካ የሞተባቸው ፋሺስታዊ ነፍሰ ገዳዮችና አውድሞች መሆናቸውን በገሃድ አረጋግጠው የኢትዮጵያን መላ ሕዝብ በማንበልበላቸው ኢትዮጵያ የድሏን ብርሃን እያየች ተፍነክንካለች፡፡

ክብርና ያልዘገየ ድል መቻቻልን ለሚያውቅበት ኅብረተሰባችን!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...