Sunday, April 21, 2024

የትግራይ ጦርነትና ኢኮኖሚያዊ መዘዙ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የትግራይ ክልል ጦርነት ከአምስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎችን ለችግርና ለምግብ ተረጂነት፣ ብሎም ለተለያዩ አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስና ጥሰቶች ዳርጓል። 

ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑትን ነዋሪዎችን ከቀዬአቸው እንዳፈናቀለና በዚህም የተነሳ 4ዐዐ ሺሕ በላይ የሚሆኑት በረሃብ አደጋ ውስጥ መሆናቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) መረጃ ያመለክታል። 

ጦርነቱ ከትግራይ ክልል ተሻግሮ የውጊያ ዓውዱን በአፋርናአማራ ክልሎች ካደረገበት ሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም. አንስቶ ባሉት ሁለት ወራት ብቻ 300 ሺሕ በላይ ነዋሪዎችን ከሁለቱ ክልሎች አፈናቅሎ ለተረጂነት ዳርጓቸዋል። ከአፋርናአማራ ክልሎች ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች በተጨማሪ፣ በእነዚሁ ክልሎች እየደረሰ ያለው ቀውስ 1.7 ሚሊዮን ነዋሪዎችን ለተረጂነት እንደሚዳርግም ተመድ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በትግራይ ክልል በኅዳር ወር 2013 ዓ.ም. የተጀመረው ጦርነት በሁለቱም ተዋጊ ወገኖች ያደረሰው የሕይወትና የአካል ጉዳትን የተመለከተ መረጃ ባይኖርም፣ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ጦርነቱ እያደረሰ ያለው ሰብዓዊ ኪሳራ አስከፊና የአገሪቱ የወደፊት የታሪክ ጠባሳ እንደሚሆን እየተነገረ ነው። 

ጦርነቱ እያስከተለ ከሚገኘው የሰዎች እንግልትሕልፈት፣ የአካል መጉደልና ማኅበራዊ ቀውስ በተጨማሪ የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚን እያቆሰለ ይገኛል። 

የተመድ የፀጥታ ምክር ቤት የትግራይ ክልል ጦርነትና ሰብዓዊ ቀውሶችን አስመልክቶ ከአንድ ሳምንት በፊት ባደረገው ውይይት ሪፖርት ያቀረቡት የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ፣ ‹‹ጦርነቱ እስካሁን ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ከአገሪቱ ከግምጃ ቤት ወስዷል፤›› ብለዋል።

የኢትዮጵያ አጠቃላይ ዕዳ መጠንም እያሻቀበ እንደሚገኝ የተናገሩት ዋና ጸሐፊውለልማት የሚውል የብድር አቅርቦት እየደረቀ መምጣቱንና ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትም በአገሪቱ ሕዝብ ላይ እየወደቀና መሠረታዊ የምግብ ሸቀጦች አቅርቦትም እያሽቆለቆለ መምጣቱን ተናግረዋል። 

በተጨማሪም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሥርጭት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በከፍተኛ ደረጃ እየተሠራጨ እንደሚገኝ፣ ከአፍሪካ አኅጉርም በቫይረሱ ሥርጭት አምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልጸዋል። 

የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ የገለጹት እንዳለ ሆኖጦርነቱ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች ውጪ ያሉ የኢትዮጵያ ከተሞችና አካባቢዎች ነዋሪዎች እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ጫና እየቀመሱትና አቤቱታቸውንም እያሰሙ ናቸው።

በዚህም ምክንያትም ቀላል የማይበሉ የክልል መስተዳድሮችና ከተሞችን የሚያስተዳድሩ አመራሮች አዲስ አበባን ጭምር አስገዳጅ የዋጋ ተመን ወደ መጣል፣ ዋጋ ጨምረዋል ያሏቸውን የንግድ ተቋማት መዝጋትና ሸቀጣቸውንም የመውረስ ተግባር ውስጥ ገብተዋል። 

በሌላ በኩል አጠቃላይ የአገር ውስጥና የውጭ ውዝፍ ዕዳ በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 2.4 ትሪሊዮን ብር ወይም 55.6 ቢሊዮን ዶላር እንደደረሰ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሰሞኑን ያወጣው የዕዳ መግለጫ ሰነድ አመልክቷል። 

ከአጠቃላይ የዕዳ መጠን ውስጥ 1.29 ትሪሊዮን ብር የሚሆነው የአገሪቱ የውጭ ብድር ዕዳ እንደሆነ ሰነዱ ያመለክታል። ከአምስት ዓመት በፊት የነበረው የአገሪቱ አጠቃላይ የውጭ የብድር ዕዳ መጠን 539.5 ቢሊዮን ብር እንደነበርም መረጃው ያሳያል።

መንግሥት ያለበትን የውጭ ዕዳ ለማቃለል 2013 በጀት ዓመት 1.8 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ክፍያ ማድረጉን የሚያመለክተው ሰነዱ፣ በዚሁ ዓመት ከውጭ አበዳሪዎች ያገኘው አጠቃላይ የብድር መጠን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ሲሆንይህም ባለፉት አምስት ዓመታት ከተገኘው በእጅጉ አነስተኛ እንደሆነ ያስረዳል።

የውጭ ብድርና ዕርዳታው ከቀነሰበት ምክንያት አንዱ የውጭ አጋሮች በትግራይ ክልል ጦርነት እንዲገታ ባላቸው ፍላጎት፣ ከመንግሥት ጋር ልዩነት ውስጥ በመግባታቸው በወሰዱት የተናጠል ዕቀባ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

በዚህም የተነሳ መንግሥት 2013 ዓ.ም. የከፈለው 1.8 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ክፍያ በበጀት ዓመቱ ከተገኘው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ ገቢ 432 ሚሊዮን ዶላር የበለጠ ሆኗል።

ይህም የሚያሳያው አገሪቱ ካገኘችው ዶላር ውስጥ ቀላል የማይባል መጠን ለዕዳ ክፍያ ለማዋል መገደዷን ነው።

መንግሥት የዋጋ ንረት አሳስቦት ወደ ነጠላ አኃዝ ለመቀየር ዕቅድ አስቀምጦ የነበረ ቢሆንም፣ ላለፉት ሦስት ዓመታት ዕቅዱን ማሳካት እንዳልቻለና የአገሪቱ የዋጋ ንረት በዓመት በአማካይ 22 በመቶ እየጨመረ መቀጠሉን ሪፖርተር ያነጋገራቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ ይገልጻሉ።

ዘንድሮ በሐምሌ ወር ላይ የዋጋ ንረቱ 25 በመቶ መግባቱን የሚገልጹት ባለሙያውይህ ምጣኔ አምና ከነበረው የዋጋ ንረት ተነፃፅሮ የተቀመጠ በመሆኑ ዓመታዊ ሁኔታውን እንጂ የችግሩን ጥልቀት የሚገልጽ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።

‹‹የችግሩ መሠረታዊ ምክንያት ጦርነት አይደለም። መሠረታዊ ምክንያቱ የአቅርቦት እጥረት ሲሆንበዋናነትም ግብርና ነክ የሆኑ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎች እጥረት ነው፤›› ብለዋል።

የኢኮኖሚ መሠረቱን በግብርና ላይ የጣለ አገር ለተከታታይ ዓመታት በግብርና ምርት እጥረትና በፍላጎት አለመጣጣም ምክንያት የዋጋ ግሽበት ወስጥ መግባቱ ጤናማ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

በዚህ ችግር ውስጥ ችግሩን ለመፍታት የነበረው የመጀመርያ አማራጭ የምርት እጥረቱን ከውጭ ገበያ ማስገባት መሆኑና ይኼንንም በአነስተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወይም በውጭ ብድር እየተሸፈነ ስለሆነ፣ የውጭ የዋጋ ንረትን አብሮ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ከማድረጉ ባለፈ በአገሪቱ የውጭ ብድር የዕዳ መጠን ላይ ተጨማሪ ጫና እንዳደረሰ ያስረዳሉ።

‹‹በተለይ ደግሞ አሁን ያለው መንግሥት የተረከበው ከፍተኛ የውጭ ብድር ዕዳ ጣሪያ በመንካቱ በዚህ ላይ ተጨማሪ ብድር ለማግኘት አስቸጋሪ እንዳደረገውቢገኝም የአገሪቱን የዕዳ መጠን በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች መሠረት ከጣሪያ በላይ እንደሚወስደውና ኢትዮጵያ ዕዳ መክፈል የማትችል ተብላ በጥቁር መዝገብ ውስጥ እንድተገባ ያደርጋታል። አንዴ እዚህ መዝገብ ውስጥ ከሠፈሩ በኋላ ይህንን ለመፋቅ አስቸጋሪ ነው። ያለው ብድር የአገሪቱን ውስብስብ መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት በተመሳሳይ መጠን አስቸጋሪ ነው፤›› ሲሉ ባለሙያው ይገልጻሉ።

የትግራይ ጦርነት የመጣው በዚህ ችግር ውስጥ መሆኑና ጦርነቱ እንደታሰበው ቀላል አለመሆኑ፣ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ ተዳምሮ የዋጋ ንረቱ እንዲባባስ እንዳደረገው የሚገልጹት ባለሙያውየዚህ ጦርነት ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ መዘዝ አፍጦ የሚመጣው ከጥቂት ዓመታት በኋላ እንደሆነም አስረድተዋል።

የፈረሱ ድልድዮችን፣ ትምህርት ቤቶችንየፈረሱ ማኅበራዊ መስተጋብሮችን መልሶ መጠገን ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስከትልየውጭ ኢንቨስተሮችን እምነት መልሶ መገንባትም አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል። 

እስካሁን ለጦርነቱ ወጪ የተደረገ ሀብት በተለይም የውጭ ምንዛሪን የሚጠይቁ ወታደራዊ ወጪዎች ለሌላ ኢኮኖሚያዊ ዓላማ የሚውሉ የነበሩ በመሆናቸው፣ ያንን ለማሳካት የውጭ ምንዛሪውን መልሶ ማግኘትና ዓመታትን መጠበቅ እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ። 

‹‹ይሁን እንጂ የማኅበረሰብ የመለወጥ ፍላጎት እየጨመረ ይሄዳል እንጂ ዓመታትን ቆሞ አይጠብቅም፤›› የሚሉት ባለሙያውመንግሥት ይህንን ጦርነት ፈጣን መቋጫ ካላገኘለት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያመጣና ተሸጋጋሪ ውጤቱ ደግሞ ወደ ፖለቲካው የሚያልፍ መሆኑን ተገንዝቦ ልዩ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ይመክራሉ።

ሐሙስ ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታና አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው እዮብ ተካልኝ (/)፣ የትግራይ ጦርነት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ መፍጠር የጀመረው ጫና የሚታይና መንግሥት የማይክደው መሆኑን ገልጸዋል።

ጦርነቱ ያስከተለው ወጪና እየፈጠረ ያለው ጫና ቀላል ባይሆንም፣ ኢኮኖሚው የቆመባቸው መሠረታዊያን እንዳልተሸረሸሩ ይልቁንም የተሻለ አፈጻጸምና ተስፋ መኖሩን አስረድተዋል።

‹‹ጦርነቱ ካደረሰው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ ከፍተኛ ወጪና ጫና በኢኮኖሚው ላይ ማድረሱ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን በዝርዝር ተጠንቶ የጉዳቱ መጠን መታወቅ አለበት፡፡ ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለማሳየት ያህል ባለፈው አንድ ወር ብቻ መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት ለፈጠረው ሰብዓዊ ዕርዳታ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር አውጥቷል፤›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህ ላይ ወታደራዊ ወጪዎች ሲታከሉበት ከባድ የዋጋ ግሽበት ጫና በኢኮኖሚው ላይ እንደፈጠረ ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት ሕግ ለማስከበርና የአገሪቱን ሰላም ለመመለስ ሲል ከፍተኛ ሀብት ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ለማዘዋወር መገደዱንም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ሳቢያ ኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ ያስከተለውን ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ለመቋቋም ወደ ኢኮኖሚው ፈሰስ የተደረገው የገንዘብ መጠን ተዳምረው ያባባሱትን የዋጋ ግሽበት ለመግታት፣ ብሔራዊ ባንክ ከሰሞኑ ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መሣሪያዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ መወሰኑን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም መሠረት ባንኮች በብሔራዊ ባንክ የሚያስቀምጡት የመጠባበቂያ ገንዘብ መጠን በዕጥፍ እንዲጨምርና ከብሔራዊ ባንክ በሚወስዱት የአጭር ጊዜ ብድር ላይ የሚጣለውን የወለድ ምጣኔ ከፍ በማድረግ፣ በኢኮኖሚው ውስጥ ያለውን የገንዘብ መጠንና ዝውውር ለመቀነስ፣ በዚህም የዋጋ ጥረትን የመገደብ ሥራ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡

ይህ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ መጠነኛ ቅናሽ የሚያስከትል ቢሆንም፣ እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ሸክም ማቅለል ቅድሚያ እንደተሰጠው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የመሠረታዊ ፍጆታ የምግብ ምርቶች አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ መንግሥት ስንዴ ከውጭ በግዥ እያስገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ጫና የገጠመው ቢሆንም፣ የአገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚወስኑ መሠረታዊያን ጥሩ አፈጻጸም ያሳዩ በመሆናቸው በተጠናቀቀው የበጀት ዓመትም ኢኮኖሚው ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ተናግረዋል፡፡

የኢኮኖሚ መሠረታዊያን ካሏቸው ውስጥ ግብርና ባለፉት አሥር ወራት የአምስት በመቶ የምርት ዕድገት ማስመዝገቡን፣ የኤክስፖርቱ  ዘርፍ አፈጻጸም 3.6 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስገኘት ታሪካዊ አፈጻጸም ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በዘንድሮ ዓመት በከፍተኛ ደረጃ ማደጉንም ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረታዊ ችግር የዋጋ ግሽበት እንደሆነ ያስረዱት እዮብ (ዶ/ር) ይኼንን ችግር ለመቅረፍ ፈርጀ ብዙ የፖሊሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም በሁሉም አቅጣጫ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው (ፕሮፌሰር) ዓለማየሁ ገዳ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሠረታዊ ችግር የዋጋ ግሽበት መሆኑን ይስማማሉ፡፡ ነገር ግን ለዋጋ ግሽበቱ መፈጠር ቁልፍ ምክንያት የኢኮኖሚው መዋቅራዊ ችግር እንደሆነና በዚህ ውስጥም መንግሥት እየተከተለ ያለው የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ እያወሳሰበው እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹የዋጋ ግሽበት ሲጨምር የብር የመግዛት አቅም ይወድቃል፡፡ ይህ ችግር ባለበት ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ የብር የምንዛሪ ተመን እንዲያሽቆለቁል ሲደረግ መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የሚያስፈልገውን ዶላር ለማግኘት ከፍተኛ የብር ምንዛሪ ወጪ ይጠይቃል፡፡ በዚህ መንገድ ከውጭ የሚገባው ምርት ለገበያ ሲቀርብ ዋጋው የሚቻል አይሆንም፡፡ በመሆኑም ኢኮኖሚው በምንዛሪና በዋጋ ግሽበት አዙሪት ውስጥ ወድቋል፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ ላይ የጦርነቱ መከሰትና በኢኮኖሚው ውስጥ ዋነኞቹ ተዋናዮች ከቀድሞው ገዥ ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው በመሆናቸው፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴውን እየጎዳው እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ሀብት የማሸሽ ድርጊት መኖሩ ለኢኮኖሚው አደጋ መፍጠሩን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እኔ ባጠናሁት ጥናት ኢሕአዴግ በሥልጣን በቆየባቸው ዓመታት ከ31 እስከ 37 ቢሊዮን ዶላር ከአገር እንዲሸሽ ተደርጓል፡፡ ይህ የሆነው በሰላም ጊዜ ነው፡፡ አሁን ጦርነት ባለበት ወቅት ምን ያህል ሀብት ሊሸሽ እንደሚችል መገመት ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -