Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተግዳሮቶችን በመወጣት በበጀት ዓመቱ ውጤታማ የሆነው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2013 የሒሳብ ዓመት በኩባንያውም ሆነ በኢንዱስትሪው ታሪክ ከፍተኛ የሆነ ትርፍ ያስመዘገበና ዓመታዊ የዓረቦን መጠኑንም ከ6.1 ቢሊዮን ብር በላይ ያደረሰ ቢሆንም፣ በተወሰኑ ዘርፎች ላይ በተፈለገው ደረጃ መጓዝ ያላስቻሉ ችግሮች ገጥመውት እንደነበር ይገልጻል፡፡

የኩባንያውን የ2013 ዓ.ም. አፈጻጸም በተመለከተ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ነፃነት ለሜሳ ባቀረቡት ሪፖርታቸው፣ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያቸው ውጤታማ ሥራ ቢሠራም፣ ውጤቱን ለማምጣትም ሆነ በተወሰኑ ዘርፎች የተፈለገውን ያህል መጓዝ ያላስቻሉት ችግሮች አጋጥመውት ነበር፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ እንደ ችግር ካነሷቸው ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል የኢትዮጵያ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች ይጠቀሳሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ረዥም ወራት ያስቆጠረውና አሁንም ፈተና ሆኖ የቀጠለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝም ለኢንዱስትሪው እንቅስቃሴ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ያመለከቱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በተለይ ከፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች፣ በተለይም በትግራይ ክልል የሚገኙ ቢሮዎቻቸውን ሥራ ለማሠራት አለመቻላቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ከውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ጋር ተያይዞም የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋና የጥገና ወጪ መናር ሌላው እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ሲሆኑ ይህም የኩባንያውን ወጪ ከታቀደው በላይ እንዲሆን እያደረገ ነው፡፡

አቶ ነፃነት በሒሳብ ዓመቱ እንደ ችግር ያነሱት ሌላው ጉዳይም ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር የተያያዘ ሲሆን፣ ይህም በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች በመቀነሳቸው የመርከብ ላይ ጉዞ ዋስትና ሽፋን ላይ በእጅጉ እንዲቀንስ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ አጋጠሙ ተብለው የተጠቀሱት ሌሎች ችግሮች ደግሞ ከሕንፃ ፕሮጀክት ግንባታ ጋር በተያያዘ ያለው አፈጻጸም በልዩ ልዩ ተግዳሮቶች ምክንያት ዝቅተኛ ሆኖ መገኘት፣ በግዥ ሒደትና በትግበራ ላይ ያሉ የማማከር አገልግሎት ሥራዎች ከተጠበቀው በላይ ጊዜ መውሰዳቸው እንዲሁም፣ በገበያው ላይ እየተስተዋለ ያለው በዋጋ ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ ፉክክር ኢንዱስትሪው ከገጠሙት ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተጠቀሱት ችግሮች ጎልተው የታዩ ቢሆንም፣ የኩባንያው አፈጻጸም አመርቂ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ነፃነት፣ በሁሉም ዘርፍ ዕድገት የታየበት ውጤት መገኘቱን በአኃዝ በተደገፈ ሪፖታቸው አሳይተዋል፡፡  

በተለይ ከዓረቦን ገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ በኩባንያው ከፍተኛ የሚባለውን  የ6.1 ቢሊዮን ብር የዓረቦን ገቢ ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱ በላይ 17.1 በመቶ ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የተመዘገበው የዓረቦን መጠን ካለፈው ሒሳብ ዓመት የ23.5 በመቶ ወይም የ1.2 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከተመዘገበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 5.9 ቢሊዮን ብር ወይም 96.5 በመቶው ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የተመዘገበ ሲሆን፣ ቀሪው 216 ሚሊዮን ብር ወይም 3.5 በመቶ ደግሞ ከረዥም ጊዜ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተመዘገበ መሆኑንም የዋና ሥራ አስፈጻሚው ሪፖርት ያሳያል፡፡ ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ የሰበሰበው ዓረቦን ከአጠቃላይ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ዘርፍ አንፃር ያለው ድርሻ 44 በመቶ እንደሆነ የገለጹት አቶ ነፃነት፣ ቀደም ካሉት ዓመታት ሲንከባለል ከመጣው ተሰብሳቢ ሒሳብና በሒሳብ ዓመቱ ከተመዘገበው ዓረቦን ውስጥ 85 በመቶውን ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ 76 በመቶውን ተሰባስቧል ብለዋል፡፡ ይህም የዓመታዊ ዕቅዱ 89 በመቶ ሲሆን፣ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ የ52 በመቶ ብልጫ ያሳየ አፈጻጸም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

ከእነዚህም ውስጥ ከውል ሽያጭ ጋር ተያይዞ በሒሳብ ዓመቱ ለተሸጡ ውሎች የተሰጠው ዋስትና ሽፋን መጠን 3.2 ትሪሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም መጠን አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው የ8.6 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ለቅናሹ አስተዋጽኦ ያደረገው በአቪዬሽን ዋስትና ዘርፍ በኮቪድ-19 ምክንያት የተጓዦች ቁጥር መቀነስ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ገልጸዋል፡፡  

በ2013 ሒሳብ ዓመት አፈጻጸም በአጠቃላይ የ162,890 ውሎች ሽያጭና ዕድሳት ያከናወነ ሲሆን፣ ይህም ከአምናው በተመሳሳይ ወቅት ከተመዘገበው አንድ በመቶ ከፍ ያለ ነው፡፡ በዕቅድ ተይዞ ከነበረው ቁጥር ማሳካት የተቻለው 98.7 በመቶውን ነው፡፡ ይህም በፀጥታ ችግር ምክንያት በመቀሌ ዲስትሪክትና በሥሩ የሚገኙትን ቅርንጫፎችን መረጃ በተሟላ መልኩ ያካተተ እንደሆነም አስታውሰዋል፡፡  

 ኩባንያው በደንበኞች ንብረትና ሕይወት ላይ ለደረሰ አደጋ፣ እንዲሁም ሕጋዊ ኃላፊነት በአጠቃላይ ያወጣውን ወጪ በተመለከተም በሒሳብ ዓመቱ የ1.3 ቢሊዮን ብር የካሳ ክፍያ እንደፈጸመ ታውቋል፡፡ ይህ መጠን ከዕቅዱ የ81 በመቶና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ከተከፈለው ጋር ሲነፃፀር የ18 በመቶ ቅናሽ ያሳየ ነው ተብሏል፡፡ ከተከፈለው የካሳ ክፍያ ውስጥ የጠቅላላ መድን ድርሻ 1.2 ቢሊዮን ብር ወይም 93.8 በመቶ ሲሆን፣ የረዥም ጊዜ መድን ዘርፍ 79 ሚሊዮን ብር ወይም 62 በመቶ ድርሻ እንደያዘም ተገልጿል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የኩባንያውን ወጪ በተመለከተም በሒሳብ ዓመቱ የጉዳት ካሳ ምጣኔ 47 በመቶ ሲሆን፣ ይህም ከዕቅዱም ሆነ ከኢንዱስትሪው የጉዳት ካሳ ምጣኔ ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ በመሆኑ ይበል የሚያሰኝ ስለመሆኑ አቶ ነፃነት ተናግረዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ኩባንያው ከፍተኛ የሚባለውንና የ1.12 ቢሊዮን ብር ትርፍ ለማስመዝገብ ከቻለባቸው ምክንያቶቸ መካከል አንዱ ይኼው የካሳ ክፍያ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘት ነው፡፡

በኩባንያው ዓመታዊ ሪፖርት መሠረት በ2013 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም የ1.4 ቢሊዮን ብር የውል ሥራ ውጤት የተመዘገበ መሆኑንም ያሳያል፡፡ የጠቅላላ መድን ዘርፍ 1.39 ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም የረዥም ጊዜ መድን ዘርፍ 13.2 ሚሊዮን ብር ድርሻ የነበራቸው ሲሆን፣ ይህም ከተያዘው ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር በ32.7 በመቶ፣ እንዲሁም ካለፈው ሒሳብ ዓመት ውጤት ጋር ሲነፃፀር በ54.7 በመቶ ብልጫ ያለው ሆኗል፡፡  

የኩባንያው የኢንቨስትመንትና ሌሎች ገቢዎችን አፈጻጸም በተመለከተ በአጠቃላይ ከወለድ፣ ከሕንፃ ኪራይና ከሌሎች ገቢዎች 479 ሚሊዮን ብር ገቢ ያሳያል ተብሏል፡፡ ይህም ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር የ23.3 ሚሊዮን ብር ወይም 5.1 በመቶ ጭማሪን እንዲሁም ካለፈው ሒሳብ ዓመት ከተገኘው የ65.3 ሚሊዮን ብር ወይም የ15.8 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በአሁኑ ወቅት በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ከሚገኙ 19 ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ ብቸኛው በዘርፉ የተሰማራ በመንግሥት ባለቤትነት የተመዘገበ ኩባንያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ኩባንያው በኢንዱስትሪው ገበያ አንበሳውን ድርሻ በመያዝ ለዓመታት የዘለቀ ሲሆን ወቅታዊ የገበያ ድርሻውም ወደ 50 በመቶ እየተጠጋ ነው፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች