Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጊዜያዊ መፍትሔ ሩቅ አያደርስምና የኑሮ ውድነትን ለማርገብ ዘላቂ መፍትሔ ይኑር

ከሰሞኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቤት አከራዮች በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ምንም ዓይነት የቤት ኪራይ ጭማሪ እንዳያደርጉ ደንግጓል፡፡ ለዚህ ድንጋጌው እንደ ምክንያት ያመላክተው ደግሞ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታውንና እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ንረት ነው፡፡

ወቅታዊና አገራዊ ሁኔታን በመገንዘብ አስተዳደሩ እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን አሳልፎ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ለማድረግ መነሳቱ በራሱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር ነው፡፡

የዜጎች የመግዛት አቅም እየተዳከመ ባለበት ሰዓት የኑሮ ውድነቱን ሊያባብሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን በሚገባ መርምሮ መፍትሔ ይሆናሉ የተባሉ ዕርምጃዎችን የመውሰዱ ልምድም መዳበር አለበት፡፡

ይሁን እንጂ ከቤት ኪራይ ዋጋና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አሠራሮች ወትሮም ቢሆን ሕጋዊነት የሚጎላቸው፣ በዘፈቀደ የሚከናወኑ በመሆናቸው ከፍተኛ እሮሮ የሚቀርብባቸው ሆነው መቆየታቸውን ማስታወስ አስፈላጊ ነው፡፡

የመኖሪያ ቤት እጥረት የመኖሪያ ቤት ኪራይ እንዲጨምር ማድረጉ አንድ ሀቅ ሆኖ ይህንን ሰፊ ክፍተት ያለበት ጉዳይ ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ያለመቻሉም ለችግሩ መባባስ ምክንያት ነው፡፡

በመሆኑም የመኖሪያ ቤት እጥረት በፈጠረው ክፍተት ገበያንና የኅብረተሰቡን የመክፈል አቅም ያላገናዘበ እንዲሆን በር ከመክፈቱም ሌላ ግድ የሌላቸው አከራዮችና ደላሎች እንዳሻቸው እንዲፈነጩበት ሆኗል፡፡  

በየትኛውም ገበያ እጥረት እስካለ ድረስ ዋጋ መጨመሩ አይቀርም፡፡ በቤቶች ኪራይም ተመሳሳይ ችግር ይታያል፡፡ ስለሆነም በእጥረት ሰበብ ብቻ አከራዮች እንዳሻቸው መሆን እንደማይችሉ እንኳን ማሳወቅ ያለመቻሉ ሌላው የችግሩ አካል ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞች የራሴ የሚሉት ቤት የሌላቸው ዜጎች ከፍተኛ ወጪያቸው ይኸው የመኖሪያ ቤት ኪራይ ሆኖ ኑሯቸውን ለማሻሻል እንቅፋት እስከመሆን መድረሱ ችግሩ ዘርፈ ብዙ መሆኑን ያሳያል፡፡

አሁን ላይ ነጋ ጠባ አከራዮች የሚጨምሩትን ዋጋ ለመቋቋም ያልቻሉ ተከራዮች ቋሚ አድራሻ እንዳይኖራቸው እስከማድረግ መድረሱም መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ከቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ቀውሶች እንዲበራከቱ ከሚያደርጉት ምክንያቶች ውስጥ በዋናነት ሊጠቀስ የሚችለው ደግሞ አከራይና ተከራይን የሚገዛ ራሱን የቻለ ሕግ ወይም ደንብ ያለመኖሩ ነው፡፡ አለ የሚባለውን መመርያ እንኳን በአግባቡ መተግበር ያለመቻሉንም ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡

የመኖሪያ ቤት እጥረት፣ አከራይና ተከራይን የሚገዛ ሕግ አለመኖርና የተጋነነ የቤት ኪራይ ዋጋ ከኅብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች መካከል አንዱ መሆኑ ታውቆ የተከራይና አከራይ እንዲሁም የቤት ኪራይ ዋጋ ተመን ሕግና ሥርዓት እዲኖረው አለመደረጉ እየተባባሰ ለመጣው የዋጋ ንረት የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህ ለምን ሆነ ካልን ደግሞ መንግሥት መሥራት ያለበትን ሥራ አለመሥራቱን የሚጠቁመን ይሆናል፡፡

ሰሞኑን የአዲስ አበባ አስተዳደር ለሦስት ወራት የቤት አከራይ ዋጋ እንዳይጨምርና ተከራዮችንም ማስወጣት አይቻልም ብሎ ሲያውጅ ወዲያው በብዙዎቻችን ዘንድ አንድ ጥያቄ እንዲያጭርብን አድርጓል፡፡ አስተዳደሩ የዚህን ያህል ሥልጣን ያለው ከሆነ የተከራይና አከራይን ግንኙነት ሕጋዊ እንዲሆን ማድረግ የሚችል አቅም እንዳለው ያመለክታል፡፡

ይህ ከሆነ የሆነ ችግር ሲከሰት ብቻ ጊዜያዊ መፍትሔ ከመስጠት ባሻገር ዘላቂ መፍትሔውን ማበጀት ጠቀሜታው ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለነገም ጭምር መሆኑን አብሮ በማሰብ በነካ እጁ አከራይና ተከራይን የሚዳኘውን ሕግ በአስቸኳይ ያውጣልን ብለን ድምፃችንን ከፍ አድርገን ለመጠየቅ እንገደዳለን፡፡

ስለቤት ኪራይ ጉዳይ ሲነሳ ሁሌም የምናስታውሰው ደግሞ አከራይና ተከራይን የተመለከተውን ረቂቅ ሕግ ነው፡፡ ይህ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበ ቢሆንም ረቂቁ እዚያው ተዳፍኖ ተቀምጧል፡፡

ስለዚህ የከተማው አስተዳደር የቤት ኪራይ የዋጋ ተመንና አጠቃላይ የተከራይና የአከራይ ግንኙነት ሕጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖረው ለማድረግ በፌዴራል ደረጃ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቁን ሕግ እንዲሆን መወሰን አለበት፡፡

ይህም አሁን ያለውን የዘፈቀደ አሠራር በማስተካከል ሁሉንም ወገን በጋራ የሚጠቅም አሠራር ለመዘርጋት የተሻለ አጋጣሚ አለው ተብሎ ይታመናል፡፡ ስለዚህ የቤት ኪራይ ተመንን የሚደነግገውን ሕግ በቶሎ ሥራ ላይ ማዋል ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን መታደግ ነውና ጉዳዩ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

ዛሬ የመኖሪያና የንግድ ቤቶች የኪራይ ዋጋ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንዲሁም የዜጎችን የመግዛት አቅም ባላገናዘበ መልኩ በዘፈቀደ መከናወኑ እየፈጠረ ያለው ቀውስ በቀላሉ የሚታይ ባለመሆኑ እንዲሁም ችግሩ እየተባባሰ መሄዱ ታውቆ አስተዳደሩ ዕርምጃውን ማፋጠን ይኖርበታል፡፡

ለተሸከምነው የዋጋ ንረትም አንዱ መንስዔ በዘፈቀደ የሚጨመር የቤት ኪራይ ዋጋ በመሆኑ የአከራይና ተከራይ ሕግን ሥራ ላይ በማዋል የዋጋ ንረትንም ለመቆጣጠር የሚችልበት አንድ መንገድ መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

እንደየቤቱ ዓይነት እንዲሁም ቦታን መሠረት ያደረገ የቤት ኪራይ ተመን መጥቶ እንዲሠራበት ካልተደረገ ዜጎች ያለ ሥጋት እንዴት ሊኖሩ ይችላሉ? ብሎ በማሰብም መንግሥት ኃላፊነቱን መወጣት አለበት፡፡

ስለዚህ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጊዜያዊነት የወሰነው ሰሞናዊ ውሳኔ ለዘለቄታውም በሕግ የሚታወቅ የዋጋ ተመን በማስቀመጥ ዜጎቹን ሊታደግ ይገባል፡፡ ለዚህም ራሱን የቻለ ተቋም በማደራጀት ከአከራይ ሊሰበሰብ የሚገባውን ግብር በአግባቡ ለመሰብሰብም ያግዛል፡፡

አከራዮች እንደ አንድ አገልግሎት ሰጪ መታየት ያለባቸው በመሆኑ ይህ ታውቆ አጠቃላይ አሠራሩ በሕግ በተደገፈ አሠራር መጓዝ አለበት፡፡ ሁሌም ጊዜያዊ መፍትሔ ሩቅ አያደርስም፡፡ እንደውም ሁሌም ለነገሮች ጊዜያዊ መፍትሔ እያስቀመጡ መሄድ ነገሩን ሊያባብስ የሚችል በመሆኑ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

ከዚህ ጎን ለጎን ትላልቅ አፓርትመንቶችን በመገንባት ቢያንስ የመኖሪያ ቤቶች በኪራይ የሚቀርቡበትን አሠራር መተግበርም የግድ ይላል፡፡ ከሥር ከሥር የቤት ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ በመሆኑ የቤት ችግርን ሊያቀሉ የሚችሉ ተጨማሪ ሥራዎች ካልተሠሩ ነገ የባሰ ችግር ውስጥ መዘፈቃችን አይቀርም፡፡

በመሆኑም የአዲስ አበባ አስተዳደር በነካ እጁ የመኖሪያ ቤቶች የተከማቸ ችግር የበለጠ ቀውስ እንዳያመጣ ከወዲሁ ቢያንስ ለኪራይ የሚቀርቡ መኖሪያ ቤቶችን መገንባት ለሚቻልበት አሠራር መንገድ ይክፈት፡፡

ከመኖሪያም ሆነ ከንግድ ቤቶች ኪራይ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብ ከፍተኛ በመሆኑ ከዚህ የሚሰበሰበውንም ታክስ በአግባቡ ለማግኘት ሕጉ የግድ ነው፡፡ አሁን በብዙ ቦታ የአከራይና ተከራይ ውል ሲፈረም የኪራዩ ዋጋ ተከራዩ ከሚከፍለው ባነሰ እንዲሆን አከራዮች የጠመዘዙት ነገር በጉዳዩ ዙሪያ ያለው ችግር ምን ድረስ እንደሆነ የሚያመላክተንም ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት